0 0
Read Time:3 Minute, 4 Second

የትግራይ ወራሪ ቡድን ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት “ሀለዋ ወያነ” በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎችን ማግኘቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አስታውቋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የትህነግ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል።

አካባቢውን የጀርመኑ ናዚ 1 ሚሊዮን 4 መቶ ሺ በላይ እስራኤላውያንን ከጨፈጨፈበት “ኦሽዊዝ” የተባለ ማጎሪያ ጋር አነጻጽረው “የኢትዮጵያው ኦሽዊዝ” ሲሉ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት “ገሃነም” በተባለው የትህነግ የድብቅ እስር ቤት በርካታ ሺህ ንጹሃን ማለቃቸውን በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩና ከሞት የተረፉ የወራሪ ቡድኑ የጥቃት ሰለባዎችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።

ትህነግ ይህን ድብቅ እስር ቤት የመረጠበት ምክንያት አካባቢው ሰው ከሚኖርበት ርቆ የሚገኝ ዙሪያው በከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራራ የተከበበ ከመሆኑም ባሻገር በኃይል ይዟቸው የነበሩትን የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች አማካኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከሁሉም አካባቢዎች ንጹሃንን እያፈነ ወስዶ ለማጎርና ለመጨፍጨፍ ምቹ በመሆኑ ነው ተብሏል።

በዚህ አሰቃቂ እስር ቤት የታሰሩ ንጹሃን በሚደርስባቸው ሰቆቃ ምክንያት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን፣ የትህነግ ታጣቂዎች በየቀኑ ታሳሪዎችን እየወሰዱ ይገድሉ እንደነበርና የብዙዎቹ አስከሬን በአካባቢው የሚገኝ ቃሌማ ወንዝ ላይ ይጣል እንደነበር ከሞት የተረፉት አዛውንቶች ለጥናት ቡድኑ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የድብቅ እስር ቤቱ ውስጥ በበሽታና በርሃብ፣ በድብደባ ተሰቃይተው እንዲሁም በትህነግ ታጣቂዎች ለሚገደሉት እስረኞች ቀብር ይቆፍሩ የነበሩት እስረኞች እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።

ባለቤቷ “ከፋኝ” የተባለ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ህዝብና መሬት ላይ የተቃጣውን ወረራ ለመቀልበስ የተቋቋመ ታጣቂ ኃይልን ተቀላቅሎ ትህነግን በመታገሉ የታሰረችው የወልቃይት አማራ እናት ለጥናት ቡድኑ እንዳስረዳችው እስር ቤቱ እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ ባሻገር የትህነግ ታጣቂዎች ይፈፅሙት የነበረው ወንጀል አስከፊ እንደነበር ገልፃለች።
“በላይ ድንጋይ የተረበረበበት ጉድጓድ ዉስጥ ነበር የሚያስሩን፡፡” የምትለው የአይን እሟኛ በአንድ ጉድጓድ ቢያንስ 10 ሰዎች ይታሰሩ እንደነበር ትናገራለች። “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ጉድጓዶች እና ዋሻዎችም የንጹሃን ማሰሪያ የነበሩ ሲሆን ምግብና ውሃ በ24 ስዓት አንዴ ብቻ ይቀርብ እንደነበር እማኞቹ አስረድተዋል።

የጥናቱ እማኝ ሆና የቀረበችው ሌላ እስረኛም “ሁሌም ማታ ማታ ከመካከላችን ስም ይጠሩና ይዘዋቸዉ ይወጣሉ፣ ከዚያ በኋላ በግምት ግማሽ ሰዓት ገደማ ይቆዩና ብዙ ጥይት ይተኮሳል፡፡ ከእኛ ራቅ አድርገዉ ነዉ የሚረሽኗቸዉ፡፡ በቃ ሁሌም እንደ መልአከ ሞት ማታ ይጠሩሃል፣ ትሄዳለህ ጥይት ይተኮሳል ከወጣህ መመለስ የለም፡፡ በተገደሉት እስረኞች ምትክ አዲስ እስረኛ ይመጣል፡፡” ስትል በገሃነም እስር ቤት የነበረውን ሁኔታ ትገልጸዋለች።

ትህነግ ወልቃይት ጠገዴን ከያዘ በኋላ ለትህነግ እገዛ ሲያደርግ የነበረና በአካባቢው የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ቆይቶ መረዳቱን የገለጸው የአካባቢው ተወላጅ ወንጀሉ የትህነግ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ይፈጸም እንደነበር ለጥናት ቡድኑ አስረድቷል።

“ከፋኝ” በሚል ለወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ማንነት ሲታገል የነበረውን ቡድን አመራሮች፣ አባላትና የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላትም በአካባቢው ታስረው በነበረበት ወቅት አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ የትህነግ አመራሮች ትዕዛዝ ይሰጡ እንደነበር ለጥናት ቡድኑ እማኝነቱን ሰጥቷል።

የአካባቢው ተወላጅ በመሆኑ ወደ ድብቅ እስር ቤቶቹ እንደማያስጠጉት የገለጸው ግለሰብ አቶ ስብሃት በራዲዮ መገናኛ ስንት ሰው እንዳለ ጠይቆ ከ59 ሺህ በላይ ታሳሪ መኖሩን እንደተገለጸለትና አቶ ስብሃት ነጋም “ሬሽን የለንም፣ መረጃ ተቀብላችሁ ቶሎ ቶሎ አስወግዷቸው” ማለቱን እንደሚያስታውስ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ተናግሯል።

በወቅቱ ትህነግን ይደግፍ የነበር ሌላኛው ግለሰብ ሀምሌ 7 ቀን 1982 ዓ.ም. በአካባቢው የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ለአብነት በመጥቀስ ለጥናት ቡድኑ እንደሚከተለው አስረድቷል።

“በቅርብ ርቀት በርካታ ጊዜ አውቶማቲክ ጥይት ተተኮሰ፡፡ ጨለማ ስለነበር ለማጣራት ጠጋ ብየ ቁጭ አልኩ፡፡ ባሩድ ይሸታል፣ የሚያወሩት ትግርኛ ነው፡፡ ህወሓቶች መሆናቸውን አረጋገጥኩ፡፡ መጀመሪያ የእርስ በርስ ጠብ መስሎኝ ነበር፡፡ ቀስ ብዬ ስጠጋ የተወሰኑት መሳሪያ ይዘው ቆመው ይታያሉ። ሌሎች ጉድጓድ አፈር ይሞላሉ፣ ፈርስና ባሩድ በጣም ይሸታል፡፡ በመጨረሻ ጉድጓዱን ከመሬቱ ጋር አስተካክለው በአፈር ጠቀጠቁት፡፡ ድንጋይ ስር ቁጭ ብዬ በጨለማ ጆሮየን ተክዬ የተወሰነውን አዳምጣለሁ። በትግርኛ ቋንቋ ‘አስማማው በለጠ 36 ራሱን ተሸኘ’ ሲል ሰማሁት፡፡ አስማማው ደግሞ በጣም ታዋቂ ጀግና እንደነበርና እንደወሰዱት አውቃለሁ፡፡”

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ለረዥም ጊዜ መረጃ ከሰበሰበ በኋላ ገሃነም በተባለ አካባቢ በሚገኙ በርካታ እስር ቤቶች ጭፍጨፋ ከተፈጸመባቸው መካከል የተወሰኑት ሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሟች ቤተሰቦችና የአካባቢው ፀጥታ ኃላፊዎች በተገኙበት አፅማቸው እንዲወጣ ተደርጓል።

የጅምላ መቃብሮች በመቆፈር የወጣው የንጹሃን አፅም መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተቀበረ ሲሆን በአካባቢው ካሉት በርካታ ድብቅ እስር ቤቶችና የጅምላ መቃብሮች በቀጣይ የበርካታ ንጹሃን አፅምን ለማውጣት እቅድ መያዙም ተገልጿል።

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator