0 0
Read Time:4 Minute, 9 Second

ከ “ሃሌታ ሚድያ” (ሀሌታ ሚዲያ Haleta Media) ጀርባ ተደብቆ የሚጽፈው ግለሰብ ‘ተድላ የሚጽፈው ጽሑፍ ታሪክ ይሁን ተረት የታሪክ ምሑራን ያስተካክሉታል’ ሲል ጽሑፉን ጀምሮአል። እንግድህ የታሪክ ምሑራን ማን ናቸው፤ (አንዱ የታሪክ ምሑር ከሌላው የታሪክ ምሑር ተሽሎ ያንዱን የሚያርመው በምን መንገድ ነው?)፤ በማስረጃ ነው። አንድ የታሪክም ሆነ ማንኛውም ምሑር ሳይንሳዊ ያጠናን መንገዶችን ተከትሎና ተአማኒነት ያላቸውን ማስረጃዎች አስደግፎ ሲጽፍ እውነት ወይንም ተረት መሆኑን ለማወቅ ያጠናን ዘዴውን እና የሚያቀርባቸውን ማስረጃዎች እንጂ ሌሎች ምሑራን የሚያዩት ጽሓፊው የጻፈውን ጽሑፍ እነሱ አራሚ ወይንም ተስማሚ ነን ስላሉ ጸሓፊው የጻፈው ታሪክ እውነትነት ወይንም ተረት ተረትነት አይገመገምም።

ይህ የተሳሳተና ቅንነት የሌለበት ኢምሑራዊ አስተሳሰብ ደግሞ በሦስተኝነት በምጠቅሰው የሥነ አምክንዮ ግድፈት (logical fallacy) ሚዛን ውድቅ የሚሆን ነው (እስካሁን ይህ ግለሰብ Ad Hominem እና Straw Man የሚባሉትን የሥነ አመክንዮ ግድፈቶች መፈጸሙን አሳይቼአለሁ። ይህ ሶስተኛ ያስተሳሰብ ስሕተት ወይንም ያመክንዮ ግድፈት (Appeal to Authority / argumentum ad verecundiam) ይባላል። ይህ ደግሞ ያንድን መረጃ እውነትነት በቀረቡት ማስረጃዎች መዝኖ እንደ ማየት ፈንታ ሌሎች ምሑራንን ጠቅሶ ከሌ ወይንም ከሌ ልክ ነው ካሉ ልክ ነው፤ እነሱ ልክ አይደለም ካሉ ደግሞ ልክ አይደለም የሚል ኢምሑራዊ አስተሳሰብ ነው (ይህ ሳያንስ ግለሰቡ እንደ አራሚና አስተካካይ አድርጎ ያቀረባቸው የእኔ አካባቢ የሚላቸውን ሰዎች ነው)።

ይልቅ ሳይንሳዊ ታሪክ ሲጽፍ አይተነው የማናውቀውን በውቀቱ ስዩምን የተድላን ታሪክ እውነትና ውሸቱን ያርማል ብሎ ጠቅሶአል። ይህ እጅግ አስቂኝ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሌሎች የጠቀሳቸው ሁለት የታሪክ አጥኚና ምሑራን አቻምየለህ ታምሩና ዶክተር ሐብታሙ ናቸው። አቻምየለህ ታምሩ በቅርበት እየተነጋገርን፣ መረጃ እየተለዋወጥን የምንጽፍ (አቅማችንን የምንተዋወቅና እንደ ወንድም የምንከባበር) ሰዎች ነን። ዾክተር ሃብታሙም እንዲሁ፤ በራራ ለሚለው መጽሓፋቸው ሪቪው እንደምጽፍላቸው ቃል ተገባብተን ነው (አሁን በቀናት ውስጥ ስለጻፉት በማስረጃ የተሞላ ድንቅ መጽሓፍ ሪቪው እጽፋለሁ)። ከዚያ በተረፈ ከሀሌታ ሚድያ ጀርባ ተደብቆ የሚጽፈው ግለሰብ ምሑራዊ ሜቶዶሎጂዎችን አያውቃቸውም። ቢያውቃቸውና አንብቦ የተጻፈውን ነገር የመረዳት አቅም ቢኖረው እነ በውቀቱ ስዩም እውነት ወይንም ተረት መሆኑን ይወስኑ ብሎ አመክንዮአዊ ግድፈት አይፈጽምም ነበር።

በተጨማሪም ይህ ግለሰብ ተድላ ለአማራ ጥቅም ሳይሆን ለዘውድ ነው የሚታገለው ብሎ ጽፎአል። ትልቁ ስሕተቱ ለአማራ ጥቅም መታገልንና ለዘውድ መታገልን እንደ ተቃራኒ (mutually exclusive) ነገሮች አድርጎ ማቅረቡ ነው። ልጅ ተድላ ለአማራ ጥቅም መታገሉንና አለመታገሉን ለማወቅ ተድላ ስለ ዘውድ ጻፈ ወይንም አልጻፈም አይደለም ሚዛን የሚሆነው። ተድላ አማራን የሚጠቅም ነገር ሰርቶአል ወይ ነው። እንግድህ፤ እኔ ላለፉት አራት እና አምስት አመታት የአማራን ሕዝብ ታሪክ እና ፖለቲካ በሳይንሳዊ ማስረጃ የተሞላ እጅግ አልፊ መጽሓፍ (ክብረ አምሓራ) ከመጻፍም በላይ አሁን ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ሥራዎችን ሥሰራ ቆይቼአለሁ፤ ይህን ሕዝብ ራሱ ስለሚያውቀው መናገር አይጠበቅብኝም። ከዚያ በተጨማሪ አማራን ይጠቅማሉ የምንላቸውን ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ደከመን ሳንል ሠርተናል። አሁን ለምን ተድላ ዘውድ ለሕዝብ ይጠቅማል ብሎ (እንደማንኛውም ሥርዓት ወይንም ሲስተም) ጥናታዊ ጽሑፍ ጽፎ አቀረበ፣ ለምን ተድላ ዘውዳዊነት የሕዝባችን ክብር እና አገር በቀል ሥርዓት ነው ብሎ ሞገተ፤ ለምን ተድላ በዘውድ አደራጃለሁ አለ ብሎ ልክ ይህ ምግባር ለ አማራ ከመታገል ጋር ተቃራኒ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ እጅግ የወረደ እና ኢምሑራዊ አስተሳሰብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በተጨማሪም ተድላ አማራን “exploit” ለማድረግ ነው ዘውዳዊ ሥርዓትን የሚሰብከው፣ ማቆም አለበት ብሎ ጽፎአል። ሲጀመር ሕዝብን መጠቀም (exploit ማድረግ) ማለት እኮ ሕዝብን ለራስ ጥቅም ማዋል ማለት ነው። እስኪ ሕዝብን ለራሳችን ጥቅም ያዋልነው በምን መንገድ እንደሆነ ይነገረን። ይህን ሁሉ ውድ ጊዜአችንን እና ወጣትነታችንን መስዋዕት አድርገን በነጻ የምንሠራው እኮ ለሕዝብ ጥቅም ነው። ሕዝብም እንዲከተለን አላስገደድነውም። ሓሳባችንን መርምሮ እና ትክክለኝነቱን አምኖበት የሚከተለንን ሕዝብ ‘በሴራ ተጠቀማችሁበት’ ብሎ ክስ ማቅረብ ሕዝብን መሳደብ ነው። ሕዝብ የሚመርጠውን አያውቅም የማለት ፀረ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው። አምባገነንነትም ነው።

የአማራ ትግል የዴሞክራሲ ትግል እንጂ የዘውድ ትግል አይደለም ብሎ ግለሰቡ ጽፎአል። ይህ ሲጀመር ሕዝቡን እኔ አውቅልሃለሁ ማለት ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ሰዎች ይጠቅማል የሚሉትን ሥርዓት በነጻነት የመስበክ መብታቸው የሚጠበቅበት ሥርዓት እንጅ “እኔ እጠላዋለሁ” የምትለውን ሥርዓት የሚያራምዱን መብታቸውን በዲሞክራሲ ሥም መከልከል ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ነው። በዚያ ላይ ግለሰቡ አሁንም ዘመናዊ የዘውድ ሥርዓት ምን እንደሆነ አያውቅም። ምንም ግንዛቤ ዬለውም። እንደ ምሑር ጥናታዊ ጽሑፉን እንኳ አንብቦ የመረዳትና የመተቸት አቅም የለውም። ፓርላመንታዊ የዘውድ ሥርዓት (parliamentary Monarchy) ዲሞክራሲን ከማንኛውም ሥርዓት በላይ እንደሚያጠናክርና ዘመናዊ የዘውድ መንግሥታት ሙስና የሌለባቸውና ኃያል ኢኮኖሚ ያላቸው መሆኑን ጥናታዊ ጽሑፉን ቢያነበው ድንገት ይገባው ነበር። ግን እርሱን ለመጻፍ ያነሳሳው ጥላቻ እንጅ እውቀት ስላለሆነ ምንም አይጠበቅም።

በዚህ ዘመን በደም ሳይሆን በእውቀት ነው ሃገር መመራት ያለበት ብሎም ጽፎአል። ሀገር ሁልጊዜም በእውቀት ነው የሚመራው። በድሮው ዘመን በዘውድ ሥርዓት ኢትዮጵያ በእውቀት ነበር የምትመራው። በሥርዓተ መንግሥት፣ በፍትሐ ነገሥት፣ በሊቃውንት አማካሪነት ነበር የምትተዳደረው። ዛሬም በዘመናዊ የዘውድ ሥርዓት ፓርላማዊ ዲሞክራቲክ ምርጫዎችን ማካሄድ፤ ሁሉም የተማሩ ሰዎች በትምሕርታቸው ዘርፍ እየተሳሰተፉ መምራት የሚያግዳቸው ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥ የተጀመረው በዘውድ ፓርላማዊ ሥርዓት ነው። እነ ፅሓፌ ትእዛዝ አክሊሉ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ነበሩ። ወደ ሥልጣን የመጡት በደማቸው ሳይሆን በእወቀታቸውና በምርጫ ነበር። ስለዚህ አሁንም ይህ ክስ ውሃ አይቋጥርም። ይልቅ ደማዊ የንግሥና ባሕሉ ጥንታዊነትን እና ሃገራዊ ቀጣይነት የሚያመለክት ነው። የብዙ ነገሮች ምልክት ነው ። እንደ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ስፔን እና ዴንማርክ ያሉ ዘመናዊ የዘውድ መንግሥታትም ይህን የሚጠቀሙበት ምክኒያት ይህ ነው (እርሱን በሌላ ጊዜ እንተነትነዋለን)። ቅንነት የሌላቸው፣ ምሑራዊ ያልሆኑና ልባቸው ውስጥ ያለውን ክፋት በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያዩ ከንቱ ሰዎች ፖለቲካውን ካላቦካነው እያሉ አምባገነናዊ አስተሳሰባቸውን እስካራመዱና የሰዎችን ሓሳብ እንደመሞገት የሰውን ስብዕና ለማጥቃት እስከተነሱ ድረስ እንደ ሕዝብ ብዙ ርቀት መሄድ አንችልም። ይቆሸሹ አስተሳሰቦች እስካልተጸዱ ድረስና ከካድሬነት ተወጥቶ ምሑራዊነት ባሕል ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ የሕዝባችንን ትንሳኤ የውስጥ ጠላቶች አርቀው ይቀብሩበታል።

በመጨረሻም ሃሌታ ሚድያ ከታች የሚታየውን የእኔን (የልጅ ተድላ) ፎቶ ለጥፎ ብዙ “ላይክ” መሰብሰብ ችሎአል። አብዛኛው ሰው ፎቶውን እንጅ ጽሑፉን ላይክ ያደረገው አይመስልም። ከታች አማራውም እውነታውን ስለሚያውቅ አጸፋውን በኮሜንት መልሶአል። የግለሰቡን አስተሳሰብ የሚከተሉት አብዛኛዎቹ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ሆነውም ተገኝተዋል።እኔን ያዋረደ መስሎት እያዋረደ ያለው የሕዝብን ታሪካዊ ተቋማት መሆኑንም ሊነገረው ይገባል።

አግርር ፀሮ ታሕተ እገሪሁ!!!

ልጅ ተድላ መላኩ ከ የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ጉባኤ

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator