እናት ፓርቲ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!

በተለምዶ ዘመናዊ ትምህርት የሚባለውና ኹለ ነገሩ ከውጭ የተቀዳው የሀገራችን ትምህርት በአጠቃላይ አራቱን “የዘመናዊ” ሥርዓተ ትምህርት ምሶሶዎች(foundations) የሚባሉትን ፍልስፍናዊ (philosophical)፣ ታሪካዊ(Historical)፣ ማኅበራዊ(sociological) እና ሥነ አእምሯዊ(psyschologal) መሠረቱ የተዛባ እንደሆነና ትውልዱን ከራስ ማንነት የመንቀል አባዜ የተጠናወተው መኾኑን ከተረዳን ዋል አደር ብለናል፡፡

እንዲያውም “ኢትዮጵያውያን በጦር ሜዳ በጀግንነት ተዋድቀው ቢያሸንፉም በሌላ ግንባር (በትምህርት ሥርዓቱ በኩል) ያለ ጦርነት ተሸንፈዋል” እያሉ የሚያዝኑልን ወዲህም የሚሳለቁብን እንዳሉ ይነገራል፡፡

ለወትሮው በጥራትና ተደራሽነት ብሎም ጠባቂ እንጂ ፈጣሪ አያደርግም እየተባለ የሚኮነነው የትምህርት ሥርዓታችን አኹን አኹን ደግሞ ሌላ ከባድ ፈተና ገጥሞታል፣ ሥርቆት!

ከሕገ መንግስቱ በሚቀዳው የተንሸዋረረው ፌዴራላዊ አወቃቀር ወደግራና ቀኝ ሲሳሳብ “እንኳን ዘንቦብሽ…” የኾነውን የትምህርት ሥርዓታችንን ያላጋው ይዟል፤ አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገለት ፈጽሞ ላለመውደቁ ዋስትና የለውም፡፡

ክልሎች በተሰጣቸው(በወሰዱት) የተለጠጠ መብት ትምህርቱን ባሻቸውና ለእነርሱ የፖለቲካ ትርክት መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡

እንዲህ ያለው አደገኛ አዝማሚያ በጊዜ ባለመታረሙ ወይም ኾነ ተብሎ በመተው እነኾ ዛሬ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ጭምር በቁጥጥራቸው ስር አውለው ያቦኩት ይዘዋል፡፡

በሠራው ውጤት ተመሥርቶ ለሀገር ምን ዓይነት ብቁ ዜጋ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገባል ሳይኾን “ከእኔ ክልል ስንት የጎጤ ሰዎች ያልፋሉ?” ወደሚል ተቀይሯል፤ ይኽ ደግሞ በሥራ ሳይኾን ፈተናን በመሥረቅና በማሠራት ላይ መሠረቱን ጥሏል፡፡

በዚኽ በኩል ደግሞ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉም የፖለቲካ ልኺቃን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡

በ ፳፻፲፫ ዓ.ም የትምህርት ዘመን በተለይ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አንዱና ዋና ተጠቂ የነበረው የትምህርት ዘርፉ ነው፡፡

በዚያ ጫና ውስጥ ኾኖ ብዙ ዝግጅትና ልፋት የሚጠይቀውን የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የወሰደ ተማሪ ውጤቱ ምን ሊኾን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

ነገር ግን በአብዛኛው አማራና አፋር ክልሎች የነበሩ ተማሪዎች በ“አሳክተናል” ሪፖርት የተሳከረው አስፈጻሚ እኒኽን የነገ ተስፋቸውን በጉጉት የሚጠብቁ ልጆችን ማሰብ አልፈለገም፡፡

ከነበረባቸው ጫና እንዲላቀቁና በተረጋጋ ኹኔታ እንዲፈተኑ አልፈቀደላቸውም፡፡

“የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን እጠግናለሁ” የሚለው ትምህርት ሚኒስቴር የተጎዳ የልጅነት አእምሯቸውን ግን መጠገንን ማሰብ አልፈለገም፤ ታንክና መድፍ ድምጽ ሲጮኽበት የኖረን አእምሮ ማገገሚያ ጊዜ እንኳን ሳያገኝ ለፈተና አስቀመጡት፤ ውጤቱም በገሃድ ታዬ፤ ለወትሮው የተሻለ ውጤት ይመዘግብባቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ጭምር በአኹኑ ግን አንድም እንኳን ማለፊያ ነጥብ ያመጣ የሌለበት፣ በአንዳንዱ ደግሞ ከተፈተነው ብዛት ከመቶ አንድ አንኳን ማለፍ ያልቻለበትን ሂደት ተመልክተናል፡፡

በአንጻሩ ራሱ ሚኒስቴሩ እንዳመነው ፈተና ተሰርቆ በመታደሉ ምክንያት የተጣለ ትምህርት ዓይነትም እንዳለ ለመታዘብ ችለናል፡፡

ይባስ ብሎ አጠቃላይ አሠራርና አስተራረም (Administration) ላይም ከዚኽ ቀደምም የነበረና የገነገነ ችግር ቢኾንም በአኹኑ ዓመት ደግሞ ብሶበት ታይቷል፡፡

አንዳንድ ተማሪዎችም በዚኹ ሰበብ ለከፋ ጤና ችግር መዳረጋቸው ተሰምቷል፡፡

ወላጆችም በሌለ አቅም አራሚውን ተቋም ለማረም ብዙ ርቀት ተጉዘው መሐል ሀገር ድረስ መምጣታቸውን ታዝበናል፡፡

ጉዳዩን የአንድ ክልል፣ ጥቂት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች አድርጎ መውሰድ ካለፈው ትምህርት ያለመውሰድና ልብን ማደንደን ነው ብለን እናምናለን፤ በዚኹ የተማሪዎችን ውጤት የሚጎዱ ሳንካዎችን አለመቅረፍ በንጹሓን ላይ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ከመተኮስ አይተናነስም፡፡ ኹለቱም ትውልድን ያመክናሉና፡፡

ስለሆነም፦
፩. በጦርነቱ ሰበብ ሥነ አእምሯዊ ጫና ደርሶባቸዋል ተብለው የሚታመኑ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችን እና የወላጆቻቸውን የድካም ውጤት “በመሠረታዊነት” ሊቀይር የሚችል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

፪. ትምህርት ሚኒስቴር እና የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ነገሮችን ከሚያባብሱና ወደጸብና ነውጥ ከሚወስዱ መግለጫዎች ተቆጥበው ተማሪዎችና ወላጆች በእርጋታ በቤታቸው ኾነው በውል የታሰበበት መፍትሔ እስከሚሰጥ እንዲጠብቁ ማረጋጊያ መልዕክት እንዲያስተላልፉ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

፫. መንግስት በአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያሉ ከፍተኛ ስብራቶች ተባብሰው ወደከፋ አዘቅት ውስጥ ከመገባቱ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሮ ወጥ መፍትሔ እንዲያበጅ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

ፈጣሪ ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator