በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የሚገኙ ሁለት የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅት ፋብሪካዎች ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ በአሸባሪው ሕወሓት አማካኝነት ውድመትና ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው ተገልጧል።
ከልማት ድርጅቶቹ አንዱ የሆነው ጎሽ ሜዳ ቧንቧና ፕላስቲክ ድርጅትን አሸባሪው የትሕነግ ኃይል በመዝረፍ የማይጠቅመውን በማውደም ድርጅቱን 120 ማሊየን ብር አሳጥቶታል ነው የተባለው።
ድርጅቱ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ትልቅ የውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን በማምረት ከውጭ የሚገባውን የጠብታ መስኖ የሚያገለግል ፓይፕ ምርት በአገር ውስጥ በማምረት ውሃ አጠር ለሆኑ ለምስራቅ አማራ አካባቢዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክት እንደነበር ተመላክቷል።
አሁን ላይ ምርት ማምረት በማይችልበት ደረጃ ላይ ሙሉ ለሙሉ በመውደሙ በአጭር ጊዜ ወደ ምርት ለመግባት እንደማይችልም ታውቋል።
ሌላው የክልሉ የልማት ድርጅት የአማራ ህንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የደሴ ግንባታ ግብዓት ማዕከል አሸባሪው ኃይል 1 ቢሊየን የሚጠጋ የማምረቻ ማሽኖች፣ መጋዘኖችና ተሽከርካሪዎች ዘረፋና ውድመት አድርሶበታል።
የደሴ ግንባታ ግብዓት ማምረቻ ድርጅት ለምስራቅ አማራና ለአፋር ክልል የተገጣጣሚ ግድግዳ፣ የአልሙኒየም፣ የብረታብረት፣ የብሎኬትና የህንፃ መወጣጫ ምርቶች የሚያቀርብ ድርጅት ሲሆን አሁን ላይ የሽብር ቡድኑ ባደረሰው ዘረፋና ውድመት ማምረት እንደማይችል ተገልጿል ያለው ኢትዮ መረጃ ኒውስ ነው።