0 0
Read Time:107 Minute, 53 Second

የአማራ ህዝብ ትግል ዳራ እና የትግል አቅጣጫዎች
(የመነሻ ሃሳብ ሰነድ)
በመስከረም አበራ

PDF View
5/23/2014

ይዘት
መግቢያ
የሰነዱ አስፈላጊነት
የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ አብዮተኞች ዕይታ- ከትናንት እስከ ዛሬ
ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት፣የዘውግ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ መስተጋብር
የዘውግ ፖለቲካ ከ1983-2010ዓም በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳትና የጋረጠው ፈተና
በድህረ-ህወሃት የአማራ ህዝብ የገጠሙት ፈተናዎች
የአማራን ህዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ማዕቀፍ ውስጥ መመለስ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
የአማራ ንቅናቄ አስፈላጊነት እና ተፈጥሮ
የአማራ ንቅናቄ ትግል ውስንነቶች
የአማራ ንቅናቄ ሃይሎች በትግል ጉዟቸው ከግንዛቤ ሊያስቧቸው የሚገቧቸው አንኳር ጉዳዮች
የአማራ ህዝብ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ
የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችና የመደራደሪያ ነጥቦች
በብሄራዊ የምክክር መድረኩ የአማራ ህዝብ በማን ይወከል?
በምክክር መድረኩ የአማራ ተደራዳሪዎች ሊገጥማቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
ብሄራዊ ምክክር ለአማራ ህዝብ ሊያመጣው የሚችለው ፋይዳ
የአማራ ንቅናቄ የወደፊት ትግል እንዴት መቃኘት አለበት?
መደምደሚያ

  1. መግቢያ
    የአማራ ህዝብ1 ከኢትዮጵያ የሃገረ-መንግስትነት ታሪክ ጋር ጥብቅ የስነ-ልቦና ቁርኝት ያለው ህዝብ ነው፡፡በመሆኑም ለምዕተ-ዓመታት ከአማራ ማንነቱ ይልቅ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ላይ ትኩረት ያደረገ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያራምድ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ባለፈችበት የታሪክ ምዕራፎች ሁሉ ልዩ ተጠቃሚነት ያለው ህዝብ ነበር ማለት አይደለም፡፡ይልቅስ በሃገሪቱ የተነሱ አገዛዞች በሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ላይ ያደርሱት የነበሩት በደልና ጫና ሁሉ በአማራ ህዝብ ላይም ደርሷል፡፡በመሆኑም ሌሎቹ የሃገሪቱ ህዝቦችና የአካባቢ መሪዎች የተበደሉ ሲመስላቸው በነገስታቱ ላይ ያካሂዱ የነበረው አመፅ አሁን የአማራ ክልል በተባለው ህዝብና በአካባቢው ባላባቶችም ሲደረግ የኖረ ነው፡፡
    የአማራ ህዝብ ነገስታቱ ያደርሱብኛ ያለውን የአስተዳደር ግድፈት፣ብዝበዛ እና በደል በህዝባዊ ግጥሞቹና የተለያዩ ስነ-ቃላዊ ተግባቦቶቹ ሲገልፅ ኖሯል፡፡በደሉ ከፍ ያለ ሲመስለውም ነገስታቱን የሚቃወም ግልፅ ዓመፅ ሲያካሂድ ነበር፡፡ ለዚህ ቀዳሚው ተጠቃሽ እማኝ የጎጃም ገበሬዎች አማፅ ነው፡፡ይህ አመፅ በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች ከተደረጉ አመፆች አንዱ ነው ፡፡ በባሌ ፣ በጌዲኦ ፣ በትግራይ ከተደረጉ አመፆች እኩል በጎጃምም የገበሬዎች አመፅ ተካሂዷል፡፡ይህ ሁሉ የሚያሳየው ዛሬ በበርካታ አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች እንደሚታሰበው የነገስታቱ ስርዓት ለአማራው ህዝብ የተለየ ምቹ ፖሊሲ እንዳልነበረው ነው፡፡
    ከገበሬው አመፅ በተጨማሪም በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች እንደ ካዎ ጦና ያሉ የአካባቢ ባላባቶች በንጉሰ ነገስቶች አስተዳደር ላይ ያምፁ እንደነበረው ሁሉ በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ተብሎ በተከለለው አካባቢ የነበሩ ባላባቶችም ያመፁ ነበር፡፡ ለምሳሌ በማይጨው ጦርነት በርካቶቹ የጎጃም፣የወሎ እና የየጁ መኳንንት ንጉሰ ነገስቱን በመቃወም በጦርነት እንዲሳተፉ የቀረበላቸውን ጥሪ እስከ መግፋት ደርሰው ነበር፡፡በተመሳሳይ በዛሬው የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ይመሩ የነበሩ ራስ፣ደጃዝማቾች በአንድ የአማራ ማንነታቸው ህብረት ፈጥረው ሌሎችን የሚወጉ ሳይሆኑ እርስ በእርሳቸው የማያባራ ደም መፋሰስ ያስከተለ ውጊያ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በሸዋው ንጉስ ምኒልክና በጎጃሙ ራስ ተክለሃይማኖት መካከል የተደረገው በደም አፋሳሽነቱ ወደር የሌለው የኢምባቦ ጦርነት ነው፡፡
    እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረዥም የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ አማራው እንደ ህዝብ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪና ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ የመውሰዱ ነገር ከሰላሳ አመት ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኗል፡፡ በዚህ ስሁት እሳቤ ላይ ተቁሞ ህገ-መንግስት ተፅፏል፡፡በመሆኑም የትናንት ጨቋኝ ተደርጎ የተወሰደውን የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ማሳደድ፣ መግደል፣ ማፈናቀል፣ ንብረቱን የመንጠቁ ወንጀል ህጋዊ ማዕቀፍ አግኝቷል፡፡በመሆኑም የአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ መከራ በህገ-መንግስት የተፈቀደ ተገቢ ተግባር እስከ መምሰል ደርሷል፡፡ስለሆነም ሰላሳ አመት የዘለቀው በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገው ዘር ማጥፋትን/ማፅዳትን የጨመረ ወንጀል ጠያቂም ተጠያቂም የሌለው ቀጣይቱን የጠበቀ ሰንሰለታማ የወንጀል ትርዒት ሆኗል፡፡
    በሃገሪቱ ለውጥ መሰል ነገር በመጣ ቁጥር(የ1983ዓምን ለውጥ ተከትሎ በበደኖ፣አርባጉጉ ወዘተ የታየው አሰቃቂ የአማራ ህዝብ ፍጅት)፣ ሌላው ቀርቶ የግለሰቦችን ሞት አይነት ድንገተኛ ክስተት(የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ያስታውሷል) በተከሰተ ቁጥር ሳይቀር የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት እንደ ዋዛ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡አማራው በተወሰነለት ክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ በህይወት የመኖር መብቱ ያለምንም ጠያቂና ከልካይ ይጣሳል፡፡በተለይ በኦሮሚያ ክልል አማራውን የሚጨፈጭፉ ታጣቂዎች በግልፅ ሰልጥነው፣በገፍ ታጥቀው፣ያለምንም ከልካይ በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ ህፃን አዋቂ ሳይለዩ፣ በቀንም ሆነ በሌሊት “አማራ” ያሉትን ሁሉ ይረሽናሉ፣ንብረቱን ይዘርፋሉ ያፈናቅላሉ፡፡አማራው አማራ መሆኑ ብቻ ወንጀል ሆኖ ይህ ሁሉ በደልና መከራ ሲወርድበት ጠበቅ አድርጎ የሚጠይቅ አካል ስለሌለ በወንጀሉ የሚጠየቅም አይኖርምና የአማራው በደል እንደ ተገቢ ነገር ቀጥሏል፡፡
    የአማራ ህዝብ ከሰላሳ አመት ወዲህ እያስተናገደው ያለው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የጨመረ በደል ስምረት ያገኘው አማራውን ጨቋኝ አድርጎ የሚያቀርበው አስተሳሰብ ስልጣን በመያዙ ምክንያት ነው፡፡የአማራውን ህዝብ ጨቋኝ አድርገው የሚፈርጁት እነዚህ ቡድኖች ኢትዮጵያን የሰራውም አማራ ነው ብለው ያስባሉ፡፡በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያም መፍረስና ወደ ተለያዩ ዘውጎች ቅርጫነት መቀየር አልያም ፈርሳ እንደገና መሰራት ያለባት ሃገር ነች ብለው ያምናሉ፡፡ኢትዮጵያን በአማራ በኩል ሲጡሉ የኖሩት እነዚህ አማራ ጠል የፖለቲካ ሃይሎች በህወሃት የትጥቅ ትግል ድል አማካይነት ወደ ቤተ-መንግስት ሲገቡ አማራን የሃገሪቱ መርገም ሁሉ መነሻ አድርጎ የሚያስበውን እሳቤያቸውን የህገ-መንግስትም ሆነ የሌሎች ማህበረ-ፖለቲካዊ ደምባደምብ ማዕቀፎች ሁሉ ማጠንጠኛ አድርገዋል፡፡
    እነዚህ ቡድኖች ይህን ሲያደርጉ የአማራው ልሂቅ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል ሁሉ ወደ እርሱ የተወረወረ ለዘመናት ለመንቀል የሚያስቸግር ፍላፃ መሆኑን ሊረዳና አደጋውን በሚመጥን ሁኔታ ሊታገለው አልቻለም፡፡ በምትኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የከሳሾቹንና የአሳዳጆቹን አማራ-ጠል መንገድ ሲያቀና የኖረ/እያቀና ያለ ነው፡፡ ይህ የአማራ አብዛኛው ልሂቅ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታን ያለመገንዘብ አደገኛ አካሄድ የአማራን ህዝብ ከሩብ ምዕተ-ዓመት ለበለጠ ዘመን በህይወት የመኖር መብትን ማጣትን የጨመረ ውድ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
    ይበልጥ የሚያሳስበው አማራ ጠሉ አስተሳሰብ ስልጣን ከያዘበት ዘመን(1983ዓም) አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የአማራ ህዝብ ያለበት አደገኛ ሁኔታ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ለሰራው ታሪካዊ በደሉ የሚከፈል ተገቢ የታሪክ ማካካሻ ተደርጎ እየተወሰደ ያለ መሆኑ ነው፡፡ይህን አደገኛ ሁኔታ ለመቀልበስ ከአማራ ልሂቃን የሚቀድም አካል አይኖርም፡፡ስለሆነም ነገሩ ከሆነው በላይ እንዳይከፋና ጭራሽ አማራ የሚባለውን ህዝብ የሚያጠፋ እንዳይሆን መታገል የአማራ ልሂቃን እና ህዝብ ድርሻ ነው፡፡ አመርቂ ትግል ለመታገል ደግሞ የችግሩን አስከፊነት በሆነው ልክ መረዳትና ችግሩን በትክክል ሊያስወግድ የሚችለውን የትግል መስመር መያዝ ያስፈልጋል፡፡
    የአማራ ህዝብ ማንነቱን መነሻ አድርጎ የተሰነዘረበትን አጅግ አሰቃቂ የጥፋት በትር ለመመከት በማንነቱ መደራጀት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑ ብዙ ማከራከሩ እያበቃ ነው፡፡በመሆኑም በርካታ በማንነታቸው የተደራጁ የአማራ ሃይሎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ሆኖም የአማራውን ህዝብ ጊዜ የማይሰጥ አንገብጋቢ በደል ነቅሶ አውጥቶና የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችን በግልፅ አስቀምጦ ህዝቡን ማታገል ላይ ብዙ የሚቀር መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ይህን ክፍተት ለመድፈን የአማራ ህዝብ ያለበት ጊዜ የማይሰጥ ችግር የሚያሳስበው አካል ሁሉ ሊረባረብ ይገባል፡፡ይህ ሰነድ የተዘጋጀውም ክፍተቱን በመሙላት በኩል የሚጠበቀውን ስራ ለማስጀመር ያህል ነው፡፡ ሰነዱ በአሁኑ ወቅት እንዲዘጋጅ ያደረገው የወዲያው ምክንያት ደግሞ በሃገራችን በቅርቡ እንደሚካሄድ የሚነገርለት የምክክር መድረክ ላይ የአማራ ሃይሎች የሚወክሉት ተደራዳሪዎች የአማራ ህዝብ ያለበትን ችግር ግዝፈት ለማጤንና ችግሮቹን ለመፍታት ከሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ለመደራደር የሚረዱ መነሻ ሃሳቦችን ለመጠቆም ነው፡፡
  2. የሰነዱ አስፈላጊነት
    በሃገራችን ዘውግ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ተሰጥቶት የፖለቲካችን ዋነኛ ማጠንጠኛ ከተደረገ ከሰላሳ አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡የዘውግ ፖለቲካው ዋነኛ መሰረት ደግሞ ‘የአማራ ዘውግ ሌሎችን ዘውጎች ጨቁኗል’ የሚል እሳቤ ነው፡፡በመሆኑም የአማራ ህዝብ እና የአማራ ማንነት አላቸው የሚባሉ ምልክቶች ሁሉ ለአደገኛ የህልውና አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ የአማራ ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደልና ደክሞ ያፈራውን ንብረቱን እንዲያጣ ሆኗል፣የማንነቱ መገለጫ የተባሉ ባህሎቹ እንዲጣጣሉ፣እንዲወድሙና ቀጣይነታቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ሆኗል፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን የአማራ ህዝብ በማንነቱ የመጣበትን አደገኛ ፈተና በማንነቱ ተደራጅቶ ሳይመክት ረዥም ዘመናትን አሳልፏል፡፡በዚህም ምክንያት በአማራው ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ አደገኛ ትርክቶችን ተከትለው የሚከሰቱ አሰቃቂ ጥቃቶች የሚመከቱበት የተደራጀ ስትራቴጂ ሳይነደፍ ቆይቷል፡፡
    አማራው ተጠቂ የሆነባቸው መንገዶች ፈርጀ ብዙ ቢሆኑም የአማራ ህዝብ ከእነዚህ ጥቃቶች የሚድንበትን መንገድ መተለም ቀርቶ በዘውግ በተደራጀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማራውን እንደ አንድ ዘውግ ወስዶ ከዘውጉ ጋር በተገናኘ የሚደርሱበት አሰቃቂ በደሎችን ለማስቆም የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ሰንዶ ማቀረቡ በአማራ ሊሂቃን ዘንድ በቅጡ ያልተሰራበት ጉዳይ ነው፡፡በመሆኑም በጣም ዘግይተውም ቢሆን በአማራው ስም የተደራጁ የተለያዩ ድርጅቶች ከልዩነታቸው ባሻገር ለአማራ ህዝብ በመቆማቸው ሳቢያ የህዝባቸውን ፋታ የማይሰጥ አንገብጋቢ መከራ ለማቃለል ሲባል የሚጋሯቸውን የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎች አጠናቅረው ለማቅረብ የሚችሉበትን መድረክ መፍጠር አልቻሉም፡፡
    በተቃራኒው አማራው በድሎናል የሚሉት ወገኖች ከአንድ ዘውግ ሳይሆኑ እንኳን አማራውን በተመለከተ በጋራ የሚያቆማቸው በርካታ አጀንዳዎችን በፍጥነት ማቅረብ የሚችሉበት መግባባት ላይ ከደረሱ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ በአማራው እና “አማራው በድሎናል” በሚለው ልሂቅ መካከል ያለው ሰፊ የዝግጁነት ልዩነት የአማራን ህዝብ ፈተና የሚያከብድ ብቻ ሳይሆን መከራውን እያባባሰ የሚያራዝም አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ ይህን ለማስቀረት በተለያየ ስም የሚጠሩ የአማራ ሃይሎች ከልዩነታቸው ባሻገር ቢያንስ የአማራ ህዝብን ህልውና ለማስቀጠልና እንደ ሰው ሊከበሩለት የሚገቡትን ሰብዓዊ መብቶቹን ለማስከበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሚይዙት የጋራ አቋም ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሰነድ ያስፈለገውም የአማራ ህዝብን ህልውና ለማስከበር በአማራ ሃይሎች መሃከል ሊኖር የሚገባውን የጋራ አቋም ሊያመጡ የሚችሉ የጋራ የመታገያ አጀንዳዎች እና ከተለያዩ ሃይሎች ጋር ለመደራደር የሚስችሉ ነጥቦችን ለመጠቆም ነው፡፡ በሃገራችን በቅርቡ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች የሚሳትፍ ሃገራዊ ምክክር እንደሚደረግ መንግስት ይፋ ማድረጉ ደግሞ የዚህን ሰነድ አስፈላጊነት አስቸኳይ ያደርገዋል፡፡
  3. የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ አብዮተኞች ዕይታ – ከትናንት እስከ ዛሬ
    ኢትዮጵያ ረዥሙን የታሪኳን ዘመን ያሳለፈችው በዘውዳዊ አስተዳደር ስርዓት ስር ነው፡፡ዘውዳዊውን አስተዳደር ለመገርሰስም ሆነ ከዛ በኋላ የመጡ ስርዓቶችን ለመቀየር ግብታዊ አብዮቶች፣ተራዛሚ የትጥቅና ሰላማዊ ትግሎች ተደርገዋል፡፡እነዚህን ትግሎች የመሩ አብዮተኞችና ተከታዮቻቸው የሚታገሉትን ስርዓት በደሎች ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከአማራ ህዝብ/ዘውግና ከአማራ ማንነት ጋር ያቆራኛሉ፡፡2እነዚህ አብዮተኞች የኋላ ኋላ ራሳቸውን ሻዕብያ፣ህወሃት፣ኦነግ፣ኦብነግ ወዘተ አይነት ግልፅ የዘውግ ብሄረተኝነት ቀይረዋል፡፡የተቀሩት እንደ መኢሶ፣ኢሰፓ፣ኢህአፓ፣ኢጭአህአት፣ወዝሊግ ወዘተ ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያዊ ምልከታ ያለው ፓርቲ ይዘው ተጉዘዋል፡፡ሆኖም በሁለቱም ጎራ ያሉ ታጋዮች ይነስም ይብዛ ኢትዮጵያ በፊውዳሉ ዘመን ያለፈችበት ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ በአንድም በሌላ መንገድ ከአማራ ህዝብ ጋር ያገናኛሉ፡፡
    ኢትዮጵያ በታሪኳ ላለፈችበት ሁለንተናዊ ችግር አማራውን ሃላፊ አድርጎ የማቅረቡ አካሄድ በማታገያ ርዕዮትነት ድምፀት ሲገለፅ “በሃገራችን የብሄር ጭቆና፣የተዛባ የብሄረሰቦች ግንኙነት ነበር” የሚል ተደርጎ ይቀርባል፡፡ እዚህ ላይ ጨቋኝ ሆኖ የቀረበው የአማራ ዘውግ ሲሆን ተጨቋኙ ደግሞ የተቀሩት የኢትዮጵያ ዘውጎች ናቸው፡፡አሁን ላይ የአማራ ዘውግ ተወላጆችን ከኢትዮጵያ ዳርቻ ሁሉ የሚያሳድደው አማራ-ጠል ትርክት ውልደቱ ይህ እሳቤ ነው፡፡
    የዚህ አማራ-ጠል ትርክት መሃንዲስ ደግሞ አማራው ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡በእርግጥ የአማራ-ጠል የዘውግ ብሄርተኝትን በኢትዮጵያ ያስጀመረችው በአፄ ምኒልክ መሪነት አሳፋሪ የሸንፈት ማቅን የተከናነበችው ጣሊያን ነች፡፡3 ሆኖም በፋሽስት ኢጣሊያን የተጀመረውን አማራን የማጠልሸት ደብዛዛ ጅማሮ በፅሁፍ አጠናቅሮ ለነጥቆ በረሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ማፋፋሚያነት ያቀረበው ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡ ዋለልኝ “On the Question of Nationalities in Ethiopia” በሚል ርዕስ የፃፈው ባለ አምስት ገፅ ፅሁፍ የኢትዮጵያን ድህረ-ዘመናዊ ፖለቲካ በመዘወሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
    ዋለልኝ በዚህ ሰነዱ በአብዛኛው የአማራን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የትግሬ ዘውግ የተቀሩትን ኢትዮጵያዊያንን በሁለንተናዊ መልኩ በመጨቆንና በመደፍጠጥ ይከስሳል፡፡ሁለቱ ጨቋኝ እና ደፍጣጭ ብሄሮች ዋናና ምክትል ሆነው የራሳቸውን ባህል፣ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የበላይነታቸውን እንደተቀደጁ ይገልፃል፡፡ይህ ሰነድ ራሱ ፀሃፊው በመንደርደሪያው እንዳመነው በርካታ እንከኖች ያሉበት፣በቅጡ ያልተብላሉ ችኩል ማጠቃለሎች የሞሉበት ፣ ያነሳውን ሃሳብ ውስብስብነት የሚመጥን በቂ/በሳል ትንታኔ ያልተደረገበት፣ተጨባጭ መንደርደሪያዎችን አስቀድሞ ያላመጣ፣የይድረስ ይደረስ የተፃፈ ሰነድ ነው፡፡5
    የዋለልኝ ሰነድ ራሱ ፀሃፊው ያመነው በርካታ ውስንነቶች ያሉት ሆኖ ሳለ የሃገራችንን ፖለቲካ በመዘወሩ ረገድ እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ግዙፍ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከሰነዱ ዋነኛ ውስንነቶች አንዱ በተደጋጋሚ በጨቋኝነት የሚያነሳው የአማራ ዘውግ የተባለው ማን እንደሆነ እንኳን ግልፅ ትርጉም አላስቀመጠም፡፡በጨቋኝነት ፈርጆ ያስቀመጠው አማራ “አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነው” ከማለቱና ሸዋ የሚለውን ቃል በአሻሚ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ ከማሰቀመጡ በቀር ቢያስ በእሱ ፅሁፍ ሁኔታ አማራ የተባለው ዘውግ የሚኖርበትን ቦታ ጨምሮ ሌሎች በአማራነት የሚያስፈርጁ መገለጫዎችን አላስቀመጠም፡፡
    ዋለልኝ በሰነዱ “ኢትዮጵያዊነት ማለት አማርኛ በመናገር ይገለፃል” ሲል ያስቀመጠ ሲሆን በእርሱ አገላለፅ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ የማይችለው አማርኛ ተናጋሪ የሃገሪቱ ህዝብ ሁሉ እርሱ ጨቋኝ ነው በሚለው አማራ ዘውግ ውስጥ ይግባ አይግባ ግልፅ አይደለም፡፡አማራነትን በሃይማኖታዊ ገፁ ሊገልፅበት በሞከረው ትንታኔው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ለአማራ የሰጠበት ትንታኔውም እንዲሁ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን የሚከተል ሁሉ አማራ ሊባል ይችላል ወይ የሚል ተመሳሳይ ጥያቄን የሚያስነሳ ነው፡፡አማራነትን የኦርቶክስ ሃይማኖትን በመከተል፣አማርኛ ቋንቋን በመናገር፣ሸማ በመልበስ አይነት ከመወለድ በኋላ በሚለመዱ ባህላዊ ገፅታዎች ሲገልፅ የቆየው ዋለልኝ በመሃል ደግሞ “አማራ ሆኖ መወለድ እንደ መባረክ ይቆጠራል” ሲል5 አማራነትን ከዘረመል ጋር የሚገናኝ፣በውልደት የሚገኝ ስነፍጥረታዊ ማንነት አድርጎ ያቀርበዋል፡፡
    በተጨማሪም ከአማራው ጎን ጨቋኝ አድርጎ ያቀረበው የትግሬ ዘውግ በቋንቋ ረገድ በቀዳሚነት ትግርኛን እንጅ አማርኛን የሚናገር አይደለምና ኢትዮጵያዊነት ማለት አማራ ሆኖ አማርኛ ከመናገር ጋር ካቆራኘው ትንታኔው ጋር የትግሬ ዘውግ ቦታ የት እንደሆነ ግልፅ እይደለም፡፡የኋላ ኋላ ደግሞ ትግሬ ከአማራ ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን ብሄረሰቦች ጨፍልቆ ባህሉን ጫነባቸው ማለቱን ረስቶት ኢትዮጵያዊ ለመባል የአማራ ጭምብል (Mask) ማጥለቅ ግድ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡6በዚህ ሁኔታ ትግሬነት ቦታው የት እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
    የዋለልኝ ሰነድ የፅሁፉ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውን አማራ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ትርጉም በግልፅ ለማስቀም እንኳን ጊዜ ያልወሰደ በርካታ ህፀጾች የተሞላ ቢሆንም ሰነዱ የያዛቸው ስሁት ሃሳቦች ከዋለልኝ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ የተነሱ ታጋዮችን ልብ መግዛት ችሏል፤የትግል ፍኖተ ካርታ፣የማታገያ ማኒፌስቶ የሚቀዳበት “ሰፊ ምንጭ” ተደርጎ ተወስዷል፡፡የዋለልኝን ሰነድ በተንተራሱ እንደ ትህነግ፣ሻዕብያ፣ኦነግ፣ኦብነግ ወዘተ ያሉ አብዮተኞች እሳቤ መሰረት የዘውዱ ስርዓት ሙሉ በሙሉ የሚዘወረው የአማራ ማንነት ብቻ ባላቸው መሪዎች አለያም ዘውጋዊ ማንነታቸውን ለአማራ አሳልፈው በሰጡ ሌሎች መሆኑ ለጥርጣሬ ቦታ ሳይጠው የሚታመን “ሃቅ” ነው፡፡
    ነገሩ ሲብስ ደግሞ ከዘውዱ ስርዓት በኋላ የመጣውን የደርግ ስርዓት ራሱ የአማራ ስርዓት እንደሆነ እርግጠኛ ሆነው ይናገራሉ፡፡ስለዚህ በዘውዱም ሆነ በወታደራዊው ስርዓት “ተከፋንበት” የሚሉትን ጥፋት ሁሉ ለአማራ ህዝብ በዕዳነት ያሸከማሉ፡፡እነዚህ አብዮተኞች አንዳንዴ ለይስሙላ “የአማራ ህዝብ” እና “የአማራ ገዥ መደብ” የሚል ነገር የሚያነሱበትና ፀባቸው እና ትግላቸው ከአማራ ገዥ መደብ እንጅ ከአማራ ህዝብ ጋር እንዳልሆነ የሚናገሩበት አጋጣሚ አለ፡፡
    ከዋለልኝ ደቀመዛሙርት ውስጥ ኮስተር ያለ የትጥቅ ትግል አድርጎ ስልጣን ለመያዝ የበቃው ትህነግ የትጥቅ ትግሉን ሲጀምር “ጠላቴ ጨቋኟ የአማራ ብሄር ነች” ሲል የዋለልኝን ስብከት ከፍሎ የማመን መናፍቅነት ውስጥ ገባ፡፡ህወሃት የዋለልኝ ደቀመዝሙር መሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም ራሱ የወጣበትን የትግሬ ዘውግ ከጨቋኝነት ከመርገም ለማዳን ሲል ከዋለልኝ እውቀት ላይ ከፍሎ ማወቅን መረጠ፡፡በመሆኑም የአማራ ዘውግን በብቸኛ ጨቋኝነት ፈርጆ የትግሬ ዘውግን በአማራ ጨቋኝነት የሚማቅቅ ዘውግ አድርጎ፣የዋለልኝን አስተምህሮ ለራሱ በሚጠቅመው መንገድ ከልሶ የትግል ማኒፌስቶ በመፃፍ7 ተራዛሚውን የትጥቅ ትግል አሃዱ አለ፡፡
    የዋለልኝን አማራ-ጠል አስተምህሮ አንግቦ ወደ ትጥቅ ትግል የገባው ትህነግ የትጥቅ ትግሉን በድል አጠናቆ ቤተ-መንግስት በመግባቱ የዋለልኝ አስተምህሮ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መንፈስ ሆኖ ዛሬ ድረስ አማራውን እንዲያሳድድ አድርጓል፡፡ትህነግ ክንዱ የሚችለውን ያህል ደቁሶ በሃይል ከገዛ በኋላ “ብሄር ብሄረሰቦች” ሲል በሰየማቸው ደቀመዛሙርቱ ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም ቢሆን የዋለልኝ መንፈስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በከፍታ ተቀምጦ አማራውን ማሳደዱን ቀጥሏል፡፡
    ትህነግም ሆነ ከእርሱ በኋላ ስልጣን የያዙ ደቀመዛሙርቱ በለስ ቀንቷቸው ስልጣን ሲይዙ ፀባቸው እነሱ አማራ ብለው ከፈረጁት ፍጡር እና የአማራ ምልክት ካሉት ጉዳይ ጋር ሁሉ መሆኑን በአማራው ዘወግ ተወላጆች ላይ የሚወስዱት ዘር ማጥፋትን የጨመረ እርምጃ ምስክር ነው፡፡ እነዚህ አማራ በደለን ብለው የተነሱ አብዮተኞች “ኢትዮጵያ ራሷ የአማራ የእጅ ስራ ነች”ብለው ያምናሉ፡፡ስለሆነም በአማራ በኩል ኢትዮጵያን ራሷን ይታገሏታል፡፡ትግላቸው ኢትዮጵያን ራሷን አፈራርሶ ወደ ብሄረሰቦች ቅርጫነት ሊቀይራት እንደሚችል ማጤንም አይፈልጉም፡፡ቢያጤኑ እንኳን የኢትዮጵያ መፍረስ አለመፍረስ የሰሪዋ የአማራ ብቻ ራስምታት እንደሆነ ያምናሉና የሚያሰጨንቃቸው ጉዳይ አይደለም፡፡
    ከአማራ ጋር ያለን ግንኙነት የጨቋኝ ተጨቋን ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት የአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ሰልፈኞች አማራው ይፈልገዋል ብለው ለሚያስቡት ነገር ሁሉ ጠላትነትን ያሳያሉ-ለኢትዮጵያም ጭምር፡፡በአጭሩ በአማራ በኩል ኢትዮጵያን ይጣላሉ፡፡የሚጠሏትን ኢትዮጵያ ለማፍረስ እንደሚሰሩ በግልፅ ሲናገሩም ኖረዋል፡፡ሆኖም እነዚህ ወገኖች በትህነግ በኩል ስልጣን ላይ የመውጣት እድል ሲያገኙ ደግሞ ኢትዮጵያን ከማፍረስ ይልቅ አማራ ቀደም ብሎ ከሰራት የተለየ አድርጎ ሰርቶ መግዛቱ የበለጠ ተመራጭ እንደሆነ አምነው ይህንኑ ሲያደርጉ ኖረዋል፡አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ይህን ሃሳብ በዕለት ተዕለት ፖለቲካዊ ንግግራቸው ውስጥ አስገብተው ሲገልፁትም ‘ከአሁን በኋላ የድሮዋ ኢትዮጵያ ተመልሳ አትመጣም’ ይላሉ፡፡ በዚህ አባባል ውስጥ በርካታ ሃሳቦችና ፍላጎቶች አድፍጠዋል፡፡
    የመጀመሪያው እሳቤ የድሮዋ ኢትዮጵያ አማራ ለራሱ ጨቋኝነት፣የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ እና ባህላዊ የበላይነት እንድትመች አድርጎ የሰራት፤ ለአማራ ብቻ የምትመች ነች የሚል ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሃሳብ ይህች አይነቷ ኢትዮጵያ ፈርሳ ስትሰራ የቀድሞዋን ኢትዮጵያን ሰርቷል ብለው የሚያምኑትን አማራን በሚበቀል፣በሚያገል እና በሚቀጣ መንገድ መሰራት አለባት የሚል ነው፡፡ይህ አፍርሶ የመስራቱ አካሄድ በተለያየ መንገድ የሚገለፅ ሲሆን ዋና ዋናዎቸ አማራውን ከመላ ሃገሪቱ በማሳደድ፣የአማራን ዘር በማፅዳት/በማጥፋት፣የአማራ ተብለው የተፈረጁ መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሃብቶችን በማጣጣል/በማቃለል/በማውደም እንዲሁም አማራውን ከዋነኛ የፖለቲካ ስልጣን በማግለል ይገለፃሉ፡፡ይህን ሲያደርጉ አማራ ኢትዮጵያን የመስራቱ ምልክቶች ናቸው የሚሏቸውን አማዳት ሁሉ አጥፍተው የሚፈልጓትን አይነት ኢትዮጵያ መስራታቸው ነው፡፡
    አሮጌዋን ኢትዮጵያ አፍርሶ አዲሷን ኢትዮጵያ የመገንባቱ ፕሮጀክት ከ1983ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ የቀጠለ ነው፡፡አዲስ በመሰራት ላይ የምትገኘዋ አዲሲቷ ኢትዮጵያ አይነተኛ መልኳ ደግሞ ለአማራው የማትመች ይልቅስ አማራውን ለመቅጣት ታስባ የተሰራች መሆኗ ነው፡፡ለዚህ በርካታ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡የመጀመሪያው ከ1983ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ በዘለቀ ሁኔታ በበደኖ ፣ በወለጋ ፣ በቤኒሻንጉል ፣ በጉራፈርዳ ወዘተ አማራው በማንነቱ ተለይቶ የዘር ማጥፋት/ማፅዳት ወንጀሎች እየተፈፀሙበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም፤ ሌላው ቀርቶ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት የአቶ ጃዋር መሃመድን የተከበብኩ ጥሪ አይነት ድንገቴ ክስተቶችን ተከትሎ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አማራው በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደለ ቢሆንም ይህን ወንጀል የሚመረምር አንድም የወንጀል ፋይል ተከፍቶ የተጠየቀ አካል የለም፡፡ በፍርድ ቤት መጠየቅ ቀርቶ በሞራል ህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ጠበቅ ያለ ውግዘት ከሃይማኖት ተቋማት እንኳን ተሰምቶ አያውቅም፡፡
    ይህን አይነቱ የዘር ማጥፋትን ለሚያክል ወንጀል የሚሰጠው የዝምታ መልስ “በአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስራቾች” እሳቤ መሰረት በአማራው ላይ የሚደረገው ማንኛውም ወንጀል ለተዛባው የታሪክ ማስተካከያነት የሚደረግ በጎ እርምጃ ተደርጎ የሚተረጎም መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ በተመሳሳይ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስራቾች እሳቤ “የአማራ ሃይማኖት” ተደርጋ በምትወሰደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የሚደረገው ህገ-መንግስቱን ጭምር የጣሰ ወንጀል በመንግስት በኩል በዝምታ የሚታለፍ ነው፡፡
    በተመሳሳይ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመስራት በሚጥሩ አካላት እሳቤ የአማራ ሃይማኖት ተብላ የተፈረጀችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የማይደርስ በህይወት የመኖር መብታቸውን ከመንጠቅ፣ የማምለክ መብታቸውን ጥያቄ ውስጥ እስከማስገባት የደረሰ ወንጀል ይፈፀምባቸዋል፡፡ይህ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግስት ሹማምንት ሳይቀሩ የሚሳተፉበት ነው፡፡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ የቤተክርስቲያኗ አማኞች “የአማራ/ነፍጠኛ ሃይማኖት ተከታዮች” በሚል በሃይማኖታቸው ተለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡
    ይህ ሲሆን የመንግስት ባለስልጣናት በተገቢው ሁኔታ ሃላፊነታቸውን በሚመጥን መንገድ ተንቀሳቅሰው የምዕመናኑን ህይወት ለማትረፍ እንዳልሰሩ በመንግስት ስር ያለው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር በሪፖርቱ ያመላከተው ጉዳይ ነው፡፡በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ የሃዲያ ዞን መቀመጫ በሆነችው ሆሳዕና ከተማ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች የጥምቀት በዓልን የሚያከብሩበት ቦታ አጥተው ሲቸገሩ የመንግስት ባለስልጣናት እስከ ዘንድሮው ጥምቀት በዓል ድረስ የረዷቸው ነገር አልነበረም፤ከማስፈራራት እና አባቶችን ከማቃለል በቀር፡፡በዘንድሮው ጥምቀት ከብዙ ዘመን ደጅ ጥናትና እንግልት በኋላ ቤተ-ክርስቲያኒቱ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ አግኝታለች፡፡የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሚያሳየው የቀድሞዋን ኢትዮጵያ የአማራ የእጅ ስራ ስለሆነች አፍርሰን እንሰራለን የሚለው እሳቤ ሊፈጥራት እየጀማመራት ያለችው ኢትዮጵያ አማራ-ጠል መልኳ የበዛ መሆኑን ነው፡፡
    ኢትዮጵያን አፍርሶ የመስራቱ እሳቤ ሁለት ስህተቶችን አጣምሮ የያዘ አካሄድ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስህተት ከ1983 በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ለአማራው ብቻ እንደ እናት ማህፀን የምትመች አድርጎ የማሰቡ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ይህች ኢትዮጵያ ለአማራው ብቻ የምትመች አለመሆኗን ለማወቅ ቀላሉ መንገድ ወደ አማራ ክልል ጎራ ብሎ ህዝቡ የሚኖርበትን የድህነት ልክ መመልከት ነው፡፡ ሁለተኛው ስሁት እሳቤ አማራን የምትቀጣ አዲስ ኢትዮጵያ ስትፈጠር አማራው ዝም ብሎ ያያልና በዚህ መልክ የታሪክ ስህተት ለማስተካከል ይቻላል ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፈርሳ መስራት ካለባት እንኳን መሰራት ያለባት ሁሉንም እኩል አድርጋ እንድታስተናግድ ተደርጎ እንጅ በአንድ ብሄር ላይ የምትዘምት ኢትዮጵያን መስርቶ ሃገር አድርጎ መኖርን ማሰብ የማያስኬድ መንገድ ነው፡፡
    4.ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት፣ የዘውግ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ መስተጋብር
    የዘውግ ማንነት እንደ ማህበራዊ ክስተት ከጥንት ግሪኮችና ሮማዊያን ዘመን ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ፖለቲካዊ ሆኖ በዓለማችንም ሆነ በአህጉራችን አፍሪካ የፖለቲካ ስልጣን መያዣ መሳሪያ የሆነው ግን በጣም በቅርቡ ማለትም በ20ኛው ክፍለዘመን መባቻ ነው፡፡8ይህ በርካታ የዓለማችን ምሁራን የተስማሙበት ሃቅ ቢሆንም በሃገራችን የዘውግ ፖለቲከኞች ዘንድ ግን ኢትዮጵያ ከተፈጠረችበት ዘመን ጀምሮ አማራ በዘውግ ማንነቱ ተደራጅቶ ሌሎችን ዘውጎች እየጨቆነ ሲገዛባት የኖረች ተደርጎ ብያኔ ይሰጣል፡፡ይህ ስሁት ብያኔ ኢትዮጰያን የተቀሩት የዓለም ሃገራት ካለፉበት የታሪክ ምዕራፍ የተለየ የፖለቲካ ቀመር ያላት ሃገር አድርጎ ያስባል፡፡ከዚህ አልፎ ይህ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የአማራ የበላይነት/ትምክህተኝነት ሌሎችን ለመጨቆን ሲል ራሱን የሚደብቅበት ጎሬ አድርጎ እስከ ማሰብ ይዘልቃል፡፡
    በመሆኑም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን መዋጋት አማራን መዋጋት፤በግልባጩ አማራን ማሳደድ፣ማሸማቀቅ እና ከሃገራዊ ፖለቲካ ስዕሉ ገሸሽ እንዲል ማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማፈራረስ አድርገው ያስባሉ፤ለዚሁም ይሰራሉ፡፡በአጭር አገላለፅ አማራውን በማሳደድ ኢትዮጵያዊ ብሄርኝነትን ይዋጋሉ፤ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት በማፈራረስ አማራውን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ገሸሽ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡
    የሃገራችን የዘውግ ፖለቲከኞች ከክርስቶስ ልደት በርካታ ዘመናት በፊት በኢዛና ሃተታ (Izana Inscription) የተገለፀውና ጥንታዊ ህልውና ያለውን የብሄረ-ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት9 ዛሬ እንኳን በቅጡ መቀጣጠል ያልቻለው የአማራ ትምክህተኝነት/የበላይነት ጎሬ ነው ብለው ማሰባቸው የሃገራችን ፖለቲካ በአጠቃላይ እና የአማራ ንቅናቄ በተለይ ትልቁ ፈተና ነው፡፡እነዚህ ወገኖች ሃገራዊ ስልጣን የመያዝ ዕድል ማግኘታቸው ደግሞ ፈተናውን ይበልጥ ከባድና ውስብስብ አድርጎታል፡፡አማራ ጨቁኖናል የሚሉት የሃገራችን የዘውግ ብሄርተኞች የፌደራል ስልጣን መንበር ላይ መቀመጣቸው ስሁት ሃሳባቸው የረባ ተግዳሮት እንዳይገጥመው ጉልበት ጭምር የሚጠቀሙ በመሆኑ የተሳሳተው ትርክት እንከን የለሽ እውነት መስሎ አማራውን በተለይ ማንገላታቱን ቀጥሏል፡፡
    የአማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች የሚያምኑት አስተሳሰብ (ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ርዕዮትን የአማራ ትምክህተኝነት ጭንብል አድርጎ የማሰቡ) ስልጣን ላይ የመውጣት በለስ ቀንቶታል፡፡ ሆኖም ስልጣን ላይ መውጣቱ ስሁትነቱን አይለውጠውም፡፡የዚህ እሳቤ ስሁትነት የሚረጋገጥበት አንዱ መንገድ የአማራ ህዝብ ከልሂቃን እስከ አርሶ አደሩ ድረስ ከትህነግ ጋር የነበራቸው የአጋርነት መስተጋብር ነው፡፡
    እንደሚታወቀው ትህነግ በ1968 በግልፅ “አማራ ጠላቴ ነው” ብሎ ማኒፌስቶ ፅፎ ትግል የጀመረ ድርጅት ነው፡፡ድርጅቱ የኋላ ኋላ ይህን የ1968 ማኒፌስቶ የሚተካ ሌላ የማታገያ ሰነድ ፃፍኩ ባለበት ሰነዱም አማራውን ሊታገሉት የሚገባ ጨቋኝ ዘውግ እንደሆነ ከመግለፅ እልተቆጠበም፡፡ይህም ሆኖ የአማራ ልሂቃን እና አርሶ አደሮች ከትህነግ ጋር በትጥቅ ትግል ከመሰለፍ ጀምሮ የጦር ሜዳ ደጀን እስከመሆን በደረሰ ሁለንተናዊ ድጋፍ ቤተ-መንግስት እንዲገባ ረድተዋል፡፡ ስልጣን ከያዘ በኋላም በግልፅ በአማራው ህዝብ ላይ የጥፋት አዋጅ እያወጀና እያስፈፀመ ባለበት ሁኔታ ጭምር የአማራ ልሂቃን ወይ እንደ ኢህዴን/ብአዴን ባሉ ፓርቲዎች ስር ገብቶ አብሮ በማስፈፀም ወይ በዝምታ አብረውት ተሰልፈዋል፡፡
    ከዚህ መረዳት የሚቻለው ለረዥም ዘመናት የአማራ ዘውግ ተኮር እሳቤ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ውስጥም ሆነ ለብቻው ህልውና ያላገኘ እሳቤ እንደነበረ ነው፡፡ይህ ደግሞ የዘውግ ብሄርተኞች የአማራ ዘውገኝነት በረቀቀ መንገድ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ወስጥ አድፍጦ ኖሯል የሚሉት እሳቤ ከእውነታው የተፋታ መሆኑን ያስረግጣል፡፡ምክንያቱም የአማራ የዘውገኝነት እሳቤ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነትም ሆነ በሌላ መንገድ አድፍጦ ቢኖር ኖሮ ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣበት ዘመን ጀምሮ እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ አማራው በየተገኘበት ሲታደን ለማስቆም ሲንቀሳቀስ በታየ ነበር፡፡
    እውነታው የአማራ ህዝብ ከግለሰባዊ ማንነቱ ባለፈ ኢትዮጵያዊነትን ዋነኛ ማንነቱ አድርጎ የኖረ፣ሌላው ኢትዮጵያዊም እንደዚሁ የሚያስብ አድርጎ ሲገነዘብ ዘመናትን ያሳለፈ መሆኑ ነው፡፡”አማራ ጠላቴ ነው” የሚል የትግል ሰነድ ቀርፆ የመጣውን ትህነግን ለድል እንዲበቃ እስከማገዝ ያደረሰው አካሄዱም ከዚሁ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወገን አድርጎ ከማየቱ የመነጨው የአማራ ህዝብ/ልሂቅ ግንዛቤ ነው፡፡ከሁሉም በላይ አብዛኛው የአማራ ልሂቅ፣ከተሜውም ሆነ አርሶ አደሩ ስለ ኢትዮጵያ እና ታሪኳ የነበረው ግንዛቤ ትህነግንም ሆነ የትግራይን ህዝብ የጨመረ ነበረ፡፡በየአማራ ህዝብ ዘንድ ስለትህነግ የነበረው ግንዛቤ ትህነግ የወጣው ብዙውን ታሪክና ባህል ከአማራ ህዝብ ጋር ከሚጋራው ከትግራይ ህዝብ ውስጥ በመሆኑ ለኢትዮጵያዊነት ታማኝ ከመሆን ያለፈ ሌላ ጥቅምና ፍላጎት ይኖረዋል ብሎ የማያስብ ነው፡፡ የዚህ ጥልቅ ዕምነት መዘዝ ነው የአማራ ህዝብ በትህነግ የደረሰበትን የክህደት መራር ፅዋ ሲጎነጭ እንዲኖር ያደረገው፡፡
    የአማራ ህዝብ የትህነግን አመጣጥና ወደ ስልጣን ግስጋሴ እንደ ጥንቱ የነአፄ ዮሃንስ ዘመኑ ዘይቤ አድርጎ ያስባል፡፡በቀድሞው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ የአካባቢያዊ መሳፍንት፣ሽፍቶችና የጦር አበጋዞች አመፅ የተለመደ ነበር፡፡እነዚህ አማፅያን በመጀመሪያ አመፃቸውን የሚጀምሩት በአካባቢያቸው ያሉ ሃይሎችን ዘውግ ሳይለዩ አስተባብረው ነው፡፡ቀስ በቀስ ጉልበት አግኝተው የንጉሰ ነገስትነት ስልጣን መጨበጥ ከቻሉ የሚመሰርቱት አስተዳደር ግን ዲሞክራሲያዊ ባይሆንም ሁሉንም የሚያካትት(በዘውግ ልዩነት ያላደረገ) ነበር፡፡የአማራ ህዝብም የትህነግን ግስጋሴ ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ሊያስብ የሚችልበት የታሪክም ሆነ የባህል መሰረት አልነበረም፡፡
    በዚህም ምክንያት ትህነግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ሲፈፅም የነበረው የመድሎኝነትና የዘረኝነት ተግባር ሁሉ በአማራው ህዝብና ሊሂቅ ዘንድ እንደ አላፊና ጊዜያዊ ሁኔታ ተደርጎ ነበር የተቆጠረው፡፡ በጊዜው ለአማራው ልሂቅ ጎልቶ ይታየው የነበረው ትህነግ የመንግስቱ ሃይለማርያምን ወታደራዊ አምባገነን አስተዳደር ደምስሶ መጣሉ ብቻ ነበርና ለረዥም ዘመን ይህንኑ በማዳነቅ ላይ ተጠምዶ ቆይቷል፡፡በመሆኑም ትህነግ የተፀነሰበትን አማራን በሌሎች የሃገሪቱ ዘውጎች ሁሉ እንደጠላት እንዲታይ የማድረጉን ሁለንተናዊ ደባ በአደገኝነቱ መጠን ለአማራው ልሂቅ ሊታየው አልቻለም፡፡ በሃገራችን ከ1983 ዓም ጀምሮ የረበበው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ ማጠንጠኛ አማራውን ጠልቶ የማስጠላት እና የማሳጣት አካሄድ በትህነግ ፊታውራሪነት በሌሎች ደቀመዝሙርነት የተዳወረ ነው ፡፡
    በሌላ አባባል ከ1983 ዓም ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንሰራፍቶ የተተከለው የዘውግ ፖለቲካ ዋነኛ ዓላማውና መለዮው አማራውን የተቀሩት ብሄረሰቦች አጥብቀው ሊታገሉት የሚገባ፣በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሁለተኛ ተመልሶ ስልጣን መያዝ የሌለበት፣እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በከፍተኛ አንክሮ መታየት ያለበት አይነተኛ ባለጋራ አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡እንዲህ አይነት ዓላማን ባነገበ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ አማራው እንደ አንድ በሃገሩ የሚኖር ህዝብ መብቱ ተከብሮለት ሁለንተናዊ ደህንነቱ ተጠብቆ ሊኖር የማይችል መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡
    በህግ የፀናው የዘውግ ፖለቲካ ያመፀበት የአማራ ህዝብ እጅግ በማይመች ፖለቲካዊ ከባቢ ውስጥ የሚኖር ግዞተኛና ባይተዋር መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡በሃራችን በተተከለው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ ውስጥ አማራ መሆን ትልቅ ፈተና አዝሎ የሚመጣ ማንነት ነው፡፡ የአማራው ህዝብ ይህ ሁሉ ፈተና የተደቀነበት ቢሆንም የአማራው ልሂቅ ይህን የዘውግ ፖለቲካው የደቀነበትን አደገኛ ሁኔታ ወዲያው ተገንዝቦ በእንቁላሉ መቅጨት አለመቻሉና ረዥም የቸልታ ዘመን ውስጥ መክረሙ የአማራን ህዝብ ከባድ ዋጋ አስከፍሏል፤ እያስከፈለም ይገኛል፡፡
  4. የዘውግ ፖለቲካው ከ1983-2010 ዓም በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳትና የተጋረጠው ፈተና
    በኢትዮጵያ ከ1983 ዓም ጀምሮ ስሩን የተከለው የዘውግ ፖለቲካ ዋነኛ ተልዕኮው ባለፉት የሃገሪቱ ረዥም የታሪክ ምዕራፎች አማራው ይዞት ነበረ ብሎ የሚያስበውን የአዛዥ ናዛዥነት፣የሃገር ባለቤትነት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ምዕራፍ መዝጋት ነው፡፡በአስተሳሰቡ ቀንቃኞች እምነት ባለፉት ዘመናት ነበረ የሚሉትን የአማራውን ሁለንተናዊ የበላይነት ታሪክ ምዕራፍ መዝጋቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ይልቅስ አማራውን መበቀልም ትግላቸውን ይበልጥ ትርጉም ሰጭ የሚያደርግ እርምጃ እንደሆነ ያስባሉ፡፡በመሆኑም አማራውን ነበረበት ከሚሉት የበላይነት አውርዶ በበቀል ለበቅ ለመግረፍ የሚያስችላቸውን በህጋዊ ማዕቀፍ የታገዘ ተበቃይ ስርዓት መዘርጋትን ዋነኛው የሃገሪቱ ዘውግ ፖለቲካ ዘይቤ አደረጉ፡፡
    የዘውግ ፖለቲካው አማራውን የሚበቀልበት አካሄድ ህጋዊ፣ፖለቲካዊ፣ባህልዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ገፅታዎች ያሉት ነው፡፡የአማራው ህዝብ የዘውግ ፖለቲካውን የበቀል በትሮች የሚያስተናግድበት መንገድም የተለያየ ነው፡፡የአማራ ክልል ተብሎ ከተከለለው ግዛት ውጭ ያለው የአማራ ህዝብ እነዚህን የበቀል እርምጃዎች የሚያስተናግድበት መንገድ በክልሉ ከሚኖረው አማራ የባሰና የተለየ ነው፡፡በተጨማሪም በክልላቸውም ሆነ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ አማሮች የሚጋሯቸው የጋራ ፈተናዎችም አሉ፡፡
    5.1 የአማራ ክልል በተባለው ግዛት የሚኖረው የአማራ ህዝብ ዋነኛ ፈተናዎች
    የአማራ ክልል ተብሎ በተከለለው ክልል ውስጥ የሚኖሩ አማሮች የሚገጥማቸው ዋነኛ ፈተና የክልሉ ህዝብ ይወክሉኛል በሚሉት መሪዎች ሳይሆን የዘውግ ፖለቲካው በአማራው ህዝብ ላይ ያለውን የበቀል አጀንዳ በሚያሳልጡ፣ አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ከመንበሩ ሆኖ የአማራ ህዝብን የሚመታበት ረዥም ዱላ ሆነው የሚያገለግሉ ምስለኔዎች መሆናቸው ነው፡፡ስለእነዚህ ግዙ መሪዎች በሰፊው ብዙ የተባለበት ስለሆነ በዚህ ላይ ብዙ ጊዜን ማጥፋት አያስፈልግም፡፡
    የአማራ ክልል በምስለኔ መንግስት የመተዳደሩ ዋነኛው ምክንያት “አማራ ከዚህ በፊት ሲጨቁን የኖረ ወንጀለኛ ዘውግ ስለሆነ ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ዋነኛ ሃገራዊ መንበረ ስልጣን መምጣት የለበትም” ከሚለው የዘውግ ፖለቲካው የህጎች ሁሉ ራስ ከሚመስለው ዘይቤ የሚቀዳ ነው፡፡በዚህ ያልተፃፈ ግን በሃገር ደረጃ መግባባት የተያዘበት በሚመስል ሁኔታ አማራው በዋነኛ የሃገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ቀርቶ የህብረ-ብሄራዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋነኛ ስልጣን ላይ ከተቀመጠ እንኳን ፓርቲው በነፍጠኛ ፓርቲነት ይፈረጃል፤ የፓርቲውን እድሜ የሚያሳጥር አሳዳጅ ይበዛል፡፡ነገሩ ሲብስ ደግሞ ፓርቲው ህብረብሄራዊ ፓርቲ ነኝ እስካለ ድረስ ሊቀመንበሩ/ሯ፣ ዋኛ ስራአስፈፀሚዎች ከሌላ ዘውግ ቢሆኑም እንኳን ፓርቲው “የነፍጠኛ አማራ ፓርቲ” ተብሎ ከመፈረጅ የሚያድነው ነገር የለም፡፡
    ሌላው በክልሉ የሚኖረው የአማራ ህዝብ ፈተና ክልሉ ሆን ተብሎ በኢኮኖሚ፣በመሰረተ-ልማት፣በማህበራዊ ግልጋሎት(የትምህርት፣የጤና አገልግሎት) ዕድገት ወደኋላ እንዲቀር በመደረጉ ሳቢያ ለከፍተኛ ድህነትና ሁለንተናዊ ጉስቁልና እንዲጋለጥ መደረጉ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ በሃገራችን ባለው የዘውግ ስርዓት ለክልሎች የሚበጀተው በጀት መጠን የሚወሰነው በክልሉ በሚኖሩ ዘውጎች ቁጥር በመሆኑ “የተወሰነው የአማራ ህዝብ የገባበት ጠፋ” በሚል ሰሚን በሚያስገርም ምክንያት ቁጥሩን ሆን ብሎ ተብሎ ተቀንሷል፡፡ስለሆነም የአማራ ህዝብ ከአጠቃላዩ የሃገሪቱ በጀት የሚገባውን ያህል ድርሻ እንዳያገኝ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ድሮም በቋፍ ያለውን የክልሉን የድህነት መጠን አንሮታል፡፡
    አራተኛው የአማራ ህዝብ ፈተና ባህሉን ለማሳደግና የታሪክ ትዝታዎቹ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የትምክህተኝነቱ አካል ተደርጎ ከመታየቱም ባሻገር የአማርኛ ቋንቋን ጨምሮ የአማራ ህዝብ ባህል እና ማንነት መገለጫ የተባሉ ነገሮችን ሁሉ ለማውደም የሚደረገው ጥረት ነው፡፡እንደሚታወቀው አሁን ሃገራችን የምትመራበት አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ሁሉ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ማንነታቸውን እንዲጠብቁ መብት እንደሰጠ ይሰበካል፡፡ ሆኖም ነገሩ ወደ አማራ ዘውግ ሲመጣ ልዩ መልክ ይይዛል፡፡
    አማራው ባህሉን ለመሳደግ፣የታሪክ ትዝታዎቹን ለመዘከር የሚያደርገው እንቅስቃሴ በአማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው ቀሳውስት ዘንድ የትምክህተኝነቱ፣እበልጣለሁ ባይነቱ መገለጫ ተደርጎ ይፈረጃል፡፡ በታሪክ ትዝታው ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገስታትን በሚዘክርበት ጊዜ የተለያዩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ትንኮሳዎችን ያስተናግዳል፡፡ እንደ ዘውጋዊም ሆነ ሃገራዊ ምልክቶች የሚወስዳቸው እንደ ባንዲራ ያሉ መገለጫዎቹን በነፃነት ይዞ እንዳይንቀሳቀስ በአዋጀ ሳይቀር የሚከለከልበት ወቅት አለ፡፡ ይህ ለሌሎች ብሄረሰቦች በገፍ የተፈቀደ ለአማራ ህዝብ ሲሆን ግን የሚከለከል የዘውግ ፖለቲካው በአማራ ማንነት ላይ የጋረጠው ስነ-ልቦናዊ መልክ ያለው ፈተና ነው፡፡
    ሌላው በአሳሳቢነቱ ዋነኛ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው የአማራ ህዝብ ፈተና የአማራ ክልል በውስጡ የሚኖሩ ብሄረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለመስጠት ሲል ባዋቀራቸው ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች በኩል የሚመጣው ፈተና ነው፡፡የዘውግ ፖለቲካው አማራ የተባለውን ዘውግ የሌሎችን ባህል ባለማክበር ጨፍላቂነት፣”በአሃዳዊነት”፣ “በፀረ-ህብረብሄራዊነት” የሚከስ ነው፡፡ በአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ምስለኔዎች የሚመራው የአማራ ክልል መንግስት ከዚህ ክስ የዳነ መስሎት የአማራ ክልል ከሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች እጅግ በተለየ መንገድ በውስጡ ለሚኖሩ ሌሎች ዘውጎች ከፍ ያለ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም በአማራ ክልል የተለያዩ የብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች እና የልዩ ወረዳዎች መዋቅሮች ዘርግቷል፡፡
    ይህም ሆኖ አማራን በደህና ለማንሳት ተፈጥሮው የማይፈቅድለት በሃገራችን ያረበበው አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ አማራውን በጨፍላቂነት፣ በአሃዳዊነትና በፀረ-ህብረ ብሄራዊነት ከመክሰስ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡የአማራ ክልል በውስጡ ለሚኖሩ ሌሎች ዘውጎች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩባቸው (የአዊ፣የቅማንት፣የኦሮሞ፣የአርጎባ፣የዋግህምራ) የብሄረሰብ አስተዳደር መዋቅሮች መዘርጋቱ የዘውግ ፖለቲካው አማራውን የሚከስበትን የጨፍላዊነት ክሱን የሚያስቀርለት ሳይሆን የዘውግ ፖለቲካው አማራውን ክልሉ ድረስ ተጉዞ የሚዋጋበት መቆናጠጫ ቦታ የሆነበት ሁኔታ አለ፡፡
    በአማራ ክልል የሚኖሩ እነዚህ ብሄረሰቦች በአማራው ክልል የሚተዳደሩበት ሁኔታ በሃገሪቱ ሌሎች ክልሎች ህዳጣን(Minority) ሆነው ከሚኖሩ ዘውጎች አኗኗር እጅግ የተሻለ የመብት ይዞታ እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ ቢሆንም አማራውን መክሰስ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ዋነኛ ዓላማ አድርገው የሚያስቡ የዘውግ ፖለቲካው ቀሳውስት ግን እነዚህን ብሄረሰቦች በአማራ ክልል ህዝብ እና መንግስት የተበደሉ አድርጎ በማቅረብ ክልሉን ላለመረጋጋት በሚዳርግ እንቅስቃሴ ውስጥ ጭምር እንዲገቡ ከፍተኛ ግፊተና እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ የአዊ እና የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደሮች የዘውግ ፖለቲካውን ግፊት እምብዛም ጆሮ ያልሰጡ ናቸው፡፡ በአንፃሩ በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን አስተዳደር ኦነግ የተባለው ታጣቂ እና በቅማንት አስተዳደር ዞን የቅማንት ታጣቂዎች የሚባሉ አካላት ግን የክልሉን ሰላም አደጋ ውስጥ የሚከቱ ደም አፋሳሽ የነውጥ ድርጊቶችን ይፈፅማሉ፡፡
    ይህን ድርጊት የሚፈፅሙት የቅማንት ሃይሎች በህወሃት ሞግዚትነት የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ የአጣየ ከተማን እስከማጥፋት የደረሰው የኦነግ ታጣቂ ቡድን ደግሞ ኦነግ ዘመም በሆኑ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሁሉ ድጋፍ የማያጣ ነው፡፡ለዚህ ምስክሩ በከሚሴ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው ሃይል በፓርላማ ኦህዴድ ብልፅግናን ወክለው በተቀመጡ የብሄረሰቡ የፓርላማ ወኪሎች ሳይቀር ጥብቅና ሲቆምለት በሃገሪቱ ቴሌቪዥን የታየ መሆኑ ነው፡፡የቅማንት ታጣቂችም ሆኑ በከሚሴ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የኦነግ ታጣቂዎች የዘውግ ፖለቲካው በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን እረፍት የመንሳት ተልዕኮ የሚያስፈፅሙ ወኪሎቹ ናቸው፡፡
    የአማራውን ህልውና የማይፈልገው የዘውግ ፖለቲካ የአማራ ክልል የሚባለው ሰፊ ክልልና አማራ የሚባለው ማንነት ራሱ መኖሩን የሚፈልግ አይደለም፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ስልጣን ላይ ባሉት የዘውግ ብሄርተኞች ዘንድ አማራ ከሚባለው ሰፊ ክልልና አማራ ከሚባለው ማንነት ይልቅ ጎጃም፣ጎንደር፣ወሎ፣ሸዋ የሚባል ማንነት እንዲኖር የመስራት ዝንባሌ አለ፡፡ይህ ዝንባሌ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያበበ የመጣው የአማራ ንቅናቄ የዘውግ ብሄርተኞችን አማራውን የማሳደድ አጀንዳ የሚገዳደር በመሆኑ ስጋት ስለፈጠረባቸው ነው፡፡
    ይህን በአሰጊ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአማራ ንቅናቄ ለመገዳደር ደግሞ አማራውን በአካባቢ በታትኖ ማጥቃቱ ውጤታማ ስልት ነው፡፡ ስለሆነም የቅማንት እና የኦነግ ታጣቂ ቡድኖችን ማስታጠቅና ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው የአማራ ክልል እንዳይረጋጋ ብቻ ሳይሆን አማራ ክልል የሚባለው ክልል ህልውናው እንዳይኖር ለመበታተን የሚጠቀምባቸው ፖለቲካዊ ጠጠሮቹ ናቸው፡፡የዘውግ ብሄርተኞቹ በአዊ እና ዋግህምራ በኩልም ተመሳሳይ የነውጥ ሃይሎችን ለማስነሳት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም እምብዛም አልተሳካላቸውም፡፡
    የዘውግ ብሄርተኞች በአማራ ክልል የሚገኙ ብሄረሰቦችን ሁሉ ባለታጣቂ ለማድረግ የሚመኙበት ዋነኛው ምክንያት ትልቁን የአማራ ክልል ሲበታትኑ በእነዚህ ብሄረሰቦች ውስጥ ቅርጫ አድርገው ማስቀመጥ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ይህም ማለት የቅማንት ታጣቂዎች የሚያስፈልጉት ጎንደርን የቅማንት ክልል በማድረግ፣ጎጃምን የአገው ብሄረሰብ ግዛት በማድረግ፣ወሎንና ሸዋን የኦሮሞ በማድረግ የብሄረሰቦች ባለጋራ አድርገው የበየኑትን የአማራ ክልልና የአማራ ማንነት በማጥፋት “አዲሲቱ” የሚሏትን “ከአማራ የበላይነት” ነፃ የሆነች ሃገር ለመመስረት በምኞት ፈረስ ይቃትታሉ፡፡ ለዚህ ትልቅ ተግዳሮት የሆነባቸው ሰፊ ግዛታዊ ክልል ባለው በአዊ አና ዋግ ህምራ ዞን አጀንዳቸውን ተቀብሎ ሊንቀሳቀስ የፈቀደ ጉልህ ታጣቂ አካል አለመኖሩ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የአማራ ንቅናቄ ጎልብቶ፣የጠራ መስመር ይዞ የተከፈተበትን ጥቃት መከላከል ካልቻለ የክልሉም ሆነ የአማራ ማንነት ህልውና ቀጣይነት አደጋ ውስጥ ያለ ነገር ነው፡፡
    5.2 ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማሮች የሚገጥማቸው ፈተና
    5.2.1 የሰብዓዊ መብት ጥሰት
    የሃገራችን የዘውግ ፖለቲከኞች የአማራው ዘውግ ጨቁኖናል ከሚሉበት ምክንያት አንዱ የአማራ ዘውግ አባላት በመላ ሃገሪቱ ተበትነው መኖራቸው ነው፡፡የጉልበት ስራ ሊሰራ ወደ ክልላቸው የሄደውን አማራ ሁሉ ለመጨቆን የሄደ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ የአማራ ህዝብ በመላ ሃገሪቱ ሊበተን የቻለበት ምክንያት በጥናት ሊረጋገጥ የሚገባው ነገር ሆኖ ከጥናት በመለስ ግን አሁን አማራ ክልል በሚባለው ቦታ ላይ ያለው ጥልቅ ድህነት ሰዎች ስራ ፍለጋ ከአካባቢያቸው ርቀው እንዲሄዱ ማድረጉ፣የአካባቢው ድህነት የአንድ አመትን የዝናብ ማጠር መቋቋም ስለማያስችል ተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ የማስፈሩ መንግስታዊ መፍትሄ(በተለይ በደርግ ስርዓት) በርካታ አማሮች በመላ ሃገሪቱ ተበትነው እንዲኖሩ ማድረጉ ነው፡፡
    የአማራን ነገር ሁሉ ከጨቋኝነት ትርክት ጋር የሚያገናኘው የዘውግ ፖለቲካችን ታዲያ አማራው ተቸግሮ ያደረገውን ነገርም በሆነው ልክ የመመርመር ስክነት የለውምና የአማራ ክልል ከሚባለው ግዛት ውጭ የተገኘ አማራን ሁሉ በጨቋኝነት ፈርጆ ያሳድዳል፡፡ የዘውግ ፖለቲካውን ዘይቤ የቀረፁ ልሂቃን የዘውጋቸው ጥንታዊ ግዛት በአማራ ገዥዎች አስገዳጅነት ወደ ኢትዮጵያ ኢምፓየር እንዲካለል ተደርጓል፣የአማራ ባህልም በግድ ተጭኖበታል ብለው ያምናሉ፡፡በመሆኑም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የኖሩበት ዘመን ሁሉ በአማራ ቅኝ ግዛት ስር የኖሩበት ዘመን አድርገው ያስባሉ፡፡በመሆኑም ከክልሉ ውጭ የሚኖረው አማራ ሁሉ የአማራ ነገስታትን ቅኝ አገዛዝ ለማሳለጥ የመጣ ነፍጠኛ ነው የሚል ሰፊ ተቀባይነት ያለው ትርክት ፈጥረዋል፡፡
    ትርክቱ ብቸኛ እውነት ለመሆን በመድረሱ ሳቢያ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ አማሮች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምንም ተጠያቂነት የማያመጣ ተገቢ ድርጊት እስከመምሰል ደርሷል፡፡ስለሆነም የአማራ ከሚባለው ክልል ውጭ ያሉ አማሮች አማራ መሆናቸውና በሌላ ክልል መገኘታቸው ብቻ ወንጀል ሆኖ በአሰቃቂ ሁኔታ ዘውግ ተኮር ጭፍጨፈ ይፈፀምባቸዋል፣ንብረታቸው ይዘረፋል፣ይፈናቀላሉ፣ በታጣቂዎች ታግተው ከመገደላቸው በፊት ቁም ስቅል(torcher) እንዲያዩ ይደረጋል፣በመንግስት ስራ ተቀጥረው ያሉ የአማራ ዘውግ ተወላጆች አማራ መሆናቸው ብቻ ወንጀል ተደርጎ ከስራቸው እንዲባረሩ ይደረጋል፡፡ትህነግ ስልጣን እንደያዘ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያባረራቸው የሃገሪቱ ምርጥ ምሁራን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ አማሮች ናቸው፡፡ትህነግ ስልጣን ላይ ውሎ ሲያድርም በመንግስት ሲቪል ቢሮክራሲ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆች በተጠና መልኩ ስራቸውን እንዲለቁና ለትህነግ ካድሬዎች እንዲያስረክቡ ተደርጓል፡፡
    ከአማራ ክልል ውጭ ሄደው ኑሯቸውን በቋሚነት የመሰረቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀርቶ ለተወሰነ ጊዜ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ከክልላቸው ውጭ የሄዱ አማራ ተማሪዎች ዘውጋቸውን መሰረት ያደረገ እገታ፣አሰቃቂ ግድያ፣የስነ-ልቦና ጫናን የሚያስከትሉ ማስፈራሪያዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ከክልላቸው ውጭ ያሉ የአማራ ተማሪዎች ይህ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲደረግባቸው የፌደራሉ መንግስትም ሆነ ወንጀሉ የሚፈፀምበት ክልል መንግስታት ወንጀሉን ለማስቆም ይህ ነው የሚባል እርምጃ ሲወስዱ ታይቶ አይታወቅም፤በአንዳንድ ክልልሎች (ለምሳሌ ኦሮሚያ እና ቤኒሸንጉል ጉሙዝ ክልሎች) መንግስት ራሱ ባመነው ሁኔታ የመንግስት መዋቅር ላይ ያሉ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በወንጀሉ የሚሳተፉበት ሁኔታ አለ፡፡
    5.2.2 የእገታ(Hostage) ፖለቲካ ሰለባነት
    ከላይ እንደተጠቀሰው ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖረው የአማራ ህዝብ የፊውዳሉ ስርዓት የአማራ የበላይነት ቅሪት ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡በዚህም ምክንያት በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያስተናግዳል፡፡በእዚህ የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁለት ምክንያቶችን ያዘለና መንታ ቱርፋት ያለው ነገር ነው፡፡
    አንደኛው ሰዎቹ የፊውዳሉ ስርዓት በአማራ በኩል ሃገሪቱን ሲበዘብዝ የነበረበት ጨቋኝ ስርዓት ቅሪት ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡በመሆኑም በእነሱ ላይ የሚደረገው የመብት ጥሰት ሁሉ ጨቋኙን አማራ ሰራሽ የቀድሞ ስርዓት የመዋጋት ትግል ተደርጎ ይቆጠራልና ሰፋሪ፣ወራሪ፣ቅኝ ገዥ፣ነፍጠኛ የሚል ስም ተለጥፎባቸው ይሳደዳሉ፡፡ይህን በማድረግ አካባቢውን ከአማራ አፅድቶ ባለቤት ለተባለው የአካባቢው ዘውግ ተወላጅ ማስረከብ ያስችላል፡፡ ይህ በዘውግ ፖለቲካው ዘንድ “የሃገር ባለቤትነትን ማረጋገጥ” ተብሎ የሚጠራ እንደ ወሳኝ ድል የሚቆጠር ነገር ነው፡፡ይህ ድል ለአማራ-ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ተደራቢ ፖለቲካዊ ጥቅም አዝሎ የሚመጣ ነገር ነው፡፡
    ሁለተኛው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ አማሮች ላይ የሚያሳድረውን ሁለንተናዊ ጉዳት በአማራ ክልል ያለው ሰፊ ህዝብ በሚቃወምበት ጊዜም ሆነ በአጠቃላይ በዘውግ ፖለቲካው ስርዓት ላይ ተቃውሞ እንዳያነሳ የፖለቲካ ሙቀቱን የሚቆጣጠርበት ልጓም ሆኖ የሚያገለግል መሆኑ ነው፡፡ በክልሉ ያለው ህዝብ ከክልሉ ውጭ ያሉ አማሮች የሆነ ቦታ ላይ የደረሰባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የመቃወም እንቅስቃሴ ሲጀምር “የባሰ እንዳታስጨርሷቸው አርፋችሁ ተቀመጡ” የሚለው የዘውግ ፖለቲካው ቀሳውስት ማስፈራሪያ ይሁን ማስጠንቀቂያ ወይ ምክር የማይታወቅ ነገር ይከተለላል፡፡ይህ ነገር ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ አማሮች ራሳቸውም “አንድ ቦታ ስለተደረገው ግድያ ስታወሩ የእኛ ህይወት አደጋ ላይ ስለሚወድቅ ስለግድያው አታንሱ” የሚል ልመና ያስከትላሉ፡፡በዚህ መንገድ የዘውግ ፖለቲካው ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ አማሮችን እንደ እገታ በመያዝ በአማራ ክልል ያለው አማራ የዘውግ ፖለቲካው በማንነቱ ምክንያት ለሚያደርስበት በደል የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ምላሽ እንዳይኖር ይቆጣጠራሉ፡፡
    5.2.3 ማንነትን የማጣት ስጋት
    አማራ ከሚባለው ክልል ውጭ የሚኖረው የአማራ ህዝብ በዘውጋዊ ማንነቱ ምክንያት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጨምሮ ፈርጀ ብዙ ተፅዕኖዎችን ማስተናገዱ የጋረጠበትን ፈተና ለማለፍ አማራነቱን መካድንና የማያስገድለውን ዘውጋዊ ማንነት ተላብሶ መኖርን እንደ የቢቸግር አማራጭ ይወስዳል፡፡በመሆኑም በሃገራችን ህገ-መንግስት ለሌሎች ብሄረሰቦች በሰፊው የተፈቀደውና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግጋት የተረጋገጠው የሰው ልጆች ማንነታቸውን ጠብቀው የመኖር፣ባህላቸውን የማሳደግ መብት ከክልሉ ውጭ ላለው የአማራ ህዝብ በህይወት ከመኖር እና ካለመኖር ጋር የሚያያዝ ፈተና ይዞ የሚመጣ ነገር ይሆናል ማለት ነው፡፡
    ይህ ማንነትን የማጣት የግዴታ ውሳኔ ሌላ መዘዝ ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በማንነት ምክንያት ላለመሞት ማንነትን የመቀየር ውሳኔው ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማሮች ወይ የሌሉ ወይ ቁጥራቸው በጣም አናሳ እንደሆነ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ አማሮች ለወደፊቱ እንኳን በአካባቢው አስተዳደራዊ መዋቅር ህልውናቸውን በሚመጥን መንገድ መወከል አለባቸው የሚል የፍትሃዊነት ትግል ለማንሳት አስቸጋሪ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማሮች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ጥሰት፣የስነ-ልቦና ጉዳት፣ ሁለንተናዊ ዋስትና የማጣት የመብት ጥሰቶች በማያቋርጥ አዙሪት(vicious circle) ውስጥ እንዲቀጥሉ ያደርጋል፡፡
    ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በአንድ አካባቢ ያሉ ህዳጣን ማህበረሰቦች የቋንቋ፣የባህል እና ስነ-ልቦና ማንነታቸው ብዙሃን በተባሉት በሌሎች እንዳይዳጥና እንዳይጠፋ ዋስትና ለመሰጠት ነው፡፡የፌደራል መዋቅሩ ስኬት በዋናነት የሚለካውም ከዚሁ አኳያ ነው፡፡10አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች የብሄረሰቦችን መብት በማክበር የሚያንቆለጳጵሱት የሃገራችን ፌደራሊዝም ከክልላቸው ውጭ ህዳጣን ሆነው የሚኖሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆችን ማንነት የሚድጥ መሆኑ የፌደራላዊ አስተዳደር ስርዓትን ዋነኛ ዓላማ የሳተ ያደርገዋል፡፡
    5.2.3 ፖለቲካዊ ውክልና የማጣት ችግር
    በሃገራችን የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ አሁን ያለው ዘውግ ተኮር ፖለቲካ የህዝቦችን ብዝሃነት ለማክበር ታስቦ የተዘረጋ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሆኖም በሃገሪቱ በሚገኙ ክልሎች ያለው እውነታ የተገላቢጦሽ ነው፡፡በኢትዮጵያ ያሉ የክልል ህገ-መንግስቶች በአመዛኙ ክልሎችን የአንድ ዘውግ ወይም የተወሰኑ የክልሉ ባለቤት የተባሉ ዘውጎች ብቻ አምባ የማድረግ ከነባራዊ እውነታ ያፈነገጠ ተልዕኮ ያዘሉ ናቸው፡፡ነባራዊው እውነታ በሁሉም ክልሎች ብዙሃን እና ህዳጣን የሚባሉ ዘውጎች የሚኖሩ መሆናቸው እንጅ በአንድ ዘውግ ብቻ የተሞላ ክልል አለመኖሩ ነው፡፡
    ሆኖም የኢትዮጵያ ክልላዊ ህገ-መንግስቶች ይህን እውነታ ባገናዘበ መንገድ የህዳጣንን መብት ጭምር ታሳቢ በሚያደርግ መንፈስ ያልተፃፉ ናቸው፡፡ በመሆም በክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ የክልል ባለቤት የተባሉ ብዙሃን ዘውጎች እና ህዳጣን ዘውጎች የተዛባ መብት አሰጣጥ የሚያመጣው ቀውስ የሃገሪቱ ፌደራሊዝም ትልቅ እንከን ሆኖ ይታያል፡፡11የፌደራሊዝም ስርዓትን በዋነነት አስፈላጊ የሚያደርገው ደግሞ በአንድ አስተዳደራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህዳጣን ህዝቦች ሁለንተናዊ መብት፣ህልውና እና ጥቅም ለማስከበር ሲባል ነው፡፡12
    ይህ በብዙሃን እና ህዳጣን መካከል የሚታየው የተዛባ ግንኙነት ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ዘውጎች ሁሉ ፈተና ቢሆንም ከክልላቸው ውጭ በሚኖሩ የአማራ ዘውግ አባላት ላይ ደግሞ ችግሩ በጣም የገዘፈ ነው፡፡የዚህ ምክንያቱ የአማሮቹ ጉዳይ ህዳጣን ከመሆናቸው በተጨማሪ የሃገሪቱን ፖለቲካ የሚዘውረው አማራ-ጠል ትርክር ሰለባም ስለሆኑ ነው፡፡ አማራ ያልሆኑ ሌሎች ዘውጎች ከክልላቸው ሲወጡ የሚገጥማቸው ፈተና በንዑስነታቸው ብቻ የሚመጣ እንጅ ትርክት የተደገፈ የጨቋኝነት ክስም የታከለበት አይደለምና ፈተናቸውም ከአማራው ፈተና ያነሰ ነው፡፡የአማራ ዘውግ ከሌሎች ዘውጎች በበለጠ ቁጥር ከክልሉ ውጭ በሆኑ ከተሞች የሚኖር መሆኑ ደግሞ ችግሩ በጉልህ ሁኔታ እንዲስተዋል አድርጎታል፡፡
    በኢትዮጵያ ከተሞች በርከት ያለ ቁጥር ያለው የአማራ ዘውግ ይኖራል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ከተሞች የአማራው ቁጥር የብዙሃንነትን ድርሻ(50+1) ያለፈ ቁጥር ቢኖረው እንኳን በከተሞቹ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ውክልና እንዲኖረው አይደረግም፡፡ውክልና ሊሰጠው ቀርቶ በእነዚህ ከተሞች መገኘቱ ራሱ የጨቋኝነቱ ማስረጃ ተደርጎ የሚቀርብ ነገር ነው፡፡ በአንፃሩ ያለ ክልላቸው ያሉ ሌሎች ዘውጎች በርከት ብለው በሚገኙባቸው ከተሞችም ሆነ ክልሎች ቁጥራቸውን በሚመጥን ምጥንታ(Ratio) በተሰላ ሁኔታ አስተዳደራዊ ውክልና ይኖራቸዋል፡፡ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት የድሬዳዋ አስተዳደር እና የሃረሬ ክልል አስተዳደራዊ ቀመሮች ናቸው፡፡
    እንደሚታወቀው የድሬዳዋ አስተዳደር በማንኛውም ክልል ውስጥ ያልተዋቀረ የራሱ አስተዳደር ያለው የሃገራችን ግዛት ክፍል መሆኑ በፌደራል ህገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጠው ነው፡፡ ይህ ማለት ድሬዳዋ የኦሮሚያም የሶማሌ ክልልም አካል አይደለም ማለት ነው፡፡ ሆኖም በዚህ አስተዳደራዊ ግዛት ውስጥ የሚኖሩት የኦሮሞ እና የሱማሌ ዘውግ አባላት ቁጥር ከአማራ ዘውግ ተወላጆች ይብለጥ ይነስ በማይታወቅበት ሁኔታ አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው በከተሞች ያለውን የአማራውን ድምፅ ለማፈን ሲል አስተዳደራዊ መዋቅሩ ለኦሮሞ-ሱማሌ-ሌሎች እንደ ቀደም ተከተላቸው 40-40-20 የሚል የውክልና ምጥጥን ያለው አስተዳደር ዘርግቷል፡፡ በተመሳሳይ በሃረሬ ክልል ከሃራሬ ዘውግ ተወላጆች በመቀጠል የኦሮሞ ዘውግ ተወላጆች የአስተዳደራዊ ምጥንታውን ተጋርተው በህገመንግስት የሃራሪዎች የተባለውን ክልል በጋራ ያስተዳድራሉ፡፡
    ይህ አይነቱ ምጥንታ ከክልላቸው ውጭ ለሚኖሩ በቁጠር በርካታ አማሮች የተሰራበት የኢትዮጵያ ክልል ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡አማሮች በተለያዩ ክልሎች በብዙ ቁጥር በመኖራቸው መጠን አስተዳደራዊ ውክልና ሊያገኙ ቀርቶ ጉልህ እና ነባር ብዙሃን በሆኑበት እንደ መተከል ባለ አካባቢ እንኳን ምንም አይነት የአስተዳደራዊ ውክልና ድርሻ የላቸውም፡፡በመሆኑም በአማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው የሚያደርስባቸውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚከላከሉበት፣ወንጀሉን የፈፀመባቸውን አካል ተጠየቂ የሚያደርጉበት ፖለቲካዊ ፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ ከለላ የለም፡፡
    በተለያዩ ክልሎች በብዙ ቁጥር ተበትኖ የሚኖረው የአማራ ህዝብ በሃገሪቱ ከተሞች በርከት ብሎ ይኖራል፡፡በመሆኑም የዘውግ ፖለቲካው የኢትዮጵያ ከተሞችን የዘውግ ፖለቲካው ዋነኛ ተግዳሮቶች አድርጎ ይወስዳል፡፡በሃገሪቱ ያሉ ከተሞች በዘውግ በተከለሉ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም በአንዳንድ ከተሞች ከክልሉ ባለቤት ዘውጎች የበለጠ ቁጥር ያለው የሌላ ዘውግ ህዝቦች ይኖራሉ፡፡ከነዚህ ዘውጎች ውስጥ የአማራ ዘውግ አባላት በርካታውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡የኢትዮጵያን ከተሞች በአንድ ዘውግ ስር በዘውጋዊ አስተዳደር ለማስተዳደር የህዝቦቻቸው የዘውግ ስብጥር ስለማይፈቅድ የኋላ ኋላ ከተሞቹ በከንቲባ በሚመራ የከተማ አስተዳደር መዋቅር እንዲተዳደሩ ተደርጓል፡፡ሆኖም ይህ መዋቅር ራሱ በዘውግ ፖለቲካው ትልቅ ተፅዕኖ ስር ከመውደቅ አልዳነም፡፡
    የከተሞችን የዘውግ ስብጥር ባገናዘበ መልኩ ለማስተዳደር የተዘረጋው የከተማ አስተዳደር መዋቅር በሁለት መንገድ የሚወራለትን የከተሞችን ህብረብሄራዊነት ባገናዘበ መልኩ ለማስተዳደር አልቻለም፡፡አንደኛው የከተሞቹ ከንቲባዎች በቀጥታ በዘውግ ክልሉ ፕሬዚደንቶች የሚሾሙ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በከተማ አስተዳደሮቹ ፓርላማዎች ውስጥ የዘውግ ኮታ በክልሉ ትዕዛዝ የሚቀመጥ መሆኑ ነው፡፡ይህ ኮታ የማስቀመጥ አሰራር በመጀመሪያ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን የደቡብ ክልልም ይህን ልምድ ቀስሞ ተግባራዊ አድርጎታል፡፡13
    በኮታ ስርዓቱ መሰረት የኦሮሞ ዘውግ ነዋሪዎች ብዙሃን ባልሆኑባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ፓርላማ ውስጥ 30 ፐርሰንት ኮታ ለኦሮሞ ይሰጣሉ፡፡ሆኖም የኦሮሚያ ክልል ትንሽ ቆይቶ የ30ፐርሰንት ኮታውን ወደ 50 ፐርሰንት አሳድጓል፡፡ በዚህ መንገድ የከተማ አስተዳደር መዋቅሩ ለይስሙላ በከንቲባና የዘውግ ስብጥር ባለው ካውንስል የሚመራ ነው ይባል እንጅ ዞሮ ዞሮ የከተሞችን ስብጥር የማይመስል ነው፡፡ ይልቅስ የዘውግ ፖለቲካው የቀመረውን በአንድ ክልል ውስጥ የክልሉ ባለቤት የተባለውን ዘውግ አድራጊ ፈጣሪነት ማስጠበቀን ያስቀጠለ ነው፡፡ይህ አካሄድ በኦሮሚያ ከተሞች አማራው በአመዛኙ የብዙሃንነት ቁጥር ይዞ የሚገኝ ቢሆንም በዘውግ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ወክልና ያሳጣዋል፡፡በመሆኑም በዘውግ ፖለቲካው ሳቢያ የሚመጣበትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሞገት፣መከላከልና ማስቀረት የሚችልበት መንገድ በማጣቱ በኦሮሚያ ከተሞች የአማራው ዘውግ ተኮር ጥቃት እንዲቀጥል ሆኗል፡፡
    5.3 በአማራ ክልል ውስጥም ከክልሉ ውጭም የሚኖሩ አማሮች የጋራ ተግዳሮቶች
    5.3.1 ህገ-መንግስታዊ መገለል
    ህገ-መንግስታዊ ስርአት መገንባት ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ ብሎም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነገር ነዉ፡፡ህገ-መንግስት ከግጭት እና ከአለመረጋጋት በኋላ የሚገኝ ማህበረሰብ ግጭትን አዎንታዊ ወደሆነ ገንቢ ሃይል በመቀየር ሰላምን በማምጣት፣ በመጠበቅና በመገንባት የሰላም ሰነድ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡በመሆኑም ህገ-መንግስት የሚዘጋጅበት ሂደት ከህገ-መንግስቱ ዉስጣዊ ይዘት እና አፈፃፀም እኩል የሆነ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡ህገ-መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ውጤት ብቻ ሳይሆን የህዝቡ እና ሌሎች ያገባናል የሚሉ ሃይሎች፣ ማህበራት፣ ተቋማትና አደረጃጀቶች ትርጉም ያለዉና የነቃ ተሳትፎ ዉጤት መሆን ይኖርበታል፡፡
    ፖለቲካዊ ተቃርኖ ባየለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማህበረሰብ ህገ-መንግስት የሚዘጋጅበት ሂደት ከህገ-መንግስቱ ዉስጣዊ ይዘት እና አፈፃፀም እኩል የሆነ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡አንድ ህገ-መንግስት የተረቀቀበት፣ የተዘጋጀበት እና የፀደቀበት ሂደት የህገ-መንግስቱን ይዘት፣ ስኬትና ህዝባዊ ተቀባይነት ይወስናል፡፡ በተለይም ሂደቱን ጥቂት ልሂቃን የመሩት መሆኑ ወይም ሂደቱ ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ የነበረበት መሆኑ ለህገ-መንግስቱ ህዝባዊ ተቀባይነትም ሆነ ለይዘቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

የህገ-መንግስት ዝግጅት አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ማርቀቅ (Drafting)፣ መምከር/ህዝባዊ ዉይይት(Deliberation)፣ መቀበል (Adoption) እና ማፅደቅ (Ratification) ሲሆኑ በእነዚህ ሂደቶች ሁሉ ሁሉን አቃፊነት፣ አሳታፊነት እና ነፃ ፈቃድ በጣም አስፈላጊ ነዉ፡፡ ስለዚህ በእነዚህ በአራቱ ሂደቶች ዉስጥ ማን ተሳተፈ፤ ማንስ በእነዚህ ሂደቶች በሁሉም ወይም በአንዱ አልተሳተፈም የሚለዉ ጥያቄ ህገ-መንግስቱ የማን ህገ-መንግስት ነዉ የሚለዉን የሚመልስ ሲሆን የህገ-መንግስቱ ቅቡልነትም የሚወስነዉ በዚህ ነዉ፡፡ከዚህ አንፃር አሁን በስራ ላይ ያለዉን ህገ መንግስት የተዘጋጀበት ሂዳት ያሳተፋቸው ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ወካይነት ጉዳይ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሳበት ነው፡፡14
ከደርግ ዉድቀት ማግስት ደርግን አሸንፈናል በሚል ስልጣን የተቆጣጠሩት ብሄር-ተኮር የፖለቲካ ቡድኖች በትህነግ ፊት አዉራሪነት የሰላም ኮንፈረንስ ያካሄዱ ሲሆን በኮንፈረንሱም ደርግን ለመጣል በትጥቅ ተሳትፎ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለኮንፈረንሱ ሲባል የተፈጠሩ ድርጅቶች በድምሩ ወደ 27 የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ኮንፈረንሱን የጠራዉ፣ አጀንዳዉን የቀረጸዉ፣ የሽግግሩን ቻርተር ያዘጋጀዉ፣ የኮንፈረንሱን ተሳታፊዎች ማንነት የወሰነዉና ፓርቲዎች የሚኖራቸዉን መቀመጫ የደለደለው ደግሞ ትህነግ መራሹ ኢህአዴግ ብቻ ነበር፡፡

ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮንፈረንሱ የሚሳተፉበት ሁሉንም ያስማማ፣ ግልጽ መመዘኛ ማውጣት እና ይህንም በገለልተኛነት የሚያስፈጽም ዲሞክራሲያዊ ተቋም ማቋቋም ሲገባዉ የኮንፈረንሱን ተሳታፊዎች ለብቻዉ ወስኗል፡፡በመሆኑም ከትህነግ ፖለቲካዊ አቋም እና የህገ-መንግስት ምርጫ ጋር የማይስማሙ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድኖች እና ማህበረሰቦች በሂደቱ እንዳይሳተፉ ተደርጓል፡፡ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ አብዛኛዉ የህብረተሰብ ክፍልና ባለድርሻ አካላት ማለትም የገበሬዎች ማህበር፣የከተማ ነዋሪዎች ማህበር፣ የቀበሌ ማህበር፣ የሰራተኞች ማህበር፣ የመምህራን ማህበር፣ የሴቶች ማህበር፣ ወጣቶች ማህበር፣ የተማሪዎች፣ ሃኪሞች፣ የህግ ባለሙያዎች እና ሌሎች የንግድ እና የሙያ ማህበራት የሀገሪቱን እጣ ፈንታ በወሰነዉ ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊ አልነበሩም፡፡15

ከሁሉም በላይ በጣም የሚገርመው በሃገሪቱ ህዝብ ብዛት ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚጠራው የአማራ ህዝብ የሽግግሩን መንግስት ለማቋቋም በተደረገዉ በዚህ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ እንደ ዘውግ በአንድም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ቡድን ያልተወከለ መሆኑ ነው፡፡ በኮንፈረንሱ ለኢህአዴግ 34 መቀመጫ፣ ለኦነግ12 መቀመጫ እና ቀሪዉ 43 መቀመጫ ድግሞ ለሌሎች ብሄር ተኮር ድርጅቶች የተመደበ ሲሆን በወቅቱ አማራን ወክሎ መቀመጫ ያገኘ አንድም ፓርቲ አልነበረም፡፡ ሆኖም ይህ አማራ እንደ ዘውግ በጭራሽ ያልተወከለበት ኮንፈረንስ ከአማራ ህዝብ ፍላጎት አንፃር ምንም አይነት ጥልቅ፣ ሰፊ እና ሁሉን አቀፍ ውይይት ሳይደረግበት የሽግግር መንግስቱን ቻርተር በማጽደቅና የሽግግሩን መንግስት በማቋቋም ተጠናቋል፡፡

እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቁምነገር አለ፡፡የአማራው ህዝብ እንደ ዘውግ ያልተወከለበት ኮንፈረንስ የሽግግር መንግስት ቻርተር አፅድቆ የሽግግር መንግስት መስርቷል፡፡የሽግግር ቻርተሩ ደግሞ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገመንግስት ዋነኛ ይዘት የቀረፀ ዶክመንት ነው፡፡አማራው ባልተወከለበት መድረክ የተረቀቀውና(የተረቀቀው በዲማ ኮንፍረንስ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ፣በአቶ ሌንጮ ለታ እና በአቶ መለስ ዜናዊ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው) የፀደቀው የሽግግር መንግስት ቻርተር አሁን ህገ-መንግስት ለሆነው ዶክመንት ዋነኛ ምንጭ በመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ አማራው እንደ ዘውግ ያልተወከለበት ኮንፈረንስ የሃገራችንን ፖለቲካ እስከ ዛሬ ድረስ በእጅጉ የሚዘውሩ ጉልህ ውሳኔ ያሳለፈውን የሽግግር መንግስት ያቋቋመ ነው፡፡

ይህ አማራው እንደ ዘውግ በምንም መልክ ያልተወከለበት የሽግግር ምክር ቤት ያቋቋመው የሽግግር መንግስት ከ1983 ዓም ወዲህ ስልጣን የያዘውን አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ ስር የሚያስይዙ ትልልቅ ፖለቲካዊ ተግባራትን ከውኖ መሰረታዊ ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡የሽግግሩ መንግስት ከከወናቸው ዋነኛ የፖለቲካ ተግባራት መካከል የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋም፣ ክልላዊ የአካባቢ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግና የህገ-መንግስት አጽዳቂ ጉባኤ አንዲቋቋም በማድረግ ህገ-መንግስቱ እንዲዘጋጅ ማድረግ ነዉ፡፡በሌላ አባባል የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን የማቋቋም እና ረቂቁን ህገ-መንግስት አጽድቆ ህዝብ እንዲወያይበት የማድረግ የሚያክሉ ትልልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አንዲወስን ስልጣን የተሰጠው የሽግግሩ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማራው እንደዘውግ በጭራሽ ያልተወከለበት ነበር፡፡
በተጨማሪም የሽግግሩ መንግስቱ ቻርተር ህገ-መንግስቱ በሚዘጋጅበት ጊዜ ተግባራዊ መሆን ስላለባቸዉ እና ከግምት ዉስጥ መግባት ስለሚኖርባቸዉ አንኳር መርሆዎችም ሆነ የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አባላት እንዴት እንደሚመረጡ ምንም ያስቀመጠዉ ነገር አልነበረም፡፡16 ከዚህ ዉጭ በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገዉ ህገ-መንግስቱ በሚረቀቅበት ሆነ በሚፀድቅበት ጊዜ ጠቅላላ ክትትል የሚያደርግ ገለልተኛ አካል አልተቋቋመም ነበር፡፡

ምንም እንኳን በኮንፈረንሱ የህገ-መንግስት የህግ ምሁራን እና ባለሙያዎች እንዲከታተሉት የተጠቆመ ቢሆንም ኢህአዴግ ህገ-መንግስቱ የህግ ሰነድ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድ በመሆኑ የሚያስፈልገዉ ፖለቲካዊ ክትትትል እና ቁጥጥር እንጅ የህግ ክትትል እና ቁጥጥር አይደለም በማለት ሃሳቡን ዉድቅ አድርጓል፡፡17 ትህነግ መራሹ ኢህአዴግ በወቅቱ ራሱም እንዳመነው ህገ-መንግስቱ የፖለቲካ ሰነድ ነው፡፡የትህነግ መራሹ ኢህአዴግ የፖለቲካ ዘይቤ ደግሞ አማራውን ቅጣት የሚገባው ጨቋኝና ትምክህተኛ፣ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡በዚህ መንፈስ በተፃፈ ህገ-መንግስት በምትመራ ሃገር ውስጥ የአማራው ስቃይ ይቆማል ብሎ ማሰብ የህወሃት በአማራው ላይ ያላትን የጠላትነት አቋም መጋራት ነው፡፡

ወደ ሽግግር መንግስቱ አማራን አግላይ አካሄድ ስንመለስ አማራው ያልተወከለበት የሽግግሩ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 87 አጠቃላይ መቀመጫ የነበረው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ትህነግ እንደፈለገ ይዘውረው የነበረው ኢህአዴግ 32 መቀመጫ፣ኦነግ 12 መቀመጫ ሲኖረው ቀሪው 37 መቀመጫ በኮንፍረንሱ ለተሳተፉ ሌሎች የዘውግ ፓርቲዎች ተሰጥቷል፡፡ይህ ምክር ቤት 29 አባላት ያሉት ተጠሪነቱ ለሽግግር መንግስቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የሆነ የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት ስብስብ ሲታይ ሁሉም ባላቸዉ ሙያዊ ብቃት የተመረጡ ሳይሆን ለኢህአዴግ ባላቸዉ ታማኝነት የተመረጡ እንደሆኑ ግልጽ ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የረቂቅ ህገ-መንግስቱ አዘጋጆች ህገ-መንግስቱን በሚያረቁበት ጊዜ የትህነግን ዕቅድ፣ አላማ እና ፍላጎት እንዲያካቱ ግልጽ የሆነ ትእዛዝ እና መመሪያ እንደተሰጣቸው ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ አዘጋጆቹ ራሳቸው የተናገሩት ነው፡፡ሆኖም በኮሚሽኑ የተዘጋጀዉ ሰነድ በወቅቱ ሲቀርብበት የነበረዉ ትችት ስለ ህገ-መንግስታዊነት እና ስለዲሞክራሲ መርሆዎችና እሳቤዎች ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ ሰነዱ የኢህአዴግን ብሄር ተኮር ፖለሲና ፕሮግራም የሚያንፀብርቅ ብቻ ነበር የሚል ነዉ፡፡

በብዙ ሀገራት እንደሚደረገዉ ህገ-መንግስት ከመረቀቁና ለህዝባዊ ዉይይት ክፍት ከመደረጉ በፊት ለህዝቡ ሰፊ የሆነ የስነ-ዜጋ እና የንቃተ ህግ ትምህርት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዉ ህዝብ በዚህ ዙሪያ የሚኖረዉ ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ስለሚሆን ህዝቡ ስለህገ-መንግስቱ አስፈላጊነትና ወሳኝነት አዉቆ በንቃት ትርጉም ያለዉ ተሳትፎ ለማድረግ እንዲቻል ነዉ፡፡በመሆኑም ህዝቡ ህገ-መንግስቱ ስለሚወጣበት ሂደት፣በህገ መንግስቱ ስለሚካተቱ አንኳር ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ እንዲኖረዉ፣ ለሂደቱ ተገዥ እንዲሆንና በሂደቱም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረዉ መደረግ ነበረበት፡፡
ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ዉስጥ የሽግግሩ መንግስቱም ሆነ የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽንኑ የኤሌክትሮኒክስ እና ህትምት ሚዲያዎችን በመጠቀም ህዝቡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ የሚኖረዉ ህዝብ ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ምንም አይነት ሙከራ አላደረገም፡፡ በመሆኑም ህዝቡ የእራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል፤ ፖስት ዘ ፈርስት ፓስት በሚባለዉ የምርጫ ስርዓት፤ ብሄር ተኮር ወይስ መልክአ-ምድራዊ ፌደራሊዝም፤ ፓርላሚንታዊ ወይስ ፕሬዜዳንታዊ ስርዓት እና በሌሎች አንኳር ጉዳች ላይ ምንም አይነት ግንዛቤ ሳይኖረዉ ነዉ ዉይይት ለማድረግ የተሞከረዉ፡፡በተጨማሪም በወቅቱ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሂደቱ ራሳቸዉን በማግለላቸዉ እና የሂደቱን ተአማኒነት/ቅቡልነት ጥያቄ ዉስጥ በመክተታቸዉ ምክንያት ህገ-መንግሰቱን የማርቀቅም ሆነ የማጽደቅ ተግባር ህዝባዊ ተሳትፎ ሳይኖረዉ ኢህአዴግ በብቸኝነት የከወነዉ ተግባር እንደሆነ ነዉ፡፡

በመጨረሻም አርቃቂው ኮሚሽን ትርጉም ያለዉ ህዝባዊ ዉይይት ሳያደርግ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎቱን በሚገባ ሳይገልጽ ህገ-መንግስቱን አርቅቆ ለሽግግሩ መንግስት ምክር ቤት አስረክቧል፡፡ ሆኖም ግን ህገ- መንግስቱ ከተረቀቀ በኋላ ሙሉ ረቂቁ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስ ተደርጎ ህዝቡ በረቂቅ ህገ-መንግስቱ ዉይይት አላደረገም፡፡ የአርቃቂ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “በትልቁ ከሚፀፅተኝ እና ከሚቆጨኝ ነገር ዉስጥ” ብለዉ ከጠቀሱት ነገር መካከል አንዱ ረቂቅ ህገ-መንግስቱ ከተዘጋጀ በኃላ ለህዝቡ ቀርቦ በቂ ዉይይት አለመደረጉ እንደሆነ ደጋግመዉ ገልፀዋል፡፡

ይህን ሁሉ በሃገራችን ፖለቲካ ላይ ዘላቂነት ያለው ፖለቲካዊ ውሳኔ ያሳለፈው ኮንፍረንስ/ሽግግር መንግስት ውስጥ ያልተወከለው የአማራ ህዝብ በሽግግሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በሽግግር ቻርተሩ ዝግጅት ምንም አይነት ተሳትፎ አልነበረውምና የአማራ ህዝብ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ አንዳች ድርሻ ያልነበረው፣ሆን ተብሎ የተገለለ ህዝብ ነው፡፡በመሆኑም ህገ-መንግስቱን ጨምሮ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ወጥተው እስከ ዛሬ የሃገሪቱ ፖለቲካ ዋነኛ ማጠንጠኛ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የአማራ ህዝብ የመገዛት ግዴታ የለበትም፡፡ እነዚህ የአማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው ዋነኛ አማዳት እንዲቀየሩ መታገልም የአማራው ህዝብ ቀዳሚ ስራ ነው፡፡ “ለአንድ ክልል ብለን ህገ-መንግስት አንቀይርም” ለሚለው ወቅታዊው የአማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው ዝንባሌ ሁነኛ መልስ የሚሆነው ባልተሳተፈበት ህግ የመገዛት ግዴታ ያለበት ክልልም ሆነ ህዝብም እንደሌለ መታወቅ አለበት የሚል ነው፡፡
አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ለአንድ ክልል ብለን ህገመንግስት አንቀይርም ከሚለው ዘይቤው በተጨማሪ የአማራ ህዝብ በህገመንግስቱ አለመወከሉን ጠቅሶ ተገቢውን ህገ-መንግስታዊ ውክልና ለመጠየቅ እንዳይታገል በኮንፈረንሱ በኢህዴን በኩል ተወክለሃል የሚል ደካማ ክርክር ይዞ ይመጣል፡፡ ይህ ያልሆነ ምክንያት በማምጣት አማራውን ለማግለል በጥንቃቄ የተሰራውን የድህረ 1983ዓም ስርዓት ለማስቀጠል የሚደረግ መሟሟት ነው፡፡ እንጅ ከስሙ ጀምሮ “ኢህዴን” በሚል ሃገራዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተመሰረተ ፓርቲ “የሃገሪቱን ህዝብ የማውቀው እንደ ዘውግ ብቻ ነው” በሚል መሰረታዊ እሳቤ ላይ ቆሞ በተዘጋጀ ህገመንግስት ውስጥ ኢህዴን የሚባል ህብረብራዊ ፓርቲ የአማራን ህዝብን መወከል እንደማይችል ማወቅ ከብዶ አይደለም፡፡

የኢህዴን አፈጣጠርና ማንነት ከአማራ ህዝብ ጋር ያለው ቁርኝት ይመርመር ከተባለ ደግሞ በህገመንግስቱ አማራ በኢህዴን ተወክሎ ነበር የሚለው ክርክር አማራውን ማግለል ትክክል ነው የሚለውን የአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካን ዋኛነኛ አስኳል ያረገዘ አደገኛ እሳቤ እንደሆነ ግልፅ ይሆናል፡፡ኢህዴን አማርኛ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች የተሞላ፤ የህወሃትን አማራ ጠል አላማ ለማስፈጸም የተፈጠረና ፈጽሞ የአማራን ህዝብ የማይወክል እንደ ነበር የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም አማራ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በግለሰብ ደረጃ በኮንፈረንሱ ከመሳተፋቸው በቀር በሽግግሩ መንግስትም ሆነ በሽግግሩ መንግስት አማካኝነት ህገ-መንግሰቱን ለማርቀቅ እና ለማጽደቅ በተፈጠሩት አደረጃጀቶች ውስጥ የአማራ ህዝብ እንደዘውግ ያልተወከለበት እና የዚህ ህዝብ ይሁንታ የሌለበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በወቅቱ የአማራ ህዝብ እየደረሰበት የሚገኘዉን ጥቃት ለመመከት በማለም የተቋቋመዉ የአማራ ህዝብ ተወካይ መአህድ እንኳን የተቋቋመዉ ኮንፈረንሱ ከተካሄደ በኋላ ነበር፡፡ በመሆኑም የአማራ ህዝብ የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ በወሰነዉ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ እንዲሳተፍ ባለመደረጉ ምክንያት ፍላጎቱንና ጥቅሙን ለማስከበር አልቻለም፡፡ በተጨማሪም ኢህአዴግ በአማራ በኩል በሚጠላት በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ላይ ይዞት ለመጣዉ አፍራሽ ራዕይና አደገኛ ሴራ በተደራጀ መልኩ ተቃዉሞዉን የሚያሰማበት እድል አልነበረዉም፡፡ በዚያን ጊዜ የአማራ ህዝብ ሀገሪቱን እንደገና በብሄር የማደራጀትን የህወሃትን አካሄድ አምርሮ የሚቃዎም እንደነበር ለማንም ግልጽ ሲሆን የህወሃትን ሀገር የማፍረስ ራዕይ አምርሮ በመቃወሙ እና በመታገሉ ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል፡፡
5.3.2 በሃገራዊ ፖለቲካው ከስልጣን ድርሻ መገፋት
በአማራ ክልል የሚኖሩም ሆኑ በተለያየ ምክንያት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ዘውግ አባላት በጋራ የሚያስተናግዱት ተግዳሮት ስልጣን ላይ ያለው የዘውግ ፖለቲካ በየትም ቦታ ያለን የአማራ ዘውግ አባል ባለጋራ አድርጎ የመመልከቱ ዝንባሌ ነው፡፡ይህ አስተሳሰብ በየትም ቦታ ያለ አማራ የዘውዳዊ ስርዓትን መልሶ ለማምጣት ይሰራል ብሎ ያስባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአማራ ዘውግ የተገኘ ሰው ወደ ሃገራዊ ስልጣኑ ዋነኛ መንበር ከመጣ የድሮው ስርዓት ተመልሶ መጣ ማለት ነው የሚል ሰፊ እምነት አለ፡፡በመሆኑም በሃገሪቱ የአማራ ዘውግ አባላት የፌደራሉ መንግስት ዋነኛ ስልጣን ላይ መምጣት እንደሌባቸው ባልተፃፈ ህግ ስምምነት ላይ የተደረሰ እስከሚመስል ድረስ መግባባት አለ፡፡
የዚህን አስተሳሰብ ሰፊ ህልውና አማሮቹ ራሳቸው ስለሚረዱት በብሄራዊው ፖለቲካ መንበረ ስልጣን ላይ ሁለተኛ መሆንንን እንደ ዕጣ ክፍላው አድርገው ወስደዋል፡፡በሌላ አባባል የአማራ ዘውግ አባላት በዘውጋቸው ምክንያት በሃገራቸው የፖለቲካ ስልጣን ላይ የመሳተፋቸው ዕድል ተገድቧል ማለት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ለሃገሪቱ ዘውጎች ሁሉ የተሰጠውን የፖለቲካ ተሳትፎ የማድረግ መብት የሚፃረር ነው፡፡የሚብሰው ችግር ደግሞ አማራው በሌሎች ብሄረሰቦች ዘንድ የጨቋኝነት መልክ የተሰጠው ዘውግ ስለሆነ ከስልጣን ተገልሎ በቀጠለ ቁጥር ስልጣን ጠቅልለው በያዙ ዘውጎች የበቀል በትር ሊያርፍበት የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ከትግራይ ዘውግ የተነሱት የትህነግ መራሹ መንግስት ሹማምንት እና አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የኦሮሞ ብሄር ሹማምንት በአማራው ህዝብ ላይ ያደረጉትን/የሚያደርጉትን ማየት በቂ ነው፡፡

  1. በድህረ-ህወሃት የአማራ ህዝብ የገጠሙት ፈተናዎች
    ትህነግ ከተፀነሰበት ከ1968 ዓም ጀምሮ በግልፅ የአማራ ዘውግን በጨቋኝነት ፈርጆ፣ትግሉም ከአማራ ህዝብ ጋር እንደሆነ አስቀምጦ የተንቀሳቀሰ አካል ነው፡፡የኋላ ኋላ ትግል የማደርገው “ከአማራ ገዥ መደብ” ጋር ነው ቢልም በስልጣን ዘመኑ የበቀል በትሩን አንስቶ ሲገርፈው፣ሲያሳድደው፣ ሲያፈናቅለው ፣ሲገድልና ሲያስገድለው የነበረው የአማራውን አርሶ አደር ነው፡፡ ከትህነግ ከስልጣን መነሳት በኋላ የመጣው በዋናነት የኦሮሞ ልሂቃን የሚመሩት ስርዓት ደግሞ ወደ ስልጣን እንደመጣ ሰሞን በአፉ ትህነግ አማራውን ማሳደዱን፣በሌሎች ዘውጎች እንዲጠላ ማድረጉን የሚነቅፍ ሲሆን በሆዱ ያለውን ለማወቅ ግን ረዥም ጊዜን የወሰደ ነበር፡፡ሆኖም ይህ ስርዓት እንደ ትህነግ ማኒፌስቶ ፅፎ “የአማራው ዘውግ ባለጋራየ ነው” አይበል እንጅ በተግባር የሚሰራው ሲመረመር ግን በአማራ ጠል ፖለቲካዊ ስነልቦና ከትህነግ ጋር አንድና ያው፣ ፈለጉንም ተከታይ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም፡፡አሁን ሃገሪቱን የሚመራው ቡድን ከትህነግ አንድ ስለመሆኑ በህወሃት ዘመን አማራው ዘውግ ተኮር ጥቃቶችን ባስተናገደባቸው ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልል አሁንም ጥቃቶቹ እንደ አዲስ መቀጠላቸው ነው፡፡
    በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ እየደረሰበት ያለውን ዘውግ ተኮር አሰቃቂ የዘር ማፅዳትና ዘር ማጥፋት ወንጀሎችን በማህበራዊ ድረገፆች ከማዘዋወር ባለፈ በመደበኛ ሁኔታ በፓርላማና በመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን መዘገብ፣ማውገዝ፣መነጋገሪያ ማድረግና ተጠያቂ አካል እንዲኖር የማድረጉ ስራ አልተሞከረም፡፡ጭራሽ ስለዚህ ሽፍንፍን ዘውግ ተኮር ጭፍጨፋ ማውራት ለውጥ ማደናቀፍ፣ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት፣ዘረኝነት የሚሉ የተገላቢጦሽ የሆኑ ፍረጃዎችን የሚያመጣ ሆኗል፡፡ በመንግስት ስር ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነገሩን ለማጣራት አንዳንድ ሙከራዎችን ቢያደርግም ችግሩን በሆነው ልክ ያላቀረበና ቀጣይነቱን ማስቆም ያልቻለ ነው፡፡
    በድህረ-ትህነግ ዘመን ለአማራው ጭፍጨፋ ትኩረት እንዳይሰጠው ያደረገው ዋናው ምክንያት የለውጥ አመራር ነኝ የሚለው ኦህዴድ/ብልፅግና መራሹ መንግስት የሚያወራው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት፣ህብረ-ብሄራዊ አንድነትና መደመር የሚለው ፍልስፍናው በተግባር ከሚሰራው እጅግ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ የመንግስት ባለ ሁለት መልክ ተፈጥሮ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈፅመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም በህዝቡ ዘንድ ሊኖር የሚገባውን የጠያቂነት መንገስ ገድሎታል፡፡ ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በሰፊው ህዝብ ዘንድ ቢያንስ ሰብአዊ መብት እንዳይጣስ የመጠየቅ፣የማስገደድ የአንድነት መንፈስ ነበረ፡፡ አሁን ግን የመንግስት እስስታዊ ባህሪ በሚያስተዳድረው ሃገር ግዛት ስር የሚደረግን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም የመንግስት ትንሹ ግዴታ መሆኑንና ይህን ማስጠበቅ ያልቻለ መንግስት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት በህዝብ ዘንድ መግባባት እንዳይኖር ከልክሏል፡፡በመሆኑም በተለይ በቤኒሻንጉል እና በወለጋ የአማራ ህዝብ በየዕለቱ የሚጎነጨውን መራራ የግፍ ፅዋ በስሜት እንኳን የሚረዳው ጠፍቷል፡፡
    በመሆኑም በቤኒሻንጉል እና በወለጋ የሚፈሰው የንፁሃን ደም ከሚከረፋው ይልቅ የእንጦጦ ፓርክ መገንባት የሚያስፈነድቀው በርክቷል፡፡የመንግስት ቀዳሚው ግዴታ ህዝብን መጠበቅ እንጅ ማዝናናት እንዳልሆነ ማወቅ ከባድ ባይሆንም እንደ ከባድ ነገር ብዙ አከራክሯል፤በሟቾቹ አማሮች ጫማ መቆም ከባድ ነገር ሆኗል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት እስስታዊ ባህሪ ምክንያት በርካታ ለሰብዓዊ መብት መከበር ሲሞግቱ የነበሩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ጭፍጨፋውን ማስቆም ላልፈለገው/ላልቻለው መንግስት ወግነው በተጨፍጫፊው የአማራ ህዝብ ላይ ፊት እንዲያዞሩ ሆኗል፡፡ስለ ጭፍጨፋው ከተነሳም የሚወቀሰው ቸልተኛው መንግስት ሳይሆን ጭፍጨፋውን የሚቃወሙ ሰላላ ድምፆች ናቸው፡፡
    ከሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ ከትህነግ መወገድ በኋላ በተለይ በክልሉ የሚኖረው የአማራ ህዝብ የገጠመው ፈተና በክልሉ የሚደረግ ማንኛውም ነገር በፌደራል መንግስቱ በአንክሮና በጥርጣሬ የሚታይ መሆኑ ነው፡፡ለኦህዴድ መራሹ የፌደራል መንግስት ሱዳን ኢትዮጵያን ለመውረር፣ትህነግ ሃገር ለማጥፋት ከሚያደርገው ግዙፍ ዝግጅት ይልቅ የአማራ ህዝብ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገው የቢቸግር ጥረት ያሳስበዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ለሌሎች ክልሎች የተፈቀደው የክልሎችን ወታደራዊ ሃይል በተደራጀ ልዩ ሃይል የማጠናከር ተግባር ለአማራ ክልል ሲሆን የበጀትን ጉዳይ እንደ ምክንያት በማንሳት የከለከለ መሆኑ ነው፡፡
    ይህ ተግዳሮት ሌሎች ክልሎች በበቂ ሁኔታ ልዩ ሃይል ሲያሰጥኑ፣በኦሮሚያ ክልል እንደውም ልዩ ሃይል ቀርቶ እንደ ኦነግ ሸኔ አይነት አማፂ ቡድኖች እንኳን በነፃነት ሰፊ የወታደር ስልጠና ሲያደርጉ፣በትግራይ ክልል መከላከያን የሚበልጥ የውትድርና ስልጠና ሲደረግ የአማራ ክልል ተመሳሳዩን ለማድረግ ሲሞክር በግልፅም ሆነ በስውር እንዲከለከል አድርጓል፡፡የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት አማራ ክልልን አጥር የሌለው ቤት አድርጎታ፤የአማራን ህዝብም ሲዘጋጅ የኖረን አደገኛ ጠላት ቁጭ ብሎ ጠብቆ መሞትን የመሰለ አማራው አይቶት የማያውቀው ውርደት ውስጥ እንዲገባ ግድ ብሎታል፡፡
    የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል የሚደረገውን እንቅስቃሴ በአንክሮ፣በጥርጣሬ የማየቱ አዝማሚያ የመነጨው ክልሉ ጠንክሮ ከወጣ አማራውን በማጥቃቱ ድል አድራጊነቱን ለሚያረጋግጠው የዘውግ ፖለቲካ ተግዳሮት ስለሚሆን ነው፡፡ በመሆኑም በሌሎች ክልሎች የአማራውን ሞት ማስቆም ያልቻለው ጭራሽም አላወቅኩም የሚለው የፌደራል መንግስት የአማራ ክልል የፀጥታ ሃይሎች አማራው ወደ ሚጨፈጨፍበት ክልል ገብተው የህዝባቸውን ህይወት ለመታደግ የሚያቀርቡትን ጥያቄ መቀበል አይፈልግም፡፡
    የሰው ልጆችን በህይወት የመኖር መብት ማስጠበቅ የማንኛውም ህጋዊ አካል ሃላፊነት ስለሆነ የአማራ ክልል መንግስት አንዳንድ ባለስልጣናት ይህንኑ የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት ለማስጠበቅ የሚያደርጉት አነስተኛ እንቅስቃሴ የፌደራል መንግስት በአንክሮ አይቶ ወዲያውኑ የማስቆም እርምጃ ወስዷል፡፡የአማራ ህዝብ በተለያዩ ክልሎች ለተከታታይ ሶስት አመት አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሲደረግበት ወንጀሉን ለማስቆም ግን ተመሳሳዩን ፈጣን እርምጃ ሲወስድ አልታየም፡፡ በአማራ ህዝብ ላይ ዘውግ ተኮር ጭፍጨፋ የሚያደርጉ ክልሎች ባለስልጣናትን ተጠያቂ አላደረገም፡፡የአማራ ህዝብ የሚደርስበት ዘውግ ተኮር ጭፍጨፋ መቆም አለበት በሚል የሚንቀሳቀሱ በጣም ጥቂት የአማራ ክልል ባለስልጣናትን በአንክሮ ተከታትሎ የማሳደዱን የፌደራል መንግስቱን አቋም ሁሉም የዘውግ ብሄርተኞች በፕሮፖጋንዳ የሚደግፉት ነው፡፡
    የአማራ ህዝብ በጉልበት በህወሃት እንደ ተወሰዱበት አምኖ እንዲመለስላቸው የሚታገልባቸውን ራያ፣ወልቃይት፣ሁመራን፣መተከልን፣ደራን የመሳሰሉ መሬቶችን አስመልክቶ የድህረ-ትህነግ መንግስት አቋም አይታወቅም፡፡ይህን አስመልክቶ ጠ/ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ “የወልቃይት ጥያቄ የመልካም አስተዳደር እንጅ የማንነት አይደለም” ሲሉ አሁን ያለው መንግስት እነዚህን ቦታዎች በተመለከተ ከአማራ ህዝብ ይልቅ ወደ ትህነግ የተጠጋ አቋም እንዳለው ፍንጭ ከመስጠቱ ባለፈ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ትህነግ እና ጠ/ሚው የወጡበት የኦህዴድ ብልፅግና “አማራው ተስፋፊና ጨቋኝ ነው” የሚሉ የአንድ ጎራ ሰልፈኞች በመሆናቸው የአማራ ህዝብ በእነዚህ ታሪካዊ ግዛቶቹ ላየ የሚያነሳውን ጥያቄ አስመልክቶ ተመሳሳይ አቋም እንደሚያራምዱ ማወቅ አይከብድም፡፡
    በአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ አስተሳሰብ አማራው የሚያነሳቸው በሃይል የተነጠቁበት ግዛቶች የማስመለስና የማንነት ጥያቄዎች የተስፋፊነት እብሪት ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን ሌሎች ዘውጎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ግን የብሄረሰቦች የነፃነት ትግል ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡በድህረ-ትህነግ ዘመን የአማራ ህዝብ የግዛት ወሰንን በተመለከተ የፌደራል መንግስቱ ቸልተኝት የሚያሳየው ትህነግ በሃይል በወሰዳቸው መሬቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ግዛት ያለውን የአልፋሽቃ አካባቢ ላይ ጭምር ነው፡፡እነዚህን ግዛቶች አስመልክቶ መንግስት በግልፅ “ለመሬቶቹ ስንል አንዋጋም” እስከማለት ደርሷል፡፡ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በድህረ ትህነግ ዘመን ወደ ስልጣን የመጣው አስተዳደር ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝትን በአፉ የዘውግ ብሄርተኝነትን በተግባሩ እያስኬደ ለመቀጠል የሚያስችለው የማደናገር እና የማሳመን (Confuse and Convince) የተባለ የፖለቲካ ቀመርን ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን አጥብቆ የሚወደው የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ሽፋን ተጠቅልሎ የመጣበትን የህልውና አደጋ እንዳይገነዘብ አድርጎታል፡፡በተጨማሪም በድህረ ትህነግ ስልጣን ላይ የወጣው ኦህዴድ መራሹ ሃይል እገነባዋለሁ የሚለው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት ካለም ዋነኛ መልኩ አማራ-ጠልነት እንደሆነ መረዳቱ ኢትዮጵያ ሲሉት ብቻ ለሚበቃው ለአማራው ልሂቅ እጅግ ከብዶ ይገኛል፡፡የዚህ ዋናው ምክንያቱ የአማራ ህዝብ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን አንግቤያለሁ የሚል አካልን በቀላሉ የማመን ዝንባሌ ስላለው ነው፡፡
    ትህነግን የተካው ስርዓትም ይህን ጠንቅቆ ስለሚረዳ የአማራን ህዝብ የሚወደውን የኢትዮጵያ ስም በመጥራት በህልውናው ላይ ያንዣበበውን አደጋ ጭምር እስከማይረዳ ድረስ አደናግሮ በአማራው ላይ የከረመውን ግልፅ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ለመታገል ሲል እንኳን አማራው በአንድ ላይ እንዳይቆም አድርጎታል፡፡በመሆኑም የዘውግ አቻዎቻቸው ሶስት አመት ሙሉ በግፍ ሲጨፈጨፉ የሚያዩ የሚሰሙ አማሮች ጭፍጨፋውን በማድረግም ሆነ ባለመከላከል የሚያሳልጠውን ኦህዴድ መር መንግስት ከኦሮሞ ሊሂቃን በበለጠ ሲደግፉ ይስተዋላል፡፡
    ይህ የአማራ ልሂቃን በአስገራሚ ሁኔታ ስልጣን ላይ ላለው መንግስት የሚያሳዩት ጠንካራ ድጋፍ አማራው ሲጨፈጨፍ ማስቆም የማይፈልገውን፣የአማራውን እንግልት እንደ ትግል መልስ የሚቆጥረውን፣አማራ-ጠል ኢትዮጵያን ለመገንባት ጎንበስ ቀና የሚለውን ኦህዴድ/ብልፅግና መር ስርዓት “የአማራ ስርዓት” እስከማስባል ደርሷል፡፡ይህ በሌላ ክልል በተለይ በኦሮሚያ ክልል “ቄሮ ታግሎ ባመጣው ድል የአማራ ስርዓት ተመሰረተ” በማለት አማራው ሌላ ጭፍጨፋ እንዲካሄድበት ያደረገ አደገኛ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
  2. በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲዎች ማዕቀፍ ውስጥ የአማራን ህዝብ ጥያቄ መመለስ ያልተቻለው ለምንድን ነው?
    ከግማሽ ምዕተ አመት ወዲህ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአጠቃላይ ከ1983 ዓም ወዲህ ባለው ዘመን ደግሞ በተለይ የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብቱን ጭምር አደጋ ላይ የጣለ ትርክት ተኮር አደጋ እንዳዣበበትና በተግባርም እጅግ አሰቃቂ የመብት ጥሰቶችን እንዳስተናገደ ከላይ በመጠኑ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ይህ እጅግ አደገኛ ሁኔታ በአማራ ህዝብ ላይ ደርሶና ለወደፊትም በአስፈሪ ሁኔታ አንዣቦበት እያለም የአማራ ህዝብ አደጋውን ለማስቀረት በዘውጉ ተደራጅቶ መታገልን እንደ መፍትሄ ወስዶ ለመንቀሳቀስ አልቸኮለም፡፡ይልቅስ ችግሩን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ነን በሚሉ ፓርቲዎች ጥላ ስር ሆኖ ለመፍታት ሞክሯል፡፡እነዚህ ፓርቲዎች ደግሞ ችግሩን በሚመጥን መንገድ እየሰሩ እንዳልሆነ በተግባር እያየም፣ከየሃገር ዳርቻ የመሳደድ መራራ ፅዋን መጎንጨቱም ጋብ ሳይልለትም ቢሆን ለረዥም ዘመናት በእነዚህ ፓርቲዎች ስር ሲታገል ቆይቷል፡፡
    ሆኖም በኢትጵያዊነት ማዕቀፍ በተደራጁ ፓርቲዎች ስር ሆኖ አንገብጋቢውንና እጅግ አጣዳፊ መልስ ሊሰጠው የሚበገባውን የአማራን ህዝብ የህልውና ጥያቄ መመለስ እንደማይቻል የሰላሳ አመት ተሞክሯችን ግልፅ አድርጓል፡፡በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የትግል ማዕቀፍ በተደራጁ ፓርቲዎች ጥላ ስር ታቅፎ በመታገል የአማራ ህዝብ በዘውጉ ምክንያት የሚደርስበትን የህልውና ስጋት ጨምሮ ፈርጀ ብዙ በደል ማስቆም የማይቻልባቸውን ምክንያቶች መመርመር ያስፈልጋል፡፡
    ከነዚህ ምክንያቶች ዋነኛው የሃገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ጎራ የሚመራው አማራውን በጨቋኝነት ፈርጆ ይንቀሳቀስ የነበረው የ1960ዎቹ ዘመን ቅሪት ልሂቃን በመሆኑ ነው፡፡እዚህ ልሂቃን የዘመናችንን ፖለቲካ በመዘወሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩና አሁንም የሚጫወቱ ናቸው፡፡ልሂቃኑ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የሚታገል ፓርቲ መሰረትን ቢሉም ፖለቲካን የጀመሩበትን የአማራን ህዝብ የሃገሪቱ ፖለቲካ መርገም ሁሉ ተጠያቂ የማድረግ አባዜያቸው አብሯቸው አለ፡፡በመሆኑም በአማራ ጠልነታቸው በግልፅ አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካን እናራምዳለን ብለው ካወጁት የዘውግ ፖለቲከኞች የሚተናነስ አይደለም፡፡
    ሆኖም ይህን በግልፅ እንዳይናገሩ የፓርቲዎቻቸው ዋነኛ አባላት ደጋፊዎችና የበጀት ምንጮች ኢትዮጵያን ከሚወደው የአማራ ዘውግ የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው አካሄዱ ሩቅ አያስኬድም፡፡ከዚህ አደገኛ ስህተት ለመዳን ታዲያ አማራ ጠል አቋማቸውን በተለያየ የፓርቲ ደምባደምብ እና ህግጋት ግልፅ ባልሆነ አሳሳች ሁኔታ አስቀምጠው እጅግ በረቀቀ መንገድ ያስኬዱታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋነኛው ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ የሚናገር ሰው ለፓርቲዎቻቸው አመራርነት ቅድሚያ እንደሚሰጠው የሚደነግጉት ቅን መሰል አማራን ከዋናው የአመራርነት ድርሻ የመግፋት የዘውግ ፖለቲካ ጎራው ቅጅ ነው፡፡
    ሌላው ምክንያት የአማራ ህዝብ የገጠመውን አንገብጋቢ የህልውና አደጋ በተመለከተ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማዕቀፍ በተደራጁ ፓርቲዎች ስር ባሉ ልሂቃን ዘንድ አንድ ወጥ መረዳት የለሌ መሆኑ ነው፡፡በኢትዮጵያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ከሚታገሉ ልሂቃን ውስጥ በግልፅም ሆነ በስውር የአማራ ህዝብን ጨቋኝ አድርጎ የሚያስበውን ትርክት የሚቀበሉ ልሂቃን አሉ፡፡ በመሆኑም በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ የተዛባ ታሪክን ማስተካከያ አድርገው የሚወስዱ አሉና የችግሩ ክብደት፣አሰቃቂነት፣አስቸኳይነት ለሁሉም እኩል ትርጉም አይሰጥም፡፡ስለዚህ በአማራው ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ለማስቆም መስራት ቀርቶ ጥቃቱ የሚፈፀመው ዘውጋቸው ተለይቶ በአማሮች ላይ መሆኑን በስም ጠርቶ ችግሩን ለመግለፅ እንኳን በፓርቲው ልሂቃን ዘንድ መስማማት ላይ አይደረስም፡፡ስለዚህ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩ የሚጠራበትን ስም በመምረጥ ጊዜ/ጉልበት ያልቃል፤ በስሙ ላልተጠራ ችግር መፍትሄ ማምጣት ደግሞ አይታሰብም፡፡
    ሶስተኛው ችግር የአማራ ልሂቃን የአማራን ህዝብ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማዕቀፍን መከተልን መርጠው በመኖራቸው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ በሚታገሉ ፓርቲዎች ውስጥ አማሮች በርካታ ቁጥር አላቸው፡፡በመሆኑም ፓርቲዎቹ “የአማራ/የነፍጠኛ ፓርቲዎች” የሚል በዘውግ ፖለቲከኞች የተሰጠ መደበኛ ያልሆነ ስም አላቸው፡፡ይህን ስም ለመሸሽ ደግሞ የአማራ ልሂቃን በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ በብዙ ቁጥር ይኑሩ እንጅ የአመራርነት እርከን ላይ ቁጥራቸውን በሚመጥን መንገድ እንዲቀመጡ አይደረግም፡፡በመሆኑም የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ የሚባሉ፣ በዘውግ ብሄርተኞች ዘንድ ደግሞ የአማራ ፓርቲ በመባል የሚታወቁ፣በርካታ አማራ አባላትን የያዙ ፓርቲዎች አማራ ባልሆኑ አመራሮች እንዲመሩ ይደረጋል፡፡አማራ ያልሆኑ አመራሮች ደግሞ የአማራ ህዝብን በተመለከተ ያላቸው አተያይ ከዘውግ ብሄርተኞች ብያኔ ብዙም ያልራቀ እንደሆነ ጠቋሚ ተጨባጭ መረጃዎች አሉ፡፡
    አማራ የሆኑ አመራሮች ቢመሯቸው እንኳን እነዚህ ሰዎች የሚታየውን የአማራ ህዝብ ችግር አጉልተው ካሳዩ የአማራ ዘውገኛ የሚል ልጥፍ ይሰጣቸዋል፡፡በኢትዮጵያዊ ብሄርኝነት ፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉ አማሮችም በበኩላቸው ዘውገኛ እንዳልሆኑ ያስመሰከሩ የሚመስላቸው በወጡበት የአማራ ህዝብ መከራ ላይ ምንም ስሜት ባለማሳየት ወይ ጭልጥ አድርጎ ችግሩን በመካድ ነው፡፡ይህን ማድረግ ያልቻሉ በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ከፓርቲዎቹ እየወጡ አዲስ የአማራ ብሄርተኝነት ፓርቲዎችን ለማቋቋም ተገደዋል፡፡እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲዎች ብቸኛ የመዳን መንገድ አድርጎ ያሰባቸውን የአማራ ህዝብ ከመከራው ሊያስጥሉት ቀርቶ ችግሩን በተገቢው መንገድ ሰምተው፣ተረድተውና ተርጉመው ሊያስተጋቡለትና ማታገያ አጀንዳ ሊያደርጉለት አልቻሉም፡፡
    ባለፉት ሰላሳ አመታት በተሰበከው የመነጣጠልና የመጠራጠር ፖለቲካ ሳቢያ በሃገሪቱ የሚኖሩ ዘውጎች አንዱ የአንዱን ችግር ለመረዳት የማይፈቅድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ላይ የአማራ ህዝብ በበዳይነት ሲከሰስ የኖረ በመሆኑ ችግሩ በሌሎች ህዝቦች ዘንድ የሚታይበት መንገድ ችግሩን የሚመጥን ሆኖ አልተገኘም፡፡ በተጨማሪም ከሰላሳ አመት ወዲህ የተመሰረተው ስርዓት የሃገሪቱን ህዝቦች በተለይ በዘውጋቸው ለይቶ ለሚያደርሰው ጉዳት ያለው ተጋላጭነት እኩል አይደለም፡፡የአማራ ህዝብ ተጋላጭነት ደግሞ በብዙ እጥፍ የበለጠ ስለሆነ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ታግሎ በዘውግ ማንነቱ ላይ ተመስርቶ በአማራ ህዝብ ላይ የመጣውን ግዙፍ መከራ ማስቆም የማይቻል ነገር ነው፡፡በመሆኑም አማራው እንደ ዘውግ የመጣበትን ችግር ለመፍታት እንደ በዘውጉ መደራጀት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ሆኗል፡፡በመሆኑም የአማራ ብሄርተኝነት እንደቀድሞው ሊያስቆሙት በማይቻል ሁኔታ እያደገ መጥቷል፡፡
    8.የአማራ ንቅናቄ አስፈላጊነት እና ተፈጥሮ
    የዘውግ ፖለቲካው በሃገራችን ከመጧጧፉ በፊት ባለው ዘመን “አማራ” ለሚለው ቃል በሃገር ውስጥ ሃገርኛው አገላለፅ(Indiginous narrative) የሚሰጠው ትርጉም በውጭው ዓለም ምሁራዊ ክበብ (Foreign scholarship) ከሚሰጠው ትርጉም እጅግ የተለየ ነው ፡፡ቆየት ባለው ሃገርኛ አገላለፅ አማራ የሚለው የማንነት አገላለፅ ከተለያዩ የባህል፣ የቋንቋ ፣ የስነልቦና፣የሃይማኖት ማንነታዊ መለያዎች ጋር በተገናኘ ሲገለፅ የነበረ ህውና የነበረው ሲሆን ፡፡ከሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ግን “አማራ” የሚለው ቃል በውጭ ፀሃፍት ዘንድ በሰፊው አገልግሎት ላይ ይውል ጀመር፡፡ ይህ የውጭ ፀሃፍት አገላለፅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት የመያዝ ምኞት፣ሙከራ እና ክሽፈት ጋር ግንኙነት ያለው ነው፡፡18
    “አማራ” የሚለው ቃል በውጭ ፀሃፍት አገልግሎት ላይ ሲውል ይዞት የመጣው ትርጉም ግን በሃገርቤት በሃገርኛ ቃሉ ከያዘው ትርጉም በእጅጉ በተለየ፣ በአመዛኙ ማህበራዊ ዳርዊኒዝምን በተከተለ መንገድ ነው፡፡ይህ የውጭ መዛግብት ኢትዮጵያን በጉልበትና በንጥቂያ በአማራ ገዥዎች የተመሰረተች፣በአማራ ባህል ተፅዕኖ ስር የወደቀች ኋላ ቀር ሃገር አድርጎ የሚያቅርብ ነው፡፡እንዲህ ያለው የውጭ ምሁራን አገላለፅ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያለት የቅኝ አገዛዝ አጀንዳና ፍላጎት ኢትዮጵያን ለማሰልጠን፣ከአማራ ባህል ተፅዕኖ ነፃ ለማውጣት ሲባል የተደረገ ነው የሚለውን ፕሮፖጋንዳ የሚደግፍና መንገዱን ቀና የሚያደርግ ነበር፡፡
    የእነዚህ ምሁራን ድርሳናት ጣሊያን አማራ የሚለውን ገዥ ቡድን እና ኦርቶዶክስ ክርስትናን ኢትዮጵያን ኋላ ያስቀሩ ጨቋኞች አድጎ የሚያቀርብበትን ፕሮፖጋንዳውን በምሁራዊው ዓለም በኩል ድጋፍ የሚሰጡ ነበሩ፡፡19ይህ ይበልጥ ግልፅና ተጨባጭ እንዲሆን ግራዚያኒ በአንድ ወቅት ያወጣውን አዋጅ ይዘት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡ አዋጁ እንዲህ ይላል “extermination of all Amhar Chiefs great and small must be speeded up for if this is not done we can only except trouble”20 የአዋጁ ተዛማጅ ትርጉም “የአማራ ልሂቃንን ትንሹንም ትልቁንም መፍጀቱ በፍጥነት መከናወን ያለበት ነገር ነው ይህ ካልተደረገ የሚጠብቀን ነውጥ ነው”፡፡
    ከዚህ አዋጅ የምንረዳው ትልቅ ቁምነገር ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት፣ለማዳከምና ለመበታተን ቀድሞ አማራውን መፍጀትና ማዳከም በጣሊያን ተጀምሮ ለሃገራችን የዘውግ ብሄርተኞች የተላለፈ ቀመር መሆኑን ነው፡፡ይህ ነገር የሚያስረዳን ሌላ ትልቅ ቁምነገር የአማራ ህልውና በእጅጉ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተሳሰረ ታሪካዊ መሰረት ያለው መሆኑ ነው፡፡የአማራ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አጋዥና አዳኝ ይሆናል እንጅ የሚጋጭ ነገር እንደሌለው የሚከራከረው የአማራ ንቅናቄ ወቅታዊ እሳቤ ተጨባጭ ታሪካዊ ድጋፍ ያለው ሙግት ነው፡፡በመሆኑም ይህ የግራዚያኒ አዋጅ የያዘው ቁምነገር በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የአማራ ልህቃን ዘንድ አማራውን ከመሳደድ ለማስቆም ሲባል በግድ የተገባበትን የአማራ ንቅናቄ መደገፍ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን መክዳት ወይም ለድርድር ማቅረብ ተደርጎ የሚወሰደውን ነገር የአላዋቂ ስጋት ያደርገዋል፡፡
    የአማራ ንቅናቄን መገንባት፣መደገፍና ማበረታታት ኢትዮጵያን መክዳት ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ ታሪካዊ ዳራዎችን አይቶ አካሄድን ማስተካከል ለአማራ ህዝብ መከራ መቆምም ሆነ ለኢትዮጵያ ህልውና ቀጣይነት ዋነኛውን ሚና የሚጫወት አካሄድ ነው፡፡ይህን ለማጤን ደግሞ የአማራ ንቅናቄ እንዲፈጠር ያደረጉ አስገዳጅ ሁኔታዎችን፣አፍጥጠው የመጡ አደጋዎችና የአማራ ንቅናቄን ተፈጥሮ መርምሮ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡የአማራ ብሄርተኝነት እንዲፈጠር ያደረጉት ምክንያቶች ደግሞ የብሄርተኝቱን ተፈጥሮ በእጅጉ ይወስናሉ፡፡
    የአማራ ህዝብ ለሰላሳ አመት የቆየበት ዘውግ ተኮር ጥቃትና አሁንም በአስፈሪ ሁኔታ ያንዣበበትን ተጨባጭ አደጋ ምክንያት አድርጎ ህልውናውን ያገኘው የአማራ ንቅናቄ ዋና ዓላማው አማራው በዘውጉ ተለይቶ የሚደርስበትን የህልውና ስጋት መቀልበስ ነው፡፡ስለዚህ የአማራው ንቅናቄ ራስን የመከላከል ተከላካይ ንቅናቄ እንጅ ሌሎችን በጠላትነት ፈርጆ ለበቀል የመነሳሳት ወይም በሃገሪቱ ዋነኛ የስልጣን ቦታዎች ላይ የአማራ ዘውግ መቀመጥ አለበት የሚል ቅንጦት መሰል ጉዳይ አይደለም፡፡በተጨማሪም አማራውን ኢላማ ያደረገው ጥቃት መነሻው አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን መበታተን የሚለው የጣልያን አጀንዳ በመሆኑ አማራውን መታደግ ኢትዮጵያንም ከመታደግ ጋር የሚገናኝ እንጅ ኢትዮጵያን የማጥፋት ወይም የመክዳት ተልዕኮ የተሸከመ አይደለም፡፡የአማራ ንቅናቄ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ይጋጭ ዘንድ ተፈጥሮውም አይፈቅድም፡፡
    የሆነው ሆኖ የአማራ ንቅናቄ አስፈላጊነቱ ከ28 ሚሊዮኑ(?) የአማራ ህዝብ ህልውና አስፈላጊነት ጋር የሚተሳሰር ሆኗል፡፡ከላይ በተደጋጋሚ እንደ ተገለፀው የአማራ ህዝብ በትርክት ላይ የተመሰረተ የጥላቻ ዘመቻ የተዘመተበት፣በህገመንግስት የፀና አደጋ የተጋረጠበት እና ስልጣን በያዘ አካል ጭምር የሚደገፍ የህልውና ስጋት የተጋረጠበት ህዝብ ነው፡፡ የአማራ ንቅናቄ ይህን ስጋት መከላከል፣መቀልበስና ህልውናን የማስጠበቅ እንቅስቃሴ ነው፡፡
    በመሆኑም የአማራ ንቅናቄ ነፃ-አውጭ ግንባር መስርተው ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እንደሚያልሙ ግራዘመም ብሄርተኝነቶች ያለ ተፈጥሮ ያለው አይደለም፡፡ይልቅስ የአማራ ንቅናቄ ትግልን ግድ ያደረገው የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብትን መነጠቅን የጨመረ የህልውና አደጋ የተጋረጠበት መሆኑ ነው፡፡በመሆኑም የትግል ዘይቤውም በህልውናው ላይ የተቃጣውን አሰቃቂ ህይወት የሚቀማ አደጋ መከላከል በመሆኑ ባህሪው የተከላካይነት ነው፡፡በህይወት የመኖር መብቱን በተጨባጭ የተነጠቀ ህዝብ ራሱን መከላከል የሚያስችል የተከላካይነት ትግል ማድረጉ ደግሞ ህጋዊ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊም ድጋፍ ያለው ተግባር ነው፡፡
    የአማራ ንቅናቄ ትግል ሁለት መንታ ተፈጥሮ ያለው ነው፡፡የመጀመሪያው በአማራ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን ህልውናን የማጣት አደጋን መከላከልን ያለመ የተከላካይነት መልክ ያለው (Defensive)ትግል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአማራን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ የጣለውን አማራ-ጠል ትርክት መቀልበስ (Reverse) የሚያስችል አይነት ተፈጥሮ ያለው ትግል ነው፡፡ የአማራ ህዝብ የመጣበትን ትርክት አዘል ግልፅ አደጋ እና በቀን ተቀን ህይወቱ እያስተናገደው ያለውን ዘውግ ተኮር ጥቃት ለመቀልበስ በዘውጉ ተደራጅቶ የሚያደርገው ትግል በማንኛውም ማህበረሰብ የሚስተዋል ተጠባዊ መልስ(Reaction) እንደሆነ ታዋቂው የፈረንሳይ ፈላስፋ ፉኮት ይገልፃል፡፡21ይህን ተከትሎም የመቀልበስ እንቅስቃሴ አውድ(Reverse Discourse) ይፈጠራል:: የአማራ ህዝብም በዓለም ላይ ካሉ ህዝቦች የተለየ ተፈጥሯዊ አወቃቀር የለውምና የተጋረጠበትን ግልፅ አደጋ የመቀልበስና የመከላከል ትግል ውስጥ ገብቷል፡፡
    የቆየውን ትርክት ለመቀልበስ በሚደረግ የአንድ ማህበረሰብ የትግል ጉዞ ውስጥ ዋነኛ ምዕራፍ የሚሆነው ትግሉን የሚያደርው ማህበረሰብ አንድ አሰባሳቢ የጋራ ማንነት ያለው መሆኑን ማስረገጥ ነው፡፡22ይህ ንድፈ ሃሳብ በአማራ ህዝብ ሁኔታ ሲታይ በአማራነቱ እየተሳደደ ያለው ኢትዮጵያዊነቱ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ የኖረው፣አንዳንዴም “አማራ የሚባል ማንነት የለም” ሲባል የነበረው ህዝብ “አማራ” የሚባል ለመጠቃቱ ምክንያት የሆነ አሰባሳቢ ማንነት ያለው በመሆኑ ላይ እንዲግባባ ማድረግ ነው፡፡ እንዲህ በማድረግ አማራነት ተመሳሳይ የጋራ የታሪክ ትዝታ፣ አንድ አይነት አሁናዊ ስጋት/ዕድልና የወደፊት እጣ ፋንታ ያለው ህዝብ መጠሪያ ማንነት መሆኑ ላይ መግባባት ላይ መድረስ ነው፡፡
    የተከላካይነት ተፈጥሮ ያለው የአማራ ንቅናቄ የአማራን ህዝብ ከጥቃት የሚታደጉ ህጋዊና ፖለቲካዊ ማዕቀፎች በሃገሪቱ እንዲዘረጉ የማድረግ መዳረሻ ያለው ቀላል የማይባል ትግል የሚፈልግ የቤት ስራ ያነገበ ትግል ነው፡፡ የአማራ ህዝብ በሃገሪቱ ዳርቻ በሰፊው ተበትኖ የሚኖር መሆኑ ደግሞ ትግሉን ከበርካታ የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሃይሎች ጋር መነጋገርንና መደራደርን የሚጠይቅ ውስብስብ ያደርገውል፡፡ሌላው የአማራ ንቅናቄ ትግል ትርክትን የመቀልበስ መልክ ያለው ሲሆን ፖለቲካዊ መሰጠት ብቻ ሳይሆን ምሁራዊ ምርምሮችን አድርጎ የታሪክን እውነተኛ ገፅ ማሳየትን የሚጠይቅ፣የብዙ የአማራ ሃይሎችን ርብርብ የሚፈልግ ትግል ነው፡፡ወቅታዊውን የአማራ ንቅናቄ ትግል ከሌሎች ብሄርተኞች ትግል የተለየ አስቸጋሪ ገፅታ እንዲኖረው የሚያደርገው ይህ ነባሩን ተረክ የመቀልበሱ ትግል ነው፡፡
    ከአማራ ንቅናቄ ውጭ ያሉ የሃገራችን ዘውግ ብሄርተኝነቶች ትግላቸውን የሚያደርጉት በሰፊው ተነግሮ ተቀባይነት ባገኘ ትርክት ላይ ቆመው ሲሆን የሚቀለብሱት ሌላ ትርክት ደግሞ የለም፡፡በአንፃሩ የአማራ ንቅናቄ ነባሩን ትርክት የመቀልበስ ከባድ ትግል ይጠብቀዋል፡፡በተጨማሪም ነባሩን ትርክት ከመቀልበሱ ጎን ለጎን አዲስ የማታገያ ትርክት መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ነባሩን አማራ ጠል ትርክት የመቀልበሱ ስራ አማራው እንደ ህዝብ የተሰጠው የጨቋኝነት መርገም በታሪክ እውነተኛ ገፆች ያልተፃፈ ፣የሃሰት ክስ መሆኑን አስረግጦ ለማስረዳት ምሁራዊ ጥናቶችን ማድረግን ጨምሮ በርካታ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን መስራትን ይጠይቃል፡፡
    ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ አሁን ሃገራችን ያለችበት ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ በአማራ ህዝብ ላይ የጋረጠውን አደጋ በሚያንፀባርቅ መልኩ አዲስ የማታገያ ትርክት ወደ ትግሉ ሜዳ ማምጣት ችላ የማይባል የቤት ስራ ነው፡፡በተመሰረተና ብዙ ዘመን ባስቆጠረ ትርክት ላይ ተመስርቶ ትግል ማድረግና በተጨባጭ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታውን የሚያንፀባርቅ አዲስ ትርክት አስተዋውቆ ፣ በህዝብ ዘንድ እንዲሰርፅ አድርጎ የትግልን ግቦች ማሳካት ሁለንተናዊ መሰጠትን እና ትኩረትን የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡
    የአማራ ንቅናቄ አማራውን ለተጠቂነት የዳረገውን የዘውግ ብሄርኞች ተረክ ለመቀልበስ ከመታገሉ ባሻር የህልውና አደጋ ላጠላበት የአማራ ህዝብ ማታገያነት ወቅቱን የጠበቀ የማታገያ ትርክት ሲያስተዋውቅ አይታይም፡፡ ሆኖም አሁን የአማራ ህዝብ ካለበት ሁለንተናዊ ሁኔታ በመነሳት የማታገያ ትርክት ቀርፆ ማስተዋወቅ የአማራ ሃይሎች ትልቅ የቤት ስራ ነው፡፡ይህም ከትህነግ መውደቅ በኋላ የመጡ አዲስ ፖለቲካዊ ተለዋዋጮችን በቅጡ ማጤንን ይፈልጋል፡፡ በትህነግ ልሂቃን በሚመራው ስርዓት ውስጥ የነበረው ሁኔታ አማራውን በጨቋኝነት መውቀስና ማሳደድ ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ራሷን ስሟን ለመጥራት እንኳን ያለመፈለግ ዝንባሌ የሚያሳይ አካሄድ ነበር፡፡ ይህ አማራውም ሆነ ሌላው ህዝብ በግልጽ የሚረዳው የትህነግ አቋም በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጠል ይፈልግ የነበረው ህዝብ ሁሉ ትህነግን እንደ ሃገር ጠል አደገኛ ቡድን በመቁጠር ለውድቀቱ ተባብሮ ሰርቷል፡፡
    ከትህነግ ውድቀት በኋላ የመጣው ኦህዴድ/ብልፅግና መራሹ አስተዳደር በመሰረታዊ ተፈጥሮው እንደ ትህነግ ዘወግ ተኮር ነው፡፡ይህ ቡድን የኢትዮጵያን ቀጣይነት የሚበይነውም ለኦሮሞ ዘውግ ልሂቃን በምትሰጠው የስልጣን ድርሻ ነው፡፡ ሆኖም ትህነግን ያስጠላውን ኢትዮጵያን የማጣጣል አካሄድ አሻሽሎ፣ ጭራሽ የኢትዮጵያ ጠበቃ በመሆኑ ረገድ “ከአማራ የበለጥኩ ነኝ” ለማለት የሚቃጣው ሆኖ ታይቷል፡፡ለዚህ አንድ ማሳያው ጠ/ሚ አብይ ስልጣን ላይ በወጡ ሰሞን ወደ ባህርዳር ተጉዘው የአማራ ወጣቶችን ባናገሩበት መድረክ የአማራ ዘውግ ተኮር ንቅናቄ ማደግ እንደሚያሳስባቸው የገለፁበት ሁኔታ ነው፡፡ ተጨማሪ መጥቀስ ካስፈለገ ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው የሚለው የአቶ ለማ መገርሳን ንግግር እማኝ ማድረግም ይቻላል፡፡
    ከጅማሬው “የለማ ቡድን” ይባል የነበረው ይህ ቡድን በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያዊ ብሄርኝነትን አጀንዳ ቀዳሚ አድጎ መምጣቱ በርካታ የአማራ ልሂቃንን ግራ ቀኝ ሳያገናዝቡ በጭፍን የለውጥ አመራር የተባለው ቡድን ደጋፊዎች አደረጋቸው፡፡ ጊዜ እየገፋ ሲሄድ ይህ የለውጥ አመራር የተባለ ቡድን ሊመሰርታት የሚመኛት ኢትዮጵያ አማራውን እንዴት አድርጋ የምታስተናግድ ነች የሚለው ገሃድ እየወጣ መጣ፡፡
    ለዚህ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ለውጥ መጣ ከተባለ ወዲህ በአማራው ህዝብ ላይ የደረሰውን ያላባራ ጭፍጨፋ ለማስቆም “ኢትዮጵያን እወዳለሁ” የሚለው አዲስ አስተዳደር ምን እርምጃዎችን ወሰደ የሚለውን ማሰብ ነው፡፡ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ የለውጥ አመራሩ እገነባታለሁ የሚላት ኢትዮጵያ ከትህነግ በባሰ አማራውን የምታሳድድ፣የሞት የጣር ጩኽቱን እንደ ተዛባ ታሪክ ማስተካከያ የምትወስድ፣አማራ መሆንን ቅጣት የሚገባው ወንጀል አድርጋ የምትወስድ መሆኗን ያሳያል፡፡የአማራው ንቅናቄ ለማታገያነት ሊያስተዋውቀው የሚገባው አዲስ ትርክትም መሰረቱን ማድረግ ያለበት እዚህ ላይ ነው፡፡
    የለውጥ አመራር ነኝ የሚለው ስልጣን ላይ ያለው ኦህዴድ መራሽ ቡድን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጠበቃ ነኝ ማለቱ ከአማራ ህዝብ እምነት ጋር የማይጋጭ ስለሆነ ተቀባይነት ያለው ነው፤ሆኖም ይህ አመራር የሚላት ኢትዮጵያ አማራውን አንዴት የምታይና የምታስተናግድ ነች የሚለው የአማራ ንቅናቄ ለአማራ ህዝብ ሊያስተዋውቀው የሚገባው አዲስ የማታገያ ትርክት መሰረታዊ ነጥብ መሆን አለበት፡፡ይህም ማለት አማራው የኢትዮጵያን ስም ከጠራ ጋር ወዲያው አብሮ መንጎዱን ትቶ ለረዥም ዘመን ሲክፋፋ ለኖረው ለአማራው ህዝብ እንዴት ያለች ኢትዮጵያ ነች የምትመሰረተው የሚለውን መጠየቅም፣በተግባር ከሚደረገው ድርጊት ተነስቶ ብያኔ መስጠትና የትግል አካሄዱን ማስተካከል አማራጭ የሌለው፣ ነገ ዛሬ ሳይባል መተግበር ያለበት የፖለቲካ አተያይ ነው፡፡
  3. የአማራ ብሄርተኝነት ትግል ውስንነቶች
    የአማራ ንቅናቄ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ውስንነቶች አያጡትም፡፡የመጀመሪያው ውስንነቱ በዚህ ጎራ የሚታገሉ ሃይሎች ፖለቲካዊ ግባቸውን በህዝባቸው ዘንድ ለማስረፅ የሚሰሩት ስራ አጥጋቢ አለመሆኑ ነው፡፡በዚህም ሳቢያ አማራው በህልውና ስጋት ውስጥ በመሆኑ ላይ ከመስማማት በቀር የአማራ ንቅናቄን የሚደግፉ አካላት የትግል ግባቸውን ጥርት አድርጎ በማወቁ/በማሳወቁ ረገድ ብዙ የሚቀራቸው ነገር አለ፡፡
    ሁለተኛው ውስንነቱ ከኢትዮጵያ ሃገረመንግስት ጋር ያለው መስተጋብር ምን እንደሆነ ማስቀመጥ ያልቻለ መሆኑ ነው፡፡በሃገራችን የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ግራ ዘመም ብሄርተኞች ቀደም ሲል መገንጠልን የሚጠይቁ የነበረ ቢሆንም አሁን በኢትዮጵያ ሃገረመንግስት ውስጥ ሲኖሩ እንደ ዘውግ ሊሟሉላቸው የሚፈልጓቸውን ጥያቄዎች መናገር የሚችሉ ናቸው፡፡ወደ አማራ ንቅናቄ ሲመጣ ግን አማራ ከኢትዮጵያዊነት ባሻገር እንደ ዘውግ ከሃገረመንግስቱ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች እንደ ኢትዮጵያዊ ከሚጋራቸው ነገሮች በተለየ መንገድ ማቅረብ አልቻለም፡፡ይህ የአማራ ህዝብ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ከነበረው ጥብቅ ቁርኝት የመነጨ ነው፡፡
    ሶስተኛው ውስንነት የአማራ ህዝብን በተለየ ሁኔታ የሚያንገላቱ ትርክት ተኮር ችግሮችን በጥራት ነቅሶ አውጥቶ ወደ ትግሉ ሜዳ ከማውጣት ይልቅ የአማራ ህዝብ ችግር የሌሎችም የሃገራችን ዘውጎች ችግር የሆነ አድርጎ ማቅረብ ይስተዋላል፡፡የአማራ ዘውግ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ የሚያስተናግዳቸው ችግሮች እንዳሉ ባይካድም የአማራ ህዝብ በዘውግ ማንነቱ የሚያስተናግደው ችግር ግን በአይነቱ የተለየ/የከበደ መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር የሚጋራቸውን ችግሮች ጨቋኝ ዘውግ ተብሎ ከመፈረጁ የተነሳ ከሚገጥሙት የብቻ ችግሮቹ ለይቶ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡
    በአራተኛነት ሊነሳ የሚችለው የአማራ ንቅናቄ እንከን ተባብሮ መስራት ላይ ያለው ውስንነት ነው፡፡ማንኛውንም የፖለቲካ ግብ ለማሳካት የተለያዩ አካላት ትብብር ያስፈልጋል፡፡የአማራ ንቅናቄ ዋነኛ ግቦችን ለማሳካትም ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ የሲቪክ ማህበራት፣መገናኛ ብዙሃን፣በትግሉ አስፈላጊነት የሚያምኑ ታዋቂ ግለሰቦች፣ምሁራን ወዘተ መሳተፍ አለባቸው፡፡እነዚህ ወገኖች በትግሉ አካሄድ ላይ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በግቡ ላይ ተመሳሳይ አቋም የሚኖራቸው በመሆኑ ተባብረው መስራታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በአማራ ንቅናቄ ትግል ላይ ግን ተባብሮና ተደጋግፎ መስራቱ ብዙ ርቀት የሚቀረው ሲሆን አንዳንዴ እንደውም ከመተባበር ይልቅ መነቃቀፍና መጠላለፍ የሚስተዋልበት ጊዜም አለ፡፡ከዚህ ሲብስ ደግሞ ለትግሉ ተብሎ የተሰበሰበን ንብረት ለግል ጥቅም አውሎ ህዝብን በትግሉና በመሪዎቹ ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርግ አጋጣሚም ታይቷል፡፡ ግለሰቦች ትግሉ ለከቆመለት አላማ ስኬት ይልቅ የግል ተክለስብዕናቸውን ወደመገንባቱ ቁልቁለት የሚሄዱበት ሁኔታም ያጋጥማል፡፡
    ኢህዴን/ብአዴን/አዴፓ/የአማራ ብልፅግና እያለ የመጣው የአማራን ህዝብ ለመወከል ሳይሆነ ለመቅጣት ዓላማ ሲባል በአማራ ህዝብ ጠላቶች ተቦክቶ የተጋገረውን ፓርቲ ሌላው የአማራ ንቅናቄ ፈተና ነው፡፡ የዚህ ፓርቲ አመራሮችም ከድሮ እስከዘንድሮ አማራውን ሲያስገርፉ የኖሩ እንደሆኑ የታወቀ ነገር ነው፡፡እነዚህን ለአማራው ስቃይ ግድ ብሏቸው የማያውቁ ለመጣው ሁሉ ተላላኪ አመራሮችን እውነተኛ ታጋይ አስመስሎ ማቅረብ፣ እነሱ በቀደዱለት የመንደር ዘውገኝነት ቦይ በመፍሰስ፣ አማራ ተብሎ በጅምላ የሚገደለውን ህዝብ በአማራነቱ ተደራጅቶ እንዳይታገል ጎጃም፣ጎንደር፣ወሎ፣ሸዋ በሚል በመንደር ለመከፋፈል መሞከር የአማራ ንቅናቄ ትልቅ ፈተና ነው፡፡
    ሌላው የአማራ ንቅናቄ ችግር በዘውጉ ምክንያት የሚደርስበትን ችግር በዘውግ ተደርጅቶ ለመታገል ለትግል ከተሰለፈ በኋላ በመንግስት በኩል ከልብም ይሁን ከአንገት በላይ ስለ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ስለተወራ፣የአብረን እንስራ ጥያቄ ስለቀረበና መጠነኛ የስልጣን ማጋራት ስራ ስለተሰራ ብቻ ለትግሉ ዋነኛ ምክንያት የሆኑ የአማራ ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ችላ ብሎ መንግስትን የሚያስደስቱ የትግል መስመሮች ላይ መሰማራት ነው፡፡ይህ የአማራ ንቅናቄ ደጋፊውችን በእጅጉ ተስፋ ያስቆረጠ እንከን ነው፡፡
    እንደ ዘውግ የሚያቀርበውን ጥያቄ እና እንደ ኢትዮጵያዊ ሃገረ-መንግስትን ለማስቀጠል ያለበትን ሃላፊነት ለይቶ አለማየት አንዱ የአማራ ንቅናቄ እንከን ነው፡፡የፖለቲካ ትግልን ለማሳካት የጨዋታውን ህግ ጠንቅቆ ማወቅና በህጉ መሰረት መንቀሳቀስ የፖለቲከኛ የመጀመሪያው ጥበብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ያለው የፖለቲካ መንፈስ የዘውግ ብሄርተኝነትን ዋነኛ ማጠንጠኛው ያደረገ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት የሚወሰነውም ሃገረ መንግስቱ ለዘውጎች ጥያቄ በሚሰጠው መልስ አርኪነት ላይ ነው፡፡ በመሆኑን በአሁኑ የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ የሚጠየቀውም የሚመለሰውም በዘውግ በኩል ነው፡፡
    በሌላ አባባል የአሁኑ የፖለቲካ ዘይቤ መጫወቻ ህግ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት እንዲኖረው ዘውጎች የሚያነሱት ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ አለበት የሚል ነው፡፡ የአማራ ልሂቃን ደግሞ ይህን ህግ ገልብጠው የሚረዱት ሁኔታ ይበዛል፡፡ ይህም ማለት የአማራ ሃይሎች በአብዛኛው የትግል መስመራቸው የአማራ ንቅናቄን ተመርኩዘው፣ የአማራ ህዝብ እንደ ዘውግ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ከማስተጋባት ይልቅ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ ጠንከር አድርጎ መጠየቅ የኢትዮጵያን ሃገረ መንግስት ቀጣይነት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል በሚል የአማራ ህዝብን ጥያቄዎች ለማቅረብ ዳተኝነት ያሳያል፡፡በዚህም ሳቢያ የአማራ ህዝብ ሌላው ቀርቶ በህይወት የመኖር መብት ጥያቄዎቹን እንኳን ነገሬ ብሎ የሚያያቸው ጠፍቷል፡፡
    የአማራ ህዝብ እንደ ዘውግ የሚደርስበትን በደል የሚታገሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እምነት ለማሳደር ዳተኛ መሆኑ ሌላው የአማራ ንቅናቄ የተፈለገውን ያህል እንዳይራመድ እንቅፋት የሆነ እንከን ነው፡፡ በቅርቡ በሃገራችን በተደረገው ምርጫ የአማራ ንቅናቄ ዋነኛ መሪ የሆነው አብን በክልሉ ያገኘው የድምፅ መጠን አነስተኝት የአማራ ንቅናቄ በእጅጉ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አመላክቶ ያለፈ ነው፡፡በእርግጥ የአማራ ህዝብ በምርጫው እምብዛም እምነት እንደሌለው ለምርጫው ለመመዝገብ የወጣው የህዝብ ቁጥር አናሳነት ጠቋሚ ነው፡፡ ከምዝገባው ባሻገር የምርጫው ውጤትም የገዥው ፓርቲ እጅ የሌለበት ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ሆኖም የምርጫውን ውጤትየአማራ ህዝብ በፀጋ የተቀበለው መሆኑ ከበአዴን ለአማራ ህዝብ ያለመቆም ተፈጥሮ ጋር ሲደመር የሚነግረው ነገር አለ፡፡
    ይህ የምርጫ ውጤት የአማራ ህዝብ የአማራ ብልፅግናን እንደሚወድ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ይልቅስ የአማራ ብልፅግናን ባለመምረጡ ከብልፅግና መንግስት ሊመጣበት የሚችልውን በቀል ለመከላከል ሲል ያደረገው የቢቸግር ምርጫ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ሆኖም ይህ የአማራ ህዝብ ባለጋራን የመለማመጥ መፍትሄ ያልሆነ መፍትሄ ነው፡፡ምክንያቱም የብልፅግና መንግስት የቆመበት ርዕዮት ዋነኛ ማጠንጠኛ አማራ ሌሎችን ዘውጎች ሲጨቁን፣ሲበዘብዝ፣ሲገዛ የኖረ በቀል የሚገባው ህዝብ ነው የሚል ሲሆን ለትግል የተሰማራበት ዋነኛ ዓላማ ደግሞ አማራውን መበቀል ነው፡፡ ይህ ትህነግ ዘመን በአፍ ሲነገር የነበረ በብልፅግና ዘመን ደግሞ በተግባር እየተተገበረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
    የፖለቲካ ስራ ድርድር ማድረግና ሰጥቶ በመቀበልም ይገለፃል፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን በፖለቲካዊ ጉዞው የሚደራደርባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የተፈጠረበትን የትግል ዓላማ ለድርድር የሚያቀርብ ብልህ ፖለቲከኛ የለም፡፡ቀድሞ ኢህአዴግ አሁን ብልፅግና የተባለው ከዋለልኛዊ የዘውግ ብያኔ የተነሳው አሁንም ስልጣን ላይ ያለው ጎራ(የአማራ ብልፅግናን ጨምሮ) አማራውን የመበቀል ተግባር በምንም ነገር ለድርድር የማያቀርቡት ዋነኛው የፖለቲካ ህይወት ግባቸው ነው፡፡ስለዚህ የአማራ ህዝብ ብልፅግና ፓርቲን መምረጡ ይህ ቡድን ለአማራ ህዝብ ያለውን ዕይታ ቀይሮ የአማራን ህዝብ በወዳጅ አይን እንዲያየው አያደርገውም፡፡የአማራ ህዝብ ትንሽ ትልቅ ሳይል መረዳት ያለበት የብልህ አካሄድ ይህ ነው – የዘውግ ፖለቲካው እንዴት እንደሚያየው!
    የዘውግ ፖለቲካው አማራውን መቀጣት ያለበት ወንጀለኛ፣ መሸማቀቅ ያለበት ትምክህተኛ፣መሳደድ ያለበት መፃተኛ አድርጎ የሚያስብ ነው፡፡ ይህን ማንኛውም የአማራ ህዝብ የማባበል አካሄድ ሊቀይረው አይችልም፡፡ ቁርጥን ማወቅ ትክክለኛውን የትግል መስመር ለመያዝ ይበጃል፡፡ስለሆነም የአማራ ህዝብ ጣላትን ወዳጅ ለማድረግ ልክ ያልሆነ ምርጫ ከሚያደርግ ይልቅ ጠላትን መገዳደር የሚያስችለውን የማይቀረውን የትግል መስመር መያዝ አለበት፡፡ይህ የትግል መስመር አማራው በዘውጉ ተለይቶ መገደል መሳደዱን በዘውግ ተደራጅቶ መመከት ነው፡፡
    በዚህ የትግል መስመር ለመግባት የመጀመሪያው ተግባር በእውነት የአማራው ህዝብ ያለበትን አደገኛ ሁኔታ ተረድተው ከዚህ የህልውና ስጋት ህዝቡን ለመታደግ ወቅቱ የሚጠይቀውን በዘውግ የመደራጀት የትግል መስመር ተከትለው በእውነተኛ የህዝብ ወገንተኝት የተደራጁ የአማራ ንቅናቄ ፓርቲዎችን በመለየት መደገፍ፣አቅማቸውን ማሳደግ ብሎም በሃገራዊ ምርጫ መምረጥ፡፡አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካው ጎራ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ይህ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ሆኖም የአማራ ህዝብ አማራ ጠሉን የዘውግ ፖለቲካ ቢመርጥም ዋጋ መክፈሉ አልቀረለትም፣ለወደፊቱም አይቀርለትም፡፡በሁለቱም በኩል ዋጋ መክፈሉ ካልቀረ ደግሞ በትክክለኛ ምርጫ ዋጋ መክፈሉ ቢያንስ ለወደፊቱ ተስፋን የሚያሰንቅ ወደ መፍትሄ የሚወስድ መንገድ ነው፡፡
    10.የአማራ ሃይሎች በትግል ጉዟቸው ከግንዛቤ ሊያስቧቸው የሚገቧቸው አንኳር ጉዳዮች
    10.1 የርዕዮት ዓለም ጎራ ሰልፈኝነት ጉዳይ
    በፖለቲካ ዓለም መተባበር፣መገዳደር፣መወዳደርና፣ለመስማማት/ላለመስማማት መስማማት የጉዞው አካላት ናቸው፡፡ከእነዚህ ሁነቶች ማን ከማን ጋር እንደሚስማማ/እንደማይስማማ፣ እንደሚወዳደር ፣ እንደሚገዳደርና እንደሚተባበር የሚወስነው የፖለቲካ ሃይሎቹ የቆሙበት ርዕዮት ነው፡፡የአማራን ህዝብ ለማታገል የተሰለፉ የአማራ ንቅናቄ አካላት ዋነኛው የትግላቸው ርዕዮት አደጋ ላይ ያለውን የአማራ ህዝብ ህልውና መታደግ ነውና ይህን ዋነኛ ዓላማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የአማራን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ የጣለውን አማራ ጠል ትርክት መታገል ግድ ይላቸዋል፡፡
    በሌላ በኩል የአማራ ሃይሎች የሚታገሉትን ይህን አማራ ጠል ትርክት የፖለቲካ ርዕዮታቸው ማጠንጠኛ አድርገው የሚጓዙ የፖለቲካ ጎራዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰልፈኞች የትህነግ ሰልፈኞች ሲሆኑ አሁን ስልጣን ላይ ያለውን የብልፅግና(የአማራ ብልፅግና ጭምር) ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም በሃገራችን የሚንቀሳቀሱ የዘውግ ብሄርተኞች ናቸው፡፡በሌላ አነጋገር የአማራ ሃይሎች በሃገራችን ከሚንቀሳቀሱ የዘውግ ብሄርተኞች ጋር የርዕዮት ዓለም ቀጥተኛ ተቃርኖ እንጅ ምንም አይነት የትግል መስመር ዝምድና የላቸውም ማለት ነው፡፡በሌላ በኩል የርዕዮተ ዓለም ተቃርኖ ካለው ቡድን ጋር የፖለቲካ መስተጋብር ማድረግ ደግሞ የትግሉ ዋነኛ አካል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ይህ የማይቀር የፖለቲካው ዓለም ደምብ ስለሆነ ብቁ ፖለቲከኛ ማድረግ ያለበት ማንን እንዴት ባለ መንገድ ልቅረብ የሚለው የአቀራረብ ጉዳይ ነው፡፡
    የርዕዮት አለም ተቃርኖ ባላቸው የተቃራኒ ፖለቲካዊ መስመር ሰልፈኞች መካካል የሚደረገው መስተጋብር አንድን የጋራ ችግር ለማለፍ የሚደረግ ጊዜያዊ ህብረት(Tactical Alliance) ሲሆን የርዕዮት ዓለም ዝምድና ባላቸው አካላት መካከል የሚደረገው መስተጋብር ግን ዘላቂ አላማን ያማከለ ህብረት(Strategic Alliance) ነው፡፡አማራውን ከህልውና አደጋ መታደግን ዋነኛ ርዕዮቱ አድርጎ የተነሳው የአማራ ንቅናቄ ትግል ታዲያ አማራውን ህልውናውን እስከማሳጣት ድረስ በደረሰ ቅጣት መቅጣትን፣ማሳደድን፣ከሃገሪቱ የፖለቲካ ሜዳ ማግለልን ዋነኛ ርዕዮቱ አድርጎ ከተነሳው የዘውግ ፖለቲካው ጎራ ጋር ምንም አይነት ዘላቂ አላማን ማዕከል ያደረገ ህብረት(Strategic Alliacne) ሊኖርው አይችልም፡፡ስለዚህ በፖለቲካ ፓርቲ፣በሲቪክ ማህበር፣በሚዲያ ወዘተ የአማራ ንቅናቄ ዋነኛ ዓላማ ለማሳካት የተሰለፉ የፖለቲካ ሰልፈኞች ከአማራ ጠሉየዘውግ ፖለቲካ ሰልፈኞች ጋር የሚያደርጉት መስተጋብር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚገባው መሆኑ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
    በተቃራኒ የርዕዮት ዓለም ሰልፈኞች መካከል የሚደረግ መስተጋብር በጥንቃቄ የማይደረግ ከሆነ መጨረሻው መበላላት፣ጥሎ ማለፍ፣አታላይነት፣ክህደት፣ሽንፈት ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስልጣን የያዘው የዘውግ ፖለቲካ ጎራ “አባይን ተሻግረን ቁማር በላን” ሲል የገለፀው ሁኔታ የአማራ ሃይሎች መሰረታዊ የርዕዮት ዓለም ሰልፋቸውን ሳያጤኑ ካገኙት ጋር የሚያደርጉትን ችኩልና ተላላ አካሄድ የሚገልፅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአማራ ሃይሎች ያሉበት የአማራን ህዝብ ትልቅነትና በታሪክ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረውን ጉልህ ተሳትፎ በማይመጥን የፖለቲካዊ ቁመና ነው፡፡ የዚህ ዋናው ምክንያት የአማራ ሃይሎች በቂ የርዕዮት ዓለም ሰልፍ ትንታኔ ሳያደርጉ ኢትዮጵያን በአፉ ከጠራና ባንዲራዋን የሆነ ቦታው ላይ ካሰረ አካል ጋር ሁሉ የሚያደርጉት ደርሶ የማመን ተላላነት የተሞላበት ህብረት ነው፡፡
    በአጠቃላይ ስልጣን የያዘው አማራ-ጠል የዘውግ ብሄርተኞች ጎራ የአማራ ብሄርተኝነት ዘላቂ አጋር ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ጎራ ዘውግ ላይ ማጥበቁ ወይም የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ጎራው ፊቱን ካዞረበት ወደ ስልጣን መውጣቱ አስቸጋሪ እንደሆነ አውቆ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን አቀነቅናለሁ ቢል እንኳን የሚላት ኢትዮጵያ አማራውን በአንክሮ የምታይ እና የምታሳድድ መሆኗ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ጎራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ አታላይና ተለዋዋጭ መልክ ማሳየት ቢጀምርም ኢትዮጵያና አሰራሯን ስለጠላሁ ዘውጌን ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት እገነጥላለሁ በሚልበት ዘመን ኢትዮጵያን የሚጠላው በአማራ ጥላቻው በኩል እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡አሁን የስልት ለውጥ አድርጎ ኢትዮጵያን ከማፈርሳትና ዘውጌን ይዤ ከምቀር ኢትዮጵያን አፍርሼ በመልኬ ብሰራት ይሻላል ሲልም ኢትዮጵያን እንደ አዲስ ለመስራት የሚያፈርሳት በአማራው በኩል ነው፡፡ይህም ማለት ኢትዮጵያን እንደገና ለመስራት ማፍረሱ ሲጀመር የመጀመሪያው ፈራሽ “የአማራ ምልክቶች” ናቸው የተባሉ አማዳት ናቸው፡፡
    ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው የአማራ ጠሉ የዘውግ ብሄርተኝነት ጎራ ዋና መዳረሻው አማራውን በሚመስለውም በማይመስለውም መክሰስ፣ማሳደድ እና ማፋት መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ አንድ ማሳያ በደለኝ፣ጨቆነኝ፣በዘበዘኝ፣ህልውናየን አሳጣኝ የሚለው አማራ ጠሉ የዘውግ ብሄርተኞች ጎራ አንድ ሰው መጥቶ “አማራ የሚባል ነገር የለም” ሲለውም የሚደሰት መሆኑ ነው፤የሌለ ነገር እንዴት ሊጨቁን፣ሊበዘብዝ፣ቅኝ ሊገዛ ይችላል?
    10.2 አማራን በዘውግ ማደራጀትና መታገል ጥፋት እንዳልሆነ
    የአማራ ህዝብ መከራ እንዳያባራ ያደረገው የአማራ ልሂቃን በዘውግ መደራጀትን እንደ ዘረኝነት፣ኢትዮጵያን እንደመክዳት፣የነኦነግን መንገድ እንደመከተል አድርጎ ማየቱ ነው፡፡ እንዲህ የሚያስበው የአማራ ልሂቅ ሊቀርብለት የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ የአማራ ንቅናቄ ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጋር የሚጋጨው የት ላይ እንደሆነ ነው፡፡ሌላው ለዚህ ልሂቅ ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ አማራውን በዘውጉ ለይቶ ለማሳደድና ለማጥፋት የሚሰራውን ህገመንግስታዊ መሰረት ጭምር ያለው ዘረኝነት በመጣበት መንገድ ሄዶ መታገል ዘረኝነት የሚሆነው እንዴት ነው የሚለው ነው፡፡
    ሌላው ወሳኝ ጥያቄ አማራው ለሰላሳ አመታት ሌሎች በአማራነቱ ፈርጀው እየገደሉት እርሱ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለቱ ገዳዮቹ ስለ እርሱ ማንነት ያላቸውን ግንዛቤ ቀይሮ ከመገደል ታድጎታል ወይ? የሚለው ነው፡፡የዚህ ጥያቄ ሌላ መልክ ደግሞ አማራው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ነኝ ማለቱም ትምክህተኛ የሚያስብለውና ለግድያ የሚያዘጋጀው አማራነኝ ማለቱም የሚስገድለው ከሆነ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ መሆኑም ሆነ አማራ ነኝ ማለቱ ለሟቹ ህዝብ የሚያመጣው ለውጥ ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡
    ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው አማራ ትምክህተኛ አማራ ተብሎ መገደሉ የሰዎች ማንነት በባለቤቱ ብያኔ ብቻ የማይወሰን እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህ አማራው ራሱ ኢትዮጵያዊ ነኝ ቢልም ገዳዮቹ አማራ ነህ ብለው መግደላቸው ሃቅ መሆኑ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ ባሉ ፓርቲዎች ዘንድ ሳይቀር የአማራው ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ትግል እንዲደረግ የሚገፋፋ ነገር ነበር፡፡ ባለፉት አመታት በተግባር የታየው ነገር የሚመሰክረው ግን በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚታገሉ ፓርቲዎች በህይወት መኖር ለተነፈገው የአማራ ህዝብ አሳሳቢ ጉዳይ የተለየ ግድ የሌላቸው መሆኑን ለማሳየት እንደሚታትሩ ነው፡፡ባይሆን ኖሮ በዘውግ አንሰራም ካሉ እንኳን አማራውን እንደ አማራ ሳይሆን እንደ ዜጋ ቆጥረው ቢሆን እንኳን ሊታደጉት በሞከሩ ነበር፡፡
    አማራውን እንደ ዜጋ ቆጥረው ለመታደግ ደግሞ እነሱ እንደ ዜጋ ቢያውቁትም እንኳን እንደ አማራ ቆጥረው በዘውጉ ምክንያት ሊያጠፉት የሚሰሩ ሃይሎች እንዳሉ አስረግጠው አምነው፣የሰውን ህይወት ለማዳን በሚደረግ አስቸኳይ የትግል ዘይቤ ሊታገሉለት ይገባ ነበር፡፡ይህን ሲያደርግ የታየ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ ያለ ፓርቲ ደግሞ እስካሁን አልታየም፡፡በተወሰነ ደረጃ ከእናት ፓርቲ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክረሲ ፓርቲዎቸ በቀር የቀሩት ፓርቲዎች አማራውን በአማራነቱ መገደል ክደው የሚነሱ ስለሆኑ ከገዳዮቹ እምብዛም የተለየ ዝንባሌ የሌላቸው ናቸው፡፡ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሄርኝነት እናራምዳለን በሚሉ ፓርቲዎች ትግል ውስጥ የአማራ ህዝብን ጥያቄ መመለስ እንደማይቻል ተረድቶ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ተፈጥሯዊ ግጭት የሌለበትን የአማራን ንቅናቄ መደገፍና መቀላቀል ሰብዓዊ መብትን የማስከበር ጉዞ እንጅ ኢትዮጵያን የመክዳት ወይም ከዘረኝነት ጎራ የመቀላቀል የቁልቁለት ጉዞ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡የቁልቁለቱ ጉዞ እንደውም ወቅታዊ ሁኔታዎችን አጢኖ ወቅቱ የሚፈልገውን የትግል መስመር በመከተል ህይወቱ አደጋ ላይ የወደቀውን ክቡሩን ሰው ልጅ ህይወት መታደግ አለመፈለግ ነው፡፡
    በአብዛኛው የአማራ ልሂቃን ዘንድ የአማራ ንቅናቄን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ለድርድር የማቅረብ የዘረኝነት ጉዞ አድርጎ የመመልከቱ ዝንባሌ በአማራ ንቅናቄ ጎራ የተሰለፉትን ወገኖችን እንኳን የአማራ ሃይሎች መሆናቸውን በምቾት ለመናገር የማይደፍሩ አይናፋሮች እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ይህ ደግሞ የአማራውን በዘውግ መደራጀት በእጅጉ ለሚፈሩት አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች ጥሩ እድል ፈጥሯል፡፡ እነዚህ አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች ራሳቸው በዘውግ ተደራጅተው አማራውን እያሳደዱ፣እየገደሉ፣ንብረቱን እየቀሙ በዘውግ ለመደራጀት የመጨረሻው የሆነውን የአማራ ልሂቅ በዘረኝነት ሊከሱና ሊያሳፍሩ ይሞክራቸዋል፡፡ጭራሽ የአማራው በዘውግ መደራጀት ለኢትዮጵያ ህልውና ስጋት አድርገው ያቀርቡታል፡፡”አማሮች የሚያምርባችሁ ኢትዮጵያዊነት ነው” ሲሉ የየዋህ ሰው የሚመስል በውስጡ አማራውን ያለ ጠያቂ የመግደል የሰላሳ አመት ተሞክሯቸውን የማስቀጠል አደገኛ ዓላማ ያዘለ ምክር ይመክራሉ፡፡
    እንደ እውነቱ ከሆኖ የአማራን ህዝብ ወደ ዘውግ ብሄርተኝነት ጎራ የገፋው የመኖር ያለመኖር አስቸጋሪ ምርጫ ነው፡፡ በተቀረ ዛሬ የአማራን ህዝብ በዘውገኝነት የሚከሱ አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲከኞች በ1983ዓም ዘውጋቸው ልዩ ጥቅም እንደሚገባው በህገ-መንግስት ለማፃፍ ደፋ ቀና ሲሉ፣ትህነግ ወልቃይት እና ራያን ከአማራው ነጥቃ ወደ ትግራይ ስትከልል አማራውን የሚያስጨንቀው የወልቃይት/ራያ ጉዳይ ሳይሆን የአሰብ ጉዳይ ነበር፡፡ በእንደዚህ አይነት የኢትዮጵያዊነት ከፍታ የኖረን ህዝብ ቢቸግረው በገባባት የትግል መስመር ጠቅሶ በዘረኝነት መውቀስ ሊያሳፍር የሚገባው ወቃሹን እንጅ ህይወቱን ለማዳን የሚታገለውን የአማራ ህዝብ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለውን የአማራ ጠል ዘውገኞች ጨፍኑ ላሞኛችሁ፣ደንዝዙ ልብለጣችሁ አካሄድ ከቁምነገር ቆጥሮ የአማራ ንቅናቄ ሰልፈኛ መሆንን እንደሚያሳፍር ነገር መቁጠር ደጋግሞ ለመበላት መዘጋጀት እንጅ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡
    10.3 የኢትዮጵያ ህልውና የሁሉም ዘውጎች ጉዳይ እንደሆነ
    አማራው ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚገለፅ ማንነት ይዞ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ የፈረንጅ ፀሃፍት “የአማራ ነገስታት” እያሉ የሚጠሯቸው፣የሃገራችን አማራ ጠል ዘውገኞች ደግሞ “የአማራን ባህል ጫኑብን” የሚሏቸው ጥንታዊ ነገስታት ራሳቸው ማንነታቸውን በአማራነት ዘውግ ማንነት የሚገልፁ አልነበሩም፡፡ ቢሆን ኖሮ አማራው ዛሬ በዘውግ ለመደራጀት በቂ ታሪካዊ እርሾ ያለው ህዝብ ይሆን ነበር እንጅ በአማራነቱ እየተገደለ ጭምር አማራነቱን ለመልመድ የሚቸገር ህዝብ አይሆንም ነበር፡፡
    የአማራ ህዝብ ለረዥም ዘመናት በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ላይ ብቻ አተኩሮ የኖረ ቢሆንም ማንነት በራስ ለራስ በሚሰጥ፣ፀንቶ የሚኖር፣የማይቀየር ነገር ባለመሆኑ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለው ህዝብ “አማራ ነህ” በሚል የሌሎች ብያኔ መገደል መሳደዱ አማራነቱን (ቢያንስ ህይወቱን ለማዳን) የሚሰባሰብበት ማንነት አድርጎ እንዲወስድ አድርጎታል፤ አሁን ያለው ተጨባጭ ሃቅ ይህ ነው፡፡አሁን ባለው ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ቆመን ስንነጋገር ሃገራችን ኢትዮጵያ ራሷ የዘውጎች ቅርጫት ነች፡፡ አማራውም ከእነዚህ ዘውጎች አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ዘውጎችን አሰባስባ የያዘችው ኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ሌሎችን ዘውጎች ከሚያሳስበው የበለጠ ወይም ያነሰ ሊያሳስበው አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አማራውን ሊያሳስበው የሚገባው ከሌሎች የኢትዮጵያ ዘውጎች እኩል ነው፡፡ በተግባር ግን እውነታው ሌላ ነው፡፡
    አማራው ራሱም ሆነ አማራውን ኢትዮጵያን በመስራት ትምክህተኝነት የሚከሱ ሌሎች ዘውጎች የኢትዮጵያ ህልውና አማራውን የበለጠ ማሳሰብ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ በመሆኑም የዘውጋችን ፍላጎት በምሉዕ ሁኔታ ካልተከበረ ኢትዮጵያን እናፈረሳለን በሚል አማራውን ለማስፈራራት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ አማራው ራሱም አንድ ዘውግ ያውም በጥፋተኝነት የሚከሰስ ዘውግ እንደሆነ ረስቶት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የራሱን ዘውጋዊ ፍላጎት በመግታት ሳይቀር ሌሎችን ዘወጎች የማባበል ፖለቲካዊ ዝንባሌ ያሳያል፡፡
    ግራ የሚያጋባው ነገር ደግሞ አማራው ይበልጥ ለኢትዮጵያ ህልውና ማሰብ አለበት ብለው የአባባይነት ሚና እንዲኖረው የሚፈልጉ አማራጠል ዘውገኞች አማራው እንደፍላጎታቸው ሆኖ ለኢትዮጵያ ህልውና የተለየ ጥንቃቄ ሲያደርግ ደግሞ “ራሱን የበለጠ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ለእኛ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሊሰጥ የሚሞክር ትምክህተኛ” ሲሉ ይከሱታል፡፡ በተጨማሪም “አማራው ኢትዮጵያዊነትን የሚወደው በበኢትዮጵያዊነት ስም ፍላጎቱን በሌሎች ላይ ለመጫን ያለመ የደፍጣጭነት ተፈጥሮ ስላለው ነው” የሚል ክርክር ያመጣሉ፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የዘውግ ብሄርተኞች አይነተኛ ግባቸው በማኛውም የክርክር አውድ አማራውን ጥፋተኛ አድርጎ ማቅረብ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ይህ ሁኔታ አማራውን ግራ በማጋባት አንድ የጠራ የትግል አቅጣጫ ነድፎ፣ በሃገሩ ፖለቲካ ላይ ግዝፈቱን የሚመጥን ድርሻ እንዳይኖረው አድርጓል፡፡
    አማራው ሌሎቹን የማባበል ፖለቲካዊ ዘይቤ በመከተሉ ሳቢያ ራሱ ጥያቄ የሌለው፣ሁሉነገር የተሟላለት፣ጥያቄ ቢኖረው እንኳን ሊደመጥ የማይገባው፣ የሌሎችን ጥያቄ መስማት እንጅ መሰማት የሌለበት ዘውግ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡በዚህም ሳቢያ የአማራው ቀጣይነት ያለው ዘርተኮር ጭፍጨፋ ነገሬ የሚለው የለም፤ጭራሽ ለኢትዮጵያ መቀጠል ሲባል ቻሉት የሚል መልስም ይሰጣል፡፡
    ይህ የተዛባ ዕይታ የሚመነጨው አማራው ኢትዮጵያን የሰራ ቅኝ ገዥ ነው ከሚለው አማራ ጠል ትርክት ነው፡፡ ስለሆነም አማራው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ የማሰቡ ልዕልና ያመጣው ጥሩ ነገር አድርጎ በበጎ ሊያየው የሚገባ እሳቤ አይደለም፡፡ይልቅስ አማራውን እየተበደለ በዳዩን የሚያባብል ተላላ የሚያደርግ፣እንደ ሌሎች ዘውጎች ከኢትዮጵያ ሊያገኘው የሚገባውን መብትና ጥቅም እንዳይጠይቅ የሚያግድ፣እየተጎነጨው ያለው ዘውግ ተኮር መራራ ጥቃት እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው፡፡ የዚህ አጠቃላይ ድምር ውጤት ደግሞ የአማራ ጠል ዘውግ ብሄርተኞች አማራውን በማጥቃታቸው፣አማራው ደግሞ በጭምት ተጠቂነት እንዲቀጥል የሚያደርግ ፖለቲካዊ ድባብ በኢትዮጵያ ማስፈን ነው፡፡ይህ የሚመቸው አማራ አይኖርምና አማራው የሚያደርገው ትግል ይህን በጎ የሚመስል አደገኛ እሳቤን መዋጋትንም ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡
  4. የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችና የመደራደሪያ ነጥቦች
    12.1 የትርክት ፍተሻ
    የአማራ ህዝብ ከ1983 ጀምሮ እያለፈበት ያለው ሁለንተናዊ ጥቃት ዋነኛ ምክንያቱ በጣሊያን ተጀምሮ በዋለልኛዊው የ1960ዎቹ አማራን የኢትዮጵያ መርገም ሁሉ ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው አማራ ጠል ትርክት ነው፡፡ይህ ትርክት በታሪክ በኢትዮጵያ ምድር ለተደረገው በደል ሁሉ ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበውን አማራ ማን እንደሆነ እንኳን በቅጡ ያልተረጎመ፣ኢትዮጵያ የግድ ሩሲያን መምሰል አለባት በሚል ደምፍላታዊ ችኮላ ለብየና የተጣደፈ ትርክት ነው፡፡ሆኖም የተሸከመው የስህተት በብዛት(ገፅ ላይ በሰፊው ተዳሷል) ሳይገድበው መጀመሪያ የትህነግ ማኒፌስቶ፣ከዛም ህገ-መንግስት በመሆን የሃገራችንን ፖለቲካ ከግማሽ ምዕተ አመት ዘለግ ላለ ጊዜ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
    ይህን ትርክት አንግበው ከ1983ዓም ወዲህ ስልጣን ላይ የተሰየሙ አማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች አማራን እንደ ህዝብ በጨቋኝነት ፈርጀው የሚታገሉ ቢሆኑም ህዝብን አንደህዝብ መፈረጁ ብዙ ጥያቄ ሲያስነሰባቸው ደግሞ ከጊዜ በኋላ “ትግላችን ፀረ-የአማራ ገዥ መደብ ነው” ማለትን ምርጫ አድርገዋል፡፡እዚህ ላይ ማንኛውም ለአማራ ህዝብ የሚታገል አካል ማንሳት ያለበት በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡
    በመጀመሪያ መቅረብ ያለበት ጥያቄ በአሁኑ ሰዓት የምትታገሉት የአማራ ገዥ መደብ ማን ነው? የሚል መሆን አለበት፡፡ሌላው የክርክር ነጥብ ከሃምሳ አመት በላይ የምንታገለው የአማራ ገዥ መደብን ነው እንጅ የአማራ ሰፊ ህዝብን አይደለም እየተባለ ይህ አማራጠል አስተሳሰብ ስልጣን በያዘባቸው ሰላሳ ዓመታት በማንነቱ ተለይቶ ተጨፍጭፎ ሰብዓዊ ክብርን ባልጠበቀ መንገድ በጅምላ የሚቀበረው የአማራው ተራና ደሃ ህዝብ ነው እንጅ በየትኛው የአማራ ኤሊት ላይ ምን አይነት ትግል ተደረገ? የምዋጋው የአማራ ገዥ መደብን፣የአማራ ኤሊትን ነው እየተባለ መሰረታዊ ፍላጎቱን እንኳን ማሟላት የሚቸገረውን ደሃ ህዝብ የጥቃት ኢላማ አድርጎ መጨፍጨፍ፣ ዘር ማጥፋትና ማፅዳት የሚደረገው የአማራ ገዥ መደብ የሚባል ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡ይልቅስ ይህ ስልጣን የያዘው አማራ ጠል አስተሳሰብ ጠቡ ከማንኛውም እርሱ አማራ ብሎ ከሚጠራው ፍጡር ጋር ነው፡፡
    በመሆኑም እርጉዝ ሴትን ሳይቀር ሆዷን ቀዶ ፅንስ ያወጣል፡፡ይህን ሲያደርግ እንኳን ከተወለደ ገና ወደዚች ምድር ካልመጣ አማራ ከሚባል ፍጡር ጋር ጭምር ፀብ እንዳለው በአፍ ሳይሆን በተግባር እየተናገረ ነው፡፡ የአማራን ዘር ማፅዳት/ማጥፋት፣ንብረት ማውደም ፣ ማፈናቀል ፣ ማሳደድ፣የስነልቦና ስብራት በሚያመጣ መንገድ አማራውን እና ባህሉን ማንቋሸሽን የመሳሰሉት ድርጊቶች ሁሉ የሚፈፀሙት በተራው የአማራ ደሃ ህዝብ ላይ በመሆኑ የዚህ ትርክት ፀብ ከአማራ ህዝብ ጋር መሆኑን ግልፅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሲደረግ ደግሞ እንደማንኛውም በዓለማችን እንደ ታዩ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ደምብ “ነፍጠኛ” የሚል የዘር ማጥፋት ስያሜ ተሰጥቶት(Genocidal code) ነው፡፡ በዚህ የሞት ምልክት ላይ ደግሞ ትምክህተኛ፣የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ሰፋሪ ቅኝ ገዥ የሚሉ ክብረ-ነክና አሸማቃቂ ቅጥያዎች ተጨምረውበት ነው፡፡
    የአማራ ሃይሎች የሚያደርጉት ሃገራዊ ምክክርና ድርድር የአማራን ህዝብ በጅምላ በጨቋኝነት ፈርጆ የሚንቀሳቀሰው አማራ ጠል ትርክት በአማራ ህዝብ ላይ የጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ መሆን አለበት፡፡ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ ትርክቱ ራሱ ልክ አለመሆኑን ግልፅ አድርጎ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ለዚህ የመጀመሪያው አማራ ጠሉ ትርክር እታገለዋለሁ የሚለው የአማራ ገዥ መደብ ማን እንደሆነ ግልፅ እንዲያደርግ አበክረው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የምንታገለው የአማራ ህዝብን ሳይሆን ገዥ መደቡን ነው የሚለው አካሄድ ራሱ ሆን ተብሎ ለማደናገር የሚደረግ እንጅ በገቢር ትግላቸው የሚያደርጉት ከአማራ ደሃ ህዝብ ጋር እንደሆነ ተጨማጭ ማስረጃን ጠቅሶ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡
    ይህ ተጨባጭ ማስረጃ ከ1983ቱ የበደኖ-አርባ ጉጉ-ቁንቁፍቱ-አሶሳ የአማራ ጭፍጨፋ እስከ ዛሬው ወለጋ-ቤኒሻንጉል-ጉራፈርዳ ድረስ እየተገደለ ፣እየተሳደደ እየተጨፈጨፈ ፣ ንብረቱ እየተቃጠለ ያለው ደሃው አማራ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ፣ሰፋሪ ቅኝ ገዥ የሚሉ የአማራው የመገደያ ስሞች በህግ እንዲታገዱ ማድረግም የድርድሩ አካል መሆን አለበት፡፡ከ1983 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን ዘር ተኮር ጭፍጨፈ የተደረገበት የአማራ ህዝብን ለአሰቃቂ የግፍ ሞት፣መፈናቀል፣የንብረት ውድመት ተጠያቂ አካል እንዲኖር የሚሰራ ልዩ የወንጀል ምርመራ ፍርድቤት እንዲቋቋምና ለተጎዳው ህዝብ ካሳ እንዲከፈል መጠየቅ የአማራ ሃይሎች ድርሻ ነው፡፡
    በሃገራችን የታሪክ በደልና ቁርሾ እንዳለ መናገር የፖለቲካችን ዋነኛው መለያ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ንግግር አማራውን በዳይ አድርጎ የሚያቀርብ ነው እንጅ አማራው ከ30 ዓመት ወዲህ በተለይ በዘውጉ ተለይቶ የደረሰበት እጅግ አሰቃቂና ፈርጀ ብዙ በደል ይቅርታ ሊጠየቅበት እንደሚገባ በደል ሲቆጠር አይስተዋልም፡፡ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት አሁን በሃገሪቱ የረበበው አስተሳሰብ አማራው ተገቢውን ቅጣት አገኘ እንጅ ተበደለ ብሎ መቀበል ስለማይፈልግ ነው፡፡ሁለተኛው ምክንያት አማራው እንደ ዘውግ ተለይቶ በሚደርስበት በደል በከፍተኛ በደልና ሰቆቃ የኖረ ቢሆንም ይህን በተገቢው መንገድ ጠቅሶ የሚሟገትለት አካል ባለመኖሩ ነው፡፡አሁን የአማራ ብሄርተኝነት ሃይሎች ለድርድርም ሆነ ለምክክር በሚቀርቡበት ጊዜ ይህን የአማራውን በደል እንደ ዋዛ የማየቱን ዝንባሌም ሆነ የማድበስበስ ነገር ለማስቆም መታገል አለባቸው፡፡
    12.2 ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያን መጠየቅ
    አሁን በሃገራችን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት የተፃፈበት መንፈስ የሃገሪቱ ዘውጎች አማራ በሚባል ዘውግ ጭቆናና ብዝበዛ ስር የነበሩ ናቸው የሚል ነው፡፡አማራው በሌሎች ዘውጎች ኪሳራ ሲጠቀም የኖረ ዘውግ እንደሆነ በህገ-መንግስቱ አርቃቂዎች ዘንድ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡በመሆኑም በሃገራችን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት በመግቢያው የሚጀምረው “በሃገራችን ባሉ ዘውጎች መካከል የተዛባ ታሪካዊ ግንኙነት ነበረ” ብሎ ነው፡፡ ይህ የተዛባ ግንኙነት አለ የሚለው እሳቤ ሲብራራ መዛባቱ የተፈጠረው አማራውን ተጠቃሚ ሌሎችን ተጎጅና ተጨቋኝ ባደረገ ሁኔታ ነው የሚል እሳቤ ያዘለ ነው፡፡
    ይህ እሳቤ ከ1983ዓም ጀምሮ በሃገራችን ስልጣን ላይ ያለው አስተሳሰብ ዋነኛ የፖለቲካ ዘይቤ ነው፡፡ በመሆኑም በሃገራችን በተለያዩ ማዕዘኖች በአማራው ህዝብ ላይ የሚደረገው አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣የንብረት ዝርፊያ፣መፈናቀል ሁሉ ህገመንግስታዊ መሰረት ያለውን የተዛባ ታሪካዊ ግንኙነት የማስተካከል ትክክለኛ እርምጃ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡በመሆኑም የአማራ ሃይሎች በሚያደርጉት ትግል ውስጥ ገና ከመቅድሙ ጀምሮ የአማራን ህዝብ ለአደጋ የሚያጋልጠውን ህገ-መንግስት ማሻሻልን/መቀየርን ያነገበ መሆን አለበት፡፡
    በአማራ ሃይሎች ዘንድ የአማራን ህዝብ ፈርጀ ብዙ ሰቆቃዎች ለማስቀረት ሲባል በሚደረግ ትግል ውስጥ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ እንደ አንድ የትግል አካል ሲነሳ በአብዛኛው ታሳቢ የሚደረገው የፌደራሉ ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል ነው፡፡ሆኖም ከፌደራሉ ህገ-መንግስት ባላነሰ ሁኔታ የክልል ህገ-መንግስቶችም የአማራውን ህዝብ በህይወት የመኖር መብትን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች አደጋ ላይ የሚጥሉ አንቀፆችን ያዘሉ ናቸው፡፡እንደ ፌደራሉ ህገ-መንግስት ሁሉ የሃገራችን ክልሎች ህገ-መንግስቶችም የመቅድም ገፃቸውን የሚጀምሩት የጨቋኝ ተጨቋኝ ዘውግ ትርክትን በማስቀደም ነው፡፡ሁሉም የክልል ህገ-መንግስቶች በሚባል ደረጃ በመግቢያቸው ላይ የሚያትቱት የነበረባቸውን ብሄራዊ ጭቆና የነፍጠኛውን ስርዓት በትግላቸው አስወግደው ነፃ እንደወጡ ነው፡፡ይህ የፌደራሉ ህገ-መንግስት በመቅድሙ ከገለፀው የተዛባ የዘውጎች ግንኙነት ነበር ከሚለው የሚቀዳ ሲሆን የፌደራሉ ህገመንግስት ደግሞ ከህወሃት የ1968 ማኒፌስቶ የቀዳው ነው፡፡
    የአማራ ሃይሎች ከሌሎች የሃገሪቱ ዘውጎች የበለጠ ህገ-መንግስቱን ለማስቀየር/ ለማሻሻል መስራት ያለባቸው የክልልም ሆነ የፌደራል ህገመንግስቶች ከመቅድማቸው ጀምሮ ያስቀመጡት በዘውጎች መካከል የነበረ የሚሉት የተዛባ ግንኙነት ትርክት አማራውን የመብቶች ሁሉ ቁንጮ የሆነውን በህይወት የመኖር መብት የሚነፍግና የአማራው ያላባራ መከራ ዋነኛ መንስኤ በመሆኑ ነው፡፡
    የሚገርመው ደግሞ ጨቋኝ ነህ ተብሎ በግልፅም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲፈረጅ የነበረውን የአማራ ህዝብ ለማስተዳደር የወጣው የአማራ ክልል ህገ-መንግስትም ይህንን የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ይዞ መገኘቱ ነው፡፡የአማራ ክልል ህገመንግስት በመግቢያው ላይ “እኛ የአማራ ክልል ህዝቦች ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን የጨቋኝ ስርዓት ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን አፍኖ በተዛባ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲዎች ለድህነትንና ኋላቀርነት ዳርጎን መቆየቱ በጠቅላላ እድገታችን ላይ ያደረሰውን አሉታዊ ተፅኖ ለማስወገድ በመሻት እንዲሁም በአብዛኛዎቹ የሃገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ሲፈፀም በቆየው አስከፊ ብሄራዊ ጭቆና ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጉዳቱ ሰለባዎች ሆነን መቆየታችን በማያዳግም ሁኔታ መታረም እንዳለበት በማመን ……” እያለ የጨቋኝ ተጨቋኝ ተርክቱን ያትታል፡፡
    ሌላው የክልል ህገ-መንግስቶች የሚያስቀምጡትና ከክልሉ ውጭ የሚኖረውን አማራ ሰብዓዊ መብቶች አደጋ ላይ የሚጥለው ሃሳብ ከአማራ ክልል በቀር ሁሉም የክልል ህገ-መንግስቶች በክልሉ ሉዓላዊ የስልጣን የሰጡት የክልሉ ባለቤት ብለው ለጠቀሷቸው ዘውጎች ነው፡፡ይህ ለዘውጎች በክልላቸው ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ የሚያትተው ህግ በተግባር ሲተረጎም እነዚህ የክልል ባለቤት የተባሉ ዘውጎች በተለምዶ መጤ፣ሰፋሪ፣ነፍጠኛ በሚሉት አማራ እና ሌሎች ዘውጎች ላይ በህይወት የመኖር መብትን እስከመንጠቅ የሚደርስ ስልጣን እንዳላቸው የሚያሳይ ነው፡፡
    በመሆኑም ባለቤት ባልተባለበት ክልል በብዛት የሚኖረው የአማራ ህዝብ የክልሉ ባለቤት በተባሉ ዘውጎች የሚደርስበት አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ንብረት ቅሚያ፣ሰብዓዊ ክብርን ያልጠበቀ ከሞት እስከ ቀብር የደረሰ እንግልት ክልሉን በሚያስተዳድሩ አስተዳዳሪዎች ላይም ሆነ በፌደራል መንግስቱ መሪዎች ላይ አንዳች ጥያቄ አያስነሳም፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለቤት ባልተባሉበት ክልል የሚኖሩ አማራ ዘውግ ተወላጆች በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉ በኋላ “አስከሬናቸው በእኛ ክልል አይቀበርም” እስከማለት የተደረሰው ከዚሁ የባለቤትነት ህገመንግስታዊ አንቀፅ የተነሳ ነው፡፡
    ሌላው ከክልል ህገ-መንግስቶች ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ ህገ-መንግስቶቹ የክልል ባለቤት ላሏቸው ዘውጎች በብቸኝን የሚሰጧቸው መብቶች (ከመገንጠል መብት በቀር) በተለያዩ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የሰው ልጆች ሁሉ ሊኖሯቸው የሚገባ መሰረታዊ መብቶች ተብለው የተቀመጡ ናቸው፡፡በሃገራችን የክልል ህገ-መንግስቶች በአብዛኛው በአንቀፅ 39 ላይ የተቀመጡና ለክልሉ ባለቤት ዘውጎች ብቻ የተሰጡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሁሉም የሰውልጆች ሊኖሯቸው እንደሚገቡ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ህጎች የሚከተሉት ናቸው፤ ማንነትን የመጠበቅና የማስከበር መብት፣ቅርስንና ታሪክን የማስጠበቅ፣የማበልፀግና የመንከባከብ እንዲሁም ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለፅ መብት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ውስጥ በነፃነትና አድሎ በሌለበት ፍትሃዊ ሁኔታ ተሳትፎ የማድረግ መብት፣ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት የማቋቋምና በፌደራላዊ አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና ማግኘት የሚሉ ናቸው፡፡
    እነዚህ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች ለክልል ባለቤት ለተባሉ ዘውጎች ብቻ የሚያድለው የክልሎች ህገ-መንግስት ባለቤት ያልተባሉ ዘውጎችን ከዚህ መብት የሚያገልሉ በመሆናቸው ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጋር ይጋጫሉ፡፡ በተለያዩ ክልሎች በብዛትና በስፋት የሚኖሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆች ደግሞ እነዚህን መብቶች የመጠየቅ መብታቸውን በክልል ህገ-መንግስቶች ስለተነፈጉ የመገለሉ ጉዳት ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የአማራ ሃይሎች ለህገመንግስታዊ መሻሻል ቀዳሚ ታጋዮች ሊሆኑ የሚገባው፡፡
    የአማራ ሃይሎች ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል የሚጠይቁበት ሌላው ዋነኛ ምክንያት በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ለማዘጋጀትም ሆነ ለማፅደቅ በነበረው ሂደት የአማራ ህዝብ እንደ ዘውግ ሃሳቡ፣እምነቱና ፍላጎት በምንም ሁኔታ ያልተወከለበት በመሆኑ ነው፡፡አንድ ህዝብ ባልተሳተፈበት፣ ባልመከረበት፣ ሃሳቡ፣ ፍላጎቱና እምነቱ ባልተንፀባረቀበት ህገ-መንግስት መተዳደር ስለማይኖርበት ህገ-መንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በስፋት በሚሳተፍበት ግልጽ ነፃና አሳታፊ በሆነ ሂደት እንደገና ሊሻሻል ይገባዋል፡፡
    ከዚህ ዉጭ ከፍተኛ ጥያቄ የሚነሳባቸዉን የመሬት፣ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም፣ ፓርላሜንታዊ ስርዓት፣ የባንዲራ ጉዳይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን፣ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ጉዳይ፣ የህዝብ ሉአላዊነት ጉዳይ፣ የምርጫ ስርዓት፣ የፌደራል እና የክልል መንግስታት የስልጣን ክፍፍል፤ ህገ-መንግስቱን በፌደሬሽን ምክር ቤት የመተርጎም ጉዳይና መሰል አንኳር ጉዳዮች የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአማራ ህዝብ ያልመከረባቸዉ፣ በወከላቸዉ ተወካዮቹ አማካኝነት ዉይይት ተደርጎባቸዉ ያልፀደቁ በመሆናቸዉና በሀገሪቱ ከፍተኛ ዉዝግብ እያስነሱ የሚገኙ ያልተፈቱ ጉዳዮች በመሆናቸዉ እነዚህ ጉዳዮች አንደገና ህዝባዊ ምክከር ተደርጎባቸዉ ሊሻሻሉ የሚገባ በመሆኑ የህገመንግስቱን መሻሻል አስፈላጊነት የሚያደርገዉ ሌላኛዉ ጉዳይ ነዉ፡፡
    በአጠቃላይ ህገመንግስቱ ህዝባዊ ተሳትፎ ያልተደረገበትና የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአማራ ህዝብ ያተወከለበት ብሎም የአንድ ጠባብ ቡድን ፍላጎት ለማሳካት ታስቦ የወጣ እና ሀገራችን አሁን ላለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ማህበራዊ ቀዉስ ዋነኛ ምንጭ በመሆኑ ከየትኛዉም እርምጃ በፊት የህገ-መንግስት ማሻሻል ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡
    12.3 የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች
    የአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰላሳ አመት ያለፈው ቢሆንም ከዓለም አቀፍ እስከ ሃገር አቀፍ አውድ ለሰብዓዊ መብት ቆመናል በሚሉ ድርጅቶችንም ሆነ መንግስታዊ አካላትን ዘንድ ቁብ ተሰጥቶት እንደ ችግር የሚታይ ነገር አልሆነም፡፡የዚህ ቸልታ ምክንያቱ አማራ ጠሉ እሳቤ ከተፀነሰበት ሁኔታ ጋር በእጅጉ የሚገናኝ ሲሆን አማራው በዘውጉ ምክንያት የሚደርስበትን በደል በዘውግ ተደራጅቶ ጠንከር ባለ ሁኔታ ስለማያጋልጥ ነው፡፡
    አማራ ጠሉ እሳቤ ምንጩ የጣሊያን የቅኝ አገዣዝ ህልም እንደሆነ ከፍ ብሎ ተገልጧል፡፡ጣሊያን የአማራ ልሂቃንን ካላጠፋች የቅኝ አገዛዝ ጉዞዋ እጅግ ችግር የተሞላበት እንደሆነ በግራዚያኒ አዋጅ በግልፅ አውጃ ነው በአማራው ላይ አሰቃቂ ግድያዎችን የማድረጉን ጅማሬ ያስጀመረችው፡፡ ቅኝ ገዥው የጣሊያን መንግስት አማራን የቅኝ አገዛዝ እቅዱ ዋነኛ ተግዳሮት አድርጎ ሲያስቀምጥ አማራውን መዋጋት የፈለገው በአዋጅ ብቻ አልነበረም ይልቅስ አማራውን የኢትዮጵያ በዝባዥ ዘውግ አድርጎ ሊበሉ ማስተካከሉን በምሁራን የጥናት ስራዎች ጭምር እንዲሰነድ የማድረግ ሁለንተናዊ ዘመቻ በማድረግ ጭምር ነበር፡፡በዚህ ምክንያት በውጭው አለም የምሁራዊ ክበብ ውስጥ አማራው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር መነሾ ተደርጎ ተበይኖ ቀርቷል፡፡
    በዚህ ላይ የጣሊያንን ፈለግ ተከትሎ በአማራው ላይ የመዝመቱ ዘይቤ በ1960ዎቹ አብዮተኞች ሲገፋበት በአማራው ላይ ቀደም ብሎ ተከፍቶ የነበረውን የማክፋፋት ዘመቻ ይበልጥ ውጤታማ አድርጎታል፡፡የአማራው ብሄርተኝነት ደግሞ ይህን ከዓለም አቀፍ እስከ ሃገር አቀፍ በሰፊው የተዘረጋውን አማራ ጠል ትርክት ለመስበር የሚያስችል ሁለንተናዊ ቁመና ላይ አይደለም፡፡በመሆኑም የአማራው ሞት በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዝምታ፣በሃገር ውስጥ ደግሞ በአማራ ጠል ድህረ 1983 አስተዳደሮች አስተናባሪነት እየተባባሰ የቀጠለ አሰቃቂ ትዕይነት ሆኗል፡፡
    በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረጉ የአማራ ሃይሎች ለመደራደር ሲቀመጡ ለመደራደሪያነት የሚያቀርቡት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ድርድር ውስጥ ለመግባት ራሱ እንደ ቅድመ ሁኔታ ጭምር ሊያነሱት የሚገባ እጅግ አንገብቢ ጉዳይ ነው፡፡የአማራ ሃይሎች በድርድር መድረክ ሲቀመጡ በአማራው ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጀማመሩ ከጣሊያን ዘመን የጀመረና አሁን የአማራውን ግድያ የሚያሳልጠው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው ደግሞ የጣሊያንን እቅድ እያስፈፀመ እንደሆነ አበክረው ማሳወቅ አለባቸው፡፡
    ይህን ማድረግ የሚጠቅመው አማራውን መግደል ከአማራው ጨቋኝነት የተነሳ የመጣ ችግር እንደሆነ የሚያስቡ የዘውግ ፖለቲከኞች የእሳቤ ምንጫቸው ከፋሽስት ጣሊያን የቅኝ አገዛዝ እሳቤ መሆኑን ሊያውቁ ስለሚገባ ነው፡፡ ይህን ማሳወቁ ደግሞ አማራው የሚገደለው በታሪክ ባጠፋው ጥፋቱ ነው የሚለውን እሳቤ አማራ የሚሞተው ለጣሊያን አገዛዝ የማይመች በመሆኑ ምክንያት በቅኝ ገዥዎቹ በተተከለበት የጥላቻ እርሾ ነው በሚለው ትክክለኛ እሳቤ ለመተካት ያግዛል፡፡ የአማራ ንቅናቄ ትግል አሮጌውን ትርክር መዋጋትን ብቻ ሳይሆን በእውነት ላይ የቆመ አዲስ ትርክት ማስተዋወቅንም የሚጨምር ነው፡፡
    የአማራ ንቅናቄ ለአማራ ህዝብ ሰብዓዊ መብቱቶች በአስቸኳይ መከበር የሚደራደረው ድርድር ከዚህ በፊት በአማራው ህዝብ ላይ የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ተጣርተው ፍትህ የሚያገኙበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግንም የጨመረ መሆን አለበት፡፡ የአማራው ህዝብ የሰብዓዊ መብት መጣስ ሰላሳ አመት ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን ከጣሊያን ዘመን ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ነገር ቢሆንም አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃገራችንን በሚመራበት ወቅት በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግን በአይነቱም ፣ በስፋቱም ፣ በአሰቃቂነቱም በከፋ ሁኔታ የቀጠለ ነው፡፡በመሆኑም አሁን ሃገራችንን የሚመራው መንግስት ይህ ሁሉ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአማራው ህዝብ ላይ ሲደረግ በማድረግ ወይም ባለማድረግ በመተባበሩ በህግ እንዲጠየቅ ማድረግ የአማራ ሃይሎች ድርድሩን ጨምሮ በማንኛውም የትግላቸው መንገድ ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
    የአማራን ህዝብ ሰብዓዊ መብት በማስከበሩ ረገድ ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሌላ ጉዳይ ደግሞ ከተለያዩ የሃገራችን ስፍራዎች የተፈናቀሉ የአማራ ዘውግ ተወላጆች በፍጥነት ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት፣ከተመለሱም በኋላ ተጨባጭ የሆነ የደህንነት ዋስና እንዲሰጣቸው፣ኑሯቸውን የሚገፉበት መልሶ የማቋቋም እርዳታም ከመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚያገኙበት መንገድ በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን መታገል የአማራ ንቅናቄ ጊዜ የማይሰጠው ስራ መሆን አለበት፡፡
    ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራዊ ድርጊቶችን (Operational Activities) ከሚጠይቁ የድርድር ሁኔታዎች በተጨማሪ የአማራን ህዝብ ሰብዓዊ መብት በዘላቂነት ለማስጠበቅ አማራን በጨቋኝነት በሚከሰው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ እሳቤ መንፈስ የተፃፉት የፌደራል እና የክልል ህገመንግስታት እንዲሻሻሉ መሞገት መሰረታዊው የአማራ ንቅናቄ የትግል አቅጣጫ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የአማራ ህዝብ ለ30 ዓመታት በአጠቃላይ እና በዚህ ሶስት አመት ደግሞ በተለይና በአሰቃቂ ሁኔታ እያስተናገደው ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ለሰብአዊ መብት መከበር ቆሜያለሁ የሚለው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊቱን ያዞረበት ሁኔታ ሩዋንዳ ላይ በተደረገው የዘር ማጥፋት ላይ ሆን ብሎ ፊቱን ያዞረበትን እና አሁን ይቅርታ ከጠየቀበት ሁኔታ ጋር በማመሳሰል በዓለም አቀፍ መድረኮች ማስተጋባት ከአማራ ሃይሎች የሚጠበቅ ነው፡፡ይህ እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሲሆን በዲያስፖራው የአማራ ተወላጆች ቁጥር ብዙ መሆኑ ደግሞ ለውጤታማነቱ በጎ ተፅዕኖ የሚያበረክት ነገር ይሆናል፡፡
    12.4 የፖለቲካዊ/አስተዳደራዊ ውክልና ጥያቄ
    የአማራ ህዝብ በአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ትርክት ምክንያት ከአማራ ዘውግ የተወለደ ሰው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሰሉ የፌደራሉ የስልጣን ዋነኛ እርከኖች ላይ እንዳይመጣ ከመጣም በሁለተኛ ሶስተኛነት መሆን እንዳለበት ባልተፃፈ ህግ ስምምነት ላይ የተደረሰ ይመስላል፡፡ ይህ ትርክት የአማራ ተወላጆች በፌደራል ዋነኛ ስልጣን ላይ ቀርቶ እምብዛም የሃገሪቱ ፖለቲካ በማይወሰንባቸው ስፍራዎች ሳይቀር የአማራ ዘውግ ተወላጅ እንዲታይ አይፈልግም፡፡
    ትህነግ በተወገደበት ወቅት “ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል?” በሚለው እሳቤ ውስጥ በምክትልነት ትህነግ መራሹን ስርዓት ሲያገለግሉ የነበሩትና ለወንበሩ ቅርብ የነበሩት አማራው አቶ ደመቀ መኮንን ከስሌቱ ውስጥ ገብተው እንዳልነበር ግልፅ ነው፡፡ ከምክትሉ አቶ ደመቀ ይልቅ የሌላ ዘውግ ተወላጆች ነገር ግን የአቶ ደመቀን ያህል ለጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቅርብ ያልነበሩ፣በፖለቲካው መድረክም እምብዛም የማይታወቁ ሰዎች ነበሩ ለግምት ሲቀርቡ የነበረው፡፡ ይህ እንደምሳሌ ቀረበ እንጅ በብአዴን ውስጥ ያሉ አማሮች ለስልጣን መብቃታቸው የአማራን ህዝብ ችግር ይቀርፋል ለማለት አይደለም፡፡ይልቅስ ምሳሌው የተነሳው አሁን በሃገራችን ስልጣን ላይ ያለው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካው አማራ ብሎ የበየነውን ሰው የብአዴን አባል ቢሆን እንኳን ወደ ስልጣን መምጣቱን አጥብቆ እንደሚቃወም የሚያሳይ ነው፡፡
    ይህ እሳቤ ደግሞ አማራ የድሮ ስርዓት ናፋቂ ጨቋኝ በመሆኑ ወደ ስልጣን መምጣት የለበትም፣አማራ ወደ ስልጣን ከመጣ የድሮው ጨቋኝ ስርዓት ተመልሶ መጣ የሚለው የዘውግ ፖለቲካው አማራውን ከሃገሩ ዋነኛ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጭነት ገለል ለማድረግ የሚጠቀምበት እውነት የሌለበት ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡አማራው ወደ ስልጣን እንዳይመጣ የሚፈለገው ደግሞ አማራውን የመበቀሉን የሰላሳ አመት ፕሮጀክት ለማስቀጠል ነው፡፡
    ይህ አማራውን ከሃገሩ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጭነት የማግለሉ የዘውግ ፖለቲካው ረቂቅ አካሄድ ሰዎች በዘውጋቸው ሳይገለሉ በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ተሳትፎ የማድርግ መብት አላቸው ከሚለው ዓለምአቀፉ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ስለዚህ የአማራ ንቅናቄ መሪዎች በተቀመጡብ የድርድርና የውይይት መድረክ ሁሉ አማራው በአማራ ጠሉ ትርክት ምክንያት ከሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች እየተገለለ እንደሆነ ግልጥልጥ አድርገው በማቅረብ ትግል ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
    የአማራ ዘውግ አባላትን ከፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ተሳትፎዎች የማግለሉ አካሄድ ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው ያልተፃፈ አማራ ጠል ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በተፃፉ ህጎች ደጋፊነትም ይከናወናል፡፡ በተለይ የተለያዩ ዘውጎችን የክልል ባለቤት ብለው የደነገጉ የክልል ህገ-መንግስታት ከክልሉ ውጭ በብዛት የሚኖረውን የአማራ ዘውግ ተወላጅ ከአስተዳደራዊ/ፖለቲካዊ ተሳትፎ ውጭ የሚያደርጉ ናቸው፡፡በዚህም ምክንያት የአማራ ዘውግ ተወላጆች ሰብዓዊ፣ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሌሎች መብቶችን ማስጠበቅ አልተቻልለም፡፡ ይህ አግላይ ብያኔ ራሱ ኢትዮጵያ በፌደራሉ ህገ-መንግስት ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ ነው፡፡በመሆኑም የአማራ ሃይሎች ይህንኑ ጠቅሰው በመመሟገት እነዚህን መብቶች ለማስከበር መስራት አለባቸው፡፡
    12.5 የዘውግ ፌደራሊዝሙ ያስከተላቸው የግዛት ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች
    የሃገራችን ፌደራሊዝም አከላለል በዋናነት ዘውግን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡በዚህ የአከላለል ሂደት ወደ አንድ የዘውግ ክልል ለመካለል በዋናነት የሚታየው የህዝቦች ዘውጋዊ ማንነት ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሃገራችን አብዛኛው ክልሎች መጠሪያቸውን የሚያገኙት ለክልሉ መከለያነት እንደ ዋነኛ መስፈርት በሚያገለግለው የዘውግ ስም ነው፡፡ሆኖም የሃገሪቱ አብዛኛው ክልሎች ከተዋቀሩበት ከዚህ መሰረታዊ እሳቤ ባፈነገጠ መንገድ በወልቃይት፣ሁመራ፣ራያ፣ደራ፣መተከል አካባቢዎች የአማራ ዘውጋዊ ማንነት ያላቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ህዝቦች ማንነታቸውን በማይገልፅ ክልል ውስጥ እንዲካለሉ ተደርጓል፡፡በዚህም ሳቢያ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እያስተናገዱ ይገኛል፡፡
    በእነዚህ ቦታዎች ወደ አማራ ክልል ለመካለል በታሪካዊ ዳራ፣በስነልቦና፣በመልከዓ ምድራዊም አቀማመጣቸው ለአማራ ክልል አዋሳኝ የሆኑ፣ በቦታው የሰፈረው ህዝብ የዘውግ ማንነትም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ራሱን በአማራነት የሚገልፅ በመሆኑ በአማራ ክልል ለመካለል ምንም አስቸጋሪ ነገር የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እነዚህ ህዝቦች ከአማራ ክልል ተቆርጠው ወደሌላ ክልሎች እንዲሄዱ የተደረገበት የተለያየ ምክንያት አለ፡፡
    አንዱ ምክንያት እነዚህን ክልሎች በፊታውራሪነት ያካለለው አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ጨቋኝ የሚለውን የአማራ ዘውግ በሁሉም መስክ በማዳከም አከርካሪውን መስበር እንዳለበት አጥብቆ የሚያምን ነው፡፡በመሆኑም ጨቋኝ የተባለው የአማራ ዘውግ ሰፊ ክልል እንዳይዝ ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት እነዚህ ቦታዎች ለም መሬቶች በመሆናቸው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው በወቅቱ ፖለቲካዊን ሲዘውር የነበረው ልሂቅ ዋነኛ መሰረት ወደ ሆነችው ወደ ትግራይ እንዲጠቃለሉና በአማራው ኪሳራ የትግራይን ኢኮኖሚ እንዲያጎለብቱ ተደርጓል፡፡
    መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ ወደ ትግራይ ለማካለል ያልተመቸው ሌላው ለም ቦታ መተከል ደግሞ ከአማራ ተነጥቆ የትግራይ ልሂቃን እንደ ሁለተኛ ክልል በሚያዩት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስር ተካልሎ በኢንቨስትመንት ስም ወደ ቦታው ለሚያቀኑ የስርዓቱ ታማኞች ንብረት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ሌላው የአማራ ማንነት ጥያቄ የሚነሳበት ደራ የተባለው ቦታ ለም ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ከአማራ ክልል እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ወልቃይትም ከለምነቷ ባሻገር ለትግራይ ክልል ወደ ሱዳን ለሚደረግ ግንኙነት ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታዋ ታይቶ ነው ከአማራ ክልል እንድትነጠቅ የተደረገው፡፡
    እነዚህ ቦታዎች ከአማራ ክልል መነጠቃቸው ለክልሉ ህዝብ ከኢኮኖሚያና ስትራቴጅያዊ ጉዳታቸው ባላነሰ ሁኔታ ከማንነት እና ባህል ጋር የተያያዙ ጉዳቶችን አምጥተዋል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ከእለታት አንድ ቀን የአማራ ማንነት ጥያቄ ያነሳሉ በሚል የዘር ማጥፋት/ማፅዳት ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል፣ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ የሚደርጉ በደሎችን አስተናግደዋል፣ከሞትና መሰደድ የተረፉት ደግሞ በቋንቋቸው እንዳይማሩ እንዳይናገሩ ተደርገዋል፡፡
    ይህ ሁሉ ማንነት እና ባህልን ለማጥፋት የተደረገ ወንጀል ከመሬትና ግዛት መካለል በላይ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥያቄን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡በሃገራችን ከታዩ አሰቃቂ ወንጀሎች ውስጥ በቅርቡ በመተከል የታየው የሰውን ልጅ እንደ ቆሻሻ በስካቫተር ዝቆ በግሬደር የመቅበር መራራ በደል የታየው በመተከል ነው፡፡ከሞላ ጎደል የአንድን ግዛት ህዝብ ዘውግ ቀይሮ ሌላ የማድረግ የዘር ማፅዳት ወንጀል የታየው በወልቃይት ነው፡፡ ከሰሞኑ በደራ የታየው አሰቃቂ የሰውልጆች ሞት የአካባቢው ሰው የአማራ ማንነት ጥያቄ እንዳያነሳ ማደፋፈኛ ስልት ነው፡፡
    በእነዚህ ቦታዎች ላይ የደረሰው አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምንጩ የዘውግ ፌደራሊዝሙ የራሱን ህግ ጥሶ የአማራ ማንነት ያላቸውን ህዝቦች ማንነታቸው ወዳልሆነ ክልል ማካለሉ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በአማራ ሃይሎች ዘንድ ቀደሚ መሆን ያለበት በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሰፈሩ ህዝቦች አማሮች ሆነው ሳለ ወደ ሌላ ክልል የተካለሉበት አካሄድ ስህተት በመሆኑ የዘውግ ፌደራሊዝም በስራ ላይ እስካለ ድረስ እነዚህ ቦታዎች ወደ አማራ ክልል መካለል አለባቸው የሚል ትግል ማድረግ ነው፡፡ሁለተኛው መሆን ያለበት ደግሞ በእነዚህ ቦታዎች የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጣርተው መጠየቅ ያለበት አካል መጠየቅ፣መካስ ያለበት አካል እንዲካስ ማድረግ ነው፡፡
    12.6 የባህል ጥያቄዎች
    የአማራን ዘውግ በጨቋኝነት የሚፈርጀው አማራ ጠሉ የዘወግ ፖለቲካ አማራው የሃገሪቱን ሌሎች ዘውጎች ባህል ደፍጥጦ የራሱን ባህል ጭኖባቸዋል ሲል ይከሳል፡፡በዚህ እሳቤ ምክንያት የአማራጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ልሂቅ የአማራ ናቸው ሲል በበየናቸው ባህሎችና እምነቶች ላይ በቀል መሰል የአውዳሚነት እርምጃ ይወስዳል፡፡ ዘውጎች የራሳቸውን ባህል የማሳደግ መብት እንዳላቸው የሚደነግገውን ህገመንግስታዊ መብት የሚያስከብረው የአማራ ያለውን ባህል በማጥፋት ይመስላል፡፡
    በእርግጥ አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ የአማራ ያላቸው ባህሎች ሁሉ የአማራ የግል ንብረት ናቸው ወይ የሚለው ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ሆኖም የዘውግ ፖለቲካው የአማራ ሲል የሚያሳድዳቸው እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያሉ ተቋማት፣የአማርኛ ቋንቋ፣የኢትዮጵያ ነገስታትን የሚዘክሩ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ሁሉ ተጠብቀው ለሚመጣው ትውልድ መተላለፍ ያለባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድም ቅርሶቹ የሚወድሙት የአማራ ተብለው በመሆኑ ሁለትም የአማራ ህዝብም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእነዚህ ባህሎች ውስጥ የራሱን ማንነት የሚያይባቸው በመሆኑ ከጥፋት ሊያድናቸው ይገባል፡፡በመሆኑም የአማራ ሃይሎች በአማርኛ ቋንቋና በሌሎች የአማራ በተባሉ መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህሎች ላይ የሚደረገውን የጥፋት እርምጃ ለማስቆም ግንባር ቀደሞቹ መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ የአማርኛ ቋንቋን በተመለከተ ስልጣን የያዘው የዘውግ ፖለቲካ ልሂቃን ሆን ብለው ቋንቋው እንዲጠፋ እንደሚሰሩ መረጃ ተገኝቷል፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የአማርኛ ቋንቋ እንዳይሰጥ የሚከለከልበት በርካታ አጋጣሚም ያጋጥማል፡፡በዘውግ ፖለቲከኞች ዘንድ እነዚህን የመሰሉ አማርኛ ቋንቋን ሆን ብሎ የማዳከም ስራ የሚሰ በመሆኑ የአማራ ንቅናቄ አካላት በትግላቸው ውስጥም ሆነ በሚደራደሩባቸው መድረኮች የአማርኛ ቋንቋ በታሪክ ሃገራችንን ለማስተሳሰር ካለው የቆየ ጠቀሜታ በመነሳት ብሄራዊ ቋንቋ የመሆን ብቃት ላይ የደረሰ በመሆኑ ለዚሁ መታገል ይገባቸዋል፡፡ ከታሪካዊ የማስተሳሰር ጠቀሜታው ሳቢያ ቋንቋው በከፍተኛ ሁኔታ የዳበረ ስነፅሁፋዊ ብልፅግና ስላለው ብሄራዊ ቋንቋ መሆን ይገባዋል የሚለውን አቋም ማጠናከር ከአማራ ሃይሎች ይጠበቃል፡፡
    12.7 የፍትሃዊ ኢኮኖሚ እድገት ጥያቄ
    በአማራ ጠል የዘውግ ብሄርተኞች መምህር ዋለልኝ በባለ አምስት ገፅ ዕሁፉ አስተምሮ አማራ በሌሎ ዘውጎች ላይ ያደረሰው ጭቆና ኢኮኖሚያዊ ገፅታ ጭምር እንዳለው ይገልፅል፡፡ ሆኖም ይህ ኢኮኖሚያዊ ጭቆና መገለጫው እንዴት እንደሆነ በበቂ ሁኔታ አያብራራም፡፡የሆነ ሆኖ በሁለንተናዊ ጨቋኝነት የተፈረጀው የአማራ ዘውግ ክልል ነው የተባለው የአማራ ክልል በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ከሁሉም ክልሎች ኋላ የቀረ እንደሆነ ከህዝቡ ጎስቋላ ኑሮ በተጨማሪ የዓለም ባንክን የመሰሉ አለም አቀፍ ተቋማትም በሪፖርታቸው የሚገልፁት ነው፡፡
    የዓለም ባንክ በፈረንጆቹ 2017 ባወጣው ሪፖርት በሃራችን በአጠቃላይ የተመዘገበው የፍፁም ድህነት(Absolute poerty) መጠን 24ፐርሰንት ሲሆን የአማራ ክልል የፍፁም ድህነት መጠን 26.1 ፐርሰንት ደርሷል፡፡ ኢህአዴግ ስኬታማነቱን የሚገልፅበት የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ የአማራ ክልልን የዘለለ ነው፡፡ስለሆነም ክልሉ በአለም ላይ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ የመንገድ መሰረተ ልማት ትስስር ያለበት(One of the worst connected)፣እድገት ያልደረሰበትና በኢኮኖሚ ወደኋላ የቀረ ክልል (Remote and Economically lagging region) በሚል በዓለም ባንክ ሪፖርት የተገለፀ ክልል ነው፡፡የሃገራችን ሁሉም ክልሎች እምብዛም ባልታደሉት የኢንዱስትሪ ግንባታም ቢሆን የአማራ ክልል ሁኔታ የከፋ እንጅ የተሻለ አይደለም፡፡ በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትም ቢሆን በደርግ ስርዓት ከተሰራው አንድ የሃይል ማመንጫ ውጭ የተሰራ ነገር የለም፡፡ በዚህም ምክንያት የክልሉ አብዛኛው ህዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን የማያገኝ ነው፡፡23
    በክልሉ የአንደኛ ደረጃም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥባቸው ክፍሎች የፈራረሱ ጎጆዎች ሲሆኑ አንዳንዴ ተማሪዎች በድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው በዛፍ ስር የሚሰጥበት ሁኔታም አለ፡፡ የጤና አገልግሎት ሽፋን አነስተኛ በመሆኑ በክልሉ በአጠቃላይ በህይወት የመኖሪያ እድሜ እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን ከአምስት አመት በታች የሚሞቱ ህፃናት ቁጥርም በሃገሪቱ ካለው መጠን ከፊተኞቹ ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ በህፃናት መቀንጨርም ክልሉ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡24
    ሃገራችን እንደ አጠቃላይ በኢኮኖሚ እጅግ ኋላ የቀረች ብትሆንም የአማራ ክልል ይህን ኋላ ቀርነት ከፊት ሆኖ የሚመራ የሆነው ሃገራችን የምትመራበት ዘውግ ፖለቲካ አማራውን መበቀልን አንዱ የፖለቲካ ዘይቤው አድርጎ ስለሚያስብ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለአማራ ህዝብ የሚቆረቆሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆች በሃገራዊ የስልጣን ክፍፍሉ ዋነኛ የውሳኔ ቦታዎችን እንዳይዙ ስለሚፈለግ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች የሚንቀሳቀሱበት በጀት በተዛባ ሁኔታ እንዲከፋፈልና የአማራ ክልልን ድህነት ቀጠና እንዲሆን የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ በመሆኑም የአማራ ሃይሎች ይህን የተዛባ ተርክት ውጤት የሆነውን የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ሁኔታ በመቀየር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲያገኝ መታገል ይኖርባቸዋል፡፡
    12.8 የአማራ ህዝብ ቁጥር ጉዳይ
    አሁን ሃገራችን ባለችበት የዘውግ ፖለቲካ ለክልሎች የሚመደበው በጀት ክልሉ በያዘው ዘውግ ቁጥር ላይ የሚወሰን ነው፡፡የአማራን ዘውግ በሁሉም አቅጣጫ መበቀል የሚፈልገው ይሄው የዘውግ ስርዓት ታዲያ የአማራን ህዝብ ቁጥር በመቀነስ ክልሉ ከሃገሪቱ ብሄራዊ በጀት ሊያገኘው የሚገባውን ትክክለኛ ድርሻ እንዳይጋራ አድርጓል፡፡ኢህአዴግ በቆየበት ሩብ ምዕተ ዓመት የአማራን ህዝብ ቁጥር በሁለት ሚሊዮን በሚቆጠር ደረጃ “የደረሰበት ጠፋ” በማለት አማራ ጠል አላማውን በግልፅ ቢያሳይም ባለፉት ሩብ ምዕተ አመታት በተደረገው የህዝብ ቆጠራም የአማራ ህዝብ ትክክለኛ ቁጥር ስለመመዝገቡ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
    የአማራ ህዝብ ትክክለኛ ቁጥር መታወቁ ከበጀት ባለፈ በሃገራዊ ፖለቲካ ውስጥ ህዝቡ ሊጫወት የሚገባውን ሚና እንዲጫወትም ያግዛል፡፡ ስለሆነም የአማራ ሃይሎች የአማራ ህዝብ ትክክለኛ ቁጥር የሚታወቅበት እውነተኛ የህዝብ ቆጠራ እንዲደረግ መታገል ይገባቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው በዘውግ ፖለቲካ የጨዋታ ህግ የህዝብ ብዛት ወደ ዋነኛ ሃገራዊ የስልጣን እርከኖች የሚያስጠጋ መንገድ ነው፡፡ በዘውግ ፖለቲካ ከሃገርኛ ፖለቲካው ዋነኛ የስልጣን እርከን ድርሻ ማግኘት ለአንድ ዘውግ ጥንካሬ በእጅጉ የሚጠቅም ጉዳይ እንደሆነ ህወሃት በአሁኑ ወቅት ያለበትን ሁለንተናዊ ጥንካሬ አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡
    ህወሃት ሃገራዊ ስልጣን ላይ እያለ ለዘውጉ በሰራው ስራ ጠንካራ ሆኖ ለግማሽ ምዕተ አመታት መቆየትና ከዋናው የሃገራችን የስልጣን እርከን ገሸሽ የተደረገው የአማራ ዘውግ ደግሞ በሁሉም መለኪያ ከእርሱ በሚያንሰው የትግራይ ክልል ከፍተኛ ውድመት እንዲደርስበት አድርጓል፡፡አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኦሮሞ ልሂቃን የሚመሩት ሃገራዊ አስተዳደርም ከህወሃት በተመሳሳይ ሁኔታ የወጣበትን ክልል ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት እየሰራ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በሃገር ብሄራዊ ስልጣን ላይ ወጥቶ ለአንድ ዘውግ ጥንካሬ መስራት ተገቢ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ሃገራችን በዘውግ ፖለቲካ የጨዋታ ህግ እስካለች ድረስ ይህ እሳቤ ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡በመሆኑም የጨዋታው ህግ በሚያዘው መሰረት ሄዶ መጫወት ግድ ነውና አማራውም ሃገራዊ ስልጣን ላይ ወጥቶ የዘውግ ፖለቲካ ህግ በሚያዘው መንገድ በሁለንተናዊ ጉስቁልና ላለው የአማራ ህዝብ ከሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ባላገለለ ሚዛናዊነት መስራት ይጠበቅበታል፡፡
    ከአማራ ህዝብ አንፃር ከህዝብ ቆጠራ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሌላ ቁምነገር በሃገራችን የህዝብ ቆጠራ ሲደረግ በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆች ቁጥር በትክክል የሚታወቅበት ሁኔታ እንዲኖር መታገል ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአማራ ዘውግ ተወላጆች በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች በብዙ ቁጥር ተበትነው ይኖራሉ፡፡ ሆኖም በሃገራችን ያለው ስርዓት አማራ መሆንን እንደ ወንጀል የሚያይ በመሆኑ በሌላ ክልል እየኖሩ አማራ ነኝ ማለት ደግሞ እጅግ አስፈሪ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡በተለይ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልል እየኖሩ አማራ ነኝ ማለት አደጋ አዝሎ የሚመጣ ነገር ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ክልል የሚኖሩ አማሮች ከደህንነት ስጋት የተነሳ በህዝብ ቆጠራ ሰዓት አማራ ነን ከማለት ይልቅ የሚኖሩበትን ክልል ዘውጋዊ ማንነት መጋራትን ይመርጣሉ፡፡ይህ በዋናነት የሚመጣው ከደህንነት ስጋት በመሆኑ የእነዚህ ሰዎች የደህንነት ስጋት እንዲነሳና ራሳቸውን በሚገልፁበት ትክክለኛ ዘውጋዊ ማንነታቸው እንዲቆጠሩ ማድረግ የአማራ ብሄርኛ ታጋዮች ድርሻ ነው፡፡
    በሌላ ክልል የሚኖሩ አማሮች ትክክለኛ ቁጥር መታወቁ ጥቅሞች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ለማድረግ ያስችላል፡፡በሁለተኝነት ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ አማሮች በአስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ውክልና ያግኙ የሚለውን ትግል ገቢራዊ ለማድረግ ያግዛል፡፡ከሁሉም በላይ ግን ሰዎች ማንነታቸውን ያለማጣት ሰብዓዊ መብት ያላቸው በመሆኑ ነኝ በሚሉት ማንነታቸው መታወቅ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን ሰዎቹ ማንነታቸውን በመግለፃቸው ሳቢያ ከሚመጣባቸው አደጋ አስተማማኝ የደህንነት ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ይህን ማድረግ ደግሞ በአማራ ብሄርተኝነት ሃይሎች በእጅጉ ሊሰራበት የሚገባ የትግል አቅጣጫ ነው፡፡
    12.9 የአዲስ አበባ/የድሬዳዋ ባለቤትነት ጉዳይ
    በአብዛኛው የኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ ዘውጋዊ ስብጥር ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የአንድ አካባቢን አስተዳደራዊ ፈለግ በአንድ ወጥ ዘውግ የሚበይነው የዘውግ ፖለቲካ ከተሞችን የሚያስተዳድርበት ሁኔታ በውስጡ የሚኖሩትን ስብጥር ያላቸው ዘውጎች ፍላጎት በመወከሉ ረገድ ከፍተኛ ውስንነት ያለው ነው፡፡ የዘውግ ፖለቲካው አስተዳደር በአንድ ዘውግ የበላይነት የማስተዳደር ዘይቤውን ለማሟላት ሲል ብቻ ከፍተኛ ስብጥር ያለውን የከተማ ነዋሪ ከገጠር በመጡ የዘውግ ፖለቲከኞች እንዲተዳደር ያደርጋል፡፡እነዚህ ከገጠር የሚመጡ አስተዳዳሪዎች ከተሞቹ የሚገኙበት ክልል ከሚጠራበት ዘውግ የሚመጡ ናቸው፡፡
    የዘውግ ፖለቲካው ከተሞችን ከገጠር በመጡ የዘውግ ፖለቲከኞች እንዲተዳደሩ ከማድረጉም በላይ በህገ-መንግስት በየትኛውም ዘውጋዊ ክልል ስር ያልተካለሉ እንደ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ያሉ ከተሞችን ወደ አጎራባች የዘውግ ክልሎች ማጠቃልልን ይመኛሉ፣ለገቢራዊነቱም ይታገላሉ፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን በህገ-መንግስቱ በየትኛውም የዘውግ ክልል ስር ያልተካለሉትን አዲስ አበባን እና ድሬዳውን በዙሪያቸው በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ለማስገባት ይታገላሉ፡፡ ይህ ገቢራዊ ቢሆን በእነዚህ ከተሞች ያሉ የሌላ ዘውግ ህዝቦች በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የሌላ ዘውግ ተወላጆች የሚያጋጥማቸው መገደል፣መፈናቀል፣መሰደድ፣ንብረትን መቀማት፣ከአስተዳደራዊ ውክልና መገለል ማንነትን ማጣት እንደማይደርስባቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
    የዘውግ ፖለቲካው እስካለ ድረስ ለዘውግ አስተዳደር የማይመቹት እነዚህ ከተሞች ቢያንስ በህገ-መንግስቱ ያላቸውን በከተማ አስተዳደር ምክርቤት የመተዳደር መብታቸው እንዲጠበቅ መታገል የሁሉም የሃገራችን ህዝብ ፋንታ ቢሆንም በእነዚህ ከተሞች በብዛት የሚኖሩት የአማራ ዘውግ አባላት በመሆናቸው የአማራ ብሄርተኞች በዋናነት ትግሉን መምራት አለባቸው፡፡ ይህን ትግል ምቹ የሚያደርገው ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን በሻረ ሁኔታ ከተሞቹን በባለቤትነት ለመጠቅለል የሚፈልጉት የኦሮሞ ብሄርተኞች ህገ-መንግስቱንም የሚደግፉ አካላት መሆናቸው ነው፡፡
    12.10 በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች
    በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል እጅግ ፈርጀ ብዙ ችግሮችን የተሸከመ ክልል ነው፡፡ ከህወሃት ጋር የተደረገው ጦርነት በሃገር ደረጃ የተደረገ ነው ቢባልም ትልቁን የኢኮኖሚ እና የሰብዓዊ ኪሳራ የጣለው በአማራ ክልል ላይ ነው፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር የአማራ ክልል ቀድሞ ባልታቀደ መንገድ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ለጦርነቱ እንዲያውል ቢደረግም የፌደራል መንግስቱ ይህን በጀት ለክልሉ ስለሚተካበት ሁኔታ አንስቶ አያውቅም፡፡
    በሰብዓዊ ኪሳራም ቢሆን የአማራ ክልል በርካታ ህዝብ ህይወቱን ያጣበት የተፈናቀለበትና የተዘረፈበት ጦርነት ነው፡፡ ሆኖም ይህን ኪሳራ ማን ሊሸፍነው እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የዚህ ኪሳራ ተፅዕኖው ክልሉን ሰላሳ አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ወደኋላ የሚጎትት እንደሆነ የክልሉ መንግስት ጥናት እንደሰራ ጠቅሶ እያስታወቀ ነው፡፡ይህን ኪሳራ ለማካካስ ከመንግስት ጋር ከመነጋገር ባሻገር የአማራ ብሄርተኞች መንግስታዊ ካልሆኑ የበጀት ምንጮች በሚነሳ የኢኮኖሚ እገዛ ክልሉ ለማገገም ያስፈልገዋል ከተባለው ሰላሳ አመት ቀድሞ እንዲያንሰራራ መስራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ማለት ከረጅ ድርጅቶች ከሚገኙ እርዳታዎች ውስጥ በጦርነት የደቀቀው የአማራ ክልልን መልሶ ለማቋቋም የተለየ ትኩረት ባለው መንገድ መመደብ አለበት፡፡ በተጨማሪም በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ያሉ የአማራ ተወላጆችና የክልሉ ህዝብ ጉዳት የሚሰማቸው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የቻሉትን የሚረዱበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡
    ሌላው መታለፍ የሌለበት የአማራ ብሄርተኞች ያለመታከት መንግስትን መጠየቅ ያለባቸው በድርድር ወቅትም ማስተጋባት ያለባቸው ወቅታዊ አጀንዳ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ የነበሩና ከመንገድ ላይ ተጠልፈው ደብዛቸው የጠፋው የአማራ ተማሪዎች ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ቁርጡ መታወቅ ያለበት በመሆኑ መንግስት እውነተኛውን ነገር ለተማሪዎቹ ቤተሰቦችም ሆነ ለአማራ ህዝብ እንዲያሳውቅ ከፍተኛ ትግል ማድረግ አለባቸው፡፡
  5. በብሄራዊ ምክክሩ የአማራ ህዝብ በማን ይወከል?
    ሃገራዊ የምክክር መድረኩ ለድርድር የሚጋብዛቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እና በውይይቱ የሚቀመጡ ተሳታፊ አካላት ብዛት ምን ያህል እንደሚሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ ማወቅ አልተቻልም፡፡ ሆኖም የሃገራችን ፖለቲካ ማጠንጠኛው ዘውግ በመሆኑ በሃገሪቱ ያሉ ዘውጎች ወኪሎች ናቸው በሚባሉ አካላት በዋናነት የድርድሩ ተካፋይ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል፡፡ የአማራ ህዝብም በዘውጉ ወኪሎች አማካይነት እንደሚወከል ከግምት በዘለለ ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ የአማራ ዘውግ በማን ይወከል የሚለው ነው፡፡
    የአማራን ዘውግ ወክለው የሚገቡ አካላት ቁጥር ያልታወቀ ስለሆነ እነማን በምን መጠን ይግቡ የሚለውን አሁን ባለንበት ሁኔታ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ አሁን ላይ መናገር የሚቻለው የአማራን ህዝብ ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለማቅረብ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ስልት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአማራ ህዝብ በዘውግ ፖለቲካው ሳቢያ የደረሰበት በደል ፈርጀ ብዙ እና በተለያየ መንገድ የሚገለፅ ነው፡፡ ይህን ፈርጀ ብዙ ችግር በተገቢው ሁኔታ ለማቅረብ ደግሞ በተለያየ የህይወት መስመር የተሰለፉ የአማራ ዘውግ አባላት መካተት አለባቸው፡፡ ከተለያየ የህይወት መስመር የተውጣጡ የአማራ ዘውግ አባላትን ማሳተፉ የሚጠቅመው አማራ በመሆናቸው የደረሰባቸውን ወይም በሌሎች ላይ ሲደርስ ያስተዋሉትን በደል እንደየ የህይወት መስመራቸው ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑና ሁሉንም ተግዳሮቶች ይዞ ወደ ድርድሩ መግባት አስፈላጊ ስለሆነ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄ አንግቦ ወደ ድርድር መግባቱ ውጤታማ ድርድር ለማድረግ ይበጃል፡፡ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ ድርጅት መስርተው ለአማራው ህዝብ የሚታገሉ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡
    የህይወት ልምዳቸው ያስተዋወቃቸውን የአማራ ህዝብ ተግዳሮቶች ለማስረዳት በውይይቱ ሊሳተፉ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመጥቀስ ያህል የመጀመሪያዎቹ ተሳታፊዎች መሆን ያለባቸው ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆች ናቸው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በህይወት ልምዳቸው ካለፉበት ሁኔታ በመነሳት እዚህ ሰነድ ላይ ከተቀመጠው የአማራ ህዝብ ችግር በተጨማሪ የሚያመጧቸው የመደራደሪያ ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ሌሎች መሳተፍ ያለባቸው አካላት በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ አማሮች ናቸው፡፡ የአማራ ተማሪዎች ማህበርም በዚህ ድርድር መሳተፍ ያለበት ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚማሩ ተማሪዎች እገታን ጨምሮ በርካታ ዘውግ ተኮር የመብት ጥሰቶችንና እንግልቶችን የሚያስተናግዱ ስለሆነ በድርድሩ ውስጥ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል፡፡የአማራን ህዝብ ጥያቄ አንግበው የሚታገሉ የአማራ ዘውግ ተኮር ፓርቲዎች የድርድሩ አካል ሊሆኑ ይገባል፡፡በሃገራችን በተለያዩ ክልሎች በሚነሱ ዘውግ ተኮር ግጭቶች ንብረቶቻቸው የሚወድሙባቸውና ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳረጉ የአማራ ባለሃብቶችም የድርድሩ አካል መሆን አለባቸው፡፡
    የሃገራችን ፖለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ የዲያስፖራውን ሚና የሚፈልግ በመሆኑ የአማራ ዲያስፖራዎች በድርጅትም ሆነ በግል ሊሳተፉ ይገባል፡፡ ሆኖም መንግስት በድርድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ብቻ ናቸው ስላለ የዲያስፖራው ቀጥተኛ ተሳታፊነት አጠያያቂ ነው፡፡ ሆኖም ዲያስፖራው በቀጥታ መሳተፍ ባይችል አንኳን ከሚሳተፉ አካላት ወደ ድርድር መድረኩ ከመግባታቸው በፊት ተገናኝቶ ሃሳቡ በእነሱ በኩል እንዲንፀባረቅ ሚያስችሉ ውይይቶች ማድረግ ይቻላል፡፡ ሌላው በድርድሩ መሳተፍ ያለበት አካል ከቅርብ ጊዜ ውዲህ የአማራ ብሄርተኝነት አይነተኛ ወኪል ተደርጎ እየተወሰደ ያለው ፋኖ ነው፡፡ የአማራውን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃንና የማህበረሰብ አንቂዎች፣የአማራ ወጣቶች ማህበራት፣የአማራ ምሁራን መማክርት የውይይቱ ተሳታፊ መሆን ያለባቸው አካላት ናቸው፡፡ የአማራ ምሁራን መማክርት የትርክት ቅልበሳውን ትግል በሙያዊ ጥናት በተደገፈ ተጨባጭ ጥናታዊ መረጃ ማስደገፍ የሚያስችል አቅም ስላላቸው ለድርድሩ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የማይተካ ነው፡፡
    14.በድርድሩ የአማራ ሃይሎች ሊገጥሟቸው የሚችሉ ግዳሮቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
    14.1 የአማራውን በደል ለመስማት ያለመፈለግ ዝንባሌ
    አሁን በሃገራችን የሰፈነው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ አማራው በጅምላ ተገድሎ በስካቫተር ተዝቆ እስከመቀበር በደረሰ ሰብዓዊ ክብርን ባዋረደ ሁኔታ እየተበደለ እንደሆነ በግልፅ እየታየም አማራው በዳይ ሆኖ እንዲቀርብ እንጅ ተበድሏል ብሎ ማመን አይፈልግም፡፡ይህ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት ተበድያለሁ ብሎ ማመንና ሎችን ማሳመን መቻል በዘውግ ፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ዋናው ቅድመ-ሁኔታ ስለሆነ ነው፡፡ራሱ አማራ በድሎኛል እያለ ወደ ስልጣን የመጣው የድህረ 1983 አስተዳደር አማራው በደሉ ይቆምለት ዘንድ ብቻ በደሉን ሲያስረዳ አማራውም ስልጣን እየጠየቀ ይመስለዋል፡፡ስለሆነም በደሉን መስማት አይፈልግም፡፡
    አማራው በአሁኑ ወቅት እየደረሰበት ያለው አይነት አልሰማም ቢሉት የማይቻል በደል ሲሆን ደግሞ በደሉን መካድ ስለማይቻል በደሉን ማቃለልን እንደ አማራጭ ይወስዳል፡፡ በደሉን ከማቃለሉ በተጨማሪ ማስቀየስ፣በሃገሪቱ በሁሉም ሰው ላይ የሚደርስ በደል እንደሆነ አስመስሎ ማስቀመጥ፣ እናስቆማለን የሚል ከልብ ያልሆነ መልስ መስጠትን፣ለድርጊቱ አማሮችን ራሳቸውን ተጠያቂ እስከማድረግ መሄድ ወዘተ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡
    ከቅርብ አመት ወዲህ የታየውን እጅግ አሰቃቂ የአማሮች ዘውግ የተለየ ግድያ ከአንዳንድ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር ማያያዝ ጭራሽ ግድያውን ያቀናበሩት በአካባቢው ወርቅ ለመቆፈር የፈለጉ የአማራ ባለሃብቶች ናቸው፣የሞቱት አማሮች ብቻ አይደሉም የሚል እጅግ አሳዛኝ መልስ ሲሰጥ ተሰምቷል፡፡ የአማራ ሃይሎች ለድርድር ሲቀርቡም ይህንኑ አይነት የመካድ ፣ የማድበስበስ ፣ የማስቀየስና፣ሃሰተኛ ተጓዳኝ ነገሮችን መፍጠር ዋናውን በደል ማስረሳት አይነት ችግሩን በደምብ እንዳያስረዱ የሚያደርግ ተግዳሮት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡
    እንደዚህ አይነት ችግር ሲገጥም የመጀመሪያው ወሳኝ መፍትሄ እዚህ አባባሎች የዘውግ ፖለቲካው ጠላቴ የሚለውን አማራን ሲያሳድድ ለመኖር ሲል የሚጠቀምባቸው አደገኛ ዘዴዎች እንደሆኑ የአማራ ሃይሎች ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውን በተገቢ መንገድ መግለፅ ያስፈልጋል፡፡ከዚህ ቀጥሎ የአማራ ሃይሎች ግልፅ ሊያደርጉት የሚገባው ነገር የዘውግ ፖለቲካው የአማራውን በደል መስማት የማይፈልገው ወይም የሚያድበሰብሰው አማራው መበደሉን ሲገልፅ ስልጣን ስጡኝ እያለ እንደሆነ ስለሚያስብ እንደሆነ ገልፀው እውነታው ግን እሱ እንዳልሆነ ይልቅስ በህይወት የመኖር መብቴ ይከበርልኝ የሚል የህልውና ጥያቄ እያቀረበ እንደሆነ አስረግጦ መንገር ነው፡፡
    ይህ ማለት አማራው የስልጣን ጥያቄ አያነሳም ማለት አለመሆኑን፣ይልቅስ በአሁኑ ወቅት የአማራው አንገብጋቢ ጥያቄ በህይወት የመኖር መብት መሆኑን ግልፅ ማድረግም ይገባል፡፡አማራው በህይወት የመኖር መብቱን ካስከበረ በኋላ በሃገሩ ፖለቲካ የመሳተፍ ሙሉ መብት ስላለው የስልጣን ጥያቄን የማንሳት ሙሉ መብት እንዳለው ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ይህን መንገር የሚያስፈልገው አማራው ተመልሶ መምጣት የሌለበት የድሮው ስርዓት ወኪል ስለሆነ ከሃገራዊ ስልጣን መገለል አለበት የሚለውን የዘውግ ፖለቲካውን ትርክት ለመታገል ነው፡፡ በተጨማሪ ዲሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀምም የዜግነት መብቱ ነው፡፡
    የአማራ ሃይሎች በሚገኙበት የድርድር መድረክ ሁሉ የአማራውን በደል ሲገልፁ አብረው ማንሳት ያለባቸው አሁን በአማራው ላይ እየተደረገ ያለው በደል እና የመንግስት ዝምታ የዘውግ ፖለቲካው አዲስ ሊፈጥራት እያሰባት ያለችው ኢትዮጵያ አማራውን የምታሳድድና የምትገድል ለመሆኗ ምልክት ሰጭ መሆኑን ነው፡፡ በአማራው በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ስም ስለተነሳ ብቻ እንዲህ ባለው አደገኛ ሁኔታ መስማማትና ከአማራጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ጋር መጓዝ እንደማይታሰብ መንገር ያስፈልጋል፡፡
    አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ የአማራውን በደል ለመስማት ያለመፈለጉ ሌላ መልክ በአማራ ሃይሎች የሚነሳውን የህገመንግስት ማሻሻያ ጥያቄ የሚገፋበት መንገድ ነው፡፡ የዘውግ ፖለቲከኞች አሁን ያለው የአማራውን መሳደድና መገደል “ህጋዊ” ያደረገውን ህገ-መንግስት ቀጣይነት በእጅጉ ይፈልጉታል፡፡በመሆኑም የአማራ ሃይሎች ህገመንግስቱ እንዲሻሸል/እንዲቀየር የሚያቀርቡትን ጥያቄ ለማጣጣል በህገመንግስቱ አማራው ለይቶ ጠቅሶ የሚጎዳበት አንቀፅ አልተቀመጠም ይላሉ፡፡የባሰው ደግሞ ለአንድ ክልል ስንል ህገመንግስት አንቀይርም የሚለው መልሳቸው ነው፡፡
    እንዲህ ያለ ተግዳሮት ሲገጥማቸው የአማራ ሃይሎ ማንሳት ያለባቸው ክርክር ህገመንግስት በአንቀፁ ብቻ ሳይሆን በተፃፈበት መንፈስ የሚበየን መሆኑን መግለፅ ነው፡፡ይህ ህገመንግስት የተፃፈበት መንፈስ ደግሞ አማራ መቀጣት ያለበት ጨቋኝ፣ቅኝ ገዥና ትምክህተኛ ነው የሚል ሲሆን፣ይህን የሚያምኑ የፖለቲካ ቡድኖች “አማራውን አከርካሪውን ሰብረን ጨርሰናል” በሚል የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሰክረው አድራጊ ፈጣሪ በሆኑበት የአፃፃፍ ሂደት የተፃፈ እንጅ ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ አልነበረም፡፡ከሁሉም በላይ የአማራ ህዝብ በፍፁም ያልተወከለበት ነበረ፡፡አማራው እንደዘውግ ተወክሎ አብሮ ባልፃፈው ህገ-መንግስት የመገዛት ግዴታ እንደሌለበት አበክሮ ማስረዳት ይጠበቃል፡፡ ይህ ሲባልም ኢህዴንን እንደ አማራ ወኪል አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ ይኖራል ይህን ተግዳሮትም የአማራ ሃይሎች እንዴት ማለፍ እንዳለባቸው በዚህ ሰነድ ከፍ ብሎ ተገልጧል፡፡
    14.2 የአማራ ህዝብን ጥያቄዎች የሌሎች ዘውጎችን መብቶች ለመንፈግ የሚደረግ ሙከራ አድርጎ ማየት
    የዘውግ ብሄርተኞች የአማራውን አከርካሪ መስበር አለብን በሚለው መርሃቸው አማራውን በእጅጉ የሚበድሉት አማራው ተጠናክሮ ታግሎ መብቱን ካስከበረ ሌሎች ብሄረሰቦች መብታቸውን ያጣሉ የሚል አደናጋሪ እሳቤ ስላላቸው ነው፡፡ከምክንያታዊነት የተፋታ መከራከሪያን አንግቦ እንደ ትክክለኛ እሳቤ መከራከር የዘውግ ፖለቲካችን መለያ ስለሆነ የአማራው መብት መከበር ማለት የሌሎች ብሄረሰቦች መብት መነጠቅ አድርገው ያስባሉ፡፡ሆኖም የአማራው መብት መከበርን አንፈልግም የሚለውን በግልፅ መናገር ስለማይቻል አማራው ለፖለቲካዊ ውክልና የሚያቀርበውን ጥያቄ የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ ሊያድበሰብሱ ይሞክራሉ፡፡
    የመጀመሪያው ማድበስበሻ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖረው አማራ ተበታትኖ ስለሚኖር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ፖለቲካዊ ሁኔታ መፍጠር አይቻልም ይላሉ፡፡ይህ በሁለት መንገድ ልክ አይደለም፡፡ አንደኛው አማራው በብዛት ተሰባስቦ ብቻ ሳይሆን ብዙሃን በሆነባቸው (ከ50+1 በላይ የህዝብ ቁጥር ይዞ በሚኖርባቸው) ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ ከተሞች ተገቢውን አስተዳደራዊ ውክልና እንዳያገኝ የኮታ ስርዓት በማምጣት በታሰበበት ሁኔታ ከአስተዳደራዊ ውክልና እንዲገለል ተደርጓል፡፡በተጨማሪም እንደ ደራ፣ወልቃይት፣መተከል ባሉ አማሮች ብዙሃን ሆነውም በአንድ አካባቢ ተሰብስበው በሚኖሩበት ሁኔታም በአስተዳደራዊ ውክልና ተነፍገዋል፡፡
    ሁለተኛው ሰዎች በሚኖሩበት ቦታ አስተዳደራዊ ውክልና የማግኘት መሰረታዊ መብታቸውን ለመጠቀም በአንድ ቦታ ላይ በርከት ብለው በዘውግ ተሰባስበው መገኘታቸው ግድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች በርከት ብለው በሚገኙበት ሁኔታ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን እንደሚደረገው በግዛታዊ ውክልና(Territorial Representation) በአስተዳደራዊ መዋቅር የሚወከሉ ሲሆን ተበታትነው የሚኖሩ ከሆነ ደግሞ ግዛታዊ ባልሆነ የውክልና(Non-Territorial Representation) በአስተዳደራዊ መዋቅሩ መወከል የሚገባቸው መሆኑን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የደነገጉት መብት ነው፡፡ይህን ጠቅሶ መከራከር የአማራ ሃይሎች ዋኛው የትግል አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡
    14.3 የአማራ ህዝብ እንደ ዘውግ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ከኢትዮጵያ ብሄተኝነት ጭብጥ ጋር እያቀላቀሉ ማደናገር
    የአማራ ህዝብ የሚያነሳቸውን የግዛት እና የማንነት ጥያቄዎች(በመተከል፣በደራ፣በወልቃይት ሁመራ፣በራያ ግዛቶች) ለማድበስበስ የዘውግ ፖለቲካው ግዛቶቹ የትም ቢሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ በዚህ ሁኔታ መታሰብ አለበት ሲሉ ለአማራ ህዝብ ስለኢትዮጵያዊነት እሴት ሊመክሩ ይሞክራቸዋል፡፡ሆኖም የአማራ ህዝብ እነዚህን ግዛቶች ለማስመለስ የሚጠይቀው በስፍራዎች እንደ ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ሳይስተናገድ ስለቀረ፣ጭራሽ አማራነቱ ወንጀል ሆኖ ህይወቱን አደጋ ላይ የጣለ ስጋት ስላንዣበበት ነው፡፡
    የአማራን ህዝብ ሌሎች ማንነት ተኮር ጥያቄዎች ከኢትዮጵያዊነት የመጉደል ወንጀል አድርገው የሚያነሱ የዘውግ ፖለቲከኞች በተግባራዊ ስራቸው በዘውጋቸው ተደራጅተው ስልጣን የያዙ፣አማራውንም በዘውጉ ለይተው የሚያሳድዱ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ስለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚወራው የሃገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ በዜግነት ዛቢያ የሚዞር ሲሆን ነው እንጅ ለአማራው ሲሆን ብቻ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን እንደ መሸሻ ማንሳት የሚያስኬድ ክርክር አይደለም፡፡የአማራ ህዝብ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳባቸውን ቦታዎች በህገ-መንግስቱ በሌላ ክልል የተካለሉ ስለሆኑ ማንሳት ልክ እንዳልሆነም ሲነገር ያጋጥማል፡፡ይህን የሚሉ ወገኖች ራሳቸው ህገመንግስቱ ለዘውጋቸው ክልል ያልመደባትን አዲስ አበባን እና ድሬዳዋን በይገባኛል የሚያነሱ ቡድኖች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ወገኖች የሚመለሰው ቀላል ክርክር የአማራ ህዝብ ሲረቀቅ ባልተሳተፈበት ህገመንግስት የመገዛት ግዴታ እንደሌለበት ነው፡፡
  6. ሃገራዊ ድርድሩ ለአማራ ህዝብ ሊያመጣ የሚችለው ፋይዳ
    የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት የተጋረጠበት ህዝብ በመሆኑ ሃገራዊ የውይይት፣የድርድር የምክክር መድረኮች ላይ ተኝቶ ጥያቁዎችን ጥርት ባለ ሁኔታ ማስተጋባት መቻሉ በአማራው አለመደራጀትና አለመጠናከር ላይ ህልውናውን ለገነባው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ ጎራ ትርጉም ያለው መልዕክት የሚልክ ነው፡፡ይህ መልዕክት አማራው ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ህልውና ሲል ለዘውግ ፖለቲካው የስልጣን ላይ መወጣጫ መሰላል ሆኖ መቀጠሉን እንዳቆመ የሚያስረዳ ነው፡፡ ይልቅስ አማራው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሄርተኝት እና በአማራ ብሄርተኝነት መካከል ሚዛናዊ መስተጋብር ሰርቶ ሁለቱንም የማይጎዳ ግን የአማራውን የህልውና ስጋት የሚያስቀር የትግል መስመር እንደ ጀመረ ለደጋፊውቹም ሆነ በወንጀለኛነት ለሚከሱት ተገዳዳሪዎቹ ማሳየት ይችላል፡፡
    አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ እድሜውን የሚያራዝመው ከዚህ ቀደም በዘውግ ተደራጅቶ ማንንም በድሎ የማያውቀውን አሁንም ቢሆን በዘውግ መደራጀቱን በተገቢው ሁኔታ ያላወቀበትን የአማራውን ዘውግ በማያውቀው የዘውግ ፖለቲካ ዘይቤ ግራ በማጋባት ነው፡፡ የዘውግ ፖለቲካው የአማራው ግራ መጋባት ለስልጣኑ እድሜ መራዘም ዋስትናው ስለሆነ የአማራው ዘውግ በዘላለማዊ ግራ መጋባት ውስጥ እንዲኖር ይመኛል፡፡አማራው በዘወግ ተደራጅቶ እንደዚህ ባሉ ሃገራዊ የድርድር/ምክክር መድረኮች መገኘቱ አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ጎራ የሚፈልገው የአማራ ግራ መጋባት እያበቃ እንደሆነ ምልክት ይሰጣል፡፡ ከዚህ ባለፈ የምክክር መድረኩ ለአማራ ህዝብም ሆነ ለሌሎች የሃገራችን ህዝቦች የመነጋገርን እድል የሚሰጥ ሊሆን ስለሚችል የሃገራችንን ፈርጀብዙ የፖለቲካ ችግር ለማቃለል በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
  7. የአማራ ህዝብ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ
    የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ያለበት ሁለንተናዊ ጉዳት ትህነግ አማራ ጠላቴ ነው ብሎ በ1968ቱ ማኒፌስቶ ከፃፈበት ጊዜ ጀምሮ የተሰራው አማራ ጠል ፕሮፖጋንዳ ውጤት ነው፡፡ ከ1983ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ ያለው አስተዳደር የሰው ለውጥ አምጥቷል እንጅ የአማራ ህዝብን በተመለከተ ያለው የቂም፣የአውዳሚነትና የጥፋት አጀንዳ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሆኖም የአማራው ልሂቅ በአብዛኛው የአማራን ህዝብ በደል ከትህነግ ጋር ብቻ አቆራኝቶ የሚያይ በመሆኑ አሁንም በርካታ የአማራ ልሂቅ ከህወሃት በበለጠ አማራውን ለአዋራጅ ሞት የዳረገውን ኦህዴድ መራሹን የብልፅግና ፓርቲ አስተዳደር በመደገፉ ቀጥሏል፡፡ በመሆኑም የአማራ ህዝብ በኦህዴድ መራሹ የብልፅግና አስተዳደር የሚደርስበት ፈርጀ-ብዙ ፖለቲካዊ በደል በሌላው ብቻ ሳይሆን በራሱ በአማራው ልሂቅ ወይ እንደ ሌለ ይቆጠራል ወይ ለብልፅግናው መንግስት ይቅርታ ለማድረግ በሚመች መልኩ እጅግ ተዛብቶ እና ተቃሎ ይቀርባል፡፡
    የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በሁለንተናዊ ክስረት ውስጥ ይገኛል፡፡ በፖለቲካው ረገድ ሃገር ለማስቀጠል ሲል ከሰፊው የኦሮሞ ህዝብ የወጡ ልሂቃን ስልጣን መያዛቸውን በመደገፍ በቻለው ሁሉ ለመርዳት ያደረገው ቅንነት በኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ ቁማር የመበላት ፖለቲካዊ አላዋቂነት ተደርጎ ተተርጉሟል፡፡ በመሆኑም የአማራ ህዝብ ይህንኑ የመብላት መበላት ፖለቲካ አሜን ብለው በተቀበሉ ቁማር አሳላጭ ምስለኔዎች በመመራቱ ቀጥሏል፡፡
    በፀጥታና ደህንነት ረገድ ግዝፈቱን በሚመጥን መልኩ ሌሎች ክልሎች እንደሚያደርጉት በጊዜ የሰለጠነ የክልል ልዩ ሃይል እንዳያሰለጥ በእነዚሁ ምስለኔ መሪዎች በመከልከሉ ለህወሃት ወረራ አጥር የሌለው ቤት ሆኖ እንዲጠብቅ ተፈርዶበታል፡፡በዚህ ሳቢያ የደረሰበትን በትህነግ አጥፊ ቡድን የመውደም ክስረት ደግሞ በአማራው ራስን መከላከል ያለመቻል ፈሪነት የመጣ ችግር ተደርጎ ሌላ የስነልቦና ስብራት ዘመቻ ተከፍቶበታል፡፡ ይህን ሆድ ሲያውቅ ሆነ የማጠልሸት አካሄድ ወደ ጎን ብሎ ራሱ መንግስት በጠራው የክተት ጥሪ በራሱ ስንቅና ትጥቅ ለመሳተፍ ሲሞክር ደግሞ የተለያዩ አሻጥሮችን በመስራት በቻለው አቅሙ ራሱን እንዳይከላከል ተደርጓል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የደህንነት ስጋትና ግራ መጋባት ውስጥ ይገኛል፡፡በኢኮኖሚው ረገድ ድሮም በማያወላዳው አቅሙ ላይ ከትህነግ ጋር የተደረገው ጦርነት ባመጣው ውድመት መመለሻው በጣም ሩቅ በሆነ ውድመት ውስጥ ይገኛል፡፡
  8. የአማራ ንቅናቄ የወደፊት ትግል እንዴት መቃኘት አለበት?
    የአማራ ንቅናቄ+

ትግል በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡበት ነው፡፡ይህን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት ትግሉ የተጋረጠበትን ፈተና በሚመጥን ብልሃት፣ቁርጠኝነትና መሰጠት መታገል አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡የአማራ ብሄርተኝነት እስካሁን የተጓዘባቸው መንገዶች በጎ ጅምሮች ቢሆኑም በፈተና የተሞሉ እምብዛም ስኬት ያልተመዘገባቸው መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡እነዚህን ፈተናዎች ለመቀነስና ወደ ስኬት ለመራመድ ትግሉ ራሱን መፈተሽ 69ያስፈልገዋል፡፡ የአማራ ብሄተኝነት በሰላማዊ ታጋዮች በብልሃት ተይዞ ወደ ስኬት መሻገር ካልቻለ ትግሉን ያመጣው በደል ምሬት ወዳልተፈለገና የአማራን ህዝብ ራሱን ወደማይጠቅም የትጥቅ ትግል ሊቀየር ስለሚችል የሰላማዊ ትግል ጎራው በፍጥነት ወደ ስኬት በሚያራምዱት ጎዳናዎች መግባት ግድ ይለዋል፡፡
በዚህ ሰነድ ፀሃፊ እምነት የአማራ ህዝብ ትግል ከታች የተዘረዘሩትን የትግል ዘይቤዎች አጥብቆ ቢይዝ በአጭር ጊዜ ስኬታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡
17.1 ትግሉ ብዥታ በሌለው የትግል መስመር እና ከፈራተባ በፀዳ ቁርጠኝነት ሊመራ ይገባል
የአማራ ንቅናቄ ብዙ እድሜን ያስቆጠረ ባለመሆኑ ትግሉን አስፈላጊ ያደረጉ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችን ዘርዝሮ ምሉዕ በሆነ መንድ በማቅረብ ረገድና እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ትግሉ ሊከተለው የሚገባው የጠራ የትግል መስመር ይዞ መጓዝ ላይ ብዙ የሚቀረው ነው፡፡በመሆኑም የአማራ ብሄርተኝነትን የሚደግፈውም ሆነ በትግሉ ፊተኛ መስመር ተሰልፎ የሚታገለው ልሂቅ ራሱ አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ለሚያቀርብበትን የሃሳብም ሆነ ሌላ ተግዳሮት በቂ ምከታ ማድረግ አልቻልም፡፡በዚህም ምክንያት የአማራን ሰፊ ህዝብ አመኔታ ማግኘት አልቻለም፡፡ለዚህ ምስክሩ በቅርቡ በተደረገው ሃገራዊ ምርጫ የአማራ ዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያገኙት አናሳ ድምፅ ነው፡፡
የጠራ የትግል መስመር ማውጣቱ ብቻም በቂ ስለማይሆን የአማራ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄዎችን ነቅሶ አውጥቶ ከልሂቃኑ ባሻገር በማህበረሰቡ ልቦና እንዲሰርፁ ማድረግ የአማራ ህዝብ ትግሉን የራሱ አድርጎ እንዲወስድ ያግዛል፡፡የአማራ ንቅናቄ ለአማራ ህዝብ የሚነግረው ጥያቄ በህዝቡ ልቦና ያለ፣ህዝቡ ቀን ከቀን የሚኖረው ስቃዩንና ስጋቱን ነው፡፡ ስለሆነም ንቅናቄውየሚጠበቅበት እነዚህን ጥያቄዎች በየፈርጁ ሰንዶ፣ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሚስፈልገውን የትግል ስትራቴጂ አክሎ ማቅረብ ብቻ ስለሚሆን ስራውን ቀላል ያደርገውል፡፡
የጠራ የትግል መስመርን መከተል በሚለው ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ሳይነሳ የማይታለፈው ጉዳይ የአማራ ንቅናቄ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ያለውን የማይጋጭ መስተጋብር ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ ለሚወደው የአማራ ህዝብ ሳያሰልሱ ማስረዳት ለትግሉ ስኬታማነት ቁልፉ ተግባር መሆኑን ነው፡፡
17.2. ሰፊ የማደራጀት ስራ መስራት
የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች በግልፅ ካስቀመጡና ጥያቄዎቹን ለማስመለስ የሚኬድባቸውን የትግል ስልቶች ነድፎ በሰፊው ህዝብ ልቦና የማስረፅ ስራው ከተሰራ/ከተጀመረ በኋላ መከተል ያለበት ሌላ ተግባር ህዝብን ማደራጀትና ለትግል አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ማቅረብ ነው፡፡ ማደራጀት በፖለቲካ ፓርቲ፣በሲቪክ ማህበራት፣የአማራን ጉዳይ ትኩረት አድርገው በሚሰሩ ሚዲያዎች ውስጥ ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ የተለያዩ አደረጃጀት ላይ ያሉ አካላት ለአንድ አላማ በመስራት ረገድ ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት ማመቻቸትም ሌላው የማደራጀት ስራው ገፅታ ነው፡፡እነዚህ አደረጃጀቶች ደግሞ አስፈላጊው ግብዓት ሊሟላላቸው ይገባልና ሰፊ የበጀት ምንጭን ማፈላለግም የአማራ ንቅናቄን በተደራጀ መንገድ የማቆሙ ስራ ዋነኛ አካል ነው፡፡
17.3 ጥብቅ የትግል ስነ-ምግባር መርህን መከተል
ማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንዲሆን ትግሉን የሚመሩ መሪዎች፣ደጋፊዎችና አባላት ጥብቅ የትግል ስነ-ምግባር መርህ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ጥብቅ የስነምግባር መርህ የሚገለጥበት የመጀመሪያው ጉዳይ የትግል አላማን እና መስመርን ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡፡ከዚህ በኋላ የሚመጣው ደግሞ ላወቁት የትግል አላማና መስመር በሁኔታዎች የማይናወጥ ፅኑ አቋም መያዝ ነው፡፡ከዚህ አንፃር ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በኋላ የእሳቸውን የአላማ ፅናት ፈለግ ተከትሎ የአማራ ንቅናቄን በፀና አቋም መምራት የሚችሉ አመራሮች እንደ ቡድንም ሆነ እንደግለሰብ ማግኘት አዳጋች ሆኗል፡፡ በምትኩ በገንዘብም ሆነ በፖለቲካ አቋም ረገድ የህዝብን አደራ ይዘው የሚጠፉና ትግሉን የሚያዳክሙ ወገኖች ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ የአማራ ንቅናቄ የአማራን ህዝብ ልብ አግኝቶ በፍጥነት እንዳይራመድ እግር ከወርች ካሰሩ ጉዳዮች ዋነኛው ነው፡፡
የአማራ ንቅናቄን ጎራ የሚመሩ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ጥብቅ የትግል ስነ-ምግባር መሰጠት እንዲጎድላቸው ካደረጉ ነገሮች ዋነኛው የአማራን መደራጀት አጥብቆ የሚጠላው ስልጣን የያዘው አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ የሚጋርጠው ተግዳሮትና የሚቀርበው ማማለያ ነው፡፡ የሚጋርጠው ተግዳሮት በፕሮፌሰር አስራት ላይ ደርሶ ህይወትን እስከመቀማት የደረሰ ማዋከብና ነው፡፡የአማራ ንቅናቄ ትግልን መቀላቀል በአደገኝነቱ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ የትግል መስመር የተሰለፈ ሰው የትግሉን ጀማሪ ፕሮፌሰር አስራት መረዳት፣መሰጠትና ቁርጠኝት ሊላበስ ይገባል፡፡ይህን ማድረግ ካልተቻለ የዘውግ ፖለቲካው ለሚያቀርበው ስልጣንን የጨመረ የማማለያ ፈተና ወዳቂ ተፈታኝ ከመሆኑም በላይ ትግሉንም አብሮ የመጣል ችግር ያመጣል ማለት ነው፡፡
የአማራ ንቅናቄ ጎራ መሪዎችና አባላት ለያዙት ትግል ጥብቅ መሰጠት ይኑራቸው ማለት ከማንም ጋር አይደራደሩ፣የሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ ውስጥ አይግቡ ማለት አይደለም፡፡ይልቅስ ሲደራደሩና ሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ ዋናውን የአማራ ህዝብ ጥያቄ አሳልፈው ሰጥተው የዘውግ ፖለቲካውን አጀንዳ ተቀብለው አይምጡ፤የሚሰጡትንና የሚቀበሉትን ጠንቅቀው ይወቁ ለማለት ነው፡፡

መደምደሚያ
በአሁኑ ወቅት ሃገራችን የምትገኝበት የዘውግ ፖለቲካ መስተጋብር የትግል ውጤት ነው፡፡ይህ ፖለቲካዊ መስተጋብር አማራው እንደ ዘውግ ዘውጋችንን በድሏል፣ጨቁኗል፣በዝብዟል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎች በትብብርም በተናጠልም ከግማሽ ምዕተ አመት ላላነሰ ጊዜ ታግለው ያመጡት ስርዓት ነው፡፡እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች የመሰረቱት የፖለቲካ ስርዓት ጨቆነን ብለው እንደ ዘውግ ለታገሉት የአማራ ህዝብ ምቹ እና ተስማሚ እንደማይሆን ግልፅ ነው፡፡በመሆኑም በዚህ ስርዓት ውስጥ አማራው እንደ ዘውግ የህልውና ስጋትን በመሰለ ዋስትና የማጣት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፤እጅግ አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፣የዲሞክራሲያዊ መብቶች በሸራረፍን፣የስነ-ልቦና ስብራትን፣መፈናቀል፣የሃብት ንብረት ማጣትን፣ከዋነኛ ሃገራዊ ፖለቲካ መስተጋብሮች መገፋትን፣በዘውግ ተለይቶ መክፋፋትን አይነት ከባድ በደሎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
በዘውጉ ምክንያት ይህን ሁሉ የመከራ ፅዋ ሲጎነጭ የኖረው የአማራ ህዝብ ታዲያ ዘውጉን ጠቅሶ ለሚያሳድድው ስርዓት በዘውጉ ተደራጅቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አልቻለም፡፡ይልቅስ በዘውጉ ተለይቶ ለሚደርስበት ሁለንተናዊ በደል ዘውግ ዘለል በሆነ ማዕቀፍ ለመፍታት በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ስር እንታገላለን የሚሉ ፓርቲዎች እና ድርጅቶች ስር ታቅፎ ሲታገል ቆይቷል፡፡ይህም ቢሆን በአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲ ልሂቃን ዘንድ አልተወደደለትም፤በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥም ቢሆን የአማራው ህዝብ ህልውና ስጋት በተገቢው መንገድ የማታገያ አጀንዳ ሆኖ አልቀረበም፡፡ አማራው በዘውጉ ለመደራጀት መዘግየቱም ሌሎችን ብሄረሰቦች የመጨፍለቅ ፍላጎቱ፣”የበለጥኩ ኢትዮጵያዊ ነኝና የበለጠ ለኢትዮጵያ አስባለሁ የማለት የትምክህተኝነቱ” መገለጫ ተደርጎ ተወሰደ፡፡በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው መከራ እየበረታ ሲሄድ አማራውን ለማደራጀት የተደረጉ አንዳንድ ሙከራዎች ሲታዩም ደግሞ ለአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ምቾት የሚሰጥ አልሆነም፡፡የአማራ ጠሉ የዘውግ ብሄርተኝነት ዋነኛው ተፈጥሮ በየትኛውም የክርክር ገፅ አማራውን ማክፋፋት፣ማጣጣል፣መቃወምና መጠራጠር በመሆኑ ምክንያት ነው በዘውግ መደራጀቱም አለመደራጀቱም አማራውን እኩል የሚያስወቅሰው፡፡
በዘውግ መደራጀቱም፣ አለመደራጀቱም የሚያስወቅሰው የአማራው ልሂቅ ታዲያ ከሶስት አስርተ አመታት በላይ ስልጣን ላይ ያለው አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ አማራውን እንዴት እንደሚመለከተው ለመገንዘብ ረዥም ጊዜን ወስዶበታል፡፡ በመሆኑም አማራው በዘውግ የመጣበትን ፈተና በዘውግ ተደራጅቶ ለመመከት የሚደረገው ሙከራ ከአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲከኞች እኩል ከአማራው ልሂቅም ተቃውሞ ይገጥመዋል፡፡በመሆኑም “የአማራ ንቅናቄ ያስፈልጋል አያስፈልግም?” የሚለው ክርክር የዋናውን የትግል ቦታ ጋርዶ ኖሯል፡፡
“የአማራ ንቅናቄ አያስፈልግም፣የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ስር በሚገታሉ ፓርቲዎች ስር ሆኖ በመታገል ችግሩን መፍታት ይችላል” ብለው የተሰለፉ የአማራ ልሂቃን አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ለአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ጉልበት ሆነዋል፡፡እነዚህ ወገኖች ለአማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ ጉልበት የሚሆኑበት ወሳኝ ነገር ፖለቲካዋ ሁሉ ዘውግ በሆነችው ሃገራችን የአማራውን በዘውግ መደራጀት እንደ ዘረኝነትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደመተባበር አድርገው በመቁጠር በአደባባይ ሊያወግዙ የሚቃጣቸው መሆኑ ነው፡፡በዚህ ሳቢያ አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ በሄደበት መንገድ ሄደው፣ የአማራን ህዝብ መብት ሊያስከብሩ የሚችሉ የአማራ ልሂቃን ዘረኛ እና ኢትዮጵያን አፍራሽ ላለመባል ሲሉ ብቻ በህዝባቸው መከራ ላይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያን የረዱ መስሏቸው የኢትዮጵያን ስም እየጠራ አማራውን ለሚያርደው ስርዓት የድጋፍ እጅ ይዘረጋሉ፡፡እንዲህ ያለው የአማራ ልሂቃን አቋም ስልጣን ላይ ያለው አማራ ጠል የዘውግ ፖለቲካ የጥላቻውን ምሬት ያህል አማራውን ያለጠያቂ እንዲገድልና እንዲያሳድድ ረድቶታል፡፡ በመሆኑም የአማራው አሰቃቂ ሞት፣የስነልቦና ስብራት፣ጠበቃ አልቦ ተሳዳጅነት እንደ ተገቢ የአዘቦት ተግባር ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
የቀጠለው የአማራው አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣መሳደድና መገለል እንዳይመጣ ሲገፋ የነበረውን የአማራ እንቅስቃሴ ግድ ብሏል፡፡ የአማራ ንቅናቄ እጅግ ዘግይቶ በመጀመሩ ሳቢያ እንዲሁም የሚታገለው ስልጣን የያዘን አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብን እንግልት ሊረዱ ያልቻሉ/ያልፈለጉ የአማራ ልሂቃንን ጭምር በመሆኑ በብዙ ፈተና የተሞላ ነው፡፡ እነዚህን ፈተናዎች አልፎ ከትርክትነት ተሻግሮ ስልጣን የያዘውን አማራ ጠል አስተሳሰብ ለመታገልና የአማራን ህዝብ ለመታደግ ከፍተኛ መሰጠት፣ቁርጠኝነት ጥንቃቄና ብስለት የተሞላበት ትግል ይጠይቃል፡፡ይህን ለማሳካት ደግሞ የተገዳዳሪን ማንነት ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
የአማራ ንቅናቄ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ያደረገው አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ እየሄደበት ያለው አማራውን የህልውና አደጋ ውስጥ የከተተ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አሳሳቢ እርምጃ ነው፡፡በሃገራችን ከ1983ዓም ጀምሮ እስካሁን በስልጣን ላይ ያለው አስተሳሰብ አይነተኛ መለያው አማራ ጠልነት ነው፡፡ ሆኖም ስልጣን ላይ ለመውጣትም ሆነ ስልጣን ላይ ለመቆየት ደግሞ የአማራውን ድጋፍ ማግኘትን ስለሚፈልግ መሰረታዊ ባህሪው የሆነውን አማራ ጠልነት ለመደበቅ የተለያዩ የመሸፋፈኛ ስልቶችን ይጠቀማል፡፡እነዚህን ስልቶች ለይቶ አውጥቶ በመታገል አማራ ጠሉ ስርዓት አማራውን ራሱን ተጠቅሞ ተመልሶ አማራውን የሚያሳድድበትን እድሜውን እንዳያራዝም መፋለም የአማራ ንቅናቄ ዋነኛ የትግል አቅጣጫ ሊሆን ይገባል፡፡
ከሰላሳ አመታት ለበለጠ ጊዜ ስልጣን ላይ ያለው ስርዓት መሰረታዊ ባህሪው የሆነውን አማራ ጠልነት ለመሸፋፈን ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ የሚታገለው የአማራ ገዥ መደብን እንጅ ከአማራ ህዝብ ጋር ምንም አይነት ችግር እንደ ሌለበት መስበክ ነው፡፡ ሆኖም ይህን እየሰበከ የሚገድለውና የሚያሳድደው ደሃውን የአማራ ገበሬና ለፍቶ አዳሪ ህዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ አባባል “በአሁኑ ወቅት የምትታገሉት የአማራ ገዥ መደብ ማን ነው?” የሚል ወሳኝ ጥያቄ ሊቀርብለት ይገባል፡፡በተጨማሪም እያሳደደ እየገደለው ስለኖረው ለፍቶ አዳሪ ደሃ የአማራ ህዝብ ህይወት እና ንብረት ተጠያቂ እንዲሆን መታገል የአማራ ብሄርተኝነት ዋና ዓላማ ነው፡፡
ከትህነግ ስልጣን የተቀበለው የአማራ ጠል ፖለቲካው አስቀጣይ ቡድን አማራ ጠልነቱን ለመደበቅ ትህነግ ሲለው ከነበረው “የምታገለው የአማራ ገዥ መደብን ነው” ከሚለው መሸፋፈኛ በተጨማሪ እጅግ አሳሳች የሆነ፣በዘውግ ፖለቲካው ዘንድ ታይቶ የማይታወቅ ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ አቋም በማሳየት ከሚያሳድደው የአማራ ህዝብ ሁነኛ ተቃውሞ እንዳይገጥመው ለማድረግ ይሞክራል፡፡ አሁን ስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን ይህን ተለዋዋጭና አሳሳች ባህሪውን “በማሳመን እና/ወይም በማደናገር መምራት” (Rule by convinse and/or confuse) ሲል ይገልፀዋል፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ ቀመሩ መሰረት በአማራው በኩል የሚጠላትን ኢትዮጵያን እንደሚወዳት፣እንደሚጠብቃት፣ህልውናዋ እንደሚያሳስበው እየነገረ ኢትዮጵያን ሲል ብዙ መከራን እየተቀበለ ያለውን የአማራ ህዝብ በዘውጉ ለይቶ ይገድላል፣ያፈናቅላል፣ያሳድዳል፡፡ለአማራው ሞት ስደት መንግስታዊ መፍትሄ ለመስጠት አማራ ጠል ተፈጥሮው ስለማይፈቅድለት በዝምታ ወይም በማድረግ ወንጀሉን ያስቀጥላል፡፡ ይህን አደገኛ የዘውግ ፖለቲካው ልውጥ ባህሪ ተረድቶ ተገቢውን ትግል ማድረግ የአማራ ንቅናቄ የመፈጠሩ ዓላማ ነው፡፡ ይህን የአማራን ህዝብ ህልውና ያህል አስፈላጊ የሆነ ትግል መደገፍ ደግሞ አማራ ነኝ የሚል አካል ሁሉ ድርሻ ነው፡፡

የህዳግ መዘርዝር
1 በዚህ ሰነድ ሁኔታ “የአማራ ህዝብ/የአማራ ዘውግ አባላት” የሚለው አባባል ራሳቸውን በአማራ ዘውግ አባልነት የሚገልፁ ወይም በሌሎች አማራ ተብለው የሚጠሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ይወክላል
2John Markakis, National and class conflict in the horn of Africa (Shama books press, Addis Ababa, 2012).pp,261-290.; Amanuel Tesfaye, “Birth of Amhara Nationalism: Causes, Aspirations and Potential Impacts”,Addis Standard, 4 may 2018,‹https://addisstandard.com/commentarythe-birth-of-amhara-nationalism-causes-aspirations-and-potential-impacts›
3መስከረም አበራ፣ የዘውግ ፖለቲካ ስር መሰረቶች (ማንኩሳ አሳታሚ፣አዲስ አበባ ፣ 2013) .ገጽ ፣330-336)
4 Wallelign Mekonen,”On the Questions on Nationalities in Ethiopia”,HSIU;Arts IV,Nov.17,1969.pp,1.
5 Ibid, pp 2.
6 Ibid
7 የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት፣መግለጫ፣(የመጀመሪያ ዕትም፣የካቲት፣1968)፣ገጽ.15-16
8Ademola,A.,ThePoliticizationofEthnicityasSourceofConflict,pp68 .
9Seregew Hable Silase, Ancient and Medieval Ethiopian History (Addis
Ababa: United Printers, 1972) pp 34-38
10 Y.Ghai,” Ethinicity and Autonomy: A Framework for analysis”, in Y.Ghani(ed), Autonomy and Ethnicity ፡Negotiating competing claims in multi-ethnic states, Cambridge University Press(2001),pp.1-20
11 Yonatan Tesfaye and Chrisophe V.D Beken , Ethnic Federalism and Internal Minorities: the Legal protection of internal minorities in Ethiopia, African Journal of International and comparative law(2013),pp 32
12 Ibid, pp,34
13 Ibid, pp,41
14 ተገኘ ዘርጋው፣ “በኢትዮጵያ የህገ-መንግስት ማሻሻያ አስፈላጊነት” (አመታዊ የጥናታዊ ፅሁፍ ኮንፍረንስ፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣2013)
15 ያው
16 ያው
17 ያው
18 Tezera Tazebew, Amhara Nationalism: the Empire Strikes Back, Journal of African Affairs (2021), pp,298.
19ያው ፣ ገፅ 299
20 Heran Sereke-Birhan, Ethiopia: A Historical consideration of Amhara ethnicity”, In Harold G.Marcus(ed),New Trends in Ethiopian studies: proceedings of the XII International conference of Ethiopian Studies, Vol.I(Red Sea Press,Lawrenceville,NJ,1994),pp.758.
21 Michel Foucault, The history of Sexuality : An introduction, Vol.1(Pantheon Books,New York,NY,1978),p.101.
22 ያው
23 World Bank (2017).What Studies In Spatial Development Show in Ethiopia. Accessed from http://blogs.worldbank.org/africacan/what-studies-in-spatial-development-show-in-ethiopia-part-ii
24 Amanuel Tesfaye, “Birth of Amhara Nationalism: Causes, Aspirations and Potential Impacts”,Addis Standard, 4 may 2018,‹https://addisstandard.com/commentarythe-birth-of-amhara-nationalism-causes-aspirations-and-potential-impacts›

meskerem-abera

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator