0 0
Read Time:6 Minute, 46 Second


****ወንድወሰን ተክሉ****

በሰኔ 15ቱ አደጋ አንደኛ ዓመት ዋዛሜ ላይ በሆንበት በአሁኑ ሰዓት የአማራን ብሄርተኝነትን ተጋድሎ የኦሮሞ ብሄተኝነት ትግል በተጋዘበት መንገድ እንዲጓዝ የሚያደርጉ ክስተቶች ተደጋግመው ሲፈጸሙ ለማየት ተችሏል፡፡

በነጻይቷ የፍትሕ መጽሄት ላይ ለንባብ የበቃው የጄ/ል አሳምነው ጉዳይ ምናልባትም ለዚህ ለዛሬው መጣጥፍ መንስኤ ቢሆንም በመጽሄቱ ላይ ስለቀረበው ሀተታ አንዳችም ነገር ሳልጠቅስ በአጠቃላይ በአማራ ብሄርተኛ አደረጃጀትና ተጋድሎ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ምልክታዬን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡
****

ከሃምሳ ዓመታት በላይ የተጓዘው የኦሮሞ ብሄተኝነት ጎዳና እጅግ አሰልቺ፣በጎጥና መንደር የተከፋፈለ፣እጅግ አሰቃቂ እልቂቶችን ያስከተለ የእርሰ በርስ መካካድና ብሎም በእምነትና በአይዲኦሎጂ የተከፋፈለ የትግል ጎዳና ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትግልን ከአራት በላይ የሆኑ ጎጣዊና መንደራዊ ብሄርተኞች ሊዘውሩት ከአምስት አስርተ ዓመታት በላይ እርሰበርስ የተናነቁበት ጎዳና እጅግ ብዙ ያስከፈለ የመሆኑን ሀቅ ከትግል ተመኩሮአቸውና ታሪካቸው መማር ይቻላል፡፡ በወለጋ፣በአሩሲ፣በሸዋና በምስራቅ ሀረርጌ የተከፋፈለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጎዳና በውስጡ በእስልምና እና ክርስትና እንዲሁም በወለቡማ (ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ነጻይቱን የኦሮሚያን ሀገር ለመመስረት የተነሳው ቡድን) እና በቢሊሱማ (በኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ የኦሮሞን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን እንደ ወርድና ቁመቱ አስጠብቃለሁ የሚለው ቡድን) የሚባሉ Faction ፈልፍሎ ማህበረሰቡን ክፍተኛ ዋጋ በማስከፈል የሚታወቅ የትግል ጎዳና እንደመሆኑ መጠን ዛሬ የአማራውን የህልውና ተጋድሎን በዚህ የኦሮሞ ብሄርተኛ ትግል ጎዳና ላይ ለመዘወር የሚደረጉ ተግባራቶችን በአንክሮ ማየት ችለናል፡፡

በ2016 ወርሃ ሀምሌ ላይ የአማራን ብሄርተኝነትን ተጋድሎ ችቦ ለኩሶ ያቀጣጠለው ጀግናው ኮ/ል ደመቀ የወልቃይት ጠገዴን ፍትሃዊ ጥያቄን ማእከሉ አድርጎ የተነሳ የመሆኑ ሀቅ አሰቸኳይ የሆነና ፈጣን አጋር ተሳትፎን ያገኘው ከጎንደር ህዝብ ነው፡፡

ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ወዲያውኑ ተጎራባቾቹ ጎጃሞች፣ወሎዎችና ሸዋዎች ተጋድሎውን በመቀላቀል ጸረ ህወሃታዊ ትግሉን በአማራዊ ስነልቦና ላይ ተመስርተው ሊያጧጡፉት ችለዋል፡፡

ይህ እንግዲህ እታች ምድር ላይ ወርዶ ሲካሄድ የነበረ ትግል ሲሆን ከዚህ ከታሪካዊው የሀምሌ 2016ቱ ክስተት ቀደም ብሎ እታች ምድር ላይ ያልወረደና በህዝቡ ውስጥ ያልሰረጸ የonline movement ሲጧጧፍ የቆየ ሲሆን ይህ በአየር ላይ የነበረው ንቅናቄ እጅግ ስብጥርጥር ያለና በአንድ አላማና ግብ ያልተማከለ ከመሆኑም በላይ በሁለት ዋና ጠርዝ ረገጥ አቋሞች ተከፍሎ እርሰበርስ ሲከታከት እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ሁለቱ ጠርዝ ረገጥ አቋሞችም አንደኛው ቤተ አምሃራ (ሉዓላዊ የአማራ መንግስት መመስረት አለበት የሚሉ ሀሳቦች) እና የብሄረ አማራ የህልውና ተጋድሎ (የአማራን ህዝብ የተደነቀነበትን የህልውናን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነገዱ ህልውናዊ ማንነቱን ለማስቀጥል በራሱ ተደራጅቶ በመታገል በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅምን እንደ ወርድና ቁመናው ማስከበር አለብን የሚሉ ሀሳቦች) በሚባሉ ሁለት ዋና የሀሳብ ጠርዞች ተቧድኖ ከፍተኛ የሆነ የእርሰበርስ ሀሳባዊ ጦርነቶች ሲካሄዱ እንደነበረ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም እነዚህን የአየር ላይ ጠርዝ ረገጥ አመለካከቶችን የጎንደሩ ጀግና ህዝብ በሀምሌ ወር ላይ በ2016ብድግ ብሎ የህወሃትን ገዳይ አግአዚ ሰራዊትን Defy በማድረግ ትግሉን ባቀጣጠለበት ወቅት ልዩነቶቹ ከስመው ኢትዮጵያዊ የሆነ የአማራ ብሄርተኝነት ተጋድሎ እታች ምድር ለመቆንጠጥና ህልውናውን እውን ማድረግ እንደተቻለው ይታወቃል፡፡

ያ ንቅናቄም በብአዴን ውስጥ ሰርጾ በመግባት ውስን የሆኑ የድርጅቱ አመራሮችን በህወሃት ላይ አምጸው እንዲነሱና በኃላም ኦሮማራ ተብሎ የተሰየመውን የብአዴን ኦህዴድ ድርጅታዊ ጥምረትን በመፍጠር የህወሃትን አገዛዝ ከአዲስ አበባ ላይ ነቅሎ ለማባረር እንዳስቻለው አይተናል፡፡

ከህወሃት መባረር ማግስት የአማራ ብሄርተኝነት ተጋድሎ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን በመውለድ አመርቂና ተስፋ ሰጪ የሆነን አደረጃጀትን፣ህዝባችንን የማንቃት ስራንና ብሎም የህዝባችንን ጥቅምና ህልውናን የማስጠበቅ ስራዎች እስከ ሰኔ 15-2019 ድረስ ከሞላ ጎደል ሲያካሄድ እንደቆየ ይታወሳል፡፡

? ከሰኔ 15ቱ አደጋ በኃላ የአማራ ብሄርተኛ ንቅናቄ ያጋጠመው አጣብቂኝ መንገድ

የሰኔ 15ቱን ሴራዊ አደጋን ውጤታማ የሚያደርጉ ክስተቶች በእለቱ በተሰውት አራቱ የአማራ አመራሮችና የአማራው ልዩ ኃይል አባላት መሰዋት ምክንያት የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን በእለቱ ባጣናቸው አመራሮች ይበልጥ ህዝባችንን በእጅጉ የጎዱና እልባት ላይ ካልደረሱ ዛሬና ነገም የሚጎዱ ሁለት አበይት የሆኑ ክስተቶች ተፈጠሩ፡፡

እነዚህ ሁለት ክስተቶችም –

?1ኛ- በሰኔ 15ቱ አደጋ ማግስት የአቢይ መራሹ መንግስት የአማራን ብሄርተኛ አደረጃጀትን Dismantle ለማድረግ እጅግ መጠነ ሰፊ የሆነ መንግስታዊ ዘመቻን መክፈት

? 2ኛ- በሰኔ15ቱ አደጋ ማግስት ሰፊውና ታላቁ ህዝባችን (በተለይ የፖለቲካ፣የአክትቪስቱንና የሚዲያውን ጎራ ማለቴ ነው)እጅግ በሚያሳዝን መልኩ በሁለት ጎራ በመክፈል እርሰበርስ ማነታረክ የመጀመሩ ሁኔታ ማየት መቻላችን ይታወቃል፡፡

በዚህም ምክንያት የአማራ ብሄርተኝነት ተጋድሎና አማራዊ ተኮር አደረጃጀት ቅድመ ሰኔ 15ቱ አደጋ በፊት እንደነበረው በአመርቂና ተስፋ ሰጪ ሁኔታ መጓዝ ተስኖት –

? 1ኛ-በሰኔ15ቱ ሰለባ በሆኑት አራቱ አመራሮቻችን ጀርባ ለሁለት ተቧድኖ አንደኛውን ገዳይ ሌላኛውን ተጋዳይ የሚል ቡድን ማየት የመቻላችንና በአንጻሩም ይህንን ቡድን ደግሞ በመቃወም ሟቾቹን አመራሮች አንደኛውን ጀግና ሌላኛውን የአቢይ ወገን በማድረግ እርሰበርስ መጠዛጠዝ መፍጠር መቻሉን ስናይ

?2ኛ- የሁለቱ ጎራ ክፍፍል እየሰፋ በመሄድ በጎጥና በመንደር ተቧድኖ የጎንደር፣የጎጃምና የሸዋ በሚል አውራጃዊ ስሜትና ቀጠና ተከፋፍሎ የሚነታረክ ቡድን ማየት የመቻላችን

? 3ኛ- በሰኔ15 ባረፈብን ዱላ የአማራን ብሄርተኛ ንቅናቄንና አደረጃጀትን በመንግስታዊ የመንጥር ዘመቻ ንቅናቄው ክፉኛ ሲዳከምና ሲከፋፈል ለማየት የተገደድንበትን ክስተት ለማየት በቅተናል፡፡

በዚህም መሰረት የሰኔ15ቱን አደጋ አቃጆችና አስፈጻሚዎች ማንም ሆኑ ማን ዋና አላማቸው እየተጠናከረ የመጣውን የአማራን ብሄርተኛ አደረጃጀትና አወቃቀርን በጎጥና በመንደር ከፋፍሎ እርሰበርስ በማቆራቆዝ የንቅናቄውን ታላቅ ኃይል የመበታተንን አላማ one way or another way ያሳኩ በሚመስል ሁኔታ ዛሬ ከአንድ አመት በኃላም ይህ ክፍፍል ስሩን ሰዶ ህዝባችንን በብዥታ ውስጥ ሲከት ይታያል፡፡

? የውስጣዊ ክፍፍሉ መንስኤና መፍትሄውን ስንመለከት-

የሰኔ15ቱ አደጋ የአውራጃዊውን ስሜት galvanized እንዳደረገና ነፍስ እንደዘራበት ስናይ ማርከሻ መድሃኒቱንም የምናገኘው በዚያው በሰኔ 15ቱ አደጋ ውስጥ ሆኖ እናገኛለን፡፡

የሰኔ15ቱ አደጋ የአማራን ብሄርተኛ ንቅናቄን እንደ የኦሮሞው የሃምሳ አመት የልዩነትና የክፍፍል ንቅናቄ ለማድረግ ቁልፉን ሚና እንደተጫወተ ከተረዳን ዋና ሀሳቦችን ነጥለን ስናወጣ ሶስት መሪና ገዢ ሀሳቦችን መለየት ይቻለናል፡፡

እነሱም –

?1ኛ-የአቢይ መራሹ መንግስት ጸረ አማራዊ ብሄርተኛ አደረጃጀትን ሀሳብ

?2ኛ-የዶ/ር አምባቸው «ተቆርቋሪ» ወገኖች ሀሳብ

?3ኛ- የብጄ/ል አሳምነው ጽጌ «ተቆርቋሪና አድናቂ» ወገኖች ሀሳብን ለይተን ማየት ይቻለናል፡፡

እነዚህ ሶስት ገዢ የሆኑ ሀሳቦች ጉልበትና ኃይልን ፈጥረው የአማራውን ብሄርተኛ አደረጃጀትና ተጋድሎን በመከፋፈል ደረጃ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ስናውቅ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን መንግስታዊውን ጸረ አማራዊ ሀሳብን ወደ ጎን በማድረግ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ባሉት አማራዊ አመለካከቶች ላይ ብቻ በማተኮር የአማራን አንድነታዊ ተጋድሎን መልሰን ማጠናከርና መገንባት እንደምንችል መረዳት ያስፈልገናል፡፡


የውስጣዊ ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ልንጠቀምበት ከቻልን አንድ ብቻ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ያም የውስጣዊ ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ የታላቁንና ሰፊውን የአማራን ህዝብ ህልውና እና ጥቅምን ከሁሉም አስበልጦ የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ሲሆን ይህንንም መፍትሄያዊ ቁልፍ ስንጠቀም የዶ/ር አምባቸውን የብጄ/ል አሳምነውን ሚናን በተናጥል ለያይተንና ከፋፍለን የምናየው ጉዳይ መሆኑ ያከትምና በአማራነታቸው ብቻ ስለአማራ ህዝብ ጥቅምና ህልውና መሰረት አድርገን የመሪዎቻችንን ህልፈት ልናስተናግድ እንችላለን፡፡


በአማራ ህዝብ ህልውና እና ጥቅም እይታ ሁለቱም ወገኖች ማለትም የዶ/ር አምባቸውና ተከታዮቹ እና የብጄ/ል አሳምነው ጽጌና ተከታዮቹ ማንኛውም አይነት ስራ – ትክክለኛ የሆነውም ሆነ ትክክለኛ ያልሆነውም ስራ ከእነ መስዋእትነታቸው ለሰፊው የአማራ ህዝብ ጥቅምና ህልውና ተብሎ የተፈጸመ ስለመሆኑ መረዳት ይገባናል፡፡

ከዚህ ባለፈም የሁለቱንም ወገኖች አንድነት የምናይበት ሌላው ገጽታ ሁለቱም የአንድ ድርጅት ብአዴን አባልና ባለስልጣን የመሆናቸውን ሀቅ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከህልፈተ ህይወታቸው በኃላ በወዳጆቻቸውና በተከታዮቻቸው የተፈጠረውን አዲስ የማንነት መገለጫ አቋማዊ ክፍልን ፈጥነን በማፍረስ ሁለቱንም ወገን በአንድ ላይና በአንድ ጎራ በማኖር ነፍሲያቸውን እረፍት ልንሰጥ ይገባል፡፡


ከህልፈተ ህወታቸው በኃላ የተፈጠረውና እነሱ በህይወት እያሉ በራሳቸው ያልተፈጠረው የማንነታቸው መገለጫ ክፍል አንደኛውን ለአማራ ህዝብ ህልውና እና ጥቅም የቆመና ሌላኛውን ደግሞ በተጻራሪ ጎራ ሆኖ ከመንግስት ጋር በመወገን በጸረ የአማራ ጥቅምና ህልውና ላይ እንደቆመ አድርጎ በመግለጽ የተፈጠረ አርቲፊሻል የሆነ ክፍፍል አለ፡፡

ይህን አርቲፊሻል ክፍልን ደርምሶ ለማፍረስ የዶ/ር አምባቸውንና የብጄ/ል አሳምነውን በህይወት ዘመናቸው የአንድ ድትጅት ብአዴን አባልና የአመራር አካል ሆነው የኖሩና ያገለገሉ መሆናቸውን ብቻ በጸጋ መቀበልና ብሎም ይህንን መሰረት አድርጎ ሟቾቹን ማስተናገድ ሲገባ አንደኛውን ለአማራ የተሰዋ ሌላኛውን በጸረ አማራ ጎራ የተሰለፈ ማድረግ በህዝባችን ውስጥ መቼም የማይሽር ክፍፍልንና ጠባሳን ከመፍጠር የዘለለ አንዳችም ረብ ያለው ተግባርን ለማቾቹም ሆነ ለህዝባችን እንደማያመጣ በጽኑ ልናውቅ ይገባል፡፡

ይህን ለማድረግ ታዲያ ወሳኙ የታላቁን አማራ ህዝብ ህልውና እና ጥቅምን የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ስንችል ብቻ ነው ይህንን መፈጸም የሚቻለን፡፡

? የአማራን ብሄርተኛ ንቅናቄና አደረጃጀቱን እንዳይጠናከርና አማራም በአንድነት እንዳይቆም የሚፈልጉትን ኃይሎች ለይቶ የማወቁ ወሳኝ አስፈላጊነት

ዛሬ አፈሩ ይቅለላቸውና እነ ምግባሩ፣ብጄ/ል አሳምነውና ዶ/ር አምባቸው በህይወት የሉም፡፡ ግን በህይወት ሳሉ ሁሉም የአንድ ድርጅት ብአዴን አባልና አመራር ሆነው ቢከፋም ቢለማም ህዝባቸውንና ሀገራቸውን ያገለገሉ መሪዎች ናቸው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሆነው ሆነና ለህልፈት በቁ፡፡ በህልፈታቸው ግን እኛ ህያዋን ልንነጣጥላቸው ፈጽሞ አይገባም፡፡ በእነሱ ህልፈተ ህይወት አስታኮ የአማራን ብሄርተኛ አደረጃጀታዊ ንቅናቄን ባለበሌለ መንግስታዊ ኃይሉ ዘምቶ ለማፈራረስ የጣረውና ዛሬም ጭምር ተመሳሳይ ጸረ አማራዊ ስራን እየሰራ ያለውን የአቢይ መራሹን መንግስት አላማና ፍላጎት እያንዳንዱ የአማራ ተወላጅ ጠንቅቆ በማወቅ የአማራን አንድነት የማይፈልግ ጸረ አማራዊ አቋም ያለው ኃይል ብቻ ነው ብሎ በመለየት ከውሳኔ ላይ መድረስ ይገበዋል፡፡

ጸረ አማራዊ አቋም ያለው መንግስታዊው የብልጽግና መራሹ ኃይል፣ከመንበረ ስልጣኗ የተፈናቀለችው ህወሃትም ሆነች ወደ ስልጣን መሰላል ለመንጠላጠል እየተጋጋጠም ያለው አክራሪው የኦሮሞ ብሄርተኛ ኃይል የዚህን ታላቅና ሰፊ የሆነውን የአማራን ህዝብ አንድነት፣የዳበረ ንቃተ ህሊና ባለቤትነትና ብሎም የነቃ ብሄርተኛ አደረጃጀትን በእጅጉ የማይፈልጉና ይህንንም እውን ለማድረግ የትኛውንም ተግባር ከመፈጸም ወደኃላ እንደማይሉ እያንዳንዱ አማራ ማወቅና መረዳት አለበት፡፡

ይህንን በምድር ያለን ነባራዊ ሀቅ ያወቀ የአማራ ልጅ በሙሉ ዛሬ ከሚንደረደርበት አውራጃዊነትን መዘወሪያው ባደረገ የተናጥል ክፍፍላዊ ጉዞ እራሱን በፍጥነት በማውጣት ስለአማራዊ አንድነትና ስለአማራዊ ህልውና ሲል የትኛውንም መስዋእትነት ከፍሎ ክፍፍሉን ያከስማል ብዬ አምናለሁና የአማራን ፖለቲካ የምናይበትን ቅኝት የአማራን ህዝብ ህልውናን እና ጥቅሙን መሰረት ያደረገ መሆን ያለበት የግዴታ ያህል መሆኑን በጽኑ
መረዳት ያስፈልገናል፡፡

እናም በመጪው የሰኔና ቀጣዮቹ ወራቶች ውስጥም የአማራን አንድነትና ብሄርተኛ አደረጃጀቱን ከማይሹ ኃይሎች እጅግ በርካታ የሆነ ሴራና መከፋፈያ ፈጠራዎች በሰኔ15ቱ አደጋ ሰለባዎች ስም ማሰራጨታቸው አይቀሬ ነውና የአማራ ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞች፣አክትቪስቶችና መላው የአማራ ህዝብ ይህንን እውነት ተረድቶ የስነልቦና ዝግጅቱን ከወዲሁ መገንባት እንዳለበት ይረዳል ብዬ እገምታለሁና የህዝባችንን የህልውናን ተጋድሎ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከተጓዘበት የ50ዓመታት ጎዳና ለመታደግ ፈጥነን ልንረባረብ ያስፈልጋል በማለት ሀተታዬን እደመድማለሁ፡፡

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator