24 ግንቦት 2022
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከሰሞኑ ጋዜጠኞች እና ማኅብረሰብ አንቂዎች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑ አሳስቦኛል አለ።
ኤምባሲው የጅምላ እስሮቹን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሠረት የፌደራል እና የክልል ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል አለባቸው ብሏል።
ባለፈው ሳምንት ቢያንስ 10 ጋዜጠኞችና በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች አዲስ አበባእና በአማራ ክልል ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።
ኢሰመኮ ትናንት ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን ኮንኖ ነበር።
በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመታሰራቸው ባሻገር የተወሰኑት ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና በቤተሰቦቻቸው ያልተጎበኙ መኖራቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል።
“በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን” እንደተገነዘበ የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ገልጿል።
- ታይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ትምኒት ገብሩን በምን መስፈርት መረጣቸው?
- በሳዑዲ እና በኢራን በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን አምነስቲ ገለጸ
- ኤርትራ 31ኛውን የነፃነት በዓሏን በምን ሁኔታ ውስጥ ሆና ነው የምታከብረው?
ከሰሞኑ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ “የሕግ የበላይነትን ማስከበር” በሚል መውሰድ በጀመሩት እርምጃ ጋዜጠኞች እና የማኅብረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በአማራ ክልል ብቻ ከ4500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሰኞ ዕለት አስታውቆ ነበር።
የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በሰጡት መግለጫ የመንግሥትን የማድረግ አቅም እና የሕግ የበላይነትን በመፈታተን በክልሉ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ግለሠቦች እና ቡድኖች በፈጠሩት ሥርዓት አልበኝነት መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብትን፣ ሠላምእና ልማትን ለማረጋገጥ ተቸግሯል ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
በቅርቡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ጋዜጠኞች እና ማኅብረሰብ አንቂዎች መካከል ጦርነቱን በመቃወም እንዲሁም የሰላምና ድርድር መንገዶች የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ አፅንኦት በመስጠት በመናገር የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ ይገኝበታል።
በማኅበራዊና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት በመተቸት የምትታወቀው መስከረም አበራ ቅዳሜ ግንቦት 13/2014 ዓ. ም. በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውላ ፍርድ ቤት መቅረቧ ተዘግቧል።
ተቀማጭነቱን በአማራ ክልል ያደረገው እና በፋኖ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረው ዘገባዎች የሚሰራው አሻራ ሚዲያ አምስት ጋዜጠኞቹ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ባልደረባቸው ተናግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዘጠኝ አባላትም ግንቦት 10/2014 ዓ.ም. በሁለት ከተሞች መታሰራቸውን ሮይተርስ በአሜሪካ የሚገኘውን የአማራ ማኅበር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የአማራ ክልል በሕዝቡ መካከል አለመግባባትና ግጭትን ለመፍጠር በሚሰሩ እና ከሕግና ሥርዓት ውጪ በሚሆኑ ላይ ሕግን የማስከበርና የሕብረተሰቡን ደኅንነት ለማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።