“እንደዚህ አይነት ሥራ አትስራ። አገራችንን የምንገነባው አንድ ላይ ነው። የትም ቦታ ብትሆን ከእኛ አታመልጥም።’ የሚል ማስፈራሪያ ምክር ያለበት ንግግር ተናግረውኛል” ሲል ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ተናገረ።

ከአንድ ሳምንት በላይ ደብዛው ጠፍቶ የነበረው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፤ ከመኖሪያ ቤቱ ‘የተደራጀ የሕገ-ወጥ ቡድን’ በሚመስል አካል ከተያዘ በኋላ ጦር ኃይሎች አካባቢ ባለ ‘የድሮ ቤት’ ውስጥ ሳያቆዩኝ አይቀርም አለ።

ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ ግንቦት 01/2014 ዓ.ም. ወደ መኖሪያ ቤቱ የተመለሰው ጋዜጠኛ ጎበዜ፤ ተይዞ ወደቆየበት ‘የድሮ ቤት’ እስኪደርስ ድረስ እንዲሁም ጥያቄ ሲቀርብለት ዓይኑ በጨርቅ ታስሮ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ተይዞ የቆየው ጦር ኃይሎች አካባቢ ባለ ቤት መሆኑን ያወቀው የያዙት ሰዎች ወደ ሥፍራው ለመሄድ አቅጣጫ ሲነጋገሩ ከሰማ በኋላ መሆኑን ለቢቢሲ አስረድቷል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ እንዴት ተያዘ?

“የያዙኝ የኢድ በዓል ዋዜማ ዕለት እሁድ ዕለት ረፋድ 4 ሰዓት አካባቢ ነበር” ይላል። 7 ወይም 8 የሚሆኑ ሲቪል የለበሱ እና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የማይመስሉ ግለሰቦች አያት አካባቢ ወደሚኖርበት ግቢ ዘለው መግባታቸውን ጎበዜ ያስረዳል።

“የፀጥታ ኃይል ናቸው ለማለት ይከብዳል። ድርጊታቸው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አይመስልም። ግቢ ውስጥ ገብተው ሲጯጯሁ ሰው አምልጧቸው የሚፈልጉ እንጂ እኔን ሊይዙ የመጡ አልመሰለኝም ነበር። ‘አንተን ነው የምንፈልገው’ አሉኝ” ይላል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ የግለሰቦቹን ማንነት ቢጠይቅም ወዲያው ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልነበሩ ይናገራል።

“መሳሪያ ይዘዋል። ማናችሁ ብዬ መታወቂያ ስጠይቃቸው መታወቂያ ለማሳየት ፍላጎት የላቸውም። ሲሳደቡ ነበር” ይላል።

በግለሰቦቹ አለባበስ እና ሁኔታ የመንግሥት ኃይሎች ስለመሆናቸው ጥርጣሬ አደረብኝ የሚለው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፤ ሊይዙት የመጡ ሰዎችን እንዲህ ሲል ይገልጻቸዋል።

“አለባበሳቸው የተለያየ ሲሆን ኮፍያ ባለው ሹራብ የተሸፈኑ አሉበት። ፀጉራቸው ያደገ። ሁኔታቸው እንደ ‘ጋንግስተር’ [አደገኛ ቦዘኔ] ነው። . . . የተደራጀ የሕገ-ወጥ ቡድን መጣ ብዬ ነው ያሰብኩት” ይላል።

ጨምሮም ሊይዙት ከመጡት ሰዎች መካከል አንዱ ቪዲዮ መቅረጽ መጀመሩን ጎበዜ ይናገራል።

በተደጋጋሚ ማንነታቸውን ሲጠይቅ ከግለሰቦቹ መካከል አንዱ የፀጥታ ኃይል መሆናቸውን እንደነገረው እና መታወቂያ እንዳሳየው ያስታውሳል።

“ያሳየኝ መታወቂያ የመከላከያ ሠራዊት አባል እና የመረጃ ምናምን ይላል። ከዚያ ወደ ውጪ ይዘውኝ ወጡ” በማለት ጎበዜ ይናገራል።

ጎበዜ ግለሰቦቹ ይዘውት የሄዱበት መኪና የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሌዳ እንዳለው ይናገራል።

በግለሰቦቹ ተይዞ ከመኖሪያ ቤቱ ከወጣ በኋላ ዓይኑን በጨርቅ ሸፍነው ይዘውት እንደሄዱ ይናገራል። በመኪናው እየተጓዙ፤ “በጣም እየተጯጯሁ ይነጋገራሉ። ከንግግራቸው ጦር ኃይሎች አካባቢ እንደወሰዱኝ ማወቅ ችያለሁ” ይላል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ግለሰቦቹ ይዘውት ወደሚሄዱበት ቦታ ‘ጀነራል’ እያሉ ከሚጠሩት ግለሰብ ትዕዛዝ ይቀበሉ ነበር ይላል።

“አቅጣጫ እየነገራቸው ነበር ግን ያወቁት አይመስለኝም። መጨረሻ ላይ አንድ ግቢ ውስጥ ይዘውኝ ገቡ። ሰፊ ግቢ ነው። ግቢ ውስጥ ያሉት ቤቶች የድሮ ቤቶች ናቸው። ወለላቸው ጣውላ ነው። እዚያ ነው ይዘው ያቆዩኝ”።

ጎበዜ በቀጣይ ግን መርማሪ መጥቶ ጥያቄ እንዳቀረበለት ይናገራል።

“መርማሪው ሲመጣ ፊቴ ይሸፈናል” ያለው ጋዜጠኛ ጎበዜ፤ ጥያቄ ሲያቀርብለት ከነበረው ግለሰብ ሦስት ጉዳዮች በተደጋጋሚ ማንሳቱን ያስታውሳል።

“የመጀመሪያው አንተ ፋኖን ትደግፋለህ፤ የፋኖ አባል ነህ የሚል ነው። ሁለተኛ ደግሞ አንተ ኦሮሞ ጠል ነህ የሚል ነው። ሦስተኛው ደግሞ በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ እጅህ አለበት የሚል ነው” በማለት ያስረዳል።

ጋዜጠኛ ሲሳይ ጥያቄ ሲያቀርቡለት የነበሩት ጉዳዮች በመገናኛ ብዙሃኃን ከሚናገራቸው እና በማኅብራዊ ሚዲያዎች የሚጽፋቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ይናገራል።

ጎበዜ ተይዞ በነበረበት ወቅትም ስለያዙት ግለሰቦች ማንነት ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረና “አንዳንዴ መከላከያ ነን ይላሉ። መከላከያ እና ደኅንነት ተቀናጅተው እንደያዙኝም ይናገራሉ።”

ጋዜጠኛ ጎበዜ ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ ሲወጣ የአገር መከላከያ ሠሌዳ ባለው መኪና መወሰዱ እና ግለሰቦቹ መንገድ ይጠቆሙ የነበሩት ‘ጀነራል’ እያሉ በሚጠሩት ግለሰብ በመሆኑ ተይዞ የነበረው በአገር መከላከያ እንደሆነ እንደሚያምን ይገልጻል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ታስሮ በነበረበት ወቅት ምንም አይነት አካላዊ ጥቃት እንዳልተፈጸመበት እና የምግብ ችግር እንዳልነበረበት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ግንቦት 1/2014 ዓ.ም. ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ይዘውት የቆዩት ሰዎች ዓይኑን በጨርቅ አስረው መኖሪያ ቤቱ ጥለውት እንደሄዱ ተናግሯል።

ጎበዜ የያዙት ግለሰቦች ከመልቀቃቸው በፊት ” ‘እንደዚህ አይነት ሥራ አትስራ። አገራችንን የምንገነባው አንድ ላይ ነው። የትም ቦታ ብትሆን ከእኛ አታመልጥም።’ የሚል ማስፈራሪያ ምክር ያለበት ንግግር ተናግረውኛል” ይላል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ተይዞ የቆየበት ሁኔታ እና የቀረበበት ማስፈራሪያ ከሚዲያ ሥራው እንደማያዛንፈው ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ሊከታተሉኝ ይችላሉ። ቤተሰብ ጓደኛ ‘ተው ይቅርብህ’ በሚሉ ምክንያቶች ጫናዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ግን እኔን ወደ ኋላ አይመልሰኝም። በሚዲያ ሥራዬ እቀጥላለሁ።”

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከዚያም ደግሞ የኛ በሚባል ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሲሰራ ነበር።

ጋዜጠኛ ጎበዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው በገቡ ወቅት በፌስቡክ ገጹ በሚያጋራቸው መረጃዎች የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር።

በጉዳዩ ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ቢቢሲ እንደዘገበው።

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator