ጌጥዬ ያለው (በአባ ሳሙኤል እስር ቤት የተፃፈ፣ ቅዳሜ ዕለት በፍትህ መፅሄት የወጣ)

ወያኔ ከደደቢት በረሃ ተምዘግዝጎ እምዬ ምንሊክ ቤተ-መንግሥት ሲገባ፣ ከእነ ዋለልኝ መኮንን እና ምዕራባዊ ጌቶቹ የተማረውን ሰው ጠል እና ሰው ፈጅ ፖለቲካ ለማዋቀርም ሆነ የተለያዩ ብሔሮችን የሚወክሉ ዘረኛ ፓርቲዎችን እንደ ችግኝ ማፍላቱ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ አስቀድሞ በግንባር ስም የመሰረተው፣ ነገር ግን በሕወሓት የበላይነት የሚዘወረው ኢሕአዴግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዚህ ወቅትም ነው፣ የትግራዩ ቡድን ‹ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያገናኘኛል› በሚል ተስፋ ባልንጀራ አድርጎት ከነበረው ኦነግ ጋር፣ በጠመንጃ የሚፈላለግ ባላጋራ የሆነው፡፡ ይሁንና፣ እነ መለስ ዜናዊ “ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ሲሰበር፣ በአንዱ ተንጠላጠል፤” በሚለው ነባር መርሃቸው መሰረት፣ በ1982 ዓ.ም ከተለያዩ ፓርቲዎች እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረጓቸው ውጊያዎች የማረኳቸውን ጨምሮ፤ በሻዕቢያ የምርኮኛ ካምፕ ታስረው የነበሩትን ኦሮሞ ወታደሮች አሰባስበው፣ መጀመሪያ በኢሕዴን ስር እንዲዋጉ ካደረጉ በኋላ፤ ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ “የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)” የተሰኘ ተለጣፊ የፖለቲካ ቡድን የዐማራ አፅመ ርስት በሆነችው የሸዋ ደራ ከተማ ላይ እንዲመሰረቱ አድርገዋል፡፡

እንግዲህ፣ ይህ የምርኮኞች ስብስብ እርሾ የሆነው ድርጅት ነው፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ጠልፎ በብልፅግና ስም ፍፁማዊ የሥልጣን የበላይነት የያዘው፡፡ በርግጥ፣ በዚህ አቋራጭ መንገድ ሾልኩ አራት ኪሎን እንዲጠቀልል የብአዴን አስተዋፅኦም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ በገሃድ ይታወቃል፡፡ መቼም፣ ጠቅላይ ሚንስትር የነበረው ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፍቃዱ ሥልጣን መልቀቁን ተከትሎ፣ ለኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርነት በተደረገው ምርጫ፣ የብአዴን ሊቀ-መንበር ደመቀ መኮንን ከውድድሩ ራሱን አግልሎ፣ የኢሕዴዱ ሊቀ-መንበር ዐቢይ አህመድ እንዲሚረጥ ማድረጉን ራሳቸው በሚዲያ ተናገሩት ሃቅ ነው፡፡

#ፋሽዝምበአዲስአበባ

በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል በተቆጣጠረችበት ጊዜ፣ የወረራ አስተሳሰቡን ሲመራ የነበረው የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ “ፋሽስት” የሚል መጠሪያ እንደነበረው ይታወሳል፡፡ ይህ በዱቼ ሞሶሎኒ የሚመራ ወራሪ እና ቅኝ ገዢ ኃይል ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር፤ የተከተለው ሁለተኛው አማራጭ ኢትዮጵያውያንን ራሳቸውን በብሔር አስተሳሰቦች በመከፋፈል፣ አገር በቀል ፋሽስቶች ከውስጣቸው እንዲፈጠሩ እና እርስ በርስ እንዲጨፋጨፉ ማድረግ ላይ የሚያውጠነጥን ስልት ነው፡፡ ሰይጣናዊ አስተሳሰቡን ወደ መሬት በማውረዱ ረገድም ከጣልያን በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያን ለማጥቃትና ለማዳከም ሲያሴሩ የነበሩ ሌሎች የውጭ ኃይሎች እና የዐድዋ ፖለቲካ ያከሰራቸው ምዕራባውያን እጅ በስፋት መነከሩ ይታወቃል፡፡
በጥቅሉ፣ ዋለልኝ መኮንን በ5 ገጽ ቀንብቦ ካቀረበው አገር አፍራሽ ሃሳብ ጀምሮ የገንጣይ አስገንጣዮቹ የእነ ሻዕቢያ እና ጀብሃ ምስረታም ሆነ የዘረኞቹ ኦነግ እና ወያኔ መፈጠር፣ በኋላም የእነ ኦሕዴድ መበጀት ጥንስሱ ከዚህ እንደሚጀምር ልብ ይሏል፡፡

ዛሬ የአዲስ አበባን ወጣቶች በገፍ እያፈነ ያለው ኦሕዴድ/ብልፅግናም የጥፋት ህልዮቱን በስሁት ትርክት የቀመረው፣ እነዚህን አገራት ጨምሮ፤ ከኢትዮጵያ አብራክ የወጡት የእናት ጡት ነካሾቹ ወያኔ፣ ኦነግ እና የመሳሰሉት ቡድኖች የሄዱበትን መንገድ በመከተል ነው፡፡ ከእዚህ አኳያም ይመስለኛል፣ ኦሕዴድ ከቀደሙት ቡድኖችም የከፋ ፋሽዝዝምን (በተለይ በአዲስ አበባ) እና ከፋፋይ የፖለቲካ አስተዳደርን ማስፈኑ፣ ውሃ እንደ መጠጣት የቀለለው፡፡ ይህ ሁኔታም በጊዜ አንዳች መፍትሄ ሳይበጅለት በምንግዴ ማየቱ ከቀጠለ፣ ከከተማዋ አልፎ መላ አገሪቱን የማጥፋቱን አይቀሬነት ከወዲሁ ለመናገር የነብይነት ፀጋን አይጠይቅም፡፡

በነገራችን ላይ፣ አቶ እስክንድር ነጋ ከ3 ዐመት በፊት “ለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?” በሚል ዐውድ ሕዝባዊ ውይይት የጠራው፣ ኦሕዴድ እየሄደበት ያለውን አውዳሚ መንገድ ቀድሞ በመረዳቱ ነው፡፡ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ካነሳሁ አይቀር፣ ለዚያ ውይይት መነሾ የሆነውን ቆስቋሽ ምክንያትም በዐዲስ መስመር ጠቅሼው አልፋለሁ፡፡
ጊዜው መንግሥት ሽብርተኛነቱን አምኖ ይቅርታ የጠየቀበት እና ዛሬ እንደ ጉም ተኖ ቢጠፋም፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘበት ነበር፡፡ ለዐመታት ደም የተቃቡ የኦሮሞ ፖለቲከኞችም አንዱ የሌላውን ጎፈሬ የሚያበጥሩበት የጫጉላ ዘመን ሆኖ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ግና፣ ይህ ፍቅራቸው ብዙም ባለመሰንበቱ፤ ገሚሱ ጎፈሬውን እየተላጨ ከርቸሌ ሲገባ፤ የተቀረው ደግሞ የጣለውን ነፍጥ ለማንሳት ወደ ዱሩ ተመልሷል፡፡ በርግጥ፣ የቁም እስረኛ የተደረገም አለ፡፡ ምን ለማለት ነው? የእነ ባሮ ቱምሳ የመገዳደል ዘመን፣ አሁንም በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ባህል ሆኖ ቀጥሏል፡፡

እዚህ ጋ መዘንጋት የሌለበት ጥሬ ሃቅ፣ ገዳይ እና ሟች በአዲስ አበባ ጉዳይም ሆነ የአንድ ብሔር የተናጥል የበላይነትን በማስፈኑ ረገድ ቅንጣት ልዩነት የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ነው፣ በአንድ ወቅት አምስት የኦሮሞ ድርጅቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ፡- አዲስ አበባ በታሪክ፣ በሥነ-ልቦና እና በሕግ የኦሮሞ ብቻ እንደሆነች ያለ አንዳች ይሉኝታ በግላጭ የለፈፉት፡፡ በዚህም፣ ምዕራባውያን በርሊን ላይ ሆነው አፍሪካን ለመቀራመት እንደተዋዋሉት ሁሉ፤ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ልሂቃንም እዚሁ መሀል አዲስ አበባ ካዛንቺስ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ተቀምጠው፣ የመላው ኢትዮጵያውያን እና የዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብ መኖሪያ የሆነችውን አዲስ አበባ ለመሰልቀጥ ከመዶለት አልፈው፤ በመገናኛ ብዙሃን በይፋ አውጀዋል፡፡

በአጭሩ፣ በዘመነ ብልፅግና የአዲስ አበባ ፋሽዝም ተግባራዊ መደረግ የጀመረው እዚህ ጋ ነው፡፡
እስክንድር ነጋ “ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ”ን አዋልዶ ወደ ትግል እንዲገባ የገፋውም ይህ ኹነት ነው፡፡ መቼም፣ ባልደራስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመስርቶ፣ ከተማይቱን ለመጠቅለል የሚደረገውን ሩጫ እግር በእግር እየተከተለ ባያጋልጥና ባይታገል ኖሮ፤ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ የሚደርሰው ችግር፣ ከመቼውም ጊዜ የከፋ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ይህም ሆኖ፣ አዲስ አበባ ታቦታቸውን አጅበው ጥምቀት የሚያከብሩ መእምናን በኦሮሞ ፖሊስ የሚገደሉባት፣ በከተማዋ የሚኖሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች በስናይፐር የሚረግፉባት፣ ወጣቶች በሰበብ አስባቡ እየታፈሱ ከአባ ሳሙኤል ወህኒ ቤት እስከ ጦላይ በግፍ የሚታሰሩባት… መሆኗ አይካድም፡፡
በዚህ ዐውድ፣ የአራት ዐመቱን የኦሕዴድ/ብልፅግና ፋሽስታዊ ወረራ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጽመውን መጠነ-ሰፊ እስር ልዘረዝር ብል ገፅ ስለማይበቃኝ፣ ሰሞነኛው የአዲስ አበባ ወጣቶች አፈና ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡

የአዲስአበባወጣቶችአፈና

በኦሮሞ ፖለቲከኞች ፍፁማዊ የበላይነት የሚዘወረው ብልፅግና ከሩቅ ከሚለይባቸው ምልክቶቹ መካከል ዋነኛው በራሱ ታሪክ የሚያፍር እና የኢትዮጵያን ታሪክ አምርሮ የሚጠላ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ከስያሜው ጀምሮ ራሱን እንደ እስስት ሲለዋውጥ የሚስተዋለው፡፡ ተለዋዋጭነቱን ሳስብ ደግሞ፣ በዳግማዊ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት በየገበያው እየተዘዋወሩ የሚሰርቁ ሌቦች የደረሰባቸውን ቅጣት ያስታውሰኛል፡፡ እነዚህ ሌቦች በተደጋጋሚ አፈ ንጉሥ ነሲቡ መስቀሉ ዘንድ ተይዘው እየቀረቡ በሕግ ቢዳኙም፤ ስርቆታቸውን አላቆም አሉ፡፡ ይህንን የተረዱት አፈ ንጉሥም፣ በእሳቸው ችሎት ጥፋተኛ መሆናቸው የተረጋገጠባቸው ሌቦች በሙሉ በውቅራት መልክ ግንባራቸው ላይ ጌጠኛ ምልክት እንዲደረግባቸው አዘዙ፡፡ ነገሩ፣ ሰው ሌባ መሆናቸውን አውቆ ምልክቱ ያለበት ግለሰብ ሲመጣ አስቀድሞ እንዲጠነቀቅ ለማድረግ ነበር፡፡ ሌቦቹ ግን ግንባራቸው ላይ ሻሽ በመጠምጠም ምልክቱን ደብቀው ስርቆታቸውን ቀጠሉ፡፡ አሁንም ጉዳዩ አፈ ንጉሥ ነሲቡ ዘንድ በመሰማቱ፣ ምልክቱ ከግንባራቸው ጀምሮ አፍንጫቸው ድረስ እንዲወርድ ተደረገ፡፡

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥትንም በደንብ ስንመረምረው ታሪክ ጠልነቱን የሚያስረግጥ ምልክት እንዲህ በጉልህ የምናገኝበት መሆኑ ለክርክር አይቀርብም፡፡ መንግሥታቸው፣ በተለይ ‘የዐማራ ነው’ ብሎ የሚያስበውን ታሪክ በመጥላት ብቻ ሳይወሰን፤ እየተከታተለ ለማጥፋት ታጥቆ ተነስቷል፡፡ ለዚህም ነው፣ የዐድዋ እና የካራማራ የድል በዓላትን ያከበሩ የአዲስ አበባ ወጣቶችን በገፍ አስሮ ዛሬ ድረስ እያንገላታ ያለው፡፡

የክሱ ጭብጥ ደግሞ የበለጠ አስቂኝ ነው፡፡ ‹በሁለቱ የድል በዓላት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን እና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስም በመጥቀስ ተሳድባችኋል› የሚል ነው፡፡ ይሁንና፣ ከንቲባዋም ሆኑ ሌሎች ባለሥልጣናት ተሰድበው ቢሆን እንኳ፣ መክሰስ ያለባቸው ራሳቸው እንጂ፤ የግል ተበዳይ አቤቱታ ባላቀረበበት ሁኔታ፣ ፖሊስ ብቻውን የሚከስበት ሕጋዊ አግባብነት እንደሌለው በተለያዩ መዝገቦች እየተዘዋወሩ በግፍ ለታሰሩ ወጣቶች የሚከራከሩት ጠበቆቹ፡- ቤተማርያም አለማየሁ፣ ሔኖክ አክሊሉ እና ሰሎሞን ገዛኸኝ ሲሞግቱ፤ “ስድብ” የሚለውን ክስ ትተው፣ “ሕዝብን በመንግሥት ላይ ማሳመጽ፣ ብሔርን ከብሔር እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማጋጨት” በሚል ዐዲስ የፈጠራ ክስ ቀይረውታል፡፡ ነገር ግን፣ መርማሪ ፖሊሶች እየተቀያየሩ ችሎት ሲቀርቡ፣ ክሱም አብሮ ይቀያየርና፤ በየመሀሉ የመጀመሪያው ክስ በአዳነች አቤቤ ስም ታጅቦ ብቅ ማለቱ አልቀረም፡፡ ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ “…በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ ማሰብ” የሚለው ውንጀላ ነው፡፡ ልብ በሉ! የተከሰስንበት ወንጀል ‹የዐድዋ እና የካራማራ የድል በዓላት በሰላም እንዳይጠናቀቁ ማድረግ ወይም መሞከር› የሚል ሳይሆን፤ ‹ማሰብ› የሚል ነው፡፡

መቼም፣ ፖሊስ እንደ ዘንድሮ አዕምሯችንን ከፍቶ መክደኑ፣ የፊጥኝ አስሮ ቤታችንን እንደ መበርበር ቀሎት የታየበት ጊዜ ስለመኖሩ አላስታውስም። ለመሆኑ ግን፣ አዳነች አቤቤ ተሳድበው ቢሆንስ፣ ከ135 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጅምላ ለወራት የሚያሳስር ወንጀል ነው እንዴ? እስሩስ ዐማሮች እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ላይ ብቻ ማነጣጠር ነበረበት? በኢትዮጵያ ታሪክ የተሰደቡ ባለሥልጣንስ እሳቸው ብቻ ናቸው? ኧረ በፍፁም፡፡ ለማሳያ ይሆን ዘንድ ለሰማይ ለምድር የከበዱትን የንጉሠ-ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ተሞክሮ ልጥቀስ፡፡ ጃንሆይ እንኳንስ በአካል ታይተው፣ ጥላቸውም ብቻውን የሚታፈር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆነ፣ በእነ ዋለልኝ መኮንን እና ጥላሁን ግዛው የሚመሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በተደጋጋሚ በግላጭ ይዘልፏቸው ነበር፡፡

በግልፍተኝነት የወሰዱት የጅምላ ርምጃ ግን የለም፡፡
እዚህ ላይ፣ ከ1953 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የተከሰተው ጉዳይ የወቅቱ የፍትሕ ሥርዐት ምን ያህል ኃላፊነት የሚሰማው እንደነበረ አመላካች መሆኑን የሚያስረግጥ አንድ ማሳያን ከብርሃኑ አስረስ “ማን ይናገር የነበረ… የታኀሣሡ ግርግር እና መዘዙ” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ አስታውሰን እንለፍ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንድ የድሬዳዋ ወጣት በእነ ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ መዝገብ ተከሶ አዲስ አበባ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ወጣቱ የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ዜና ድሬዳዋ ላይ ሲሰማ ደስ ብሎት ጃንሆይን በመዝለፉ ነው የተከሰሰው፡፡ ችሎት በቀረበ ጊዜም ዳኛው “ስድብ” የተባለውን ቃል ደግመው ለመጥራት እጅግ በጣም ከብዷቸው፣ በደፈናው፡- “የተጠረጠርህበትን ወንጀል ፈጽመሀል ወይ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ ወጣቱም፡- “የምን ወንጀል?” ሲል ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል፡፡ ዳኛውም፡- “የተሳደብከውን ታውቀዋለህ” ሲሉት፤ ወጣቱም
እንደማያውቀው ጠቅሶ እንዲነበብለት ይጠይቃል፡፡
“ይሄን ሽማግሌ እግዚአብሔር ገላገለን፡፡ እሰይ!” ብልሃል ሲሉ ዳኛው አነበቡ፡፡ተከሳሹም፡- “በበበትክክል አልተነበበም፡፡ ተስተካክሎ እንደገና ይነበብልኝ?” በማለት ክርክሩን ቀጠለ፡፡ “ምን ተብሎ ይስተካከል? ራስህ ተናገር” ሲባል ጊዜም፣ እንዲህ አለ፡- “ይሄን አሮጌ ጣሳ ሽማግሌ እንኳን እግዚአብሔር ገላገለን፡፡ እሰይ! ነው ያልኩት”
ዳኛው ለጆሯቸው እየከበዳቸው አቀርቅረው ንጉሡ ላይ የተሰነዘረው ውግዘት ከሰሙ በኋላ፤ ‹ወጣቱ የጤና መታወክ ገጥሞት ይሆናል› በሚል ቀና አስተሳሰብ ዘብጥያ ከማውረድ ይልቅ፣ ወደ ጤና ማዕከል ልከውታል፡፡

የዚህ ዘመን ዳኞች ግን፣ አስክሬን ተከሶ በቃሬዛ ቢቀርብ ‹አይፈርዱበትም› ብሎ ለማሰብ ያዳግታል፡፡የሆነው ሆኖ፣ በእስር ላይ ከሚገኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ከልጁ ለቅሶ ላይ ታፍኖ የተያዘ አለ፡፡ “በፌስቡክ በአጋራኸው ምስል የአዳነች አቤቤን ፀጉር አሳጥረሃል!” የተባለም ይገኝበታል፡፡ የአባቶቻችንን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ መያዝማ በከባድ ወንጀል የሚያስከስስ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ በወህኒ ቤቱ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያላቸውን አልባሳት መልበስ እና የዐድዋ የድል በዓልን የሚዘክሩ ከኔተራዎችን መልበስ አደገኛ ወንጀል ነው፡፡ የግቢው ፖሊሶች “ቆጠራ” በሚል ከመኝታ ክፍላችን ካስወጡን በኋላ፣ እነኝህን አልባሳት ከየኩርቱ ፌስታላችን በርብረው ነጥቀውናል፡፡ ኦሕዴድ/ብልፅግና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን እና ፍርድ ቤቶችን አስቀድሞ በኦሮሞ ተወላጆች መውረሩም፣ ነጠቃውን እጅግ በጣም ቀላል አድርጎለታል፡፡

በዚህ ላይ፣ በአዲስ አበባ መንግሥትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ በተደጋጋሚ የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፍ ሙከራዎችም በኃይል ተጨናግፈዋል፡፡ በእነ መዓዛ መሐመድ እና ምዕራፍ ይመር አስተባባሪነት የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ ለመጠየቅ ታቅዶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጅምላ ጭፍጨፋ ለማውገዝ ተጠርቶ የነበረው የዐደባባይ ሰልፍ፣ በጦርነቱ ወቅት መንግሥት በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የተዋቸው ተማሪዎችን ህይወት ማትረፉ ላይ የበለጠ እንዲያተኩር ለማሳሰብ የተጠራውን ሰልፍ ጨምሮ፣ በርካታ መሰል እንቅስቃሴዎች በአዲስ አበባ እንዳይደረጉ ታፍነዋል፡፡ ይህ ግን፣ ‹የዐቢይ መንግሥት ለአዲስ አበባ ሕዝብ የከለከለውን ሃሳብን በሰላማዊ ሰልፍ የመግለፅ መብት፣ ለሌሎች ከተሞች ፈቅዷል› ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ ሌሎች የዐማራ ከተሞች መብታቸውን በኃይላቸው አስከብረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ግን፣ ወዳጄ አሌክስ ሸገር እንደሚለው፣ ጎጃም በረንዳ እየነደደ፣ ፒያሳ ዳንኪራ እንደ መምታት ሆኗል፡፡

መቼም፣ እንዲህ ዐይነቱን የክልከላ ክስ የጣልያን ፖሊስ ቢያደርገው የሚገርም አልነበረም፡፡ ወይም በጀኔራል ዚአድባሬ ከንቱ ጀብደኝነት በሚኮራ የሶማሊያ ፖሊስ ቢፈጸመም አይደንቅም፡፡ እኛን በሚመስል እና በእኛ ስም በሚጠራ ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑ ግን እጅግ ያማል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በግፍ የታሰሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች በአብዛኛው በአባ ሳሙኤል ወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን፤ ከዘረኛ የኦሕዴድ ፖሊሶች ጋርም በየሰበቡ እየተፋጠጡ ለከፋ ስቃይ ተዳርገዋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙትም በሳምንት ለሦስት ቀናት ብቻ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ቀናት በረሃብ እንዲያሰልፉ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ፣ ውሃ በሳምንት አንድ ቀን ማግኘት ከተቻለ፣ በግቢው ታላቅ ደስታ ነው፡፡ የነገሩን ምጸት የሚያጎላው ደግሞ፣ እነዚህ ችግሮች በተለይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች እስር ቤቱን ከጎበኙ በኋላ፣ መባባሳቸው ነው፡፡

ማሳረጊያ

አዲስ አበቤ ሆይ፡- ጨርሶውኑ ከመታነቅህ በፊት፣ ንቃ!
በአጠቃላይ፣ የዐድዋ እና የካራማራ የድል በዓላት ስም እየተጠራ ከእስር ቤት ፍርድ ቤት የሚመላለሰው የከተማይቱ ወጣት፣ የእያንዳንዱ የወንጀል ተሳትፎ እንኳን ተብራርቶ ሳይነገረው በጅምላ ታፍሶ ወደ ወህኒ ከተወረወረ ከአንድ ወር በላይ አልፎታል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ፣ የክሱ ዓላማ ዜጎች የድል በዓላቱን እንዳያከብሩ ለመከልከል ያለመ መሆኑ ነው፡፡ የባልደራስ አመራሮች ገና ከቢሮ ሲወጡ፣ የካራማራ “የድል በዓልን አታከብሩም፤ ተመለሱ!” መባላቸውን ልብ ይሏል፡፡

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator