የመተከል አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በጃዊ ከተማ እስር እና ወከባ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለፀ።
የመተከል አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በጃዊ ከተማ ጥቃት እየደረሰብኝ ነው ሲል ገልጿል።
የመተከል አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደመላሽ አንድነው ለንሥር ብሮድካስት እንደገለፁት በወረዳው አስተዳደር በኩል የመተከል አስተዳደር ኮሚቴ እና የቦርድ አባል የሆኑትን የማሰር እና ስም የማጠልሸት ተግባር የተጀመረ ቢሆንም ይህን እኩይ ተግባር በመቋቋም መተከልን ወደ አማራ ጎጃም ግዛት ለማስመለስ የሚያስችል ተግባራትን እየፈፀሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም ይላሉ ሰብሳቢው የአዊ ዞን አስተዳደር ከቤኒሻጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በሚቀበሉት የአማራነት አፍራሽ ተልዕኮ ምክንያት የመተከል አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴን በጠላትነት ፈርጀው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብለዋል።
በትናትነው ዕለትም የማንነት ኮሚቴ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ እንዳለው አዲስን ከስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ፖሊስ እና ሚሊሻ በመላክ ያሰራቸው ሲሆን ሌሎችንም ኮሚቴዎች በተመሳሳይ ለማሰር ማደኛ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በኮሚቴዎች ላይ የሚደርሰው እስርና አደን መተከልን ወደ ጎጃም ነባር ግዛትነት ለመመለስ የሚደረገውን ትግል እንቅፋት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን መላው የአማራ ህዝብ ሊረዳ ይገባል ብለዋል።
አክለውም የአማራ ህዝብ የመተከል ዕርስትን እንደ ወልቃይት፣ ራያ እና ደራ ተመለክቶ ትግሉን ከጎናችን ሆኖ እንዲመራ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ንስር ብሮድካስት እንደዘገበው።
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ