በፋኖ ላይ መዝመት በአማራ ህልውና ላይ መዝመት ማለት ነው!

በቅርቡ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ለዘመናት ተከባብሮ በሚኖረው በሙስሊሙና በክርስቲያኑ ማህበረሰብ የተፈጠረው ግጭት መነሻው የቀብር ድንጋይ ነው ብሎ መቀበል በስተጀርባ ሆነው ሴራውን ላቀነባበሩትና ጠቡን ለቆሰቆሱት ወንጀለኞች ሽፋን መስጠት ነው ብለን እናምናለን።

በተለይም ባለፈው አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ሰላም በተነሳችበት፣ ሚሊዮኖች በተፈናቀሉበት፣ በመቶ ሺዎች ሕይወታቸውን ባጡበት፤ አማራው በቤኒሻንጉል-ጉሙዝና በኦሮሚ ያ ክልሎች በየጊዜው በማንነቱ በሚታረድበት፣ በአማራና በአፋር ክልል ከተማዎች በተደመሰሱበትና ከሁሉም በላይ ዶ/ር አብይ አህድ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታትና ድራሹን ለማጥፋት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት በጎንደር ላይ የተፈጠረውን ከቀብር ድንጋይ ጋር ማያያዝ ነገሩን ማቅለል ይመስለናል።

የሀገር ሽማግሌውን ሸህ ከማል ለጋስን ለመቅበር በተሰበሰበው የሙስሊም ወግኖቻችን ላይ ቦንብ የወረወረው ግለሰብ ወይም ስብስብ ወንጀሉን የፈፀወው የኦርቶዶክስ ቤተ-ከርስቲያን ተቆርቋሪ ስለሆነ ነው ብሎ መደምደም ከላይ የተጠቀሰውን የሃገራችንን ሁኔታ አለማገናዘብና ሴራውን ላቀነባበሩት ማምለጫ መንግድ መክፈት ይመስለናል።

እውነቱን ተገንዝቦ የችግሩን መንሥኤ ፊትፊት አለመጋፈጥ ማህበረሰቡን ለተከታታይ ጥቃት ማጋለጥ ነው ብለንም እናምናለን።

በዚህ አጋጣሚ በሀገር አፍራሾች ደባ ምክንያት ለሞቱት ሙስሊምና ክርስቲያን ወገኖቻችን ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን፤ የሁለቱም የእምነት ተከታዮች የፈረሱትን መስጊዶች በጋራ እንዲሰሯቸውና ጠላትን እንዲያሳፍሩም እናሳስባለን።

ሀገር የማፍረስ ፕሮጀክት ያነገበ ጠ/ሚንስትር በሚመራት ሀገር ጎንደር በተፈፀመው አሳዛኝ ተግባር የሌሎቹ እጅ መኖሩ ሊደንቀን አይገባም።

ነገሮች የተቀነባበሩ ስለሆነ ሁኔታውን የበለጠ ማጦዝ አሰፍስፎ ይጠብቅ የነበረው የአህመዲን ጀበል ፅንፈኛ የሰለፊ ቡድን በወራቤ በርከት ያሉ ቤተክርስቲያናትን ሲያቃጥል ጊዜ አልፈጀበትም።

እሳቱን ለማጥፋት የወጡ ሰዎችንም በመደብደብ የአካል ጕዳት አድርሷል። ይህ ቡድን ለአማራ ክልል እንግዳ አይደለም።

አጣዬ በተደጋጋሚ ስትወረርና ስትወድም እንዲሁም ወራሪው ሕወሃት ደብረሲና ሲደርስ በማህበራዊ ሚድያ በደሰታ ሲፈነድቅ ነበር።

ኦሮሚያ ክልል ሙስሊም አማራዎች በማንነታቸው በየጊዜው ሲታረዱ አንድም ቀን ድምፁን አሰምቶ ኢያውቅም።

ስለሆነም ይህ ቡድን ከጎንደር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባና በደሴ በሚገኙት ጀሌዎቹ አማካይነት በምኑም ላይ በሌበት ፋኖን አሸባሪ ነው፣ ፋኖ አክራሪ ክርስቲያን ነው የሚል ዘመቻ መክፈቱ ሊደንቀን አይገባም።

ለመሆኑ ፋኖን አክራሪ ክርስቲያን የሚለው በሰሜን ወሎ ፀረ-ወያኔ ትግሉን የሚመሩትን እነ ፋኖ ጄነራል ሃሰን ከረሞን ሙሊሞች አይደሉም እያለን ይሆን?

በጄነራል አሳምነው ፅጌ ስም የተሰየመውን እና ሁሉንም ያካተተውን የፋኖ ብርጌድ አዛዥ በሆኑት በእነ መሬ ዎዳጆ የሚመራውን ጦር ለማን አሳልፎ ሊሰጥ አስቦ ይሆን?

የሕወሃትን ምሽግ ሲሰብሩ የተሰውትን እነፋኖ ሙሐምድ ደጉንና ሰይድ ገረየስን እና ሌሎችንም በእምነታቸው የማይደራደሩ ሙስሊሞች እንደሆኑ ሊክደን ይሆን?

ሃቁ ግን ከአብይ አህመድ ጀምሮ ጀዋር መሃድ ከእሥር ከተፈታ ወዲህ የጠ/ሚንስትሩ ደጋፊ የሆነው ይህ ፅንፈኛ ቡድንና እንደ ኦፌኮ የመሰሉ ድርጅቶች የከነከናቸውና እንቅልፍ የነሳቸው ነገር ቢኖር ፋኖ የአማራው የጋራ እሴትና ሁሉን አቃፊ መሆኑ ነው። በፋኖ ውስጥ የነሱ ውድቀት ፍንትው ብሎም ስለሚታያቸው ነው።

አብይ አህመድ ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጣውንና ለአማራ ሕዝብ ህልውና ብሎም ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል የቆመውን ፋኖን እንደ ዋና ጠላት አድርጎ ከቆጠረው ዋል አደር ብሏል።

ጠ/ሚንስትሩ በሕወሃት ወረራ ጊዜ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለውን ፋኖን ስንቅና ትጥቅ እንዳይደርሰውና በባዶ ሆዱና እግሩ እንዲዋጋ ያደረገውና ዛሬም የሚያሳድደው አገር የማፍረስ አጀንዳውን የሚገዳደርበት ብቸኛ ኃይል ስለሆነ ነው።

ዛሬ ሕወሃት የፋኖን ያህል ለአብይ አህመድ አጀንዳ አይደለም፤ ማስረጃውም ብርሃኑ ጁላን ሲሸልስ ድረስ ልኮ ከሕወሃቱ ጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር ፋኖን በጋራ ስለማጥፋት ተደራድሯል።

ስለዚህ ፋኖን ለመምታት መንደርደሪያ እንዲሆን የጎንደሩ ግጭት መቀነባበር ነበረበት።

ዋና ተዋንያኖቹም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ባሕርዳርና ጎንደር የሚርመሰመሱት በተመስገን ጥሩነህ የሚመሩት የአብይ አህመድ ደህንነቶችና ሁኔታውን ያመቻቸላቸው ምን ጊዜም የወገኑ ጠላት የሆነው ብአዴን መሆናቸውን ሕዝቡ ሊያውቅ ይገባል እንላለን።
ተጠያቂዎቹም ወንጀለኞቹም እነሱ ናቸው።

ይህ መግለጫ እየወጣ ባለበት ሰዓት ደቡብ ወሎ ገራዶ የሚገኘውን የፋኖ ካምፕ አስከብቦታል።

በሰሜን ወሎ ከሕወሃት ኃይል ጋር ለተፋጠጠው የፋኖ ኃይል ደጀን የነበረውን የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አንስተውታል። ሴራውም ቀጥሏል።

ጀግናው የአማራ ሕዝብ ሀይ:_

ከሀገርህ ያለህ ክብርና ፍቅር ከስነልቦናህ የማይፋቅ ስለሆነ ለማንም ጥያቄ እንዲያነሳበት አትፍቀድለት።

ስለሆነም ዛሬ ያንተ ዋና አጀንዳ ህልውናህን ማስጠበቅ ብቻና ብቻ ነው። ዙሪያህን ሊያጠፉህ በሚፈልጉ ጠላቶች ተከበሃል።

በተለይም ሕወሃትና የኦሮሞ ብልጽግና እየተናበቡ የሚያሳዩህ መከራ መቼም አያባራም። ጄኔራል ተፈራ ማሞን ከሥልጣኑ ካነሱት በኋላ የክልልህን ልዩ ኃይል እየበተኑብህ ነው።

በህልውናህ ላይ የተቃጣብህን አደጋ ፈጽሞ ማጋነን አይቻልም። ስለሆነም ከልጅህ ከፋኖ ጎን ከመቼውም በበለጠ እንድትቆም ጥሪያችንን እናቀርብልሃለን።

ዕድሜያቸውና አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ልጆችን ፋኖን አንዲቀላቀሉ አድርግ።

አንተም ራስህ ፋኖ ነህና በመንደርህ፣ በቀበሌህና በወንዝህ በጎበዝ አለቃ ተደራጅ።

ነገር ግን ሁሉም አማራ አሁኑኑ በአንድነት ተደራጅቶ ህልውናውን ካላስጠበቀ በስተቀር “አማራ” የሚባል ሕዝብ እኮ እዚህ አካባቢ ይኖር ነበር የሚባልበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።

በቅርቡ የሚታየው የአማራን ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖን ተሸላሚና ያልተሸለመ በሚል ጨዋታ የአማራውን የህልውና መከታ የሆኑትን የአማራ ኃይሎችን በመከፋፈል የሚደረግ የብአዴን ብልጽግና ሌላ ዙር ሴራን በመገንዘብ ማክሸፍ ይገባል።

ለፋኖ፣ ለአማራን ልዩ ኃይል እና ለአማራ ሚሊሻና ሽልማታቸው የአማራን ህልውና በማስከበርና ሀገራቸውን በመታደግ የገቡበትን ታሪካዊ ትግል በድል መወጣት ነው።

አማራን በመላው ሀገሪቱ የአሰቃቂ ወንጀሎች ሰለባ ተደርጎ እረፍት አልባ ህይወት እንዲመራ ቀንና ሌሊት የሚሰራው የአብይ አህመድ የብልጽግና አገዛዝ ከአማራ አብራክ ለወጡ ኃይሎች ወዳጅ ወይም ሸላሚ ለመሆን መቅረብ ትልቅ ቧልትና አይን አውጣነት መሆኑን ያለፉት አራት የነውጥና የመንግስታዊ ውሸት አመታት ምስከሮች ናቸው።

PDF View

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator