1. የሳምንታዊዋ ፍትህ መጽሄት አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ በፖሊሶች ተይዞ እንደተወሰደ ቤተሰቦቹ በማኅበራዊ ሜዲያ ካሰራጩት መረጃ ተመልክተናል፡፡ ዛሬ ከቀትር በኋላ 8 ሰዓት ላይ በዛ ያሉ ፖሊሶች ወደ መጽሄቷ ቢሮ በመሄድ፣ ተመስገንን በመኪና ጭነው እንደወሰዱት ነው ቤተሰቦቹ የገለጹት፡፡
2. ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ ተከሳሾች ግድያውን አልፈጸምንም ሲሉ ለችሎት ቃላቸውን እንደሰጡ ዋዜማ ሰምታለች፡፡ ድርጊቱን መፈጸማቸውን የካዱት ዛሬ ችሎት የቀረቡት ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ፣ አብዲ አለማየሁ እና ላምሮት ከማል ናቸው፡፡ መንግሥት ለተከሳሾቹ ያቆማቸው ጠበቃ፣ አቅም ላላቸው ጠበቃ ሆነው መመደባቸውን በመቃወም ትዕዛዙ እንዲነሳላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ችሎቱ ግን ጠበቃው ሁሉንም ተከሳሾች ወክለው አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ አዟል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ለማሰማት ቀጠሮ እንዲሰጠው እና አብዛኛዎቹ ምስክሮችም የተከሳሾች ቤተሰቦች በመሆናቸው ፖሊስ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይስጥልን ሲል ጠይቋል፡፡ ችሎቱም ዐቃቤ ሕግ ከኅዳር 23 ጀምሮ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ አዟል፡፡
3. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከቀናት በፊት በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ መነሻ የግለሰቦች ግጭት እንደሆነ የቤንሻንጉል ክልል ሃላፊዎች መግለጻቸው ስህተት እንደሆነ የአማራ ክልል ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ማስታወቁን የክልሉ ብዙኀን መገናኛ ዘግቧል፡፡ ማንነት ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ያስተባበሩት የቀበሌ አመራሮች እንደሆኑ የቢሮው ሃላፊ ተናግረዋል፡፡ በሰኞ’ለቱ ጥቃት 12 ሰዎች እንደተገደሉ የክልሉ ቃል አቀባይ ትናንት ለሮይተርስ ተናግረው ነበር፡፡
4. ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተገናኝተው የተወያዩ 2 የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት በኮሮና ቫይረስ ስጋት ራሳቸውን እንዳገለሉ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የጸጥታ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል እና የኅብረቱ የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ናቸው፡፡ ባለሥልጣናቱ ራሳቸውን ያገለሉት አብረዋቸው ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ አንድ የልዑካን ቡድኑ አባል በቫይረሱ መያዛቸው ከታወቀ በኋላ ነው፡፡
5. በፌደራል ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ማሳሰቢያ መሠረት ሃብታቸውን ላላስመዘገቡ 10 ከፍተኛ ባለሥልጣናት የፌደራሉ ዐቃቤ ሕግ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ ማስጠንቀቂያው ከተጻፈላቸው መካከል የፌደራል ሚንስትር ዴዔታዎች እና በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት ይገኙበታል፡፡ ባለሥልጣናቱ ከሚጣልባቸው ቅጣት ጋር ሃብታቸውን ባስቸኳይ እንዲያስመዘግቡ ተገልጾላቸዋል- ብለዋል ስለ መስሪያ ቤታቸው ሥራ አፈጻጸም መግለጫ የሰጡት የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፡፡
6. ከአማራ ክልል በጎጃም መስመር በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲገቡ ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ለአማራ ብዙኀን መገናኛ ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱ እየተፈጸመ የሚገኘው፣ ከአባይ ድልድይ እስከ አዲስ አበባ መዳረሻ ሱልልታ ከተማ ባለው የፌደራል መንገድ ላይ ነው፡፡ ታጣቂዎቹ ኬላዎች ላይ ከአሽከርካሪዎች ገንዘብ ይጠይቃሉ፤ ብሄርን መሠረት ያደረጉ ስድቦችንም ይሰነዝራሉ- በማለት ተናግረዋል የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሹፌሮች፡፡ በተለይ መስከረም 30 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች በጥይት የሰው ሕይወት እንዳጠፉ እና እንዳቆሰሉም እማኞቹ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ይህን ችግር ለማስቆም ርምጃ እንዳልወሰደም አክለው ገልጸዋል፡፡
7. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሼክ አላሙዲን ንብረት ከሆነው እና በክልሉ የወርቅ ልማት ከሚያካሂደው ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን የባለቤትነት ድርሻ እንደጠየቀ ሪፖርተር ጋዜጣ የማዕድን ሚንስትር ታከለ ኡማን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የሮያሊቲ ክፍያ እና የባለኔትነት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ፣ በኩባንያው፣ በክልሉ መንግሥት እና በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት እየተደረገበት እንደሆነም ሚንስትሩ ሰኞ’ለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ማዕድን ሚንስቴር ቀደም ሲል የተዘጉ ማዕድን አልሚ ኩባንያዎችንም እንደገና ሥራ እንደሚያስጀምር ሚንስትሩ አስታውቀዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]