የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሶስቱም ካምፓሶች በአሸባሪው ህወሓት ሙሉ ለሙሉ ዘረፋና ውድመት ተፈፅሞባቸዋልም ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት “ኢትዮጵያን ማፍረስ”ን ግቡ አድርጎ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የህዝብና የግለሰቦች ሃብትን እንዲሁም የመንግስት ተቋማትን በመዝረፍ የቀረውን አውድሟል።
የሽብር ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች ሴቶችን ደፍሯል፣ የእምነት ተቋማትን የውጊያ ምሽግ በማድረግ አርክሷል፤ በማቃጠልም ውድመት አስከትሏል።
በወሎ ወረራ ፈፅሞባቸው በነበሩ አካባቢዎችም ተመሳሳይ እኩይ ተግባር የፈፀመ ሲሆን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሶስቱንም ካምፓሶች ዘርፏል፤ አውድሟል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት የዩኒቨርስቲውን ደሴ፣ ኮምቦልቻና ጢጣ ካምፓሶችን ሙሉ ለሙሉ ዘርፏል፤ የቀረውንም አውድሟል።
በመሆኑም የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው ሃይል እንዳልነበር ሆኗል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ህንፃዎች፣ ዘመናዊ ቤተ ሙከራዎች፣ ቤተ መጻህፍት፣ የኢንተርኔት ሰርቨር እና ሌሎችም ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
አሸባሪው ህወሓት “ኢትዮጵያን ማፍረስ” የሚል የጥፋት እቅድ ይዞ የተንቀሳቀሰ በመሆኑ በየደረሰባቸው አካባቢዎች በተለይም የህዝብ መገልገያዎችን መዝረፍና ማውደም የተለመደ ተግባሩ አድርጎታል።
በዚህም የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአሸባሪው ሃይል ዋነኛ የጥፋት ኢላማ መሆኑን ዶክተር መንገሻ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አሸባሪው ህወሓት የሲቪል ማህበረሰብና ተቋማትን ኢላማ በማድረግ “በዓለም የጦርነት ታሪክ ያልታየ ጭካኔ የታየበት የጦር ወንጀል ፈፅሟል” ሲሉም ተናግረዋል።