በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሞ ወረዳ ቦቃ በተባለ ቀበሌ ታህሳስ 6 ቀን 2014 ተኩስ ከፍቶ የፖሊስ አዛዡን ጨምሮ 5 በመግደል 3 የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎችን ያቆሰለው አሸባሪው ኦነግ ሸኔ በጥፋት መንገዱ እንደቀጠለ መሆኑ ተገልጧል።
ታህሳስ 7 ቀን 2014 ከንጋት ጀምሮ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ድረስ በአሙሩ እና በጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ በሚገኙ አዋሳኝ ቀበሌዎች በሚሊሾችና በህዝቡ ላይ ተኩስ መክፈቱ ተሰምቷል።
በአሙሩ ወረዳ ሲደን በርከሊ ቀበሌ እና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ለገሚጫ ቀበሌ እና ቂልጡ ጬካ ቀበሌ ላይ ነው ተኩስ የተከፈተው።
ታህሳስ 7 ቀን 2014 ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ኔትወርክ በመዘጋቱ ያለውን ሁኔታ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም።
ለሽብር ቡድኑም የአካባቢው ሚሊሾች እና ወጣቶች የአጸፋ ምላሽ እየሰጡ መሆኑ ተገልጧል።
ነገሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ መከላከያ ሰራዊት እና ልዩ ኃይል እንዲገባላቸው ተጠይቋል።
የሽብር ቡድኑ በተለይ የለገሜጫ ጫካን ለመያዝ አልሞ ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል፤ ስለደረሰው ጉዳት አሚማ የደረሰው መረጃ የለም።
ተኩስ የተከፈተባቸው ሶስቱ ቀበሌዎች አዋሳኝና በደን የተሸፈኑ ሲሆኑ ኦነጎች ከቦቃ ቀበሌ ሸሽተው ነው በእነዚህ አካባቢዎች ተኩስ የከፈቱት።
እየተፈናቀሉ ያሉ ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ሀርቡ ነጋሶ እና በቂልጡ ጭካ ቀበሌ ገምቦላ አካባቢ እየሸሹ ነው።