የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ነሃሴ 30/2012 ዓ/ም የፌደሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር /ትሕነግ/ የሚመራው የትግራይ ምርጫ ጉዳይ ላይ ያሳላፈውን ውሳኔ ተመልክቷል። ከአሁን ቀደም ተቋሙ የትሕነግ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ ጥያቄዎቻችን ሲያዳፍን ከነበረበት አሰርሩ ተላቆ፣ በአሁኑ ወቅት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስለመላሽ ኮሚቴ ያቀረበውን ጥያቄ እውቅና ሰጥቶ የውይይቱ አካል ማድረጉ እና በምርጫው ሰበብ እየተፈፀመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አጀንዳ ማድረጉን ኮሚቴው ያደንቃል። ይሁንና የአሰራር መሻሻል ያሳየው ምክር ቤቱ በተጠባቂው ስብሰባ ሕዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ማንነት ተኮር ጥቃትና የጅምላ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ማስቆም ስለሚቻልበት አግባብ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለን አናምንም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ላይ ያንዧበበውን አደጋ ለመፍታት የሚመጥን ውሳኔ አስተላልፏል ብለን አናምንም። ምክር ቤቱ በዝግ ባደረገው ስብሰባ ከአሁን ቀደም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በይፋ ሕገወጥ እንደሆነ ያወጀውን፣ የመንግስት ባለስልጣናት በደተጋጋሚ ሕገወጥ መሆኑን ለሕዝብ ያስረዱትን፣ የመንግስት ሚዲያዎች በየቀኑ የሚመለከታቸውን አካላት እያቀረቡ ሕገወጥ መሆኑን እያሳዩት ያለውን ትሕነግ መራሹን ምርጫ ሂደት ሕገወጥ ነው ከማለት ባለፈ ሁኔታውን ያገናዘበ ግልፅ መፍትሔ ማስቀመጥ አልቻለም። ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው ትሕነግ በወልቃይት ጠገዴና ራያ ሕዝብ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ እንደሆነ አምኗል። አንድ የፌደሬሽኑ አባል በሕዝብ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፅም የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ገብቶ ማስቆም እንዳለበት በግልፅ የተቀመጠ ነው። የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 የሰብዓዊ መብት ረገጣን ለጣልቃ ገብነት ዋና ምክንያት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ይሁንና ምክር ቤቱ በትላንቱ ውሳኔው ወልቃይትና ራያ ላይ እየተፈፀመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዴት መቆም እንዳለበት በማያሻማ መልኩ አላስቀመጠም። የፌደሬሽን ምክር ቤትን የመሰለ መንግስታዊና ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ተቋም ቀርቶ መንግስታዊ ያልሆኑ የመብት ተሟጋቾች እንኳ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲኖር ጥሰቱ እንዴት መቆም እንዳለበት ለሚመለከታቸው አካላት ኀላፊነታቸውን ያስታውሳሉ፣ ግዴታቸውን ይጠቁማሉ። መፍትኄ ነው የሚሉትን ነገር በግልፅና በማያሻማ መልኩ ይጠቁማሉ። የፌደሬሽን ምክር ቤት ይህን ጉዳይ ያነሳው ምርጫን ያህል ጉዳይ ሕገወጥ ነው እየተባለ በማን አለብኝነት የቀጠለው ትሕነግ ላይ መሆኑ እየታወቀ የሰብዓዊ መብት ረጋጣውን ያለመፍትሔ ያለፈው የትላንቱ ውሳኔ የሕዝባችን ስቃይና መከራ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሆኖ አግንተነዋል፡፡ ውሳኔው በከፋ ጭቆና ውስጥ ያለን ሕዝብ እንደወከለ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በእጅጉ አሳዝኖናል። ይህን ውሳኔ ሲጠብቅ ለነበረው ሕዝባችንም በፌደራል መንግስቱ ላይ እምነት እንዳይጥል የሚያደርግ ነው።በተመሳሳይ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ትሕነግ መሩ ምርጫም ሆነ በምርጫው የሚሳተፉት አካላትን ተግባር ሕገወጥ መሆኑን እስካሁን የተባለውን በድጋሚ ያሳወቀን ቢሆንም እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው፣ የዜጎችን ሰቆቃ ማስቆም እንዳለበትና ሀገርን ከአደጋ መታደግ አገራዊ ሥልጣን (የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 62 (9) ያስታውሷል) እንዳለበት ተቋም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በአደጋው ልክ ማስቀመጥ አልቻለም። በትሕነግ የከፋ አገዛዝ ውስጥ ያለውን የወልቃይት ጠገዴ የአማራን ሕዝብ እንደወከለ ኮሚቴ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ሕዝባችን ሌላ ድርብ በደል እየደረሰበት ስለመሆኑ፣ የአገሪቱን ሕግ አግባብ ተከትለን በተደጋጋሚ ስናስረዳ ቆይተናል። የወልቃይት ጠገዴ አማራ አርሶ አደር የማምረቻውን ወራት ከመኖርያው ርቆ የሰብል ስራውን የሚያከናውን ሲሆን፤ በሕገወጡና የገበሬውን የማምረቻ ወቅት ባላገናዘበው ምርጫ ምክንያት ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ የሞሉትን ወንዞች አቋርጦ፣ የደከመበትን ሰብሉን ጥሎ፣ በዚህ የኮሮና ወቅት ለምርጫ ምዝገባና ምርጫው ላይ እንዲሳተፍ በአስገዳጅ አካባቢዊ ሕግጋት ተፈርዶበታል። የወልቃይት ጠገዴ ሚሊሻ በምርጫው ሰበብ ትሕነግ ለሚያደርገው የጦርነት ቅስቀሳ ፍላጎት የለኝም በማለቱ የራሱን መሳርያ እየተቀማ፣ ለእስር፣ ከዚህም ባለፈ ሕይወቱን እስከማጣት ደርሷል። በከተማ የሚኖረው ሕዝባችን ሕገወጡን ምርጫ ካልተሳተፈ የገንዘብና የእስር ቅጣት እንደሚጣልበት መንግሥታዊ ዛቻና ግዳጅ እየተፈጸመበት ይገኛል። የተሽከርካሪ ባለቤቶች ለምርጫ ቅስቀሳ አልተሳተፋችሁም በሚል የገንዘብና የእስር ቅጣት እየተጣለባቸው፤ በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ በግድ ከተያዘው ርስቱ “ውጣ” እየተባለ በምርጫም ምክንያት ለሰብዓዊ ቀውስ ተዳርጓል።የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በአንድ በኩል ከቅኝ አገዛዝም በከፋ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን ሕዝብ ድምፅ ለማሰማት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ የከፋ አገዛዝ ላይ የሚገኝ ሕዝብ በአንድ ወቅት ተስፋ ተጥሎበት የነበረውን የለውጥ ሂደት የሚጎዳ፣ የትግራይና የአማራን ሕዝብ መቃቃር ውስጥ ወደሚያስገባ ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገባ ሲያረጋጋና ሲሰራ ቆይቷል። በትሕነግ ጫና ላይ የሚገኘው ሚሊሻና ወጣት “ራሳችን እንከላከላለን” ብሎ የራሱን አማራጭ ሊወስድ ሲጥር እንኳ ከሚፈፀምበት በደል አንፃር ስሜቱን ተጭነን የመንግስትን ውሳኔ እንዲጠብቅ ብዙ ጥረት አድርገናል። በዚህም ሀገር የማዳን ተጫማሪ ተልዕኮ በራሳችን ፍቃድ ወስደን ሕዝባችንን በማረጋጋት ረገድ ስኬታማ ስራ አከናውነናል ብለን እናምናለን፡፡ ይሁንና ከትላንቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በኋላ ትሕነግ በየቀኑ ከሚፈፅመው ጭካኔ አንፃር ‹የራሳችን አማራጭ እንወስዳለን› የሚለውን ሕዝባችን ለማረጋጋት ተቸግረናል፡፡ ከሕዝባችን ትልቅ ኀላፊነት እንደተቀበለ ኮሚቴ፣ ባለፉት ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ከፌዴራል መንግሥቱ በተቃራኒ መሰለፍን እንደ ትግል ስልት የሚቆጥረው ትሕነግ የሕገወጡን ምርጫ እንቅስቃሴ ከጀመረ ወዲህ እንደ አማራ ብቻ ሳይሆን ለሀገረ-መንግሥቱም ይጠቅማል ያልነውን አዎንታዊ ሚና ይዘን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይሁንና ይህን የሀገረ-መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥለውን ሕገወጡን ምርጫ የማስቆም ትልቅ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት የፌዴራሉ መንግስት እየወሰደው ያለው አቋም ጥረታችን ከንቱ የሚያስቀር፣ ሕዝባችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሰራር አሳድሮት የነበረውን እምነትና ተስፋ የሚቀለብስ ነው፡፡ በሕዝባችን ላይ ከቀጠለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ አኳያ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የትሕነግ አገዛዝ የሚያደርሰውን በደል የሚያስቀጥል፤ ሕዝባችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ እያደረገን ያለውን ጥረት እውቅና የሚነፍግና ጭቆናውን ለመመከት ሌሎች አማራጮችን እንዲያይ የሚገፋፋው ሆኖ አግኝተነዋል።በትሕነግ ሕገወጥነት በሕዝባች ላይ እየደረሰ ያለው መከራ፣ ኢትዮጵያ የተደቀነባት አደጋ በትናንቱ መግለጫም የሚቆም እንዳልሆነ እየታወቀ፣ የምክር ቤቱ ውሳኔም ታውቆ የታደረ አቋም እንጅ የሕዝባችን ችግር የማይፈታ፣ የሀገረ-መንግሥቱን ህልውና የማይታደግ እንዲያውም ማን አለብኝነት መለያው ላደረገው ትህነግ የልብ ልብ የሚሰጥ ነው። የፌደሬሽን ምክር ቤት መግለጫ ከሰጠም በኋላ በሕዝባችን ላይ የሚፈፀመው በደል ቀጥሏል። ምርጫውን ሕገወጥ ነው ያለው፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳለ የገለፀው የፌደሬሽን ምክር ቤት በምርጫው ምክንያት ለሚቀጥሉት በደሎች ምን መፍትሄ ይሰጣል? መንግስትስ ምንድን ነው የሚያደርገው? የሚለውን የሕዝባችንን ጥያቄ የሚመልስ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም፡፡ስለሆነም ይህን ሁሉ ሕገወጥነት ማስቆም ያለበት የፌዴራሉ መንግስት ነው። የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ጉዳዩን እንደገና አጢኖ የዜጎችን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም፣ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን አሁንም እድሉ አለው። ከዚህ ባነሱ ጉዳዮች “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ውስጥ ለመጣል” ሲል የምናውቀው መንግስት፣ ትሕነግ የቀጠለውን ሕገወጥነት ከዚህ አንፃር ሊበይነው አለመድፈሩ ያስተቸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ መንግስት ትሕነግ እየሄደበት ያለውን ሕገወጥነት ከአሁን ቀደም ታውቆ ባደረው ሕገወጥነት ብቻ ከመጥራት ባሻገር ሕገወጥነቱን የማስቆም መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ይጠበቅበታል፡፡ ጠርቶ ከመበተን፣ በመሆኑም፤1ኛ. የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የፌደሬሽን ምክር ቤት ለትሕነግ ሕገወጥነት የሚመጥን፣ ተሸክሞት ባለው ሀገራዊ አደጋ ልክ ትርጉም ያለው መፍትሔ ሰጪ ውሳኔ እንዲወስን፤2ኛ. የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረበው የማንነት ጥያቄ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ወልቃይት እና አካባቢው ከትህነግ አገዛዝ እጅ ወጥቶ በፌዴራሉ መንግስት ስር እንዲቆይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ፤ 3ኛ. መንግስት ትሕነግ በምርጫ ሰበብ እየሄደበት ያለውን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ለመቀልበስ እንዲሁም መጠነ ሰፊና አስከፊ የመብት ጭፍለቃን ለማስቆም ሕገ-መንግሥታዊ አንቀጾችንና አዋጆችን መሠረት በማድረግ አስቻይ መፍትሔዎችን አቅርቦ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።

ጳጉሜ 1/2012 ዓ/ም

ጎንደር

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator