ባሳለፍነው እሁድ በEthio Tube በዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ ዙሪያ ባደረነው ክርክር የኔ ማጠንጠኛ ሀሳብ የነበረው ኦሮሞ ከግራኝ በፊት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ያልነበረ መሆኑንና የግራኝን ዘመን ተከትሎ ነባሮቹን የኢትዮጵያ ነገዶች ድምጥማጣቸውን እያጠፋ፣ ማንነታቸውን እየቀየረ፣ ቋንቋቸውን እየደመሰሰ፣ በመሬታቸው ላይ ጭሰኛ እያደረገ፣ የነበራቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔ እያወደመ፣ የኢትዮጵያን ምድር የሰው ልጅ ግዳይ ክምርና የደም ጎርፍ የሚፈስበት ገሀነም በማድረግ ግፍ እየሰራ ኢትዮጵያን እንደወረረና ዳግማዊ ምኒልክ ባለርስት አድርገውት ቀረ የሚል ነበር። እኔን በመቃወም ይከራከር የነበረው ዳናኤል አጀማ ግን ይህንን ታሪክ በመቃወም ኦሮሞ ከግራኝ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር እንደነበር ያሳይልኛል ያለውን የፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰንን “The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia: 1300-1700” እና የጀርመናዊውን የአይኬ ሀበርላንድ “Galla Sud-Athiopiens” መጽሐፍት [ይህም ስህተት ስለሆነ በሌላ ጊዘ እመለስበታለሁ] በመጥቀስ ተከራክሯል። ዳንኤል የጠቀሰውን የፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰንን መጽሐፍ በሚመለከት እኔም በሰጠሁት መልስ ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን በመጽሐፉ ያቀረበውን “ማስረጃ” የገለበጠው ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ በስህተት ካቀረቡትና ከእናት መዝገቡ ጋር ካልተመሳከረው የአምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥት በመሆኑ የፕሮፈሰር መሐመድ መጸሐፍ ኦሮሞ ከግራኝ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር እንደነበር ለማሳየት የሚጠቀስ የታሪክ ማስረጃ ሊሆን አይችልም የሚል ነበር። ይህን እንድል ያስቻለኝ ከሁለት ዓመት በፊት የፕሮፌሰር መሐመድን መጽሐፍ በማነብበት ወቅት ከጠቀሳቸው ከፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ ጋር በነበረኝ የግል ውይይት ነገሩን አውቅ ስለነበር ነው። ከፕሮፌሰር ጌታቸው ጋር የነበረን ውይይት ፕሮፈሰር መሐመድ የጠቀሰውን የሳቸውን መጽሐፍ በማንሳት የተነጋገርን ሲሆን በውይይታችን መጨረሻ ላይ ፕሮፈሰር መሐመድ ከእሳቸው የጠቀሱው ምንጭ ከእናት መዝገቡ ጋር ያልተገናዘበና የተሳሳተ መሆኑን በማውሳት እሳቸው የተጠቀሙትን ያልተገናዘበ ታሪከ ነገሥት በመጥቀስ የሚጽፍ ቢኖር ስህተት መሆኑን አውግተን ነበር። ከውውይታቸን በኋላም ፕሮፈሰር መሐመድ የጠቀሰው እሳቸው ያቀረቡት ምንጭ ከእናት መዝገቡ ጋር ያልተገናዘበ፤ ይልቁንም የተሳሳተ መሆኑን እድሜ ሰጥቷቸውን መጽሐፉን እንደገና ሲያሳትሙ እስኪያርሙት ድረስ ውይይታቸን ዋቢ አድርጌ በፌስቡክ ማስተካከያ እንድጽፍ ነግረውኝ ነበር። ሆኖም ግን በስንፍና ምክንያት እስካሁን አልተሳካልኝም ነበር። ዛሬ ግን እንደ ስሙ ትልቅ የሆነው ቴዎድሮስ ጸጋዬ እድሉን በማመቻቸት ፕሮፈሰር ጌታቸው ራሳቸው ባንደበታቸው የተሳሳቱትን እርማት እንዲሰጡ አስችሏል። ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ የአባ ባሕርይን ዜናሁ ለጋላ “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በመለሱበት መጽሐፋቸው ገጽ 26 የግርጌ ማስታወሻ 17 ላይ “ንጉሡ በሰኔ ሰባት ከሠራዊቱ ጋር ከጋላ ሀገር ተነሳ” በማለት ያሰፈሩትና ከዐፄ አምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥት እንዳገኙት የነገሩን ጥቅስ ከእናት መዝገቡ ጋር ሳያመሳከሩ ሌሎች ሰዎች የፊደል ግድፈት ፈጽመው የገለበጡትን በመጥቀስ ያቀረቡት ነው። ከእናት መዝገቡ ላይ ያለው ፕሮፈሰር ጌታቸው የጠቀሱት ትክክለኛ ቃል እንዲህ የሚል ነው፤ “ንጉሡ በሰኔ ሰባት ከሠራዊቱ ጋር ከጋሣ ሀገር ተነሳ” የሚል ነው። ይህንን ከእናት መዝገቡ ጋር የተመሳከረ ቅጂ ፓውሎ ማራሲኒ “la campagna de ‘Amda Ṣeyon I contro l’Ifāt” በሚል ባዘጋጀው የንጉሡ ታሪከ ነገሥት ገጽ 68 እና ገጽ 82 ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ የቦታው ስም ማንፍሬድ ክሮፕ “Amda Seyon Der Siegreiche” በሚል ባዘጋጀው የዐፄ አምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥት ገጽ 11 እና 18 ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ስህተቱ የተፈጠረው ከእናት መዝገቡ የገለበጡ ሰዎች “ጋሣ” በሚል በብራና ላይ ከተጻፈው ታሪከ ነገሥት ውስጥ የሚገኘውን የቦታ ሰም ሲገለብጡ “ጋሳ” በሚል ከገለበጡት በኋላ፤ ይህን የግልባጭ ግልባጭ የገለበጡ ሰዎች ደግሞ “ጋሳ” በሚል በተገለበጠው የቦታ ስም ውስጥ ያለችዋን “ሳ”ን “ላ” አድርጎ በመገልበጥ “ጋሳ” የሚለውን የቦታ ስም ወደ “ጋላ” በመቀየራቸው ነው። ሆኖም ግን እናት መዝገቡ ላይ የምናገኛው የቦታው ስም የተጻፈው በእሳቱ ሰ ሳይሆን በንጉሡ ሠ ነበር። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ይህንን ሳያመሳክሩ በስህተት የተቀዳውን በመጥቀስ ያቀረቡትን ነው ፕሮፌ ሰር መሐመድ ሐሰን እንደ ታሪክ ምሁር በራሱ ለማመሳከርና ለማጣራት ሳይሞክር የፖለቲካ ፍላጎቱን ይደግፍልኛል ብሎ ስላመነ ብቻ የተሳሳተውን ቅጂ በመጥቀስ ኦሮሞ ከግራኝ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር እንደነበረ አድርጎ ተረት የጻፈው። ሊቁ ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ ግን “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች” በሚል ባዘጋጁት ድንቅ መጸሐፋቸው ውስጥ ሳያመሳክሩ በስህተት የጠቀሱትን የዐፄ አምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥት ቅጂ የተሳሳተ መሆኑን አምነው እነሆ እርማት ሰጥተዋል። የሚሰራ ሰው ይሳሳታል። ሲሳሳት ደግሞ እንደ ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ የተሳሳተውን ያርማል! እናመሰግናለን ፕሮፍ! ፈጣሬ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይደጥዎት ዘንድ በፀሎት የሚታገዝ በጎ ምኞቴን እገልጽልዎታለሁ። ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን በመጸሐፉ ውስጥ በታሪክ ላይ ስለፈጸመው ስለዚህ ኅጢያትና ሌሎች ዘግናኝ የፈጠራ ትርክቶቹን በሰፊው የሚተች የታሪክ አዝመራ ማንበብ የሚሻ ቢኖር ፕሮፈሰር ሀብታሙ መንግሥቴ ተገኘ “በራራ ቀዳሚት አዲስ አበባ” በሚል ባዘጋቸው ድንቅ የታሪክ ምርምር ውስጥ ምዕራፍ ስድስት ላይ ያቀረበውን ታሪክ ያንብብ። የፕሮፈሰር ሀብታሙን መጽሐፍ ስታነቡ የጋሣን መንገኛም ታገኛላችሁ! ከታች የታተሙት ዶሴዎች ፓውሎ ማራሲኒ “la campagna de ‘Amda Ṣeyon I contro l’Ifāt” በሚል ባዘጋጀው የንጉሡ ታሪከ ነገሥት ገጽ 68 እና ገጽ 82 ላይ ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ በስህተት የጠቀሱት የቦታ ስም በንጉሡ ሠ ፊደል “ጋሣ” ተብሎ የተጠቀሰውን የቦታ ስም የሚያሳዩ ናቸው። አንደበተ ርቱዕው ቴዎድሮስ ጸጋዬ ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ በመጽሐፋቸው ውስጥ በስህተት የጠቀሱት ምንጭ የተሳሳተ መሆኑን እንደሚያውቁና እናት መዝጋቡ ላይ የሚገኘው የቦታው ስም ጋላ ሳይሆን ጋሣ መሆኑን ለሕዝብ ማረጋገጫ በመስጠት እንዲያሳውቁ እድሉን ስለፈጠረና ታሪካችን እንዲቃ ዘወትር ለሚያደርገው ብሔራዊ[ አገራዊ] አገልግሎት ከፍ ያለ ምስጋና ይገባዋል። መልካም ድምጫ!
https://www.youtube.com/watch?v=P406PzXngM0