ክፍል (፩)

[ባየ ተሻገር]

በተለያዩ ምክኒያቶች እና በተለያዩ ጊዜያቶች ወደ አንድ መቶ አሥር (110) የሚጠጉ የዓለም አገራት በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ለግለሰቦች ወይንም በአክሲዮን ለሚተዳደሩ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ሸጠዋል። በተለይ እንደ ማርጋሪት ታቸር ያሉ ገናና እና አወዛጋቢ አገረ-ገዥዎች በነበሩበት የአውሮጳ አህጉር እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ እና በ1980ዎቹ ፕራይቬታይዜሽን ፋሺን ተደርጎ የተከናወነ የኢኮኖሚክስ አጀንዳ ነው። በመሆኑም ተፅዕኖው በውል የሚታወቅ ጥንካሬውም ድክመቱም በጥናት የተረጋገጠ የሰነበተ ጉዳይ ነው። ምናልባት በልዩነት መታየት የሚገባው ነገር ቢኖር በርካታ አጥኝዎች ትኩረት አድርገው የተመራመሩት በአውሮጳና በአሜሪካ (በተለምዶ ምዕራባዊያን የሚባሉትና የሰለጠኑት) ያለውን ተፅዕኖ በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ህግና ሥርዓት ለማስፈን ያልቻለ እና የታወቀ የኢኮኖሚ መርሃ-ግብር በሌለው አገር ወደፊት ይኼ ይፈጠራል ወይንም ሊፈጠር ይችላል ብሎ መገመት አዳጋች ነው፤ ሳይንሳዊ ቲኦሪዎችን መሠረት አድርጎ የሚሰላ ግምት እና አናሊሲስ መነሻው የአገራቱ የፖለቲካ እና በአጠቃላይ የአገዛዝ ሥርዓት በመሆኑ በኢትዮጵያ ሊፈጠር የሚችለው በምዕራባዊው የአክዳሚክ ልኬት ተገማች አይሆንም።

ፕራይቬታይዜሽንን ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ አገራት ጭምር ዘግይታም ቢሆን በስፋት ሄዳበታለች። ህወሓት መራሹ የወያኔ መንግሥት የደርግ መንግሥት ከተወገደ በኋላ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ፕራይቬታይዜሽን በግንባር ቀደምነት ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን ይህ እርምጃ ከወያኔ በፊት የመንግሥት ፍላጎት (government will) ያልታየበትን ዘርፍ ሁሉ የነካካ ነበር። ቢሆንም ግን አይነኬ የሆኑ እንደ አየር መንገድ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን ወዘተ ዘርፎች ለፕራይቬይታይዜሽን ዝግ ነበሩ።

ከ1984 ዓ.ም እስከ 1992 ዓ.ም በነበረው ጊዜ ውስጥ ከ223 በላይ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት ተዘዋውረዋል። እስከ 1996 ዓ.ም ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 362 አድጎ ነበር። ወደ ግል ይዞታነት ከተዘዋወዋሩት ግማሽ ያክሉ (160) በማኑፋክቸሪግ ሴክተር (ጨርቃጨርቅ፣ ትንባሆ፣ ምግብና መጠጥ፣ ቆዳና ሌጦ) የተሰማሩ ነበሩ። ቀሪዎቹ ደግሞ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ሆቴል (ጊዮን ሆቴል፣ ራስ ሆቴል፣ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ ኢትዮጵያ ሆቴሎች፣ ፍልውሃ)፣ ሱፐር ማርኬት (ጣና ሱፐር ማርኬት፣ ጅንአድ)፣ ኩራዝ ማተሚያ ወዘተ ይገኙበታል።

ከላይ የተጠቀሱት ከ360 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት መዘዋወራቸው ያስከተለው ለውጥ ምንድነው በሚለውም ጥናቶች ተካሂደውበታል። ምንም እንኳን ፕራይቬታይዝድ ከሆኑት መካከል ግማሽ ያክሉ (50%) ትርፋማ ናቸው ቢባልም የምርታቸው መጠን፣ ጥራት፣ ተደራሽነት መቀነሱ ታይቷል። ወደ ሰላሳ ሁለት (32%) በመቶ የሚሆኑት ጭራሽ ኪሳራ ውስጥ ያሉ ናቸው። ቀሪዎቹ ኪሳራም ትርፍም የሌላቸው ዕድገትም ያላስመዘገቡ ናቸው።

እንዲያውም በመንግሥት ይዞታነት ሥር ያሉት (SOEs) ወደ ግል ይዞታነት ከተዘዋወሩት በአገልግሎትም በምርትም የተሻሉ ሆነው የተገኙ ሲሆን ወደ ግል ይዞታነት የተዘዋወሩት ምርታማነት በአስራ አራት በመቶ (14%) መቀነሱ ተረጋግጧል። በዚህም ምክኒያት ፕራይቬታይዜሽን ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ አቆልቁሎ የተወሰኑት ወደ መንግሥት ይዞታነት እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር።

በማይክሮ ኢኮኖሚው (Micro-economics) ዘርፍ ፕራይቬታይዜሽኙ የፈጠረው ተፅዕኖም የሚያኮራ አልነበረም። የማምረቻ ዕቃ ለባለሙያ ምጥጥን (equipment per person ratio) በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ ነበር፤ ፕሮዳክቲቭ አሴት የሚባሉትም (value of productive assets) እንዲሁ በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ ነበር። የሚያሳዝነው ወደ ግሉ ዘርፍ የተዘዋወሩት ድርጅቶች የመቅጠር አቅም/መጠን በአስራ ሁለት በመቶ (12%) የቀነሰ ሲሆን የምርት ደረጃቸው ደግሞ በአስራ አራት በመቶ (14.21%) መቀነሱ ተረጋግጧል። ለምርት መቀነሱ ዋነኛ ምክኒያት ተደርገው የቀረበት ደግሞ የጥሬ ዕቃ አለመኖር፣ የማምረቻ መሳሪያዎች ማርጀት እን መበላት ነበሩ።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዞር የማኔጅመንት ፍልስፍና መሻሻል ያመጣል ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ከአውቶክራሲ ወደ ዴሞክራሲ የተሸጋገሩት ሰላሳ አምስት (35%) የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የሰራተኞችን ስልጠና በተመለከተ ደግሞ ግማሽ ያክሉ ሙያዊ ስልጠና መስጠት እንደቻሉ ተረጋግጧል።

በማክሮ-ኢኮኖሚው (Macro-economy) ዘርፍ የተደረገውን ለውጥ ለመገምገም በተደረገ ጥናት በፕራይቬታይዜሽን እና በበጀት ጉድለት (budget deficit) መካከል ያለው ቁርኝት ደካማ ሲሆን የግንኙነት ጠቋሚው (correlation coefficient, r) በጣም ዝቅተኛ (0.224) ነበር። ይህም ማለት ፕራይቬታይዜሽኑ የበጀት ጉድለቱን የማሻሻል አቅም አልነበረውም።

በተመሳሳይ ፕራይቬታይዜሽኑ የገበያ ውድድሩን ነጻ በማድረግ ኢኮኖሚውን ነፃነት ይሰጠዋል( economic liberation) ቢባልም የዚህ ዘርፍ ጠቋሚም በጣም ዝቅተኛ (0.099) ነበር (no correlation between privatization and openness of economy)። ይህም ማለት ወደ ግል ይዞታ ማዞር በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ የነበረው ተፅዕኖ ዝቅተኛ በመሆኑ ምንም የካፒታል አኩሙሌሽን ማምጣት አልቻለም።

ታዲያ ማንን ጠቀመ የሚል ጥያቄ መነሳቱ ስለማይቀር እስካሁን የተካሄደው ፕራይቬታይዜሽን ማንን ጠቀመ የሚለውን መመልከት ተገቢ ነው። ምንም እንኳን አጠቃላይ ፕራይቬታይዜሽን የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያላሻሻለ ቢሆንም አንጻራዊ በሆነ መልኩ ለተወሰኑ ቡድኖች ጥቅም ያስገኘበት ሁኔታ ግን ነበር። የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች የወያኔ ባለስልጣናት ናቸው! ይኼውም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታነት በማዘዋወር ወደ አራት መቶ አስር ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር (USD 410 million) ከሽያጭ የተገኘ ሲሆን በገቢው መንግሥታቸውን ለማጠናከው በተለይ ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማሻሻል እንዳዋሉት ይታወቃል። ሁለተኛዎቹ ተጠቃሚዎች የትግሬው ጥረት (EFFORT) እና የሼክ አላሙዲ ሚድሮክ ናቸው። በ1987 ዓ.ም የተቋቋመው ኢፈርት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደግል ይዞታ ይዘዋወሩ በሚለው ሴራ ተጠቃሚ እንዲረግ ስለተመቻቸ በ’Sub-Saharan’ አፍሪቃ ተወዳዳሪ የሌለው የኢኮኖሚ ማማ ላይ ተቀምጧል፤ በግንባታ መሳሪውያዎች፣ በቆዳ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በጋርመንት፣ በማዕድን፣ በባንክ፣ በኢንሹራንስ፣ በመድኃኒት ወዘተ ዘርፎች በመሰማራት አገሪቱን ምጥምጥ አድርጎ ዘርፏል። መንግሥታዊ ባልሆነ የህዝብ የተራድዖ ድርጅትነት (non-governmental public charity) ሆኖ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው ጥረት አንድ ጊዜ እንኳን ኦዲት ሆኖ አያውቅም። ሚድሮክ በተመሳሳይ ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር (USD 2 billion) የሆነ መዋዕለ ንዋይ የሚገመት ካፒታል በሆቴል፣ በወርቅ ማዕድን፣ በብርጭቆ፣ በፕላስቲክ፣ በለስላሳ መጠጥ፣ በግል አየርመንገድ፣ በቤትና ቢሮ ፈርኒቸር እና ምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፍ በመሰማራት በከፍተኛ መጠን ተጠቃሚ ሆኗል!

ከአሁን በፊት የተደረገው ፕራይቬታይዜሽን ያመጣው ውጤት እየታወቀ ለምን ሌላ ዙር አገራት ፕራይቬታይዜሽን ለማከናወን ታሰበ የሚለውን ቀጥለን እንመለከታለ።

ፕራይቬታይዜሽን እንዲከናወን ዋናው ገፊው ምክኒያት (Privatization Motives) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች (SOEs) በገበያ ሁኔታ ተወዳዳሪ መሆን ሲያቅታቸው እና ይህም በደንብ (regulation) ውስብስብነት ወይም ጥብቀት (overregulated economy) ምክኒያት መሆኑ ሲታመንበት ዘርፎቹ ለውድድር ክፍት እንዲሆኑ በማሰብ የልማት ድርጅቶቹ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ ለማድረግ ነው። ይህ ኢኮኖሚክ ሊብራላይዜሽን (economic liberalization) የሚባለው ነው። ይሁን እንጅ የአሁኑ ፕራይቬታይዜሽን ትርፋማ የሆኑትን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ-ቴሌኮም ያካተተ በመሆኑ ሊበራላይዜሽን ገፊ ምክኒያት እንዳልሆነ ተጨባጭ ማሳያ ነው። በመሆኑም ሌሎች ምክኒያቶች ከጀርባው እንዳሉ መገመት አያዳግትም። የሚከተሉትን በዋናነት መውሰድ ይቻላል።

ሀ) ከፍተኛ የሆነ የብድር መጠን መኖር (large public and external debt)

ህወሓት መራሹ የወያኔ መንግሥት አገሪቱን እንደ መዥገር ተጣብቆ እንደ አለቅት ደሞን መምጠጡ የተረጋገጠ ሃቅ ነው። በተለያዩ የዜና አውታሮች እንደተረገው በርካታ ቢሊዮን ዶላር ከአገሪቱ እንዲወጣ ተደርጓል። ይህም ተረኛውን የኦሮሞ የበላይነት አስፋኝ አገዛዝ ባዶ ካዝና እንዲረከብ አስገድዶታል። በመሆኑም ካዝናውን ለመሙላት እና ተረኝነቱን ለማጠናከር የብድሩን መጠን መቀነስ ስላለበት ጥሩ ዋጋ ሊያወጡ የሚችሉ ድርጅቶችን ለመሸጥ ተገዷል።

ለ) ለጋሽ አገሮች በመደራደሪያነት ፕራይቬታይዜሽንን ማቅረባቸው (Donor Conditionality)

ኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀቷን በራሷ ማሟላት የማትችል መናጢ ደሃ አገር ናት። መንግሥት ነኝ የሚለው ፀረ-አማራ ገዥ መደብ በልመና የሚተዳደር የምዕራባዊያኑ ተመፅዋች ነው። የተረኛው የአብይ አህመድ ኦሮሟዊ መንግሥት ከተሾመ በኋላ በህዝብ ንብረት በተገዛ ቅንጡ አውሮፕላን እየተሽከረከረ ከአረቦች፣ ከቻይኖች ከሌሎችም አገሮች ልመናውን አጧጡፎታል። የትኛውም አገር በነፃ ገንዘብ አይሰጥም፤ ገንዘብ ሲሰጥህ በምላሹ የሚጠቀምነት ነገር እንዲመቻችለት ይፈልጋል። በመሆኑም የአሁኑ ፕራይቬታይዜሽን ኢትዮጵያን በግኝ ግዛት ውስጥ ለማድረግና ሪሶርሷን ለማሟጠጥ ለጋሽ አገሮች ያቀረቡት መደራደሪያ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ሐ) የኢፈርትን ፈለግ የሚከተል የኦሮሞ የንግድ ኢምፓየር ለመገንባት (ተረኝነት!)

ኦህዴድ የህወሓትን አሻራ በመከተል ላይ ያለ እንዲያውም በአንዲት ጀንበር ህዝቡን ሁሉ ውጨ ሰልቅጨ ኢትዮጵያን ኦሮሞ ካላደረኩ የሚል በግልፅ ተረኝነቱን የሚሰብክ ድርጅት ነው። ከህወሓት ሊማሩት የሚችሉት ነገር ደግሞ የኢኮኖሚ ብልጫ መሆኑ ምን ያህል የመግዛት አቅም እንዲሚያጎናፅፍ ነው። በመሆኑም ህወሓት የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ሸጦ ኢፈርትን እንደመሰረተ ሁሉ ተረኞቹ አዲስ ተመሳሳይ ድርጅት መፍጠር ስላስፈለጋቸው እንደሚሆን መላምት ማቅረብ ይቻላል።

ይቀጥላል …

ሠላም!
ቤተ አማራ – Bête Amhâra


ማጣቀሻዎች/Reference
1) Solomon Deneke (2001) – Private Sector Development in Ethiopia

2) Gebeye Worku, Alemu Getnet, Alemu Seyoum, Mekonen Alemu, Tesfaye Eyob, Ayele Gezahegn & Ishak Diwan (2000) – Has Privatization Promoted Efficency in Ethiopia?

3) Selvam J. (2008) – Privatization Programme in Ethiopia: is the cause justified?

4) Selvam J., Meenaksh, & Iuappan (2005) Privatization and Capital Accomulation: Emperical Evidences from Ethiopia

5) Tadesse Wodajo & Dawit Senbet (2017) – Does Privatization Improve Productivity? Emperical Evidence from Ethiopia

6) Wondwosen Teshome-Bahiru (2009) – Political Finance in Africa: Ethiopia as a Case Study

7) Ismail, Z. (2018). Privatisation of SoEs in Ethiopia since the1991. K4D Helpdesk Report.

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator