ለላሊበላ እና አካባቢው ማህበረሰብ የዕርዳታ ቁሳቁስ አድርሰው ሲመለሱ የነበሩ ግምታቸው 12 ሚሊየን ብር የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በትሕነግ የሽብር ቡድን ተዘርፈዋል፡፡
ንብረትነታቸው የአቶ ጋሻው ሹምየ የተባሉ ግለሰብ በአማራ ክልል መንግስት ለላሊበላ እና አካባቢው የዕርዳታ እህል እና ቁሳቁስ እንዲያደርሱ ትዕዛዝ መተላለፉን ተከትሎ ግዳጃቸውን ፈፅመው ሲመለሱ የህወሓት የሽብር ቡድን መንገድ ላይ ከባድ ተኩስ በመክፈት ዘረፋ እና ውድመት ፈጽሟል።
በዚህም የሽብር ቡድኑ አባላት አራት ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈት፥ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ እስከ ተሳቢው እና የሶስት ተሳቢዎች ተቀያሪ አካል ዘርፈው ወስደዋል።
ቀሪዎቹን 3 ከባድ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎቹ ይዘው ሊያመልጡ መቻላቸው ተመላክቷል፡፡
የተዘረፉት እና ውድመት የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች ግምታቸው 12 ሚሊየን ብር እንደሚሆን የተሽከርካሪዎቹ ባለቤት አቶ ጋሻው ሹምየ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ በግዳጅ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ወራሪውና ዘራፊው የሽብር ቡድኑ የፈፀመው አስነዋሪ ተግባር ታሪክ ይቅር የማይለው ነው ብለዋል።
ወራሪ ሃይሉ በቆየባቸው አካባቢዎች ከባድ መሳሪያዎችን ሁሉ ተጠቅሞ ጥቃት መሰንዘሩን በስራ ላይ የነበሩ
አሽከርካሪዎች ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኤፍቢሲ ነው።