በሆሮ ጉድሩ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ እስካሁን 10 የሚሆኑ የገጠር ቀበሌዎች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ መያዛቸውን ተከትሎ መንገድ ከተዘጋ ስድስት ወር አልፏል።
የሽብር ቡድኑ በሚያደርገው ዘር ተኮር ደመ ነፍሳዊ እንቅስቃሴ የተነሳ በርካቶች በአማራዊ ማንነታቸው ብቻ ተገድለዋል፣ ተዘርፈዋል፤ ቤታቸው ተቃጥሏል፤ ባልና ሚስት፣ልጅ እና እናት ጎሳቸው ተቆጥሮ እንዲለያዩ ተደርጓል።
ከዚህም ባሻገር አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶች ወድመዋል፤ አባቶች ተገድለዋል፣ ተሳደዋል፤ ተዘርፈዋል፤ አብያተ ክርስቲያናት የወታደር ማሰልጠኛ እስከመሆን ደርሰዋል።
ከሁሉም በላይ ሽህዎች ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፤ አንዳች የሰብአዊ እርዳታ የሚያቀርብላቸው አካል እንዳልተገኘ እየተናገሩ ነው።
አሁን ላይ የፌደራል ፖሊስ የገባ ቢሆንም ተቋማት ግብአት ስለሌላቸው መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተለይ የጤና ተቋማት የመድሃኒት አቅርቦት ስለሌላቸው ክፉኛ መቸገራቸውን ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑና መሰሎቹ ምንም ዓይነት የመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት በተለይም ሸቀጣ ሸቀጥ ለአማራው እንዳይሸጥ ከልክለዋል ይላሉ።
በመሆኑም ኑሮአችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ የፌደራል መንግስት አንዳች መፍትሄ ያመጣ ዘንድ እንማጸናለን ብለዋል።