አቻምየለህ ታምሩ
በየትኛውም ጎራ የተኮለኮሉት የትግሬ ብሔርተኞች የስልጣን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በአማራ ጥላቻቸው ፋሽስት ወያኔን የሚያስንቁ እንጂ የተሻሉ አለመሆናቸውን በፋሽስት ወያኔ መንበር በጊዜያዊነት ከተተኩት ደቂቀ ሕወሓት እስኪበቃን ድረስ አይተናቸዋል። ከሁለት አመታት በፊት ፋሽስት ወያኔ ከግፍ መንበሩ ከተወገደ በኋላ ትግራይን እንዲያስተዳድሩ በዐቢይ አሕመድ የተሾሙት የአረና፣ የትዴት፤ የትግራይ ብልጽግናና የፈንቅል ፋሽስቶች በተሰየሙበት ወንበር እንደተቀመጡ ቀዳሚው ጥያቄያቸው ትግራይን የማስተዳደር ጉዳይ ሳይሆን በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከ1600 በላይ ንጹሐን የአማራ ተወላጆች በትግራይ ፖሊስ፣ በትግራይ ልዩ ኃይል፣ በትግራይ ሚሊሻና ወያኔ ሳምሪ ብሎ ባደራጃቸው ነፍሰ ገዳዮች የተረሸኑበትን የደም መሬት ይገባናል የሚል ነበር።
ምን ይሄ ብቻ! የትግራይ ፖሊስ፣ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የትግራይ ሚሊሻና ወያኔ ሳምሪ ብሎ ያደራጃቸው ነፍሰ ገዳዮች በአማራ ተወላጆች ላይ የፈጸሙት የዘር ማጥፋት በዓለም እንዳይታወቅ እነዚህ ፋሽስቶች እንቅስቃሴ የጀመሩትና በተካኑበት ጩኸቴን ቀሙኝ የፖለቲካ ብልጠታቸው ውንጀላ ውስጥ የገቡት ማይካድራ አርዶ ወደ ሱዳን የሸሸውን የትግራይ ፖሊስ፣ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የትግራይ ሚሊሻና የሳምሪ ቡድን በትግሬነቱ ምክንያት እንዲፈናቀል የተደረገና በጦርነቱ የተነሳ በድንገት ስደተኛ የሆነ አድርገው ከጣራው በላይ በማስጮህ ነበር።
በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራምና በሌሎች የምዕራብ መገናኛ ብዙሐን እየቀረቡ ፋሽስት ወያኔ ወርሮ በቅኝ ግዛቱ ስር ይዟቸው ከነበሩት ከወልቃይት፣ ከጠገዴ ከጠለምትና ከሁመራ ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ የትግሬ ተወላጆች እንደተፈናቀሉ በመዋሸት በቅጥፈታቸው የፋሽስት ወያኔን ክብረ ወሰን ሰብረዋል። ፋሽስት ወያኔ በ2006 ዓ.ም. ባሳተመው የሕዝብና የቤት ብዛት ትንበያ መሰረት ምዕራብ ትግራይ እያሉ የሚጠሩት የቃፍታ ሑመራ፣ የወልቃይት፣ የጠገዴና የሑመራ ወረዳዎች በ2009 ዓ.ም. ባጠቃላይ የሚኖራቸው የሕዝብ ቁጥር 434,897 እንደሆነ ነግሮናል።
በዚሁ የፋሽስት ወያኔ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን ሕትመት መሰረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓመት ውስጥ የሚያድግበት ከፍተኛው መቶኛ ስሌት ሶስት በመቶ ነው። በመሆኑም በ2009 ዓ.ም. 434,897 የነበረው “የምዕራብ ትግራይ” ሕዝብ ፋሽስት ወያኔ ጦርነት እስከጀመረበት እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ለአራት ዓመታት ያህል በየአመቱ በሶስት ፐርሰንት በ13,046 እያደገ በ2013 ዓ.ም. ጠቅላላው ምዕራብ ትግራይ እያሉ የሚጠሩት አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 490,064 ይሆናል። ልብ በሉ! ምዕራብ ትግራይ ብለው በፈጠሩት ዞን ውስጥ በ2013 ዓ.ም. የሚኖረው ሕዝብ ጠቅላላ ቁጥር 490,064 የሚሆነው ፋሽስት ወያኔ ራሱ በሰራው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ስሌት ነው።
ዐቢይ አሕመድ በትግራይ የመሰረተው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በ2013 ዓ.ም. ፋሽስት ወያኔ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራብ ትግራይ ከሚሉት ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጅ የአማራ ክልል በሚባለው የጸጥታ ኃይል ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል ያለን በሕወሓት የሕዝብና የቤት ቆጠራ ውጤት መሰረት “ምዕራባዊ ዞን” በተባለው ዞን ውስጥ በ2013 ዓ.ም. እንደሚኖር ከነገሩን 490,064 ሕዝብ ውስጥ ነው። በሌላ አነጋገር ምዕራብ ትግራይ ከሚሉት “በአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል” የተባለው የትግሬ ተወላጅ ቁጥር በፋሽስት ወያኔ በራሱ ቆጠራ መሠረት በተፈጠረው ዞን ውስጥ ከሚኖረው የሕዝብ ብዛት በ709,936 ይበልጣል። ይህ ማለት “ምዕራባዊ ዞን” ተብሎ ወደ ትግራይ በተካተተው አካባቢ ተፈናቀለ የተባለው ሕዝብ በሕወሓት በራሱ ቆጠራ መሰረት ሕወሓት በስልጣን ላይ እስከነበረበት 2013 ዓ.ም. ድረስ “በዞኑ” ከሚኖረው ሕዝብ በ709,936 በላይ በልጦ ከሚመጣው ትውልድ 709,936 ሕዝብ ተበድረው እንዲፈናቀል ተደርጓል ማለት ነው።
የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍልን ጨምሮ እንደ ኦቻ ያሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚመጣው ትውልድ ከ709,936 ሕዝብ በላይ ተበድረው ባካባቢው የሌለ የሕዝብ ቁጥር እንደተፈናቀለ አድርገው በአደባባይ ሲዋሹ የመረጃ ምንጫቸውን ሳይጠይቁና በአካባቢው እንደሚኖር በሕወሓት በራሱ ከተቆጠረው ሕዝብ በላይ እንዴት ሊፈናቀል ይችላል ብለው ሳይሞግቱ ፕሮፓጋንዳቸውን ብቻ ተቀብለው እስካሁንም ድረስ ምዕራብ ትግራይ ከሚሉት ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጅ የአማራ ክልል በሚባለው የጸጥታ ኃይል ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል እያሉ ሕዝብ ይዋሻሉ።
ለመሆኑ የትግሬ ብሔርተኞች ሁሉ በግፍ ወርረው በቅኝ ሲገዙት የነበሩትን ወልቃይትን ይገባናል የሚሉት የትግራይ ክፍል ሆኖ የማያውቀው ወልቃይት ሕገ መንግሥት በሚባለው መሰረት የሕዝብ ፍቃድ ተጠይቆ ወደ ትግራይ ስለተካለለ ነውን? በፍጹም! ፋሽስት ወያኔ ወልቃይትን የትግራይ አካል ያደረገው የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመስረት ጫካ በገባ ባመቱ በ1968 ዓ.ም. ባዘጋጀው የድርጅቱ የመጀመሪያ ማኒፌስቶ እንጂ በሕዝብ ፍቃድ አልያም ሕገ መንግሥት በሚሉት መሰረት አይደለም። ከታች የተያያዘውን የፋሽስት ወያኔ የመጀመሪያ ማኒፌስቶ ለአስረጅነት ይመለከቷል።
ልብ በሉ! ሕገ መንግሥት ተብዮው የታወጀው በ1987 ዓ.ም. ነው። ሕገ መንግሥት ተብዮው በ1987 ዓ.ም. የታወጀው ወያኔ ወልቃይትን የትግራይ አካል አድርጎ ያቀረረበት ድርጅታዊ ማኒፈስቶች 20 ዓመታት ከሞላው በኋላ ነው። ስለዚህ የትግሬ ብሔርተኞች የሕዝብ ፍቃድ ጠይቀው ወይም ሕገ መንግሥት በሚሉት መሰረት አይደለምና ወልቃይትን ወደ ትግራይ annex ያደረጉት ወልቃይትን በሚመለከት “የሕዝብ ፍቃድ ይጠየቅ፣ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በተቋቋመው የወሰንና ማንነት ኮሚሽን መፍትሔ ይሰጠው” እያሉ የሚያላዝኑት የፖለቲካ ብልጠት መሰረት የለውም።
ወልቃይት ወደ ትግራይ የተካተተው በታሪክ የትግራይ አካል ስለነበር ነው እንዳይሉ የኢትዮጵያ ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ወያኔ እስከተፈጠረበት ዘመን ድረስ ወልቃይት የትግራይ ክፍል እንደነበር የሚያሳይ አንዳች የታሪክ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። “የወልቃይት ጉዳይ” በሚል ባዘጋጀሁት የታሪክ ጥናት ውስጥ በዋናነት የትግራይ ገዢዎችና ከትግራይ የተወለዱ የኢትዮጵያ ነገሥታት የነበሩ የታሪክ ሰዎች የሰጧቸውን የታሪክ ምስክርነቶች በመሰነድ እንዳሳየሁት ወልቃይት በአንድም የታሪክ ዘመን የትግሬ ግዛት ሆኖ አያውቅም። የወልቃይት የ1660 ዓመታት የወሰን፣ የማኅበረሰብና አስተዳድር ታሪክ በሚመለከት “የወልቃይት ጉዳይ” በሚል ያዘጋጀሁትን የታሪክ መጽሐፍ ያነቧል።
እንግዲህ! በታሪክም ሆነ በሕግ ወልቃይት የትግራይ ክፍል ሆኖ አያውቅም። ቢያንስ እስካሁን ድረስ አንድም የትግሬ ብሔርተኞች ወልቃይት በታሪክም ሆነ በሕግ የትግራይ ክፍለ እንደነበር አላሳየም። አሁን ጥያቄው የትግሬ ብሔርተኞች ሕወሓት የአማራ የደም ምድር ያደረገውን ወልቃይትን ይገባናል የሚሉት ከምን ተነስተው ነው? የሚለው ነው። ሕወሓት የዘረፈው ሁሉ ይገባናል ቅሚያ ካልሆነ በስተቀር የትግሬ ብሔርተኞች ወሰናቸውን ተከዜን ተሻግረው ወልቃይትን ይገባናል ሊሉ የሚችሉበት አንዳች አመክንዮ የለም።
በርግጥ የትግሬ ብሔርተኞች ሁሉ ወልቃይትን ይገባናል የሚሉበት አንዳች አመክንዮ ባይኖራቸውም የወልቃይትን ጉዳይ የመሬት ማስለለስ ጉዳይ አድርገው በማሳነስ ሊያሳኩት የሚፈልጉት አንድ የፖለቲካ ብልጠት አላቸው። ይህም በማይካድራ በግፍ የተፈጁትና ከአርባ አመታት በላይ ሲታረዱ፣ ለአውሬ ሲጣሉ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲታሰሩና ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ሲፈጸምባቸው የኖሩት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የአማራ ተወላጆች ላይ የተካሄደው የዘር ማጥፋት እንዲድበሰበስና ፍትሕ እንዳያገኝ፤ የማይካድራው አይነት ፍትጅ ወደፊትም እንዲቀጥልና አካባቢው ከአማራ ተወላጆች እንዲጸዳላቸው ይፈልጋሉ።
ሆኖም ግን ዛሬ ላይ የወልቃይት ጉዳይ ሲነሳ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የማይችለው አካባቢው በማን ስር ይተዳደር የሚለው ጉዳይ ሳይሆን በወልቃይት ሕዝብ ላይ ለደረሰው ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ምን አይነት ፍትሕ ይሰጥ? እንዴትስ ይሰጥ? የሚሉት ናቸው።
አንዳንዶች “የወልቃይት ጉዳይ ሕግ ይታይ” ሲሉ እሰማለሁ። የወልቃይት ጉዳይ በሕግ ይታይ ከተባለ መታየት ያለበት ፓርላማ ተብዮው በአፋጣጥኝ ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሞ በሕወሓት በጅምላ የተገደሉትን፣ የዘር ማጥፋት የተፈጸመባቸውን፣ የተፈናቀሉትን፣ አላግባብ ንብረታቸው የወደመባቸንና የት እንደደረሱ የማይታወቁ የወልቃይት የአማራ ተወላጆች የሚካሱበትንና ፍትሕ የሚያገኙበትን ሁኔታ ባፋጣኝ ለመፍጠር መሆን አለበት።
ስለዚህ ካሁን በኋላ ስለ ወልቃይት ሲነሳ ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት የወሰን ጉዳይ ሳይሆን የፍትሕና የካሳ ጉዳይ መሆን አለበት። ወልቃይት በታሪክ ይተዳደር የነበረው በማን ሥር እንደነበረ ታሪኩ በአግባቡ የተሰነደ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም። በየትም አለም ቢሄድ ሕግ የሚለው ሀሳብ የተጸነሰው ፍትሕ ለመስጠትና የተጎዳን ለመካስ እንጂ ጉልበተኛ፣ አጭበርባሪ ወይም ባለጊዜ በኃይል የቀማውን የሰው ንብረት እንዲያዘገየው ወይም ይዞታው አድርጎ እንዲጸናለት አይደለም።
ሲጀመር አንድ በጉልበት የተዘረፈን ንብረት ለማን ይገባል? የሚል ጥያቄ መነሳት የለበትም። በጉልበት የተወሰደን ንብረት ለማን ይገባል የሚል ጠያቂ በኃይል ከቀማው ተለይቶ ሊታይ አይገባም። አንድ ንብረት በኃይል ከተወሰደ በኋላ ፍትሕ ሲታሰብ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች ንብረቱ የተዘረፈበት አካል ምን አይነት ጉዳት ደርሶበታል? ምን አይነት ካሳ ያስፈልገዋል? ወንጀለኛው ዘራፊስ ምን ይቀጣ? የሚሉት ብቻ ናቸው። የትግሬ ብሔርተኞች ግን ሕወሓት የዘረፈው ለባለቤቶቹ ሳይሆን ለኛ ይገባናል የሚሉበት ሕግ ተምረናል የሚሉን ጭምር ናቸው። በመሆኑም ሕወሓት በጉልበት የተወሰደውን ወልቃይትን ለኛ ይገባል የሚል ጥያቄ ጠያቂዎቹ የትግራይ ብሔርተኞቹ ሁሉ በኃይል ከቀማው ከሕወሓት ተለይተው ሊታዩ አይገባም።
ወልቃይት በሕወሓት ቅኝ ግዛት ወይም በጉልበት የተያዘ ነው፡፡ ከወሰንና አስተዳደር አኳያ ባለቤትነቱ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በታሪክም ሆነ የትግራይ አስተዳዳሪዎችና ከትግራይ የፈለቁ የኢትዮጵያ ነገሥታት በሰጡት ምስክርነት ወልቃይት የአማራ ምድር ነው። ሕወሓት በቅኝ ግዛት በያዘበት ባለፉት አርባ ዓመታት ግን ወልቃይት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአለም ላይ እጅግ ዘግናኝ ግፍ ከተፈጽመባቸው አካባቢዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው ወልቃይት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአለም ላይ እጅግ ዘግናኝ ግፍ ከተፈጽመባቸው አካባቢወች አንዱ የሆነውን ወልቃይትን ጉዳይ በአማራ ይሁን በትግራይ እያሉ እንደ እንደሚቀልዱትና በማይካድራ በግፍ ለታረዱትና ክአርባ አመታት በላይ የግፍ መለማመጃ ሆነው ለኖሩት ወልቃይቴዎች ምንም ሰባዊነት እንደሌላቸው የትግሬ ብሔርተኞች ተራ የመሬት ማስመለስ ጉዳይ አድርጎ ማቅረብ ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም የሚሆነው። ምን አይነት አረመኔነትስ ነው ከአርባ ዓመታት በላይ traumatize ሲደረግ የኖረን ሰው traumatize ከሚያደርገው አካል ጋር አብረህ ኑር ብሎ ሊፈርድበት የሚችለው?
ባጭሩ ስለወቃይት የሚከራከሩ ወገኖች በወሰንና ማንነት ጉዳይ ጊዜ ማጥፋት የለባቸውም። ከአሁን በኋላ የወልቃት ጉዳይ በወልቃይት ለደረሰው ግፍ እንዴት ፍትሕ ያግኝ፤ የወልቃይት ሕዝብ እንዴት ይካስና ስለ መልሶ ማቋቋም መሆን ይኖርበታል፡፡ የአማራ መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ካለ እና የአማራ ባለ ጉዳይ ከሆነ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአለም ላይ እጅግ ዘግናኝ ግፍ ከተፈጽመባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በወልቃይት ምድር በሕወሓት በጅምላ የተገደሉትን፣ የዘር ማጥፋት የተፈጸመባቸውን፣ የተፈናቀሉትን፣ አላግባብ ንብረታቸው የወደመባቸንና የት እንደደረሱ የማይታወቁ የአማራ ተወላጆችን ጉዳይ የሚመረምር ገለልተኛ ኮሚሽን ፓርላማ ተብዮው በአስቸኳይ እንዲቋቁምና ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ከታች የታተመው አንዱ ዶሴ ወያኔ እነወልቃይትን ወደ ትግራይ ያካተተው በ1968 ዓ.ም. ባወጣው ማኒፌስቶ እንጂ በሕገ መንግሥት ተብዮው መሰረት አለመሆኑን የሚያሳየን የሕወሓት ፕሮግራም እናት መዝገብ ነው። ሁለተኛው ዶሴ ደግሞ ፋሽስት ወያኔ ራሱ ያሳተመው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ውጤት ሲሆን ምዕራብ ትግራይ እያሉ በሚጠሩት ዞን በ2009 ዓ.ም. የሚኖረው ጠቅላላ ሕዝብ 434,879 እንደሆነ ያሳያል። በ2013 ዓ.ም. አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ ከምዕራብ ትግራይ ዞን ተፈናቅሏል የሚሉት እንግዲህ ራሳቸው በ2009 ዓ.ም. በዞኑ የሚኖረው የሕዝብ ጠቅላላ ቁጥር 434,879 እንደሆነ ከጦርነቱ በፊት ነግረውን ነው።