26 ግንቦት 2022
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርቡ የታሰሩ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎችን እንዲፈቱና ትንኮሳ እንዲቆም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ተቋም ሲፒጄ ጠየቀ።
በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ከግንቦት 11/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ቢያንስ 11 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተቋሙ ግንቦት 17/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከጋዜጠኞቹ በተጨማሪም ከ4 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች መንግሥት የሕግ ማስከበር ብሎ በጠራው ዘመቻ በወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል ብሏል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን የሆኑት የአሻራ አምስት ጋዜጠኞች፣ አራት የቻናል ንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ኢትዮ ንቃት የተሰኘው ሚዲያ መስራች እና ዋና አዘጋጅ መስከረም አበራ እንዲሁም የገበያኑ ሚዲያ መስራችና እና ባለቤት አቶ ሰለሞን ሹምዬ ናቸው።
- የጋዜጠኞቹ እስርና በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ዘመቻ
- በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ቀናት የተከሰተው ምንድን ነው?
- ብ/ጄኔራል ተፈራ ‘ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ’ በሚል ተጠርጥረው እንደተያዙ ጠበቃቸው ገለጹ
“የጋዜጠኞቹ እስር ለኢትዮጵያ አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሦስት እርምጃ ወደኋላ የሚመልስ ነው። መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት እንዲሁም ዜጎች ከተለያዩ ምንጮች መረጃ የማግኘት መብት ግድ እንደሌለው የሚያሳይ ነው” በማለት የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጀላ ኪውንታል ተናግረዋል።
አስተባባሪዋ አክለውም ባለሥልጣናቱ ሁሉንም ጋዜጠኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠይቀዋል ።
“ባለሥልጣናቱ ጋዜጠኞቹን ያለምንም ክስ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የዘፈቀደ እስራት፣ ጭቆና እና ሳንሱር ሳይፈሩ ሪፖርት እንዲያደርጉ መንግሥት ማረጋገጥ አለበት” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በበኩሉ የሚዲያ ባለሙያዎች ከቤታቸውና ከሥራ ገበታቸው በፀጥታ ኃይሎች መታፈናቸው እንዳሳሰበው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው ዕለት ግንቦት 16/2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህንን ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ሰምተው እንዳልሰሙ መሆናቸው እንዳሳዘናነው፣ ጋዜጠኞች በሕግ አግባብ ብቻ እንዲጠየቁ እና ጋዜጠኞችን ያፈኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ” ማኅበሩ መጠየቁ በደብዳቤው ሰፍሯል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ “ታፍነው መወሰዳቸው፣ በማይታወቅ ቦታ መታገቸው እንዲሁም የቆዩና ተሰውረው ከቆዩበት ቦታ በአፋኞቻቸው የተለቀቁ ጋዜጠኞች በርካታ ናቸው” ብሏል።
በተጨማሪ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከሰሞኑ ጋዜጠኞች እና ማኅብረሰብ አንቂዎች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑ አንዳሰሰበው አስታውቋል።
ኤምባሲው የጅምላ እስሮቹን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሠረት የፌደራል እና የክልል ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል አለባቸው ብሏል።
ኢሰመኮ በበኩሉ ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን ኮንኖ ነበር።
በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመታሰራቸው ባሻገር የተወሰኑት ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና በቤተሰቦቻቸው ያልተጎበኙ መኖራቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል።
“በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን” እንደተገነዘበ ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል።
አሻራ ሚዲያ በቅርቡ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች ላይ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ፣ የመንግሥት ተቺዎች እስርና እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ጉዳዮችን አስመልክቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ዘግቦ እንደነበር የሲፒጄ ግምገማ ያመለክታል።
ሦስት ጋዜጠኞችና ሁለት የካሜራ ባለሙያዎች ግንቦት 11/2014 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከባሕር ዳር 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ንፋስ መውጫ ከተማ እስር ቤት ተዘዋውረው ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ጠበቆቻቸውንም አላገኙም ብሏል።
የንስር አራት ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ግንቦት 12/2014 ዓ.ም. ባሕር ዳር ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ሁለቱ በከተማው በሚገኝ እስር ቤት ሁለቱ ደግሞ በንፋስ መውጫ እንደሚገኙም ሲፒጄ አስፍሯል።
ንስርም በተመሳሳይ መልኩ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ መንግሥት እየወሰደው ያለውን እርምጃ እንዲሁም የዘ ኢኮኖሚስት የኢትዮጵያ ዘጋቢ ቶም ጋርድነር ፈቃድ መሰረዝን አስመልክቶ ዘገባዎች እንደሰራ ሲፒጄ አይቷል።
በተጨማሪም በአገሪቱ የተካሄደውን ጦርነት በመቃወምና የሰላምና ድርድር መንገዶች የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ አፅንኦት በመስጠት የሚታወቀው ሰለሞን ሹምዬ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስሮ የሚገኝ ሲሆን ግንቦት 13/2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት መቅረቡም ተመልክቷል።
ሰለሞን ሕዝብን ለአመፅ በመቀስቀስ እና በፌደራሉና በአማራ ክልል መንግሥታት መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ሰርቷል በሚልም ክስ ቀርቦበታል።
ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ በመጣችበት ቀን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንቦት 12/2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም አበራም፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስራ የምትገኝ ሲሆን ክሷም ከሰለሞን ሹምዬ ጋር ተመሳሳይም እንደሆነ ሲፒጄ ተመልክቷል።
በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ መምህርት የነበረችው መስከረም ግንቦት 15 እና 16/2014 ዓ.ም. ሕዝባዊ አመፅ በመቀስቀስ ወንጀል ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 29/2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
መስከረም በኢትዮ ንቃት ሚዲያዋ ለአንድ የኢትዮጵያ ጄኔራል ከፋኖ ታጣቂዎችና ከሕዝቡ ጎን እንዲሰለፍ መልዕክት ከማስተላለፍ በተጨማሪ ፋኖን በመደገፍ ፕሮግራም ሰርታለች ብሏል ሲፒጄ።
የፌደራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ሳምንት አርብ ምሽት በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የአገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሔ ነው ብሏል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ሕገ ወጥነትና የሰላም መደፍረስን መንግሥት እንዲቆጣጠር ሕዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር ያለው መግለጫው፣ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን አስታውሷል።