ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉ አማራዎች!
ከምስራቅ ወለጋ ዞን ሌቃ ዱለቻ ወረዳ ተፈናቅለው በገተማ እና ከዋዩጡቃ ወረዳ ተፈናቅለው በጉቴ ተጠልለው የሚገኙ በትንሹ ከአስር ሽህ በላይ የሚሆኑ አማራዎች ስላሉበት ሁኔታ አሚማ ለማነጋገር ሞክሯል።
ለዘመናት ከሚኖሩበት ቀዬ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ አማራዎች አሁን ላይ “በመጠለያ ሳይሆን በመጣያ ውስጥ ነው ያለን፤ የደህንነት ስጋት አለብን፤ ከተጠለልንበት በቦንብ ለማጥቃት ሁለት ሶስት ጊዜ ተሞክሯል!” ይላሉ።
አሁን ላይ በመጠለያ ውስጥ ያሉ ብዛታቸውም በጉቴ ከተማ 5,650 አባዎራ እና እማዎራዎች፣ ከእነ ቤተሰቡ ከ10,000 በላይ ይሆናሉ፤ በገተማ ደግሞ ከ1,500 በላይ አባዎራ እና እማዎራዎች፣ ከእነ ቤተሰቡ ከ2,500 በላይ እንደሚሆኑ ተገልጧል።
በደህንነት ስጋት ምክንያትም በመቶዎች የሚቆጠሩ አባዎራ እና እማዎራዎች ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ተበትነዋል።
እነዚህ ከምስራቅ ወለጋ ዞን ሌቃ ዱለቻ እና ዋዩጡቃ የተፈናቀሉ አማራዎች እንደሚሉት በጥቅምት 16 ቀን 2014
ከተፈጸመው ግድያና በአስር ሽህዎች መፈናቀል በተጨማሪ በአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ሶስት መስጊዶች እና አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲወድም መደረጉን አውስተዋል።
በመጨረሻም በቂ ሰብአዊ እርዳታ እየተደረገልን አይደለም የሚሉት ተጎጅዎቹ በቂ እርዳታ እየደረሳቸው እንዳልሆነ በመግለጽ መንግስት፣ ሀገር ወዳድ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።