“የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው የፖለቲካ ግብግብ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ለተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ እና የሰላም እጦት የአማራን ሕዝብን እና የአማራን የፖለቲካ ኃይሎች የጦስ ደሮ ለማድረግ የሚኬድበትን መንገድ አብን አጥብቆ ያወግዛል።” አብን

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ሙሉ መግለጫውን አንብቡት!

የውስጥ ችግርን መፍቻ ቁልፍ ሲቸግር በአማራ ሕዝብ እና በአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ማሳበብ ሊበቃ ይገባል።

ትናንት ሚያዚያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታዎችን አስመልክቶ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። ኦፌኮ ወቅታዊው የሀገራችን ሰላም ፣ መረጋጋት እና የኑሮ ውድነት የደረሰበትን አሳሳቢ ደረጃ በመረዳት መግለጫ ማውጣቱ የሚደነቅ እና ተገቢነት ያለው ነው። ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦነግ ሸኔ እና በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለውን ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥሪ ማድረጉ የሚደነቅ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሙሉ ድጋፉን የሚሰጠው አቋም ነው። ወቅታዊ በሆነው እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ፈተና ላይ በጣለው የኑሮ ውድነት ላይ መፍትሄ እንዲፈለግለት ያደረገውን ጥሪ በተመለከትም አብን የሚጋራው አቋም ነው።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ተራ ቁጥር 2 ላይ “ከአማራ ክልል የሚነሱ የታጠቁ ሃይሎች በአማራ ክልል መንግስት ድጋፍ እየተደረጋላቸው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለይም በምስራቅ ወለጋ ፤ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ፤ ሰሜን ሸዋ ፤ ምዕራብ ሸዋ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች፤ በተቀናጀ አኳኋን የጦር ዘመቻ እና የመሬት ወረራ እያካሔዱ እንደሚገኝ ከአባሎቻችን እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ለመረዳት ችለናል” በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በየትኛው ክልል ፣ ዞን ወይም ቀበሌ በየትኛውም ኃይል ሆነ ታጣቂ የሚፈጸም ጥቃትን ፣ ትንኮሳን እና ግጭትን ያወግዛል። ንቅናቄያችን የትኛውም ልዩነት በጦር ኃይል እና በጉልበት ይፈታል ብሎም አያምንም። ከየትኛውም ክልል ተነስቶ እና በየትኛውም አካል ተደግፎ ፣ በየትኛውም አካባቢ እና ሕዝብ ላይ ጥቃት የሚፈጽም አካል ካለ ፣ ጥቃቱን ለማስቆምም ሆነ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አብን በሙሉ አቅሙ ይደግፋል።

ነገር ግን በተለያዩ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው የፖለቲካ ግብግብ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ለተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ እና የሰላም እጦት የአማራን ሕዝብን እና የአማራን የፖለቲካ ኃይሎች የጦስ ደሮ ለማድረግ የሚኬድበትን መንገድ አብን አጥብቆ ያወግዛል። ኦፌኮ በመግለጫው የጠቀሳቸው ምስራቅ ወለጋ ፤ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ፤ ሰሜን ሸዋ ፤ ምዕራብ ሸዋ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ውስጥ በብዙዎቹ አካባቢዎች በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እና መፈናቀል የሚፈጸምባቸው ቦታዎች እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ፤ በግልጽ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸው እና ታጣቂዎቹ አብዛኛዎቹን አካባቢዎችን የሚቆጣጠሯቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ለተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ እና የሰላም እጦት አማራ ተጠያቂ የሚሆነው ፣ “ኦነግ-ሸኔ አማራ ነው ፣ ታጣቂዎቹም የአማራ ገበሬዎች ናቸው” ከተባለ ብቻ ነው፡፡ ኦፌኮ ኦነግ-ሸኔን እና ታጣቂዎችን በአማራነት እንደማይከስ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየፈጠሩ ካሉት የጸጥታ መደፍረስ እና ሰላም እጦት በተጨማሪ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ፣ በሲዳማ ክልል፣በደቡብ ክልል እና በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች እና በሕዝብ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ እንደቆዩ እና እያደረሱ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ተጨባጭ ማሳያዎች አሉ፡፡ እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በኦነግ-ሸኔ መካከል እየተካሄደ ያለውን ደም አፋሳሽ ግጭት እና በተለያዩ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ያረግባል በሚል ስሌት ኦነግ-ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው እና በሚቆጣጠራቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ፣ ከአማራ ክልል የተነሱ ታጣቂዎች ወረራ ፈጸሙ የሚል መግለጫ ማውጣቱ አብንን አሳዝኗል። ንቅናቄያችን አብን ኦፌኮ እና መሰል የፖለቲካ ኃይሎች ለሀገራችን ሰላም እና ለሕዝባችን አንድነት መጠበቅ ቁልፍ ሚና አላቸው ብሎ ያምናል ፤ የሚያራምዷቸው የፖለቲካ አቋሟች ከጊዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ባሸገር ዘላቂ የሀገር ሰላም እና ጥቅም የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ይጠብቃል፡፡

“የጋራ ጠላት በመፈብረክ እና በመፍጠር የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች አንድነት መፍጠር ይቻላል” የሚለው የፖለቲካ ስሌት ለበርካታ አስርት ዓመታት ተሞክሮ የከሸፈ እና በውጤቱም ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ ለመላው የሀገራችን ሕዝብ እና ለሀገራችን አንድነት የማይበጅ አካሄድ መሆኑ በበቂ ተሞክሮ እና ማሳያዎች የተረጋገጠ ነው፡፡ ኦፌኮም ሆኑ በመሰል የፖለቲካ ስሌት የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ኃይሎች ከመሰል አካሄዶች እንዲቆጠቡ አብን ጥሪውን ያስተላልፋል። የትኛውንም ሕዝብ እወክላለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል ፣ “እነሱ” ብሎ በሚጠራው ሕዝብ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ፖለቲካ እያራመደ ፣ “የእኛ” ብሎ ለሚጠራው ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እና ጥቅም ማረጋገጥ እንደማይችል ከአሸባሪው ትሕነግ በላይ ምሳሌ ለመሆን የሚችል የፖለቲካ ኃይል የለም፡፡ “እነሱ” ለምንለው ሕዝብ ሰላም እና ጥቅም መስራት ፣ “የእኛ” ለምንለው ሕዝብ ሰላም እና ጥቅም መስራት መሆኑን ሁላችንም ግንዛቤ ልንውሰድበት ይገባል፡፡

በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ የሰላም እጦቶች እና የጸጥታ መደፍረሶች መንስዔ መዋቅራዊ እና ሥርአት-ሰራሽ ለመሆኑ ከማንም ሀገር እና ሕዝብ ወዳድ ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡ የአንድ ቡድንን ጠባብ የፖለቲካ ጥቅም ለማስከበር ሲባል እና በሂደትም ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመበተን የተዋቀረው ሥርአት እና የአስተዳደር መዋቅር እስከቀጠለ ድረስ የየትኛውም አካባቢ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እና ጥቅም ማስከበር የሚቻል አይደለም፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከልም ሆነ በሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ የሚቻለው እና እንወክለዋለን ለምንለው ሕዝብ እና አካባቢ እንዲሁም የሀገራችን ኢትዮጵያን ሰላም እና ኅልውና ማረጋገጥ የሚቻለው ተቀራርቦ በመስራት ፣ በመደማመጥ እና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥቅሞች እና መብቶች የሚከበሩበት አማካኝ እና አስቻይ የፖለቲካ ሥርአት በመፍጠር ነው ብሎ ያምናል። ስለሆነም አብን ኦፌኮን ጨምሮ በሕጋዊ መንገድ ፓርቲ መስርተው ከሚንቀሳቀሱ ከየትኛውም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማሳወቅ ይወዳል።

አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator

Hi, How can I help you? 

00:17