0 0
Read Time:2 Minute, 29 Second

በአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ተወካይ አባላት

በአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ተወካይ አባላት በወቅታዊ ጉዳይ የሰጡት መግለጫ:_

“በአማራ ልሂቃን ላይ መንግሥታዊ እገታ በመፈጸም የሚቆም ጥያቄም ሆነ የሚጸና ሥልጣን የለም!”

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በአማራ ክልል ምክር ቤት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ተወካይ አባላት የተሰጠ መግለጫ፤

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በሚፈጸሙ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ጅምላ ጭፍጨፋዎች እና መፈናቀሎችን በዘላቂነት በማስቆም መንግሥታዊ ሚናውን እንዲወጣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እንደ ድርጅትና በልዩ ልዩ ምክር ቤቶች ሕዝብ ‘ተናገር በከንፈሬ’ ብሎ የላካቸው ተወካዮቹ ሲወተውቱ መክረማቸው ይታወቃል።

ይሁን እንጂ የአማራ ተወላጆች በግሬደር ሲቀበሩ፣ ከተሞች ሲወድሙ ጭምር የመንግሥትነት መሠረታዊ ሥራዎችን ማለትም የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ሕግና ሥርዐትን ማንበርና የተሳለጠ አመራር መስጠት ያልቻለው መንግሥት ሕዝባችን በህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ጊዜ በአማራ ሊሂቃን ማለትም በአብን አባላትና አመራሮች፣ በፋኖ አባላትና አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ የጦር መኮንኖችን ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የአፈና፣ የሕገ-ወጥ እስራት እና የመንግሥታዊ እገታ ሥራዎች ላይ መጠመዱ በአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ተወካይ አባላትን አሳዝኖናል።

ይህ መንግሥታዊ የእገታና የአፈሳ ዘመቻ ‘ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ፤ ከአማራ ጋር ሒሳብ አወራርዳለሁ’ ብሎ በዕብሪት አገሪቱን እያመሰ ያለው ትሕነግ የጦር ነጋሪት በሚጎስምበት፣ ከፊል የአማራ ሕዝብ በዚህ ዕቡይ የሽብር ቡድን መዳፍ ውስጥ ሆኖ በሚሰቃይበትና መላው የአማራ ሕዝብ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ቆሞ አሸባሪውን መመከት በሚገባው ወቅት መሆኑ ደግሞ የመንግሥታዊ አፈናው ዓላማ ሕዝብን ለዳግም ጥቃት የማመቻቸት እና ከሽብር ቡድኑ ትሕነግ ጋር እንደመተባበር የሚቆጠር ነው።

በመሆኑም እኛ በአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ተወካይ አባላት በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ ከተወያየን በኋላ የሚከተሉትን አቋሞች ወስደናል:_

፩. በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላት ላይ እየተደረገ ያለው የአፈና እና እስራት ዘመቻ እንዲቆም፣ የታሰሩትም በአስቸኳይ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።

አብን ሕጋዊና ሰላማዊ ፓርቲ ሲሆን በፓርቲው ውስጣዊ ጉዳዮች ምክንያት የሃሳብ ልዩነት የያዙ አባላት እና አመራሮች ላይ የሚደረገው ወከባ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ መንግሥት ከመሰል ተግባራት እንዲቆጠብ እንጠይቃለን።

በአንድም በሌላም መልኩ ለዚህ ሕገ-ወጥ እስራትና መንግሥታዊ እገታ ተባባሪ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የሃሳብ ልዩነቱን በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እናሳስባለን።

፪. በፋኖ አባላት፣ በሕጋዊ ታጣቂዎችና ወጣቶች ላይ እየተደረገ ያለው አፈና፣ እስራት፣ ትጥቅ ማስወረድና መንግሥታዊ እገታ በአስቸኳይ እንዲቆም እና በዚህ ሕገ-ወጥ ዘመቻና መንግሥታዊ እገታ የታፈኑና የታሰሩ ዜጎች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን።

፫. አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ የጦር መኮንኖችንና የፀጥታ አመራሮች ላይ የሚፈጸመው መንግሥታዊ እገታና ስወራ በአስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ ሰበብ በማንነታቸው ብቻ የታገቱ የጦር መኮንኖችንና የፀጥታ አመራሮች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን።

፬. ሕግ ማስከበርን ሰበብ በማድረግ የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር በሕገ መንግሥቱ ለክልልና ለፌዴራል ተለይቶ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ሚና በማፋለስ ክልሉን በሕገ-ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያቆም በአጽንኦት እንጠይቃለን።

፭. የአማራ ክልል መንግሥት በፌዴራል መንግሥቱ ለሚፈጸመው መንግሥታዊ እገታና ስወራ ተባባሪ ከመሆን ወጥቶ የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስከብር እየጠየቅን ጉዳዮቹን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ እናቀርባለን።

፮. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማራ ሊሂቃን ላይ የሚደረገውን መንግሥታዊ እገታና አፈና እንዲቃወምና ከአማራ ሕዝብ ጎን እንዲቆም እየጠየቅን ልዩ ልዩ የአማራ አደረጃጀቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና መላው ሕዝባችን የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ እና ከበባ ለመቀልበስ በአንድነት እንድትቆሙና በጋራ ጭቆናን በመቃወም ልጆቻችሁን እንድትጠብቁ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም
ባሕር ዳር፣ አማራ፣ ኢትዮጵያ

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator