0 0
Read Time:10 Minute, 6 Second

(ልጅ ተድላ መላኩ)

ዛሬ የዋግና ላስታው፣ የሰቆጣው የኢትዮጵያ ንጉሥ ያፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ዋግሹም ጎበዜ) መቶ ሃምሳ ሁለተኛ የንግሥ በዓል ቀን ነው። አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ልክ በዚህ ዕለት ከመቶ ሃምሳ ሁለት ዓመት በፊት (እ. ኤ. አ. June 11 1868) አፄ ቴዎድሮስን ተክተው ደብረ ዘቢጥ ላይ (መቄት ወረዳ) ዘውድ የደፉበት ዕለት ነው። ከዚህ ዕለት ጀምሮ ለሦስት ዓመት ሕዝቡን አንድ የማድረግን ሥራ፣ በፍትሕ መልካም አስተዳደርን እና ታላላቅ እድሳቶችን የሠሩ የዘመናዊ ታሪካችን (modern history) ትልቅ አካል ናቸው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሕዝብ አንድነት እና ሉዓላዊነት ድልድይ ሆነው መስዋዕት የሆኑ ንጉሠ ነገሥት ናቸው። ይህ ሆኖ ግን አፄ ተክለ ጊዮርጊስ በታሪክ ተራኪዎች ሥማቸው እምብዛም ሲነሳ አይሰማም። ንጉሡን የኢትዮጵያ ታሪክ ክድዋቸዋል። አንዳንዶች ረዥም ዘመን ስላልነገሡ ነው የሚል ምክኒያት ያነሳሉ፤ ኤሎች ደግሞ በአፄ ዮሃንስ እጅ የተገደሉ በመሆናቸው አፄ ዮሃንስ እርሳቸውን ገድለው በመንገሣቸው ምክኒያት ታሪካቸው እንዳይነገር ተደርጓል የሚሉም አሉ። ሌሎች ደግሞ የሁለት ሥርወ መንግሥት ወራሽ የነበሩ በመሆናቸው ሌሎች መሳፍንት የራሳቸውን ተቀባይነት ለማስጠበቅ ታሪካቸውን አደብዝዘውባቸዋል ይላሉ። የሆነ ሆኖ ታሪካቸውን አጠር አድርገን እንመልከት።

ዋግሹም ጎበዜ ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ከእናታቸው ከእመቤት አይቼሽ ተድላ እና ካባታቸው ከዋግሹም ገብረመድሕን በዋግ (ሰሜን ወሎ) ባስራ ስምንት ሃያ ስምንት ዓመተ ምሕረት ገደማ ተወለዱ። አባታቸው ዋግሹም ገበረመድሕን የዋግ ንጉሥ እና የዛጔ ሥርወ መንግሥት ነጋሲዎች ወራሽ የነበሩ ሲሆን፣ እናታቸው እመቤት አይቼሽ ተድላ መናገሻቸውን በጎንደር አደርገው ከነበሩ የኢትዮጵያ ሰሎሞናዊ ነገሥታት፣ ክአፄ ፋሲል፣ ከአፄ አዕላፍ ሰገድ (ቀዳማዊ ዮሓንስ)፣ ካፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ የሚወለዱ የጎንደርና የላስታው መስፍን የደጃዝማች ወንድ በወሰን የልጅ ልጅ ልጅ ሰሎሞናዊት ልዕልት ነበሩ። በመጀመሪያ ያፄ ተከለ ጊዮርጊስን አያቶች ትውልድና ታሪክ እንመለከታለን።

✵ ስለ ጎንደር-ላስታ ሰሎሞናውያንና ስለ ዛጔ ዋግሹሞች

ባስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የጎንደር ከተማ መስራችና ታላቁን ቤተ መንግሥት የገነቡት ንጉሠ ነገሥት አፄ ፋሲለደስ ፃዲቁ ዮሓንስ የሚባሉትን አፄ አዕላፍ ሰገድን ይወልዳሉ። ፃዲቁ ዮሓንስ አፄ አዕላፍ ሰገድ ታላቁ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድን ይወልዳሉ። ታላቁ አፄ ኢያሱ አርባ የሚሆኑን ልዑላንና ልዕልቶች ይወልዳሉ። ከነዚህ ውስጥ አራት ተክተዋቸው ነገሠዋል። የነገሡት አራቱ ቀዳማዊ ተክለ ሃይማኖት፣ አፄ በካፋ ወይንም መሲሕ ሰገድ፣ ሣልሳዊ አፄ ዳዊትና ዳግማዊ አፄ ዮሓንስ ነበሩ። ቀዳማዊ ተክለ ሃይማኖት በሥልጣን ጥም ለፀሎት በምናኔ የነበረውን አባቱን አፄ ኢያሱን አስገድሎ ስለነገሠ እርጉም ተክለ ሃይማኖት ይባላል። ካልነገሡ ልዑላን መካከል ከአቤቶ ዘድንግል ኢያሱ ሐረግ ልዕልት እመቤት የወርቅ ውሃ (ግዛ ወርቅውሃ) ይወለዳሉ። እመቤት የወርቅውሃ ባስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በዘመነ መሳፍንት ላስታን እና በጌምድርን ይገዙ የነበሩትን ታላቁን መስፍን ደጃዝማች ወንድ በወሰንን ያገቡ እና ራስ ኃይሌ ወንድ በወሰንን ይወልዳሉ። በራስ ኃይሌ ወንድ በወሰን የጎንደር ላስታ ሰሎሞናዊ አልጋ ይመሰረታል።

ያፄ ተክለ ጊዮርጊስ አያቶች ስለሆኑት ስለ ደጃዝማች ወንድ በወሰን፣ ራስ ኃይሌ እና ደጃዝማች ተድላ

ደጃዝማች ወንድ በወሰን በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በዘመነ መሳፍንት የላስታ እና የበጌምድር ታላቅ መስፍን እና ገዥ ነበሩ። በሳርባኩሳ ሦስት ጦርነቶች የዳግማዊ ተክለ ሃይማኖትና የራስ ሚካኤል ስሁልን ጦር ድል ካደረጉ መሳፍንት ዋናው ነበሩ። ከዚያም በኋላ የፋጅታ ለኮማ ጦርነት ታላቅ ጀግንነት ያሳዩበት ውጊያ ነበር። ደጃዝማች ወንድ በወሰን ከአፄ ኢያሱ (አዲያምሰገድ) ሐርግ ልዕልት እመቤት የወርቅውሃን አግብተው ደጃዝማች ወንድ በወሰን ከእመቤት የወርቅውሃ ራስ ኃይሌ ወንድበወሰንን ይወልዳሉ። መንግሥት አብቅቶለታል በሚል ፈጻሚ መንግሥት ይባሉ የነበሩት ቀዳማዊ ተክለ ጊርዮርጊስ ፍቅር ሰገድ ጦርነት ሄደው በነበር ጊዜ ዳግማዊ አፄ በእደማሪያም በሴራ ክሕደት በርሳቸው ላይ ሲሾሙ ራስ ኃይሌ ወንድ በወሰን ከዳግማዊ አፄ በእደማሪያምና ከራስ ወልደ ገብርኤል ጋር ተዋግተው ድል በማድረጋቸው እንዲያፈገፍጉ አደረጉኣቸው። ከዚያም ራስ ኃይሌ ወንድ በወሰን ራስ ወልደ ገብርኤልን በፈላቂት ውጊያ ላይ ድል አደረጋቸው። ራስ ወልደ ገብርኤል ወደ ጨጨሆ በሸሹ ጊዜ ራስ ኃይሌ ወንድበወሰን ወልደ ገብርኤልን በጻንፋ ጉመራ አጥቅተው ዳግም ድል አደረጓቸው። ከዚያም ራስ ወልደ ገብርኤል ወደ ቁራጻ ሲያመልጡ መነኮሳት መስቀል ይዘው በሁለቱ እርቅ እንዲሆን አደረጉ።

በመጨረሻም ራስ ኃይሌ ወንድ በወሰን ቀዳማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ፍቅር ሰገድ ወደ ዙፋኑ እንዲመለሱ አደርገዋል። ራስ ኃይሌ ወንድ በወሰን ከወለተ እግዝሔር ደጃዝማች ተድላ ኃይሌን ይወልዳሉ። ደጃዝማች ተድላም ኃይለኛ ቆፍጣና ጦረኛ ሆነው የላስታን አልጋ ካባታቸው ከጎንደርና ላስታ ሰሎሞናዊ ልዑል ከራስ ኃይሌ ወንድበወሰን ይወርሳሉ። ከዚያም ደጃዝማች ተድላ ኃይሌ ይዋግሹም ጎበዜ ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስን እናት ልዕልት እመቤት አይቼሽ ተድላን እና ወንድም እህቶቻቸውን ይወልዳሉ። የዋግሹም ጎበዜ ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ አባት ዋግሹም ገብረመድሕን ነበሩ። እርሳቸውም የዋግ የዛጔ ሐረግን አልጋ ካያቶቻቸው ወርሰው ዋግ ያስተዳድሩ ነበር። የዋግሹም ገብረመድሕን ሐረግ ከቷልቁ ዋግሹም ክንፉ ይመዘዛል። ታላቁ ዋግሹም ክንፉ ዋግን ባስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረስሃ እና ባስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የኦሮሞው ኃይል ወደ ሰሜን እየፈለሰ ግዛቶችን በወረረ ጊዜ ታላላቅ ውጊያዎችን አድርገው ግዛቶቻቸውን ያስጠበቁ አርበኛ ነበሩ። ዋግሹም ክንፉ ታላቁን ወሰን እና ልዕልት በተሓን ይወልዳሉ። በተሓ ዋግሹም ገብረመድሕንን እና ሌሎችን ይወልዳሉ። ከዋግሹም ጎበዜ በኋላም በዋግሹምነት ሥልጣን ከታላቁ ዋግሹም ክንፉ የተወለዱ የዋግ ነገሥታት ነግሠዋል። እነ ዋግሹም ብሩ፣ እነ ዋግሹም ተፈሪ፣ እነ ዋግሹም ጓንጉል የዓድዋው አርበኛ፣ እነ ዋግሹም ከበደ ይታወሳሉ። ከመጭረሻዎቹ ዋግሹሞች ዋግሹም አድማሱ፣ የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ልጅ ዋግሹም ወሰን ኃይሉ፣ ዋግሹም ጌታሁን ባፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አስተዳድረዋል። ዋግሹም ገብረመድሕን የደጃዝማች ተድላ ኃይሌን ልጅ እመቤት አይቼሽ ተድላን አግብተው ዋግሹም ጎበዜን ማለትም ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ይወልዳሉ።

✵ ስለ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ የንግሥና ዘመን

አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ካፄ ቴዎድሮስ ቀጥለው በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1860 እስከ 1864 ገደማ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ የዛጔ እና የሰሎሞን የሁለት ሥርወ መንግሥት ወራሽ ንጉሥ ነበሩ። በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘመን፣ ዋግሹም ጎበዜ፣ አያታቸው ደጃዝማች ተድላ ኃይለ ከተገደሉ በኋላ፣ የርሳቸውንና ያጎቶቻቸውን የላስታ አልጋ ወርሰው ደጃዝማች ጎበዜ ገብረመድሕን ተብለው በወትሃት እድሜአቸው ተሾሙ።

አባታቸው ዋግሹም ገብረመድሕንም ደብረ ዘቢጥ ላይ ከተገደሉባቸው በኋላ፣ ያባታቸውን የዋግሹምነት የዋግ የንግሥና ሹመት ወርሰው ሸፈቱ። በሸፈቱም ዘመን በእናታቸው በልዕልት እመቤት አይቼሽ ተድላ እገዛ እጅግ ታላቅ የስልሳ ሺ ወታደር የጦር ሰራዊት ያደራጃሉ። ጦራቸውንም ካደራጁ በኋላ ከሽፍታነት ተመልሰው ያባታቸው ግዛት ወደ ሆነችው ወደ ዋግ ሰቆጣ ተመልሰው ይገቡና፣ ጦራቸውን አስከትለው አፄ ቴዎድሮስ ወዳሉበት ወደ መቅደላ ያመራሉ። በመንገዳቸውም ላይ አፄ ቴዎድሮስ ላይ አምጸው የነበሩትን ጥሶ ጎበዜን መጀመሪያ ወግተው ኵሓ ላይ ድል ካደረጉ በኋላ፣ በጊዜው የትግራዩ ካሳይ ምርጫ ከእንግሊዝዋ ንግሥት ቪክቶሪያ ጋር በነበረ እልህና ጸብ ቴዎድሮስን ለመያዝ የመጣውን የእንግሊዝ ጦር አግዘው የእንግሊዙ ጦር መቅደላ ደርሶ አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ አምባ ላይ ራሳቸውን በጥይት ገደሉ። የእንግሊዙ ጦር መቅደላ የነበረን ያፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ዘርፈውና የቀረውን ነገር ሁሉ አቃጥለው ከወጡ በኋላ ካሳይ ምርጫን ለእገዛው አምስት መቶ ሺ የእንግሊዝ ፓውንድ የሚያወጣን ዘመናዊ መስኬት መሳሪያና ቁሳቁሶች ሸልመውና ጦሩን የሚያሰለጥንለት ኃይል በትግራይ አደራጅተው ሀገር ለቀው ይወጣሉ።

ይህን ተከትሎ ዋግሹም ጎበዜ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ንጉሥዋን ያጣችውን ሀገር በፍጥነት ተረክበው ባ1860 አመተ ምሕረት አባታቸው በተገደሉባቸው ቦታ ላይ በደብረ ዘቢጥ፣ የኢትዮጵያ አቢያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ሁሉ የበላይ መሪና የመላው የኢትዮጳያ ምድር መንፈሳዊ አባት በሆኑትና የቅዱስ አቡነ ተከል ሃይማኖት መንበረ ሥልጣን ላይ በነበሩት እጨጌ ተቀብተው ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በሚል ሥመ መንግሥት የመላው የኢትዮጵያ መንግሥት ንጉሥ ሆነው ዘውድ ጫኑ። ሀገረ መንግሥታቸውም ዋግ ሰቆጣ ነበር። የንግሥና ሐረጋቸውንም በእናታቸው በኩል ከዘመነ መሳፍንት በፊት ከነበሩት የጎንደር ሰሎሞናዊ አፄዎች ቆጥረው ከኢትዮጵያ መዳከም በፊት የነበሩትን አያቶቻቸውን የእነ አፄ ፋሲልን እና የዛጔ ነገሥታት አያቶቻቸውን የነ ንጉሥ ላሊበላን ሥልጣን ወደ አንድ ዙፋን አምጥተው አስቀጠሉ። ንግሥናቸውም የሁለት ሥርወ መንግሥት አንድነት ምልክት ሆኖ ታየ። ምክኒያቱም ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ በእናታቸው በኩል የአፄ ፋሲል፣ የቀዳማዊ አፄ ዮሓንስ ፣ የታላቁ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ሰሎሞናዊ ሐረግ ያላቸውና፣ በአባታቸው በዋግሹም ገብረመድሕን በኩል ደግሞ የዛጔ ነገሥታት፣ የንጉሥ ላሊበላ፣ የንጉሥ ዣን ሥዩም፣ የንጉሥ መራ ተክለ ሃይማኖት ሀረገ ሥልጣን ወራሽ ነበሩ።

ነገር ግን ለሥልጣን የሚቀናቀኑአቸው ሌሎች ሁለት ሰሎሞናዊ ልዑላን ነበሩ። እነዚህም የጎጃሙ ራስ ደስታ ተድላ እና በጊዜው የሸዋ ንጉሥ የነበሩት ንጉሥ ምኒልክ ነበሩ። የጎጃሙ ራስ ደስታ ተድላ የወንድማቸው ልጅ፣ አዳል ተሰማ (በኋላ ንጉሥ ተክለሃይማኖት) የጎጃምን አልጋ በመውረስ ተቀናቃኛቸው የነብሩ በመሆኑና፣ ራስ ደስታ ተድላ ያፄ ተከል ጊዮርጊስን ንግሥና ያልተቀበሉ በመሆናቸው አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ወደ ጎጃም ዘምተው የራስ ደስታ ተድላን ጦር ወግተው ድል ካደረጉ በህዋላ ልጅ አዳል ተሰማን ደግፈውና በራስ ደስታ ተድላ ምትክ በንጉሠ ነገሥት ሥልጣናቸው የደጃዝማችነት ሹመት ሰጥተው ቦታውን ለቀቁላቸው። ይህን ተከትሎ በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የሚሆኑትን ደጃዝማች አዳል ተሰማን እህታቸውን ልዕልት ላቀችን ዳሩላቸው። መንግሥታቸውን ለማጠናከር ልዑላኑን ከራሳቸው ጋር በጋብቻ አስተሳስረው፣ ከሸዋ ከቤተ ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ታናሽ ወንድማቸውን ደጃዝማች ኃይሉን ያፄ ምኒልክ አጎት ከሆኑት ከራስ ዳርጌ ሳህለ ሥላሴ ልጅ ከትሰሜ ዳርጌ ጋር አጋቡ። በሁለቱ ጋብቻም ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ይወለዳሉ።

ራሳቸውም የካሳይ ምርጫን እህት ድንቅነሽ ምርጫን አግብተው መንግሥታቸውን ለማጽናት የክፍላተ ሀገሩን ልዑላን በጋብቻ ከራሳቸው አስተሳስረው አንድ ቤተ ሰብ አደረጉት። አጎቶቻቸውም በመንግሥታቸው መፅናት ታላቅ ሚና ተጫውተዋል። አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑ በርሳቸው ምትክ የዋግን አልጋ ራስ መሸሻ ተድላ ተተክተው መርተዋል። ደጃዝማች ሠራዊት ተድላ፣ ደጃዝማች መሸሻ ተድላ፣ ደጃዝማች ይማም ተድላ፣ ደጃዝማች የሱፌ ተድላ፣ ደጃዝማች ይመር ተድላም ካፄ ተከል ጊዮርጊስ ቤተ ሰብ የሚጠቀሱ ናቸው። አፄ ተከል ጊዮርጊስም አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ በማድረግ ዘመቻወች ተትታና ተጎሳቁላ የነበረችውን የእናታቸውን አያቶች መናገሻ፣ ጎንደርን አቢያተክርስቲያናቱን አድሰው፣ ከተማዋንም ዳግም አልምተው በሙሉ አቅማቸው አድሰዋታል። አፄ ቴዎድሮስ የጀመሩትን ኢትዮጳያን አንድ የማድረግ ራዕይም አስቀጥለዋል። በዚህም ታልቅ ድርጊታቸው በዜና መዋዕላቸው ላይ ካፄ ፋሲል ወዲህ ለጎንደር እንደ ዳግማዊ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ያደረገላት የለም ተብሎ ተመስክሮላቸዋል።

ጎጃምንና ሸዋን ከጎናቸው ካደረጉ በኋላ በራሳቸው መነሻ በወሎ ያስቸገራቸውን የአሊ ፋሪስን ኃይል በፍጥነት ድል አድርገው መነሻቸው የሆነቸውን ወሎንም ተቆጣጠሩ። ከዚህ በኋላ ትኩረታቸው ወደ ደጃች ከሳይ ምርጫ ሆነ። ካሳይ ምርጫን ደጃዝማች ብለው በትግራይ ሾመው ነበር። ነገር ግን ካሳይ የእንግሊዙ የጦር ጀነራል ጆን ከርክሃም ጦር እያሰለጠነላቸው ቆይቶ ነበር። የጆን ከርክሃም እንግሊዛዊ ጦር የደጃች ካሳይ ምርጫን የትግራይ ጦር ላፄ ተዎድሮስ መሞት ዘመናዊ መሳሪያ አድሎ ሲያሰለጥነው ከቆየም በኋላ ካሳይ ምርጫ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ በነገሡ በሁለተኛው ዓመት ቀይ ባሕርን የመጠቀም ዕድል አግኝተው ነበር። ሌሎቹ ልዑላንና ንጉሡም ጭምር ያልነበራቸው ትልቅ ዕድል ነበር። ይህን ተከትሎም ካሳይ ምርጫ በግብፅ እስክንድሪያ ከነበረው ፓትሪያርክ ጋር ጳጳስ እንዲላክላቸው ሲደራደሩ ቆይተው ነበር። በኋላም ጳጳስ ሲላክላቸው ያፄ ተከል ጊዮርጊስን ሥልጣን ተላልፈው ጳጳሱ በተክለ ጊዮርጊስ ላይ እርሳቸውን እንዲቀባና እንዲያነግሥ መፈለጋቸው ተሰማ። ንጉሥ ምኒልክም ሁለቱ ተቀናቃኞች ይዋጣላቸው የሚል አቋም ይዘው ቀሩ። ለአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ካሳይ ምርጫን መውጋት ብቸኛ አማራጭ ሆነ። የስልሳ ሺ ወታደር ጦራቸውን ለጦርነት አዘጋጁ፤ ነገር ግን ጦራቸው የታጠቀው መሳሪያ ከካሳይ ምርጫ የእንግሊዝ መስኬት መሳሪያ አንጻር የሚያዛልቅ አልነበር። ባስራ ስምንት ስልሳ ሶስት አመተ ምሕረት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ደጃች ካሳይ ምርጫን ለመውጋት ስልሳ ሺ ወታደራቸውን እየመሩ ተከዜን አቋርጠው ትግራይ ገቡ።

አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ስልሳ ሺ ወታደሮቻቸውን እየመሩ ትግራይ በገቡ ጊዜ አዲ አርካይ በሚባል ቦታ አርፈው በዚያንም ወቅት አንድ ገብረ ማርያም የሚባሉ ባሕታዊ ተጠጉዋቸው:: ባሕታዊው ንጉሡ አርፈውበት በነበረው ድንኳን ላይ ጠጠሮች አፍሰው ወረወሩ። ይህ በሆነ ጊዜ የንጉሡ ሰራዊት ወታደሮች ተደናግጠው ባሕታዊውን ከያዙአቸው በኋላ ለምን ይህን ድርጊት እንደፈጸሙ እንዲያስረዱ ለነጉሡ አቅርበው አስጠየቁአቸው። ቢዝህም ጊዜ ባሕታዊው እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ እኔ በጠጠር ያደረግኩትን ካሳይ ምርጫ በጥይት ያደርገዋል አሉአቸው። የንጉሡም ወታደሮች በንዴት ባሕታዊውን ንጉሡን በመድፈራቸው ሊገድሉአቸው ሲሉ፤ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ተዋቸው ብለው አስቁመው በታላቅ ሰጥታ ቁጭ ብለው አሰቡ። ባሕታዊው አስቀድመው የነገሩአቸው የሚመጣባቸውን እጣ ፈንታ ነበር።

በሰኔ አስራ አራት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ እና ካሳይ ምርጫ ሙሉ ቀን የፈጀ ጦርነት ሲዋጉ ዋሉ። የደጃች ካሳይ ጦር በቁጥር የሚያንስ ቢሆንም በመሳሪያ ግን ይበልጥ ነበር፣ ምክኒያቱም ጦራቸው ሙስኬት ጠመንጃ የታጠቀ ነበር። ያፄ ተክለ ጊዮርጊስ ሰራዊት ግን ጦር፣ ጎራዴና ማችሎክ ሽጉጥ የታጠቀ ነበር። በዚህም ምክኒያት ያፄ ተክለ ጊይሮጊስ ጦር ከሙሉ ቀን ውጊያ በህዋላ ወደ ማረብ ወንዝ ለማገገም ተጠጋ። የደጃች ካሳይ ጦር ግን በሌላ መንገድ አቋርጦ ዓድዋ ላይ ውጊያ ገጠመው። ሐምሌ በሁለት ሳምንት ውስጥ የመጨረሻውን ውጊያ አፄ ተክለ ጊዮርጊስና ካሳይ ምርጫ ገጠሙ። በዚህ የመጨረሻ ውጊያ ላይ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ፈረሰኞቻቸውን በደጃች ካሳይ ጦር መሃል ይዘው በመግባት አጠቁ። ፍረሳቸውም ከሥራቸው ተገድሎባቸው እርሳቸውም ውጊያው ላይ ቆስለው ወደቁ። በዚህም ጊዜ የደጃች ካሳይ ጦር ቆስለው የወደቁትን ንጉሠ ነገሥትና የጦር መሪዎቻቸውን ከቦ ያዛቸው። እርሳቸውም በመያዛቸው አብሮአቸው የዘመተው በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሠራዊት ተማረከባቸው።

የንጉሱ ባለቤት ለደጃች ካሳይ እህታቸው መሆናቸው ካሳይ ምርጫን ከጭካኔ አላስተዋቸውም። የባሕታዊው የገብረ ማርያም ንግርትም እውነት ሆነ። የደጃች ካሳይ በእንግሊዝ የታጠቀና የሰለጠነ ጦር ያፄ ተከል ጊዮርጊስን ጦር በአሳም ጦርነት ከዓድዋ ወጣ ብሎ ባለ ስፍራ ድል አድርጎ ከንጉሣዊ ሥልጣናቸው አወረዳቸው። ደጃች ካሳይ ምርጫ አፄ ዮሓንስ በሚል ሥመ መንግሥት ዘውድ ደፉ። አፄ ተክለ ጊዮርጊስም ከንጉሣዊ ቤተ ሰቡ ጋር በአምባ አባ ገሪማ ገዳም ታሰሩ። ከእስር አምልጠው ዳግም እንዳይመለሱ አፄ ዮሓንስ ዓይናቸውን በማጥፋት አሳወራቸው። ያፄ ተከል ጊዮርጊስ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ድንቅነሽ ምርጫም ነጋሲው ወንድማቸው በመሆናቸው ባይታሰሩም አፄ ተክለ ጊዮርጊስ እስኪሞቱ ድረስ አብረዋቸው ተቀመጡ። አፄ ተክለ ጊዮርጊስም ብዙም ሳይቆዩ ተሰቃይተው ባንድ አመት ጊዜ ውስጥ በሰላሳ ስድስት ዓመታቸው ገደማ አረፉ። ካረፉም በህዋላ እቴገ ድንቅነሽ ወደ መቀሌ ሄደው ደጃዝማች ገብረኪዳን የሚባሉን የትግራይ ባላባት አገቡ። እስከ መጨረሻውም ያፄ ተክለ ጊዮርጊስ ባለቤት ስለነበሩ እቴጌ የሚለውን ርዕሰ መንግሥታቸውን ይዘው ኖሩ። አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ማረፋቸውም በተሰማ ጊዜ ለሩህሩሁ ንጉሥ ተለቀሰ።

አፄ ቴዎድሮስ ሲሞቱ፣ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ዙፋን ተረክበው መንግሥታዊ አንድነትን ያስቀጠሉና ያጠናከሩ፣ ያመጹባቸውን መሳፍንት በውጊያ ድል ያደሩገና፣ የተማረኩትን ምሕረት ብቻም ሳይሆን በጊዜው ተሰምቶ የማይታወቅ አይነት በቀድሞ ሥልጣናቸው እንዲቀጥሉ የሚያደርጉ ቅን እና ጠንካራ ንጉሥ ነበር። የእናታቸው አያቶች የእነ አፄ ፋሲል መናገሻ የነበረችው ጎንደር ተዳክማ ስለነበረም በሙሉ አቅማቸው ያሳደሰው፣ በዜና መዋዕላቸው ከአፄ ፋሲል ወዲህ ለጎንደር እንደ ተክለ ጊዮርጊስ ያደረገላት የለም የተባለላቸው፤ ሦስት ዓመት ብቻ ቢነግሡም በሦስት አመት ውስጥ የአስር አመት ሥራዎችን ያከናወኑ ሕዝብና አገር ወዳድ መሪ ነበሩ። አፄ ዮሓንስንም ከመንገሣቸው በፊት የደጃዝማችነት ማዕረግ የሰጡአቸው እርሳቸው ነበሩ።

ሆኖም ግን የታሪክ ተቺዎች ታሪክ በአሸናፊዎች ነው የሚጻፈው እንዲሉ ኢትዮጵያን ለሦስት ዓመታት የመሩትን ንጉሠ ነገሥት የታሪክ ተራኪዎች ሥማቸውን ለማንሳት አይደፍሩም። አፄ ቴዎድሮስን ከጠቀሱ በኋላ የአፄ ተክለ ጊዮርጊስን ሥም ቢያነሱ አፄ ቅጣት የሚቀጡ ይመስል እርሳቸውን ዘለው አፄ ዮሃንስን ይጠቅሳሉ። በዘመኑ አንዱም ያፄ ተክለ ጊይሮጊስ ንግሥና የተፈራበት ምክኒያት የሁለት ሥርወ መንግሥት አልጋ ወራሽ የነበሩ ብቸኛ ንጉሥ በመሆናቸው ነበር። በመካከለኛው ዘመን ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት የሰሎሞንና የዛጔ ሥርወ መንግሥታት በእርሳቸው ባፄ ተክለ ጊዮርጊስ ከልዩነት በአንድ ዙፋን ላይ ወደ አንድነት የመጡ በመሆናቸው ለራሳቸው ቅቡልነት የሰጉ አለቆች ማንነቱ እንዳይነሳ ያልፈለጉ ሆነው ይሆን?

እንኳን ለመቶ ሃምሳ ሁለተኛ ያፄ ተክለ ጊዮርጊስ የንግሥ በዓል አደረሰን።

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
50 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
50 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator