ታጋይ ጌታነህ አቡሃይ ከቃሊቲ ማ/ቤት!
ወጣት ጌታነህ አቡሀይ ይባላል፤ የአማራ ህዝብ መብት፣ጥቅምና ፍላጎት ይከበር እንዲሁም አጽመ እርስቶቹም ይመለሱ በሚል ነፍጥ አንስቶ ትግል በማድረግይታወቃል።
በሀሰት አሸባሪ ብሎ በመፈረጅ ብዙዎችን የረሸነውን፣ በየእስር ቤቱ ያንኮላሸውን አሸባሪውን የትሕነግ ስርዓት ፊት ለፊት በማውገዝና ነፍጥ አንስቶ በመታገል ረገድ ጠንካራ ተጋድሎ በማድረግ ከሚታወቁት ጀግኖች አንዱ ነው።
ታጋይ ጌታነህ አቡሃይ “የዋልድባ ገዳም ለምን ይዘረፋል? የጀግኖቻችን አጽም ስለምን ሜዳ ላይ ይደፋል?” በሚል በከፍተኛ የተቆርቋሪነት ሰሜት ትግል ሲያደርጉ ከቆዩት የአማራ የቁርጥ ልጆች ተርታም ይሰለፋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ነህ በሚል በሽብር ብሎም የዋልድባ ገዳም ከሚዘርፉ የወያኔ ታጣቂዎች ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ አንድ የደህንነት አካል ገድለሃልና በሌላኛው ታጣቂ ላይም የግድያ ሙከራ በማድረግ ተከሷል።
ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረውና ፍርዱን የሰጠውም ዘርዓይ የተባለ የትሕነግ ቀንደኛ ደጋፊ በመሆን በብዙ የወልቃይት ጠገዴ፣ የራያ ብሎም የአማራ የነጻነት ታጋዮች ላይ ፍርድ ሲሰጥና የለውጥ ትግሉን ሲያዳክም የነበረ ሰው ስለመሆኑ ተገልጧል።
በትግል ላይ የነበረው ጌታነህ አቡሃይ ታህሳስ 21 ቀን 2009 ጋምቤላ አካባቢ ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።
በአሸባሪው ትሕነግ የተያዘው ጌታነህ ወደ በማዕከላዊ እስር ቤት ተወስዶ ብዙ ግፍ ተፈጽሞበታል።
የትሕነግ አላማ አስፈጻሚዎች እነ ዳኛ ዘርዓይ እና መሰሎቹ በተኩስ ልውውጥ የተገደለውን ደህንነትን ጌታነህ እንደፈጸመው በማድረግ ሶስት ክሶች እንዲቀርቡበት አድርገዋል።
ክሱን ሆንብለው በመነጣጠልም:_
1) የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል በመሆን በሽብር፣
2) በነፍስ ግድያ እና
3) በግድያ ሙከራ ብለው በመከፋፈል በጌታነህ ላይ የተመሰረተውን ክስ ተመልክተውታል።
ወያኔ አማራን የሚበቀለው በሁሉም ዘርፍ በመሆኑ ከአምቦ የመጡትንና በተመሳሳይ ኬዝ በሌላ መዝገብ የተከሰሱትን እነ ፈረጃ ጌታቸውን ሀምሌ 30 ቀን 2010 ዓ/ም
በእኛ በኩል መዝገቡን ዘግተናል፤ የነፍስ ግድያውን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዛው መጠየቅ ይችላል በሚል ሲለቅ ጌታነህን ግን ለመልቀቅ አልፈለገም።
በሽብር የተከሰሱት ሲለቀቁ ጌታነህ ነፍስ አለበት በሚል ተለይቶ እንዲቀር በማድረግ ነሀሴ 10 ቀን 2011 ዓ/ም 12 ዓመት ፈርደውበታል።
ጌታነህ ሰበር ሰሚ ችሎት ላይ ይግባኝ በመጠየቁ ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ/ም 3 ዓመት ተቀንሶለት በ9 ዓመት ተቀጥቷል።
አቃቢ ህግም ግንቦት 14 ቀን 2013 ይግባኝ በማለት ሰበር ሰሚ ችሎትን ጠይቋል።
በመሃልም ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጌታነህ የእኛ አባል ነው፤ በጦርነት ላይ በተገደለ ሰው አላግባብ መታሰር የለበትም በሚል እንዲፈታ የሚጠይቅ አቤቱታ ስለመቅረቡ ተነግሯል።
የአሚማ ምንጭ እንደሚሉት ይህን የሰማው አቃቢ ህግም ጌታነህ ይፈታል በሚል ጉዳዩን እንደገና ማንቀሳቀሱን በመቀጠሉ ጥቅምት 16 ቀን 2014 ይግባኙ ተፈቅዶለታል፤ በይግባኙ ላይም ውሳኔ ለመስጠት ህዳር 30 ቀን 2014 ቀጠሮ መያዙ ተገልጧል።
በቃሊቲ ማ/ቤት ዞን 2 የሚገኘው ጌታነህ አቡሃይም ሆነ ጠበቃ ይርዳው አበበ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን ተቃውመውታል።
ከአሁን ቀደም በድብደባ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ የተፈጸመበት ታጋይ ጌታነህ አቡሃይ “ሕዝባዊ ትግሉ ማየሉን ተከትሎ አሸባሪ ተብለው በግፍ ከተሰቃዩት መካከል ብዙዎች በ2010 ሲለቀቁ በሕወሓቱ አገልጋይ በእነ ዳኛ ዘርዓይ ሴራ ተለይቼ እንዳልፈታ ተደርጌያለሁ፤ አሁንም ተስፋ ሳልቆርጥ ፍትህ እንዲሰጠኝ እጠይቃለሁ!” ይላል ከቃሊቲ ማ/ቤት ለአሚማ ባደረሰው መልዕክት።
ጠበቃ ይርዳው በበኩላቸው ይግባኝ ማቅረብ ማቅረብ መብት የሚሆነው በ90 ቀናት ውስጥ መሆኑ ህጉ የደነገገ መሆኑ እየታወቀ ጊዜው ካለፈ በኋላ ለአቃቢ ህግ ይግባኝ መፍቀድ አግባብ አይደለም ብለዋል።
ፍ/ቤት ጉዳዩ ያስቀርባል ካለም ያሳለፈበትን ምክንያት ጠቅሶ ተከሳሽ እና ጠበቃ ቀርበው በቂ ክርክር ሊደረግበት ይገባ ነበር ባይ ናቸው።
ለሰበር ሰሚ ችሎቱ በጽሁፍ አቤቱታ አስገብተናል ያሉት ጠበቃ ይርዳው ህዳር 30 ቀን 2014 በብይኑ ላይ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት አቤቱታችን ተመልክቶ ሁለቱን ወገኖች ያከራክረናል ብለን እናስባለን ሲሉ ገልጸዋል።