የሰው ልጅ ከደም፣ ከአጥንትና ከስጋ የተሰራ ነው። ከመቶው እጅ ዘጠናው እጅ (90%) የሚሆነው በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው ደም የተሰራው ደግሞ ፕላዝማ ከተባለ ፈሳሽ ውኃ ነው። የቀረው ከመቶው እጅ አስር እጅ የሚሆነው ደማችን ደግሞ የተሰራው ከጨው እና ከሆርሞኖች ነው። ስለዚህ ውኃ ደም ነው ለማለት ይቻላል። ውኃና አፈር የሕይዎት መሰረት ናቸው። ያለ ውኃና ያለ አፈር ሕይወትን ማሰብ አይቻልም። ታሪካቸውን ብቻ የምናነብላቸውም ሆነ እስከ አሁንም ድረስ ያሉት ገናና የዓለም አገራት አቀማመጣቸውን ያየን እንደሆነ ከወራጅ ወንዝ፣ ከባሕር፣ ከውቅያኖስ ዳር ሆነው እናገኛቸዋለን። ከውኃ በተጨማሪ እነዚህ አገራት ለም የእርሻ መሬት የነበራቸው ወይም ያላቸው ናቸው። ግብጽን፣ ሜሶፖታሚያን፣ ጃፓንን፣ ሕንድን እና ቻይናን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ታላቁ መጽሐፍ ‘መጽሐፍ ቅዱስም’፦ “ቀዳሜ ሕይዎቱ ለሰብእ እክል ወማይ፣ ወይን ወሥርናይ” (እህልና ውኃ ወይንና ስንዴ ለሰው ሕይዎት ቀዳሚ፣ መሰረታዊ ናቸው) ይላል። ለሕይወት ቀዳሚ፣ መሰረታዊ አሰፈላጊ የሆነው ነገር እህልና ወይን የሚበቅለው ደግሞ ከአፈር ላይ ነው። እህል የሚበቅለው ደግሞ በውኃ ነው። አፈርና ውኃ የሕይዎት መሰረት ናቸው። አፈርና ውኃ የምንበላውን ጣፋጭ እንጀራ እና ዳቦ የምናገኝባቸው ናቸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውኃ ማማ ናት። በኢትዮጵያ የሚገኘውም አፈር በዓለም ደረጃ እጅግ ለም ከሚባሉት የሚመደብ እና የሰጡትን የሚያበቅል ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ የለገሳቸውን ሀብት በማባከን በዓለም ቀዳሚ፣ ክብረ ወሰን የሚይዙ ናቸው ብሎ መከራከር ይቻላል። በዋናነት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የሚጠቀሙበት በተፈጥሮ ምንም አይነት የሕይዎት መሰረት የሚሆን ሐብት የሌላቸው ግብጾች ናቸው። ግብጽ በሜዲትራንያን እና በቀይ ባሕር የተከበበች አገር ብትሆንም ውኃው ጨዋማ ስለሆነ ለመጠጥም ሆነ ለእርሻ አይጠቀሙበትም። ከመቶው ከ90 በላይ እጅ የሚሆነው የግብጽ መሬት አሸዋማ ስለሆነ ሰው አይኖርበትም፣ እሕልም አያበቅልም። የግብጽ ሕዝብ የሕይዎት መሰረት የሆነው እና አገሪቱንም በዓለም ደረጃ በግብርና በቀዳሚነት ከሚሰለፉት አገሮች ተርታ እንድትመደብ ያስቻላት ከቂሎቹ አገር ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከወሎ እና ከሸዋ እየታጠበ የሚሄደው እጅግ በጣም ለም አፈር እና የአባይ ውኃ ነው። በዓመት 40 ቢሊዮን ቶን ለም አፈር የአማራ ክልል ከሚባለው የኢትዮጵያ ክፍል ታጥቦ በአባይ ወንዝ አማካኝነት ወደ ግብጽ እና ሱዳን ሄዶ ደለል ይሆናል። በዚህ ከቀጠለ የአማራ ክልል የሚባለው አብዛኛው አካባቢ ከጥቂት ትውልዶች በኋላ አፈርና ውኃ የሌለው፣ ለሕይዎት የማይስማማ፣ ያገጠጠ ተራራ ብቻ መሆኑ አይቀርም።

የግብጾች የሕይዎት መሰረት የሆነው የአባይ ወንዝ የሚመነጭበት ጣና እንቦጭ በተባለ አረም መወረሩ ከታወቀ አመታት ተቆጥረዋል። ብዙ ሰዎች ጣናን የወረረውን እንቦጭ አረም አጀንዳ አድርገው ባለፉት 9 ዓመታት ያለማቋረጥ ጽፈዋል። ጣናን ለመታደግም ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን በማጥፋት ላይ ናቸው። ይህ የሚደገፍ ተግባር ነው። ከዚህ በተቃራኒ ጣና ደረቀ አልደረቀ ግድ የማይላቸው ሰዎችም ብዙ ናቸው። ምክንያታቸውም የጣና ዋና ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያ ባለደሞች ግብጾች እንጂ ኢትዮጵያውን አይደሉም የሚል ነው። የአባይ ወንዝ እና የጣና ሐይቅ እኛ የአሁኖቹ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት የረቀቀ እደ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) የማይጠይቀውን፣ በገፀ ምድር የሚገኝን የተፈጥሮ ሀብት እንኳ ለመጠቅም የማንችል የዓለም መሳቂያዎች፣ ከንቱዎች መሆናችንን ለማሳየት በአብነት ሊቀርብ የሚችል ነዉ።

ብዙ ሰዎች ስለጭስ አባይ ፏፏቴ መጥፋት በሐዘን ይጽፋሉ። ነገር ግን የጭስ አባይን ፏፏቴ የሚፈልጉት ፎቶ ለመነሳት ነው። ከላይ ውኃ ደም ነው ብያለሁ። የጭስ አባይም ፏፏቴ ውኃ ሳይሆን ደም ነው። ደማችን ፈሶ ለግብጾች እና ለሱዳኖች የሕይዎች መሰረት ሆኗል። ደማችንን የሆነውን የጣናን ውኃ የምንፈልገው ደማችን ከሚፈስበት ከጢስ አባይ ፏፏቴ ላይ ፎቶ ተነስተን ፎቶውን ከቤታችን ግድግዳ ላይ በመስቀል ጅልነታችንን ቀን በቀን ለማየትና ሳይታወቀን ከንቱነታችችንና ገመናችንን ለማጋለጥ መሆን የለበትም።

ጣናን የምንታደገው ደማችንን ለባለደሞቻቸን አስተማማኝ የሕይዎት መሰረት እንዲሆን ሳይሆን እኛን እንዲጠቅም መሆን አለበት። ሰለዚህ እንቦጭን ማስወገድ ብቻ በቂ አይደለም። ጣናን ገድቦ ውኃውን ለመስኖ መጠቀም ያስፈልጋል። የጣናን ውኃ ገድቦ በመጠቀም ጎጃምን በሙሉና ከጎንደርም ደምብያን፣ አላፋ ጣቁሳን፣ ፎገራን እና ደራን ማልማት ይቻላል። የአባይን እና የጣናን ውኃ በመጠቀም ጎጃምንና በጣና ዳር ያሉት የጎንደር ወረዳዎችን በመስኖ በማልማት ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያና አልፎም ለአፍሪካ የሚበቃ ምርት ማምረት ይቻላል። ከመስኖና ከመጠጥ የተረፈውን የማንጠቀምበትን ደማችንን ደግሞ መሸጥ ነው ያለብን እንጂ ደማችን ዝም በብላሽ ብሎ መፍሰስ የለበትም። ደምን በነፃ መስጠት ለዚያውም ለውድቀታችን ምክንያት ለሆኑት ለባለደሞቻችን ለግብጾች መቆም አለበት። እኛ ግሮሰሪ ሄደን ብዙ ብር አውጥተን በላስቲክ የታሸገ ውኃ እንደምንገዛ እናስተውል።

በደቡብባዊ የአፍሪካ ክፍል ሌሶቶ (Lesotho) የምትባል በጣም ትንሽ የአፍሪካ አገር አለች። ሌሶቶ በደቡብ አፍሪካ የተከበበች 2 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ተራራማ አገር ነች። ሌሶቶ የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው ከተራሮቿ የሚፈሰውን ውኃ ለደቡብ አፍሪካ አገራት በመሸጥ ጭምር ነው። ኢትዮጵያውያንም የጦጣ ግንባር ከምታክለው ሌሶቶ ልምድ ቀስመው ደማቸውን ማለትም ውኃቸውን የገቢ ምንጭ ሊያደርጉት ይገባል። እስራኤል እና የተባበሩት የአረብ ኢሚሬቶች ብዙ ቢሊዮን ዶላር አፍስሰው ጨዋማውን የሜዲትራንያን እና የሕንድ ውቅያኖስን ውኃ ጨውን በማጣራት ለእርሻና ለመጠጥ ይጠቀሙበታል። በዚህ ረገድ የእስራኤሎች እደጥበብ (Desalination Technology) እጅግ በጣም የረቀቀ ነው። ግብጾች ግን ምንም ለመጠጥ እና ለእርሻ የሚሆን ወኃ ሳይኖራቸው፣ በሜዲትራንያን እና በቀይ ባሕር ተከበው እየኖሩ፣ ለdesalination አንድ ሳንቲም ሳያወጡ ከኛው ከቂሎቹ፣ ከሀፍረተ ቢሶቹና ከመሳቂያዎቹ የሚሄደውን ደማችንን በነጻ ይጠቀማሉ። እንዲያውም የእኛኑ ደም የአባይን ውኃ የእኛነው፣ ከተጠቀማችሁበት ውርድ ከራሴ እያሉ እኛኑ መልሰው ያስፈራራሉ። እኛም ሀፍረተ ቢሶች የገዛ ደማችንን ለመጠቀም ግብጾችን ተንበርክከን እንለምናለን። የአገራችን ሰዎች “ባልበላው እደፋው” የሚል ብሂል አላቸው። የአባይ ምንጭ መገኛ ስለሆን መፈ’ራት ያለብን እኛ ነበርን። Water terrorismን በዓለም ታሪክ ብዙ አገሮች ጠላቶቻቸውን ለማንበርከክ ተጠቅመውበታል። በእኛ በማፈሪያዎቹ አገር ግን ግብጾቹ በደማችን እኛን እያስፈራሩ ሲያንበረክኩን ይውላሉ። በአባይ ረገድ እኛ ኢትዮጵያውያን የዓለም ጉዶች ነን። ጣና ደረቀ አልደረቀ ለእኛ ምን እርባና አለው የሚለው ሀሰብ ምንጩ ይህ ነው።

በጣና ላይ የተደቀነው አደጋ ትኩረት የሳበው በአይን የሚታይ እንቦጭ የተባለው አረም ሰለወረረው ነው። ነገር ግን ለአደጋ የተጋለጡት የተፈጥሮ ቅርሶቻቸን እና ሀብታችን ብዙ ናቸው። በጎጃም፣ በጎንደር፣ በሸዋ እና በወሎ ብዙ የአባይ ገባር ወንዞች ደርቀዋል። በነዚህ አካባቢ ያሉት ብዙ ወረዳዎች እህል የሚያበቅለው አፈር ታጥቦ የገጠጠ መሬት ብቻ ቀርቷል። በወሎ ወስጥ ዋድላ፣ ድላንታ፣ ዳውንት፣ ሸደሆ፣ መቄት፣ ላስታ ላሊበላ፣ ሳይንት አጅባር፣ ተንታ ወረህ ይመኑ፣ ጊምባ/አቃስታ፣ ለገጎራ ወስጥ የሚገኙ ብዙ ቀበሌዎች የእህል ቡቃያ ካዩ ብዙ ዓመት አስቆጥረዋል። በጎንደርም ስማዳ፣ በየዳ፣ ጋይንት፣ አርባያ በለሳ፣ እብናት እና ፋርጣ እህል የማያበቀል እጅግ በጣም የተራቆተ መሬት ብቻ ነው የቀረው። ሌላው ቀርቶ ይሻላል የሚባለው ጎጃም በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ጎንቻ፣ እናርጅ እናውጋ፣ እነብሴ ሳር ምድር እና ሸበል በረንታ ብዙ ስፍራ አፈሩ ተሸርሽሮ መሬቱ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በተለይም እነብሴ ሳር ምድር እና ጎንቻ ብዙ ቀበሌዎች እህል አያበቅሉም። በጣም የሚያስደንቀው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትርፍ አምራች የነበረው የእነብሴ እሕል በገብያ ውስጥ አይገኝም። በእዚህ ወረዳ የሚገኙትም ጓንሳ፣ ጣታ እና ፈረስ ሜዳ የተባሉ በቀላሉ ሊገደቡ የሚችሉ ወንዞች ደርቀዋል።

አማራ ክልል ከሚባለው አካባቢ በአባይ አማካኝነት እየታጠበ የሚሄደውን አፈር (አፈር አልኩት እንጅ ዳቦ ነው) መጠኑን ለማወቅ በክረምት ወራት የአባይን ወንዝ መልክ ማየት በቂ ነው። በክረምት ወር የአባይ ወንዝ ውኃ ሳይሆን አፈር ወይም ዳቦ እና እንጀራ የሚሆነው አፈር ነው። ኋላቀሩ የኢትዮጵያ ግብርና በመሬቱ ላይ የሚያደርሰውን አሳዛኝ እና አሳፋሪ ጉዳት ለማወቅ በክረምት ወራት በጎጃም ሜዳዎች የሚፈሱትን የአባይ ገባር ወንዞችን ማየት ይበቃል። ሜዳዎቹ በክረምቱ የሚሸፈኑት በውኃ ሳይሆን አባይ ወደ ግብጽ ከሚያጓዘው በተረፈው አፈር ነው። አገርና መንግሥት ስለሌለን በእጃችን ያለውን ዳቦ እንዲህ እየጣልን ሕዝባችንን ለመመገብ ከፈረንጅ አገር የዳቦ ስንዴ የምንለምን አሳዛኝ ፍጡራን ሆነናል።

በሌላ አነጋገር በክረምት ወራት በአባይ አማካኝነት ወደግብጽ የሚሄደው ውኃና አፈር ሳይሆን ኢትዮጵያ ናት። በአጼ ዮሐንስ 4ኛ ጊዜ ግብጾች ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረጉት ሙክራ በሽንፈት እንደተጠናቀቀ የሚታወቅ ታሪክ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያን ባይቆጣጠሩም ከኢትዮጵያ ማግኘት የሚፈልጉትን አባይ በነጻ ይዞላቸው ይሄዳል። ለዚህም ነው በወቅቱ የነበረው የግብጹ መሪ ከዲቭ እስማኤል ፓሻ “Why do we even bother to control Ethiopia if the Nile flood brings the best part of that country” (የአባይ ወንዝ በጣም ለም የሆነው የአገሪቱን አፈር ካመጣልን ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ምን አደከመን) ሲል የተናገረው።

የኛን የኢትዮጵያውያንን ሀፍረታችንን የሚያጎላው ሌላው ቢቀር በጎጃምና ጎንደር ያሉትን ወንዞች አንድ ባንድ ሁሉንም፣ በቀላሉ ሕዝቡን አስተባብሮ በመገደብ ለመስኖ ማዋል እንደሚቻል ስናውቅ ነው። አማራ መንግሥት አልባ ባይሆን ኖሮ ከጎጃምና ጎንደር አንድ እፍኝ አፈር እና አንድ ብርጭቆ ውኃ ወደግብጽ እንዳይሄድ ማድረግ ይቻል ነበር። የጎጃምንና ጎንደርን ወንዞች በአግባቡ ብንጠቀምባቸው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የሚተርፍ እህል ባመረትን፤ እሕል የማያበቅሉትን፣ ማረፍ የሚገባቸውን በወሎ እና በጎንደር የሚገኙትን ብዙ ወረዳዎች ደግሞ ወደ እንሰሳት ማርባት፣ ወደ Agroforestry ትኩረት እንዲያደርጉ ማደርግ በቻልን ነበር። ኋላ ቀሩንና አውዳሚውን የእርሻ አስተራረስም ባስቀረነው ነበር።

ኢትዮጵያ በተለይም የአማራ ክልል የተባለው አካባቢ ያጣው የተፈጥሮ ቅርሱን ብቻ ሳይሆን የታሪክ ቅርሱንም ጭምር ነው። አማራ ክልል በሚባለው አካባቢ ቅርሱ ያልተመዘበረ፣ ያልተዘረፈ ቤተ ክርስቲያን አይገኝም። ይህን ለማጣራት የሚሻ ለአብነት ያህል “ምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት” በሚባለው ሀገረ ስብከት መዝገብ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ከየአድባራቱ የተዘረፉ ቅርሶች ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገበትን መዝገብ ዝርዝር ማየት ይችላል።

ስለዚህ የጣና ችግር የመንግሥት አልባነታችን፣ ውስብስብ ፖለቲካችንና ኋላ ቀነታችን የፈጠረው ችግር ነው። አሁን እምቦጩ ቢወገድም ዋናው ችግር ካልተወገደ ጣናን በዘላቂው ለማሰቀጠል አይቻልም። ምንም እንኳን ጣና ካጣነዉ በቀላሉ ልንተካው የማንችል ሀብታችን ቢሆንም ከሌላው የተፈጥሮ ሀብትና ቅርሶቻችን ግን የበለጠ አይደለም። በዘመነ ብአዴን የአማራ የተባለ የተፈጥሮ ቅርስ ሁሉ አደጋ ላይ ነው። አገርና መንግሥት ቢኖር ኖሮ ሁሉም ከጣና እኩል ትኩረት ያስፈልጋቸው ነበር። የአማራ ክልል በተባለው አካባቢ የተፈጥሮና የታሪክ ቅርስ ላይ ለደረሰው ውድመት ዋነኛዎቹ ተጠያቂዎች ከአማራ ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና እሴት የተፋቱ፣ እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊነት፣ ኅሊና እና ወገናዊነት የሌላቸው ወያኔዎች “ገ’ለን ቀብረነዋል” ያሉት አማራ መቃብሩን ፈንቅሎ እንዳይወጣ መቃብር ጠባቂ እንዲሆኑ ተደርገው የተፈጠሩት ነውረኞቹ ብአዴኖች ናቸው።

ባጭሩ ጣናም ሆነ ሌሎች የአማራ ክልል በሚባለው አካባቢ የሚገኙ የተፈጥሮ እና የታሪክ ቅርሶች በእንክብካቤ እና በክብር የሚያዙት፣ ኢትዮጵያም የምትድነው እንቦጩን በማስወገድ ብቻ ሳይሆን በልቶ ማደርን የሕይዎት መመሪያቸው ያደረጉ የአማራ ርግማኖችና አማራ መቃብሩን ፈንቅሎ እንዳይወጣ መቃብር ጠባቂ እንዲሆኑ የተፈጠሩ ሆዳም አማሮች ነውረኛ ድርጅት የሆነው ብአዴን ሲወገድ ብቻ ነው።

አቻምየለህ ታምሩ

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator