0 0
Read Time:5 Minute, 14 Second

እናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከእናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ የተሰጠ ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫ:_

ሀገራችን ኢትዮጵያን ከገባችበት የችግር አረንቋ ለማውጣት የሕግ የበላይነትን እንዲሁም መንግስት ተቀዳሚ ሚናው የሆነውን የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ኹኔታ እንዲያረጋግጥ ከላይ ስማችን የተጠቀሰው ፓርቲዎችን ጨምሮ ብዙ አካላት ወትውተናል፡፡

ሀገራችን ካለችበት ቀጠናዊና ውስጣዊ የፖለቲካ ምስቅልቅል አንጻር በቦታውና በጊዜው ተገቢ የእርምት እርምጃዎች ካልተወሰዱ በችግር ላይ ችግር እየተደራረበና እየተወሳሰበ ይሄድና ማጣፊያው ያጥረናል የሚሉ ሥጋቶች በኹሉም አካላት ይስተጋባ ነበር፡፡

የችግሮቻችን ኹሉ ምንጭ የሆነው የጎሳና ማንነት አደረጃጀት ይስተካከል የሚሉና መሰል የሕግ የበላይነት ይከበር ጩኸቶች ሰሚ አጥተው ሀገር የጥቂት ቡድኖች ሀብት ወደ መምሰል እየተጓዘች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በኹሉም የሀገራችን ክፍል ሥርዓት አልበኝነት የሕጋዊነት ያህል ነገሰ፡፡ ሕዝብ ተስፋ ያደረገው የለውጥ ጅምርም በእንጭጩ ተቀጭቶ ከየአካባቢው መፈናቀል፣ ጅምላ ፍጅትና ጦርነት ትቶልን ላይመለስ በሚመስል አኳኋን ርቆ እየሄደ ነው፡፡

እንደ አብዛኛው ሰው እኛም የለውጥ ጅምር ላይ የሚያጋጥም መንገራገጭ ነው ብለን በታጋሽነት ተመለከትን፡፡

ምርጫውና ውጤቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት አንጻር እንደማይሆን እያወቅን ከሚያነክስ መንግስት በኹለት እግሩ የቆመ ይሻላል በሚል በሚል በደሉን አፍነን የገባንበት ቢሆንም ተስፋ እንደተጣለበት ሳይሆን ገዢው ፓርቲ መጨረሻውን ለበጎ ሳያውለው እየቀረ ነው፡፡

በምጣኔ ሀብት በኩልም የገጠመን ምስቅልቅል ምን አልባትም በፖለቲካውና በጸጥታው ከገጠመን ምስቅልቅል የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም፡፡

ለምሳሌ በያዝነው ዓመት ሚያዝያ ወር እንኳን ይፋ በሆኑ መረጃዎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች አማካይ የዋጋ ግሽበት 36.6% የደረሰ ሲሆን፣ የምግብ ነክ ሸቀጦች ደግሞ 42.9% ደርሷል፡፡

ምን አልባትም በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዚሁ ሰበብ ዝቅተኛ ኑሮ የሚገፋው ማኅበረሰብና የመንግስት ሠራተኛው (ይህ ደግሞ ከፍተኛውን የሕዝባችን ቁጥር ይይዛል) ለከፍተኛ የኑሮ ቀውስ ተዳርገዋል፡፡

ሀገራችን ከውጭ ንግድ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ ሀገር በመላ ልካ ያስገባችው ሳይሆን፣ አንድ ጠንካራ ድርጅት ሠርቶ ከሚያገኘውም በታች ሆኗል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ፣ ይባስ ብሎ ጥቁር ገበያው ልጓም አልባ አካሄድ ተጨማምሮ ነገሮችን ከድጡ ወደማጡ አድርጓቸዋል፡፡

የግንባታ ግብዓቶች መወደድና ከናካቴው መጥፋት ብዙ ቀጣሪ የሆነውን የግንባታ ዘርፍ ሽባ አድርጎታል፣ ብዙዎችን ከሥራ ውጭ አድርጓል፡፡

የግብርና ግብዓቶች በተለይ ማዳበሪያ የዋጋው ሰማይ መንካት ሳያንስ እሱም አለመገኘት ገበሬው ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ላይ ያለውን የምርት እጥረት አባብሶ አደገኛ አረንቋ ውስጥ ዘፍቆታል፡፡

በአጠቃላይ የጦርነት ማግስት/ውስጥ ያለ ኢኮኖሚ እንደመሆኑ ብዙ የሚስተካከሉ ነገሮች ቢኖሩትም ኹነኛ ሀኪም በማጣቱ በማጣጣር ላይ ይገኛል፡፡

መንግሥትም ቢያንስ ለአጭር ጊዜ በገበያው ጣልቃ በመግባት ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋጽዖ ያደረጉ ጉዳዮችን በአግባቡ በመፈተሽ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ በዝምታ መመልከትን መርጧል፡፡

አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ያለው ደባና ከልክ ያለፈ ጠቅላይነት ተው ባይ አጥቶና መረን ለቆ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች ላይ አዲስ ማንነት ለመጫን በሚደረግ መፍጨርጨር ትምህርት ቤቶች ተረጋግተው የሚጠበቅባቸውን መማር ማስተማር ሂደት መተግበር ወደማይችሉበት ኹኔታ እየገፋ ይገኛል፡፡

ከዓለም ከተሞች በአንጻራዊ ሠላሟ የምትታወቀው አዲስ አበባ አኹን አኹን በሙስና፣ በጠራራ ጸሐይ ግድያ፣ ሥርቆትና አፈና የምትጠቀስ ከተማ እየሆነች መጥታለች፡፡

ሀገራዊና የከተማ ቅርሶች ጠያቂም ተጠያቂም በሌለበት በማን አለብኝነት ይፈርሳሉ፣ የመሬት ወረራ፣ አድሏይ የቤት እደላ፣ ማፈናቀሎች፣ በጸጥታ ኃይሎች የሚደርሱ ድብደባዎችና ግድያዎች አሳሳቢ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ አዲስ አበባ በአፍሪካ ብሎም በዓለም በምሣሌነት የምትጠቀስ ከተማ የነበረችውን ያህል አኹን ባለቤት አልባ ከተማ ወደ መሆን በፍጥነት እየተንደረደረች ነው፡፡

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት አማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎችን አውድሟል፤ ኢትዮጵያንም አክስሯል፡፡

በተለይ ደግሞ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ መንግስት በየምዕራፉ እያቆመ መቀጠሉ አውዳሚነቱን ምን አልባትም በብዙ መልኩ ጨምሮታል፡፡

ዛሬ ላይ የሕወሓት የጦርነት ነጋሪት መጎሰም የፌደራል መንግስቱ በህዳርና ታህሳስ ወራት ያካሄደውን ዘመቻ በቁርጠኝነት ማጠናቀቅ አለመፈለግ መሆኑና መቋጫ ሳይበጅለት ዝርው ሆኖ መተው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ሀገር በዚህ ኹኔታ ሳለች ነው እንግዲህ በአማራ ክልል ሕግ ማስከበር በሚል ዘመቻ የተጀመረው፡፡

ጦርነት ያለፈበትና አብዛኛው በዚሁ ሰበብ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከተነካካና ከደቀቀ ማግስት የተደረገ በመሆኑ አካሄዱ ላይ ጥንቃቄ መፈለጉ አያጠያይቅም ነበር፡፡

በአንድ በኩል የጦር መሣሪያ በብዙ ሰው እጅ ገብቷል፤ ይሄ ደግሞ ለሕገ ወጥነት መጋበዙ አይቀሬ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህና መሰል ምክንያቶችን በማድረግ “ማርከህ ታጠቅ” የተባለው፣ ሕዝቡ በትግሉ ወቅት እንደአልኝታ የቆጠረውን ፋኖን ለማሳደድ፣ አለፍ ሲልም የማኅበረሰቡን ሥነ-ልቡና ለመስለብ በሕግ ማስከበር ሰበብ አንገት ማስገቢያ ቀዳዳ ፍለጋ ሊገባ ይችል ይሆን ወይ? የሚሉ ጭንቀቶች በኹሉም ዘንድ እንደየመጠኑ ይንጸባረቅ ነበር፡፡

የፈሩት ይደርሳል… እንዲሉ በመጀመሪያ በክፉ ጊዜ “ድረስልኝ” ብሎ የጠሩትን “ፋኖ” ተረታ ተረቶችን እየሰደሩ በጓዳ ውይይቶችና በአደባባይ ሲያወግዙና ሲያስወግዙ ከርመው በይፋ ማሳደዱንና አፈናውን ቀጥለው ምንም የማይመለከታቸው ሕጻናትና ሴቶች ጭምር የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ እነበላይ ዘለቀ በፋኖነትና በአርበኝነት ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥተው ተፋልመው ሀገራቸውን ነጻ አውጥተው ሳለ በነገር ሠሪዎች ትብታብና አጉል የስልጣን ፍርሓትና ሽኩቻ ውለታቸው የተከፈላቸው በስቅላት ነበር፡፡

በደርግም በሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግም ለሀገራቸው ውለታ የዋሉ ምርጥ የጦር መሪዎች ገና ለገና ለአራት ኪሎ ቤተመንግስት ሥጋት ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ተቀጥፈዋል፡፡

አኹን በአማራ ክልል እየተደረገ ያለው መንግስታዊ አፈና ታሪክ ራሱን እየደገመ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ነው፡፡

የማኅበረሰብን ቅስም መስበር፣ የኃይል ሚዛንን ማስጠበቅ፣ አጉል የስልጣን ሥጋት፣ መሪ ማሳጣት እና በዚሁ አጋጣሚ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ምሑራንን፣ ጋዜጠኞችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን ከመከላከያና ልዩ ኃይል ተመላሾችን ለማሳደድ እየተጠቀመበት ነው፡፡

በሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ታፍነዋል፣ በወልዲያ፣ ሞጣ፣ መርዓዊ፣… ብዙዎች የቡድን መሣሪያ በታጠቁ አጋኣዚያዊ እርሾ ባለቀቃቸው ኃይሎች ተገድለዋል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ስማችን ከላይ የተጠቀሰው ፓርቲዎች እንዲህ ያለውን በሕጋዊነት ሽፋን የሚደረግን መንግስታዊ አፈና በጽኑ እያወገዝን ለሞቱና አካላቸው ለጎደለ ወገኖቻችን ልባዊ ሀዘናችንን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

እነዚህና መሰል ነባራዊ ሀገራዊ ኹኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እኛ በዛሬው ዕለት ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠን የፖለቲካ ፓርቲዎች፡-

መንግስት ማኅበረሰብን በሃይማኖት፣ በወንዝና በቡድን እየከፋፈለ ለመምታትና ለማፈን የሚያደርገውን መፍጨርጨር እንዲያቆም፣ ሕዝብም ይሄንኑ እኩይ የከፋፍለህ ግዛው/ምታው አካሄድ ተረድቶ አንድነቱንና ሰላሙን እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በሕግ ማስከበር ላይ የማያወላዳ አቋም ያለን ቢሆንም በአፈናና በግድያ ሕግ ማስከበር እንደማይቻል አጠንክረን እያሳሰብን፣ ማፈን መግደልና የማኅበረሰብን ቅስም የመስበር አካሄድ በአፋጣኝ እንዲቆም እየጠየቅን፣ ሚዲያው፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ዳያስፖራው፣ ፓርቲዎችና መላው ኢትዮጵያውያን ችግሩ የአንድ ክልል እዳ ብቻ አለመሆኑን ተረድተው በተገቢው ድምጽ እንዲያሰሙ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

በሕግ ማስከበር ሰበብ የታፈኑ ንጹሓን፣ ጋዜጠኞች፣ ማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የፋኖ አባላትና ቤተሰቦቻቸው፣ ምሑራን፣ የጸጥታ ተቋማት ተመላሾችና አባላት፣ የፓርቲ አመራርና አባላት እንዲለቀቁ፣ መንግስት ጠረጥሬያቸዋለሁ ብሎ ካሰበ ደግሞ ተገቢውን የሕግ ሂደት በመከተል ለፍርድ ቤት ከማቅረብ ጀምሮ መሰል ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ እንጠይቃለን፡፡

“ፋኖ” በጭንቅ ጊዜ ሀገር “ድረስልኝ”ብላ የጠራችው ባለውለታ እንጂ ለሹመትና ለሽልማት የመጣ ባለመሆኑ መንግስት አጉል ሥጋቱን አስወግዶ የያዘውን አካሄድ እንዲፈትሽ እንጠይቃለን፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሕልውና ወደባሰና ውስብስብ ችግር ከማምራቱ በፊት መንግስት ያልተገባ አካሄዶችን እንዲያርም ሕዝብም እየሆነ ያለውን ነገር በቅርበትና በትኩረት እንዲከታተል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በሰሜኑ የተቀሰቀሰው ጦርነት ካደረሰው ውድመት በላይ ሌላ ውድመትና እልቂት እንዳያደርስ ያሉ የሰላም አማራጮች ኹሉ እንዲተገበሩ እየጠየቅን፣ ሕወሓት እኒህን አመራጮች ገፍቶ ወደዳግም ጦርነት ከገባ ተገቢውና የመጨረሻውን ቅጣት ያገኝ ዘንድ ከወዲሁ መከላከያው፣ ልዩ ኃይሉ፣ ፋኖውና ሚሊሻው በቂና ከባለፈው ትምህርት የተወሰደበት የተቀናጀ ዝግጅት እንዲያደርጉ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

መንግስት አኹን ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ሚሊዮኖችን ለጎዳና እና ለከፋ ረሃብ ከመዳረጉ በፊት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ያለውን የገበያ ምስቅልቅል እንዲያርምና እንዲያረጋጋ እንጠይቃለን፡፡

አኹን አኹን አብዛኛው የሀገራችን መሬት ያለማዳበሪያ የማያበቅልና ምርታማነቱም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እየሆነ በመምጣቱ አቅርቦቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ፈጣንና አዋጭ ብሎም ዘላቂ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወሰዱና የገበሬው ብሎም የመላ ሀገሬው ጭንቀት እንዲቀል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

“ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ”

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
እናት ፓርቲ

ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator