በፋሽስት ወረራ ወቅት ተወጥኖ፤ በዘመነ ወያኔ በሕግ ተደግፎ ፣ በአማራው ሕዝባችን ላይ የተፈፀመው ግፍ ተዘርዝሮ አያልቅም። በኅልውናው፣ በታሪኩ፣ በባህሉ፣ በስነልቦናው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ እሴቶቹም ላይ በገሃድና በረቀቀ ሁኔታ ግፍ ተፈፅሞበታል፤ ያላሰለሰ ዘማቻም ተካሂዶበታል። ይሁን እንጂ ሕዝባችን በግንባርቀደምነት ባካሄደው ትግል አረመኔያዊው የወያኔ አገዛዝ ተዳክሞ ላጭር ጊዜም ቢሆን ለውጥ የመጣ መስሎት ተስፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ ለውጡ ወደ ነውጥነት ተቀይሮ አሁንም ሕልውናው አደጋ ላይ ይገኛል። ላለፉት ሁለት ዓመታት በተረኞቹ የኦረሞ ፅንፈኛ ኃይሎች እየተፈፀመበት ያለው ግፍ ለዚህ አባባል ተጨባጭ ማስረጃ ነው።
አማራው ሕዝባችን ከማንም በበለጠ አጥንቱን እየከሰከሰና ደሙን እያፈሰሰ ኢትዮጵያን እንዳቆያት ሁሉም የሚመሰክረው ነው። አሁንም ቢሆን ራሱን ለማዳን የሚያደርገው ትግል ኢትዬጵያን ከማዳን ያልተለየ መሆኑ ጥርጥር የለውም። በዚህ ረግድ በአገር ውስጥና በውጭ ያለው አማራ እያደረገ ያለው ዘርፈ – ብዙ እንቅስቃሴ አበረታች ነው።
ይሁን እንጂ መንገዱ ጠመዝማዛ እንደሆነ እናውቃለን። በብርታኒያ አማራ ማህበር የፖለቲካ ተቋም ባይሆም የሕዝብ ህልውና ከሁሉ በላይ ይበልጣልና በአማራው ሕዝባችን ወቅታዊ ሁኔታ በሰፊው ከመከረ በኋላ በአገር ውስጥና በውጭም ላለው አማራ ወገናችን፣ ወዳጆቻችንና አጋሮቻችንን ጥሪያችንን እንደሚከተለው አቅርበናል:-
1.የአገራችን ኢትዮጵያ ፖለቲካ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ መጥቶ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ በደርግ ውድቀትና በወያኔ መግቢያ መካከል ያለውን ጊዜ ይመስላል። ለዚህም ዋናው ማሳያ አማራውን አግልሎ በፀደቀው “ሕገ መንግሥት ” ዙሪያና ምርጫን በተመለከተ እየተደረገው ያለው እሰጥ አገባ ነው። ዛሬም እንደትናንቱ የአማራ ሕዝብ ደባ ተፈፅሞበት ድጋሚ ስህተት እንዳይሠራ፣ በአማራ ፖለቲካ ፓርቲወች፣ ማህበራትና ምሑራን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራበት እናሳስባለን።
2.በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ከፍተኛ ስጋት የሆነው የሳምባ ቆልፍ (ኮቪድ፣-19) ወደ አገራችን በመግባቱ ከመቼውም የበለጠ ስጋት ላይ ወድቀናል። በመሆኑም ይህንን ፈታኝ ወቅት በጋራ ለመወጣት “ሁሉም ነገር ኮረናን ወደ መከላከል” በሚል መፈክር ወገን እንዲረባረብ የአማራ ማሕበር በዩኬ ጥሪውን ያቀርባል። በሌላ በኩል በፖለቲካ መሳሪያነት ውሎ በአስቸኳይ አዋጅ ስም በአማራው ሕዝባችን ላይ የሚደረገውን ማዋከብ በጥብቅ እናወግዛለን።
3.ሰኔ 15 ወንድሞቻችንን በረቀቀ ሴራ ያጣንበትና የታሪካችን አንድ ጠባሳ ነው። በመሆኑም ይህ የታሪካችን ጠባሳ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ባይሽርም የአማራ ሕዝብ ህቁን ማወቅ አለበት። ሆኖም ግን “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” እንዲሉ፣ በብአዴን/ብልፅግና የስልጣን ዘመን ዕውነታው ይወጣል የሚል ዕምነት ፈፅሞ የለንም። እንዲያውም ብአዴን/ብልፅግና የዕድሜአቸው ማራዘሚያ መሣሪያ አድርገው አማራን ለመከፋፍል እየተጠቀሙበት በመሆኑ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የአማራ ምሑራን በመመካከር መላ እንዲፈልጉለት እንማፀናለን። የአማራ ማህበራዊ እንቂወች (አክቲቪስቶች) እውነተኛ የአማራ ዳኞች ተሰይመው ሀቁን ለሟች ቤተሰቦችና መላው የአማራ ሕዝብም እስኪያሳውቁ ድረስ (ነፍሳቸውን ይማርልንና) በማንኛውም ጉዳይ የወንድሞቻችንን ስም ከመጥቀስ እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን። ይህንን ተማፅኖ በመናቅ ከዚህ አሳዛኝ ጉዳይ ጋር በተያያዛ ሕዝብን የሚከፋፍል ጽሑፍ የሚጽፉና የሚተርኩ ቢኖሩ፤ በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ የለያላቸው የአማራ ጠላቶችና ሀላፊነት የጎደላቸው እንደሆኑ ቆጥረን፣ ሀሳባቸውን ከመጋራት እንድንቆጠብ የአማራ ማህበር በዩኬ በጥብቅ ያሳስባል።
4.ብአዴን/ብልፅግና ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በማያያዝ በእነመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ በፋኖ አባላት እንዲሁም በአማራ ወጣቶች ላይ የሚያደርገውን የእሥር ዘመቻና ወከባ እያወገዝን፣ በአስቸኳይም እንዲያቆም በጥብቅ እንጠይቃለን። ለአማራ ሽማግሌወችና እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች ሰሞኑን እየሰማንው ያለው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴታችንን የሚፈታተን ድርጊት አሳዝኖናል። ይህ ከባህላችን ባፈነገጠ መንገድ እየተካሄደ ያለው ሁኔታ ወጣቱን ትውልድ አዘናጊና አቅጣጫ አሳቺ በመሆኑ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ነውና አፋጣኝ ምክር እንዲደረግበት በታላቅ ትህትና እናሳስባለን።
ብአዴን የሽምግልና ሥርዐቱን በመጣስ ለአማራው ሕዝብ ያሳየውን ንቀትና አስነዋሪ ድርጊተ እያወገዝን መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን በሽምግልና ሰም ለብአዴን ነፍሰነዳዮች ያስረከቡ ሽማገሌዎች በአስቸኳይ እንዲያስለቅቁት እየጠየቅን በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ነገር በሀላፊነት እንደሚጠየቁ ልናሰገነዝባቸው እንወዳለን።
5.ከደምቢዶሎ ታግተው ከ6 ወራት በላይ እስካሁን ያሉበት ሁኔታ ያልታወቀው የአማራ ተማሪወችችንን በተመለከ ወገን የሚያደርገው ጥረት ያልታቋረጠ ቢሆንም፣ ዘመቻው በተጠናከረ መልክ መከሄድ አለበት። በተለይ በውጭ ያለን አማሮች፣ ከሌሎች ወደዳጆቻችን፣ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመተባበር ዘመቻውን ወደሚቀጥለው ደረጃ እንድናሸጋገረው ጥሪ እናቀርባለን።
6. “ጦር ከረታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ፣ አማራ ጠል ኃይሎች በውጭ ድጋፍ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በአማራው ትግል ላይ በተቋሞቻችንና በተጋዮቻችን ላይ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄዱብን ይገኛሉ። “እሾህን በእሾህ ” ነውና እንደነሱ ውሸትን መሠረት አድርጎ ሳይሆን፣ ሀቅን ተመርኩዞ የሚመክት የመገናኛ ሕዝብ(ሚዲያ)ባለቤት መሆን ወሳኝነት አለው። ምንም እንኳን እነዚህ የአማራ ተቋማት ብቅ ብቅ እያሉ ቢሆንም፣ እንደሌሎቹ ስልጣን ከጨበጠው ቡድንና ከሌሎች የውጭ አገሮች ድጋፍ የማያገኙ በመሆኑ አማራው ሁሉ በያለበት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ እናቀርባለን።
የአማራ ማሕበር በዩናይትድ ኪንግደም