በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ:_
እናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል:_
አፈና ለደርግና ለሕወሓትስ ምን ጠቀመ!?
ኹሉም ሥርዓቶች ከነሱ በፊት የነበሩና የወደቁ ሥርዓቶችን የጭካኔ ተግባር እየኮነኑ፣ ስላለፈው ሥርዓት ብልግና ዘጋቢ ፊልም እየሠሩና እያብጠለጠሉ የሕዝብን ልብ በመስለብ ወደ ስልጣን ይወጣሉ።
ትንሽ ከተደላደሉ በኋላ ግን ያወገዙትን ሥርዓትና ተግባር ተላብሰው ያው ሕዝብ የጠላውን ባህርይ መተወኑን ይጀምራሉ፤ ሽክርክሮሹም ይቀጥላል።
የመቼት ልዩነት ካልሆነ ሕዝብም መልሶ ያንኑ ትዕይንት በምልሰት መመልከቱን ይቀጥላል።
ብልጽግና ሲጀምር እርሱ ሲያገለግለው የነበረበት የኢሕአዴግ ሥርዓት የፈጸመውን አፈናና ሰቆቃ በመኮነን ብቻ ሳይወሰን የኢትዮጵያን ሕዝብም ይቅርታ ጠይቋል።
ከዚያም አልፎ “እኛ እንደ ሥርዓት ሽብርተኞች ነበርን” በማለት ራሱ ላይ እስከመፍረድም ደርሶ ነበር። “እኛ እንደ ኢሕአዴግ አስረን ሳይሆን የምናጣራው አጣርተን ነው የምናስረው”ም ብሎ ነበር።
ይኹንና የተለመደው የጫጉላ ቤት ፍቅር እንዳለቀ ሰውን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር፣ ከፍትሕ ሥርዓቱ ውጪ መሰወር፣ ሰዎች ከሕግ ውጭ ሲታሰሩ፣ ሲታረዱ ከመደንገጥ ይልቅ “አይመለከተኝም” በሚመስል መልኩ በዝምታ ማለፍ እየነገሰ መጣ።
የሀገራችን ሰው “እንትናን ታውቀዋለህ ወይ?” ሲሉት “አይ ተሹሞ አላየሁትም” ይላል።
ሰው ስልጣን ላይ ወጥቶ፣ ኃይልና ጉልበት ሲሰማው ነው እውነተኛ ጠባዩ የሚታወቀው ለማለት ነው።
የሕግ የበላይነት ይመጣል ብለን ስንመኝ የግለሰቦችና የቡድኖች የበላይነት እየሰፈነ መጥቷል።
ፓርቲያችን እንዲህ ያለውን አካሄድ አጥብቆ ያወግዛል፤ ከቁልቁለት ጉዞውም ተመለሱ ይላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበረውን የአፈና ሥርዓት በማውገዝ የሰው ልጆችን እያፈነ …የውሐ ኮዳ እያንጠለጠለ፣ ግብረ ሰዶም እየፈጸመ የነበረን ሥርዓት በኮነኑበት ሰዓት ሕዝብ እልል ብሎ ተቀብሏቸዋል፣ የሰላም ኖቤል ተሸልመዋል፣ የእናቶች ምርቃት ዘንቦላቸው ነበር።
ይህ የአፈና ተግባር ካልቆመ ግን ምርቃቱም ወደ እርግማን፣ ሽልማቱም እንደመሳሳት ይቆጠራል።
በተለይ ደግሞ ሀገር ተደፈረች ብለው ከጡረታቸው እየተመለሱ ሀገር ለማዳን የታገሉ ጀግኖቻችንን፣ ጋዜጠኞችን ማፈን፣ ማጥፋትና ማሳደድ እንደ ትልቅ ክህደት የሚታይና የአኹኑ የትዕይንት ክፍል ምን አልባትም ወደማለቂያው እየቀረበ ይሆን ወይ? የሚያስብል ነው።
ሥርዓቱ ከመወደድ ይልቅ መጠላትን፣ ከሕጋዊ አካሄድ ይልቅ አፈናን፣ ከመከበር ይልቅ መፈራትን ከመረጠ በሚያስገርም ፍጥነት ከሕዝብ እየተነጠለ፣ ውድቀቱንም እያፋጠነ፣ ወዲህም የሰውን ልጅ ውድ ሕይወት እየቀጠፈ መቀጠሉ አይቀሬ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻም።
ስለሆነም
፩. ባለፉት ፶ ዓመታት ተሞክሮ የከሰረን ተመሳሳይ ሥርዓት ለመድገም መሞከር ሕዝብን ወደተለመደው የአመጽ መንገድ የሚመራ ተግባር ስለሆነ ከሕግ አግባብ ውጭ የሚካሄዱ አፈናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን።
፪. የታፈኑ ዜጎች ማን በምን አግባብ እያፈናቸው እንደሆነ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ እና በወንጀል የተጠረጠሩ ከሆነም በሕግ አግባብ በአስቸኳይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ይህ ሊሆን ካልቻለ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን፡፡
፫. ቢያንስ ይችኑ የቀጨጨች የፍርድ ሥርዓት ይባስ ብሎ የሚሰብር አካሄድ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን የሚያፍኑና የሚጠልፉ ቡድኖች ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን።