0 0
Read Time:4 Minute, 41 Second

________________________________________________________

(ልጅ ተድላ መላኩ)

ከመካከለኛው ዘመንና ከግራኝ ጦርነት በኋላ (የኢትዮጵያ መንግሥት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል በሥልጣኔው መውደም ዙፋኑን ለማትረፍ ከሸዋ ወደ ጎንደር ከዞረ በኋላ) ዘመናዊው የሽዋ አምሓራ መንግሥት በአቤቶ ነጋሢ ክርስቶስ (የሽዋ አምሓራ ልዑል) ጎንደር ላይ ይነግሥ በነበረው በአፄ ፋሲል የልጅ ልጅ ቀዳማዊ ኢያሱ (አዲያም ሰገድ) ዘመን፣ በአስራ ስድስት መቶዎቹ መጨረሻ ከንደገና ተጠናክሮ ይነሳል።

(ዙፋኑ ወደ ጎንደር ሳይዞርና በነ ይኩኖ አምላክ፣ ዐምደ ጽዮን፣ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ዙፋኑ ተጉለት፣ ደብረ ብርሐን፣ በረራ (አዲስ አበባ) በነበር ጊዜ የመላው ኢትዮጵያ ሰፊ መንግሥት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኃይል ዙፋኑ ባለበት በሽዋ ተከማችቶ፣ የወርቅ ክምር በየ ቤተክርስቲያኑ ይቀመጥ ነበር። የነዚህ ነገሥታትም ሐብትና ኃይል በዓለም ደረጃ እጅግ በጣም ታላቅና ገናና ነበር። ከግራኝ ጦርነትና ኦሮሞ ፍልሰት በኋላ ሙሉ በሙሉ ወድሞ ተወረረ። ዐረቦችና ሶማሌዎች ወርቁን ተከፋፈሉት።)

የልብነ ድንግል የሸዋ መንግሥት ከወደመ ከመቶ ሀምሳ ዓመት በኋላ በሽዋ የርሱ ዘር የሆነ ልዑል ይነሳል። ሥሙም ነጋሢ ክርስቶስ ይባላል። አቤቶ ነጋሢ ክርስቶስ ከአፄ ልብነ ድንግል አምስተኛ ትውልድ ዘር ሐረግ ላይ የነበርና የሽዋን መንግሥት ከደረሰበት ታላቅ ጥፋት ዳግም ለማንሳት የተነሳ ብርቱ ልዑል እና መሪ ነበር
— አፄ ልብነ ድንግል አቤቶ ያዕቆብን ይወልዳል፣ አቤቶ ያዕቆብ በግራኝ ጦርነት ጊዜ ወንድሙ ሚናስ የመን ሲወሰድና ታላቅ ወንድሙ በጠላት ሲገደል መንዝ ተሸሽጎ ነበር። አቤቶ ያዕቆብ በመንዝ ሆኖ ብዙ ልጆችን ይወልዳል። ከነሡ ውስጥ አቤቶ ሥግወ ቃል እና አቤቶ ግራም ፋሲል ነበሩ። ሥግወ ቃል የሽዋን አምሓራ ልዑላን ሰሎሞናዊ ሐረግ ሲጀምር፣ አቤቶ ግራም ፋሲል ደግሞ ከጎጃምና ከበጌምድር የጎንደርን አምሓራ ልዑላን ሰሎሞናዊ ሐረግ ይጀምራል። ሥግወ ቃል ወረደ ቃልን ይወልዳል፣ ወረደ ቃል ሰንበልትን ይወልዳል፣ ሰንበልት ነጋሢ ክርስቶስን ትወልዳለች። (ግራም ፋሲል አፄ ሱስኒዮስን ይወልዳል፣ አፄ ሱስኒዮስ ደግሞ አፄ ፋሲለደስን ይወልዳል)።

የአቤቶ ነጋሢ ክርስቶስ መንግሥት በመንዝ የተቆረቆረ ነበር። ዙፋኑንም በአያበር በመንዝና በይፋት መካከል አደርጎ ነበር። የነጋሢ ክርስቶስ መንግሥት እያደገ፣ ከልብነ ድንግል ጊዜ ጀምሮ በደቡብና ምስራቅ በኩል ሽዋ ላይ የተወረረውን መሬት የማስመለስ ታላቅ ውጊያ እያደረገ እየጠነከረ መጣ። አቤቶ ነጋሢ ክርስቶስ ሰባት ልጆችን ይወልዳል፣ እነሱም እያንዳንዱ በተለያዩ ሥሞች ይታወቃሉ። የነዚህም ልዑላን ዘሮች በሽዋ በየሥማቸው የነሱ ዘሮች ተብለው ይለያሉ (ከሰባቱ መካከል “አቃዋ”፣ “ዳኛ” እና ሌሎችም ሥሞች የነብሩአቸው ነበሩ — አካዋ አልጋወራሽ ነበር፣ ግን ከወንድሙ ከዳኛ ጋር ተዋግተው የነጋሢ ዙፋን ለስብስቴ ተላለፈ)።

አቤቶ ነጋሢ በመንዝ ዳግም የተቆረቆረውን የሸዋ መንግሥት ሰባት አመት መርቶ ካቀና እና ካለማ በኋላ ወደ ቀዳማዊ አፄ ኢያሱ ወደ ጎንደር ይሄዳል። እዚያም ንጉሠ ነገሥቱ መርዕድ አዝማች የሚለውን የሽዋ ንጉሣዊ ርዕስ ይሠጠዋል። ከአፄ ኢያሱ እጅ ላይ አስራ ሁለት ነጋሪት ለሹመቱ ይሸለማል። ግን ወደ ሽዋ ሳይመለስ በህመም ምክኒያት ይሞታል። ከነጋሢ ሰባት ልጆች መካከል ስብስቴ ወይንም ስብስቲያኖስ የነጋሢን የሽዋ መንግሥት ዙፋን ይወርሳል። እርሱም ከአያበርና ከአንኮበር ሽዋን ይገዛ ነበር። ይህም በአስራ ሰባት መቶዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር። የስብስቴን ዙፋን የርሱ ልጅ የሆነው አብዬ (ኪዳነ ቃል በሚለውም ሥም ይጠራል) ይወርሳል። በአብዬ ዘመን የሽዋ መንግሥት ከልብነ ድንግል በኋላ ሲፈርስ የተወረረውን ርስት ለማስመለስ አብዬ ከሽዋ፣ ዳግማዊ አፄ ኢያሱ ደግሞ ከጎንደር ተባብረው ተከላክለው ነበር። አብዬ ዙፋኑን በዶቃቂት አድርጎ ነበር። ሐር አምባንም አስመልሶ እዚያው በሰባት መቶዎቹ ማጋመሻ ላይ ርስት ለማስመለስ ከከረዩ ኦሮሞዎች ጋር እየተዋጋ ውጊያ ላይ አረፈ፤ እዚያውም ተቀበረ።

አብዬን ተከትሎ የርሱ ልጅ አምኃየስ የሸዋ ን መንግሥት ዙፋን ወረሰ። እርሱም እንዳባቶቹ ብርቱ እና ኃይለኛ ተዋጊ ነበር። የሕዝቡን ርስት ለማስመለስ ያባቶቹን ተጋድሎና ሃላፊነት ተረከበ። አምኃየስም ውጤታማ ሆኖ፣ ተጉለትን፣ ቡልጋን፣ ኤፍራታን፣ አስመልሶ በሽዋ መንግሥት ውስጥ ዳግም አጠቃለላቸው። ከከረዩ እና አቢቹ ኦሮሞዎች ጋር ውጊያ እያደረገ ብዙ ርስት አስመለሰ። አስቲት ያሉትንም ቅዱስ ጊዮርጊስንና ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያኖች (ከልብነ ድንግል በህዋላ ተወረው) አገኛቸው። በደብረ ብርሃንና በአንኮበር መካከልም የተወሰደው መሬት ተመልሶ በአምሓሮች እንደገና ተያዘ። በዚህ ታላቅ ውጤታማነቱ የጎንደር መንግሥት እንዲመጣ ጋበዘው፣ እንደ ታላቅ ንጉሥም በህዝቡ ታየ። የሽዋን መንግሥት ዳግም ታላቅ አደረገው። ልጁንም አስፋ ወሰን ብሎ ሰየመው። እርሱም እንደሥሙ አባቱ ያሰፋውን ወሰን እርሱ እጥፍ ያደርገዋል። ከአምኃየስ በኋላ የርሱ ልጅ አስፋ ወሰን በሽዋ መንግሥት በአስራ ሰባት ሰባ ዓመተ ምህረት ሥልጣን ያዘ።

በአስፋ ወሰን መንዝ፣ ይፋት፣ መርሐቤቴ እና አንኮበር ሙሉ በሙሉ ተመልሰው ተጠቃለሉ። እነዚህም ቦታዎች ዛሬ ካሉት በጣም ይሰፉ ነበር። ለምሳሌ አንኮበር ቡልጋን እና ደብረ ብርሃንን ያጠቃልል ነበር። መርሐቤቴ ግሼንና ሞረትን ያጠቃልል ነበር። አስፋ ወሰን በሐብትና በሥልጣን በጣም እያየለ መጣ። በዚህ ዘመን አበጋዞች በየግዛቶቹ እየተሾሙ ሥርዐታዊ ለውጦችን በሽዋ መንግሥት አካሄዱ። ከአስፋ ወሰን ሞት (በአስራ ስምንት መቶ ሁለት ገደማ) በኋላ የአስፋ ወሰንን ዙፋን የርሱ ልጅ ወሰን ሰገድ ወረሰ።

የወሰን ሰገድ መንግሥት እጅግ ተራማጅ መንግሥት ነበር። ባህላዊና ፖለቲካዊ ብልጽግናን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን አጸደቀ። ሃይማኖታዊ መከባብርንም በፖሊሲ መልክ አስቀመጠ። ሹሞችም ክርስቲያን፣ ሙስሊምና ሌሎችም አብረው የሚሠሩበትን ተራማጅ ሕግ አረቀቀ። በይፋትና አጎባ ሙስሊም መሪዎችን ሾመ። ወሰን ሰገድ ራስ የሚለውን ሥልጣን ይዞ ከትግሬው ገዥ ራስ ወልደ ሥላሴ ጋር ተባብሮ ወራሪዎችን እያጠቃ ተከላከለ። በዚህም ዝናው በመላው አገሪቱ ተሰምቶ ወደ መላው መንግሥት ግንባር ቀደም ፖለቲካዊ መድረክ መጣ። በዚህ ሂዴት ላይ ጠላቶች አፍርቶ ነበርና በሴራ ግድያ ተፈጸመበት። ይህን ተከትሎ የወሰን ሰገድን አልጋ የርሱ ልጅ ሣሕለ ሥላሴ ወረሰ።

ሣሕለ ሥላሴ በወጣትነት የሸዋን መንግሥት ዙፋን ተረክቦ በብልሃት፣ በጉብዝና እና በጽኑ መርህ ለረዥም ዘመናት ነገሠ። ከአያቶቹ የተረከበውን መንግሥት በይበልጥ ገናና አደረገው። በርሱ ዘመን የሽዋ ሕዝብ በልብነ ድንግል የነበረውን የሽዋ መንግሥት ወሰን ሙሉ በሙሉ ይመለስልን ብሎ እምነቱን ገለጸ። ብሄራዊ ርዕዮተዓለምን ከኢኮኖሚያዊ ሥነ መንግሥት ጋር ያዋቀረ የአመራር ስልት ነደፈ። ሣህለ ሥላሴ የህዝቡን ጥያቄ የሽዋን መንግሥት ወሰን እስከ አዋሽ ድረስ በማስመለስ መለሰ። ንጉሥ የሚለውንም የሥልጣን ርዕስ ተሰጠ። የአቢቹ ኦሮሞዎች ከቱለማ ኦሮሞዎች ጋር እየተገዳደሉ የሣህለ ሥላሴን እርዳታ ፈለጉ። ደብረ ብርሐንም በኦሮሞ ጥቃት ነደደች። የሽዋ መንግሥት ይህን በሣሀል ሥላሴ መሪነት ተከላከለ። በኢትዮጵያ የሣህለ ሥላሴ ፍትሐዊነትና ፖለቲካዊ ተራማጅነትና ብልሃት ታወቀ። ለድሆችና ለመላው የሽዋ ሕዝብ ሩኅሩኅና በጎ አሳቢነቱ ይታወሳል። ንጉሥ ሣህለ ሥላሴም አልጋውን ከልጆቹ አንዱ ለሆነው ለኃይለ መለኮት አውርሶ ሞተ።

ኃይለ መለኮት አፄ ቴዎድሮስ ሊነግሥ አካባቢ ነገሠ። ኃይለ መለኮት በሸዋ ቤተመንግሥት የምትኖርን እጅጋየሁ የምትባል ልጅ ከርሱ አርግዛ ነበርና በንግሥት በዛብሽ ጣልቃ ገብነት በጋብቻ ሥርዐት እንዲጣመሩ ሆነ። ንጉሥ ሣሕለ ሥላሴም ሳይሞቱ በፊት ይህን ለማየት በቅተው ነበርና ከልጃቸው ከኃይለ መለኮት የተወለደውን ሣሕለ ማሪያም “ምኒልክ” ብለውታል። የአፄ ምኒልክ ዜናመዋዕል ጸሐፊ ገብረ ሥላሴ የምኒልክን እናት እጅጋየሁን ከጨዋ ቤተሰብ የተወለደች፣ ብሩህ ስብዕና ያላትና ሃይማኖተኛ መሆንዋን ጽፈዋል። ሣሕለ ማሪያምም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ተብሎ ዘውድ ከደፋ በኋላ ያባቶቹን የሽዋ አምሓራ ልዑላን ሀላፊነትና ክብር ተረክቦ የሽዋን መንግሥት ርስት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያን መንግሥት ርስት ከተወረረው መሬት ያስመልሳል። መንግሥታዊ ማዕከሉንም በልብነ ድንግል በነበረው በበረራ፣ አዲስ አበባ ብሎ ዳግም ይሽዋ አምሓራን ጥንታዊ ርስትና ክብር ያስመልሳል። የአውሮፓ ኢምፒሪያሊስት ጣሊያን ወራሪ ኃይሎችንም ድባቅ ይመታል፤ የሕዝቡንም ታላቅነት ለዓለም ያስመሰክራል።

ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ!!!


About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator