Nov. 11, 2022
ኅዳር 3፣ 2015 ዓ/ም
ከጋሻ የአማራ ህዝባዊ ኃይል-ፋኖ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ
በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ።
አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ – እውነተኛ የአማራ ተወካዮች ያልተሳተፉበት ድርድር
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ፈጽሞ አያመጣም!!!
የኢህአዴግ ሁለት ክፋዮች ለሥልጣን ይገባኛል ግብግብ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ህወሃት በሰሜን እዝ ክፍለ ጦር ላይ በከፈተው ክህደታዊ የጥቃት እርምጃን መፈንዳቱ ይታወሳል። በዚህ የሰሜኑ የሀገራችንን ያካተተው አጭር የሁለት አመታት ጦርነት ውስጥ የአማራ ነገድ በታሪኩ ገጥሞት በማያውቅ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ፣ ማህበራwዊ፣ ቁሳዊና ስነልቦናዊ ውድመት፣ እልቂት፣ ውርደት እና ስነ ማሕበረሰባዊ ምስቅልቅልነትን እንዲቀበል ተደርጓል።
ይህን እጅግ አውዳሚ የሆነውን የሰሜን ጦርነት ለማስቆም በአሜሪካን ዋና አስገዳጅነትና በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የብልጽግናው መንግስት እና የትግራዩ ህወሃት መካከል ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ ላይ በተካሄደ ንግግር ሁለቱ ቡድኖች ለመስማማት መቻላቸውን ጋሻ አማራ እንደ አንድ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተል የአማራ ድርጅት ዜናውን ሰምቷል።
የስምምነቱ መደራደሪያ ዋና ጭብጥ ሁለቱ ቡድኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ከማድረጋቸውም በላይ በመካከላቸው ያለውን የፖለቲካ ልዩነትና ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን ችግሮችን በሀገሪቱ ሕገ መንግስት መሰረት ተደራድረው ለመፍታት እና ግንኙነታቸውን ቅድመ ጥቅምት 24-2013 ለመመለስ መስማማታቸውን ይገልጻል።
የአማራ ሕዝብ አማራን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለመበተን ታቅዶ የተዘጋጀን ህገ መንግስት መሰረት ባደረገና ህገመንግስቱን በአረቀቁት ትህነግና ኦነግ እና ፀረ አማራና ፀረ አትዮጵያ ሆኖ የፀደቀውን ህገ መንግስት ለማስፈፀም በትህነግ በተቋቋመው ፀረ አማራ ብአዴን የሚደረግ ማናቸውንም ድርድሮችና ስምምነቶችን እውቅና አይሰጥም።
በጠላትነት ከሰላሳ አመታት በላይ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈሉት ኃይሎች በጫሩት የስልጣን ይገባኛል ጦርነት አማራው ህልውናውን ለማስከበር እና ሀገርን ለመታደግ ሲል ተገዶ ጦርነት ውስጥ ገብቷል። በዚህም የጦርነት ሂደት ውስጥ በተከፈለ ከፍተኛ ምስዋእትነት ለረጅም ዓመታት ያህል አማራነታቸውን ተነጥቀው በግፍና በስቃይ በወያኔ የባርነት ቀንበር ስር እንኖሩ የተገደዱትን የወልቃይት ጠገዴ ሁመራ እና የራያ አማራ ወገኖቹን ነጻ ማውጣት የቻለውን ያህል፤ የተከፈለው አጠቃላይ የጦርነት ዋጋ ስንመለከት መሸከም ከምንችለው በላይ እልቂትና ውድመትን መቀበል እንደተገደድን ማረጋገጥ ተችሏል። አማራው ወገናችን በጦርነቱ የከፈላቸውን ዋጋዎች በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል፦
1ኛ- ለጊዜው በውል ያልታወቀ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይላችን እንዲረግፍ መደረጉ
2ኛ – በሕዝባችን ላይ አሰቃቂ የሆነ አስገድዶ መድፈር፣ መዝረፍ፣ መደብደብና የሰውን ልጅ ከሰውነት በታች የሚያደርጉ ስነልቦናዊ ጥቃቶች የተፈጸመበት መሆኑ
3ኛ – የሕዝባችን መሰረተ ልማት ተቌማቶች የጤና፣ የትምህርት፣ የመብራት፣ የባንክ እና መሰል የሆኑ መሰረተ ልማቶች ተዘርፈው ለ30 ዓመት ወደ ኋላ እንዲመለስ የተደረገ መሆኑ
4ኛ- ታሪካዊ የቅርስ ተቌማትና እንዲሁም ጥንታዊ የእምነት ተቋማት ተዘርፈው ለወድመት መዳረጋቸው
5ኛ – የግለሰቦች ሀብት፣ ንብረት እና የቁም እንስሳትን ጨምሮ በወያኔ ወራሪዎች እይታቸው የገባን ሁሉ የተዘረፈበት ሲሆን በአጠቃላይ ከግማሽ ትሪሊዮን (ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ) በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሊውድመበት የቻለ መሆኑን እናውቃለን።
አዎ የአማራ ወገናችን ኢትዮጵያ ሰላምን በማጣቷ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፤ ሰላምን ከማንም ባላነሰ ይፈልጋታል። ጦርነቱን ለማስቆም የተደረገው ድርድር ዘላቂ የሰላምን እንዲያዋልድ ከተፈለገ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” የሚባለው አይነት እንዳይሆን አፋጣኝ ማስተካከያ ይድረግ እንላለን። የአማራ ወገናችን ለትክክለኛ ድርድርና ሰላም ለመቀመጥ የራሱን ተወካዮች ከእውነተኛ እና ታማኝ የአማራ አደረጃጀቶችና ግለሰቦች የምክክር መድረክ መርጦ እንዲሳተፉ ሲደረግ እና የሚከተሉትን ነጥቦች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ ዝግጁነት ካለ ለእውነተኛ ሰላምና ድርድር ይቀመጣል።
- የፋኖ አመራርና አባላት፤ የአማራ ልዩ ሀይል አመራርና አባላት፤ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች በሙሉ ከስር ተፈተው ወደ ነበረ ቦታቸውና ስራቸው ተመልሰው ሲረጋገጥ
- ከ20 ሚሊዮን በላይ አማራ ተፈናቅሎ በረሀብና በበሽታ እያለቀ የሚገኝን ሕዝብ ቅድሚያ ወደ ቀየው ሳይመለስና ሳይቋቋም፤ ያፈናቀሉት የገደሉት የዘረፉት ወንጀል ፈፃሚ የመንግስት ተብየው ባለስልጣናት ተጠያቂነታቸው ሳይረጋገጥ የሚደረግ ማናቸውም ድርድርና ስምምነት በአማራ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም
- በፓለቲካ ውሳኔና በማን አለብኝነት ከአማራ የተወሰዱ አፅመ እርስቶች ወደ ነባር ባለቤታቸው አማረ ተመልሰው በአማራ ቁጥጥር ውስጥ መሆናቸው ሲረጋገጥ
- አማራን ለማጥፋት በተደረገ ተደጋጋሚ ጦርነት የተፈፀመ ሰባዊ መብት ጥሰት፤ የተዘረፈ ሀብትና ንብረት ለመመለስ እና የወደመ መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት እና የሞራልና የደም ካሳ ለመክፈ አስተማማኝ ስምምነት ሲደረግ
- በጦርነቱ ሰባዊ ወንጀለ፣ ክህደትና የተለያዩ አሻጥሮችን የፈፀሙ የጦርና የፓለቲካ አመራሮች ለፍትህ እንደሚቀርቡ ማረጋገጫ ሲሰጥ ብቻ በትክክለኛና አዋጭ ድርድር በመቀመጥ ለእውነተኛ ሰላምና ደህንነት የአምበሳውን ድርሻ ይወጣል።
ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማናቸውንም አይነት ድርድርና ስምምነት የአማራ ሕዝብ እውቅና አይሰጥም።
አማራነት ያሸንፋል
ጋሻ አማራ ህዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ