የነጻነት ታጋይ ቀለብ ስዩም
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ ሸዋ
ህወሓት የመንግሥትነት መንበረ -ሥልጣኑን ሲቆጣጣር ትልቅ መሣሪያ የሆኑት ማንነታቸውን የሸጡና ለሆዳቸው ያደረጉ የክልል መንግሥታትን በመፍጠር ነበር።
ከእነዚህም የአማራ ክልል መንግሥት ተብዬው “ብአዴን” አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ ሕወሓት ያኔ የኦሮሞን ህዝብ ለጥ_ሰጥ አድርጎ የገዛውም
በ“ኦህዴድ” እንደነበር ይታወሳል፡፡
የታሪክ አጋጣሚ ሆነ “ኦህዴድ” መንበረ -ሥልጣኑን ሲቆጣጠርም ከህወሓት ያገኘውን ልምድ በመጠቀም በአማራ ህዝብ ላይ አሻንጉሊት የአማራ ብልፅግና ፓርቲን አቋቁሟል፡፡
ይህ ክልላዊ መንግሥት ማንነቱን ሽጦ እነሆ የአማራን ህዝብ አንድነት እየተፈታተነና እየሸረሸረ ይገኛል፡፡ ለኦህዴድ ጥቅምና የሥልጣን ቆይታ ሲባል የአማራን ህዝብ ያስራል፣ ያፍናል፣ ይገድላል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተበየነበትን የሕወሓት ወንበዴ ካለበት ገብቶ ለህግ ማቅረብ ያቃተው መከላከያ ሠራዊትም ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ጋር ተመሳጥሮ ሠላማዊውን የአማራ ህዝብ አንድ የምጣድ ላይ ቆሎ ያምሰዋል፤ ይቆላዋል፡፡
በእዚህ ወሳኝና ታሪካዊ ወቅት ህወሓትም ሆነ የብልፅግና ፌዴራል መንግሥት ፀባቸው ከአማራ ህዝብ ጋር እንደሆነ ብዙ ቅን አመለካከት ያላቸው ሰዎች ላይገባቸው ይችላል፡፡
ሁለቱም በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲሰነዝሩ ነው የሚታዩት፡፡
የተገደለው ህዝብና የወደመው ንብረትኮ የአማራና የአፋር ሕዝብ ብቻ እኮ ነው፡፡
እውነታው ይህ ቢሆንም ሕወሓት ዳግመኛ ተመልሶ መጥቶ ከአማራ ህዝብ ላይ የዓመት ቀለቡን ዘርፎ እንዲሄድ የፌዴራሉ መንግሥት መንገዱን ያመቻችለታል ቢባል የሚያከራክር አይደለም፡፡
ህወሓት ሣልሳዊ ወራሪ ለማድረግ ከምንግዜው በበለጠ የጦርነት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት የአማራ ሕዝብ ትጥቅ ማስመዝገብ ፋኖም ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል ውሳኔ ለማስፈጸም መሯሯጥ ለሕወሓት ወረራ መንገዱን ማመቻቸት ካልሆነ በቀር ከቶ ምን ሊባል ይችላል!?
በእኔ የግል እይታና የፖለቲካ እምነት የአማራ ህዝብ በመቃብሩ ላይ ካልሆነ በቀር ትጥቁን የሚፈታበት ምክንያ አይኖርም፡፡
ሕወሓት በገዛ ቀየው ገብቶ ምን እንዳደረገው የአማራ ሕዝብ አሣምሮ ያውቀዋል፡፡
የፊጢኝ ከወጋግራ ጋር ታስሮ የገዛ ሚስቱ፣ የወለዳቸው ሴት ልጆቹን አይኑ እያየ ተደፍረውበታል፡፡
ከእዚህ በላይ ምን ጥቃት – ከእዚህ በላይ ምን ውርደት ይደርስበታል!?
የፈለገውን ያህል የአፍዝ አደንዝዝ አዚም ቢሰራ፣ የፈለገውን ያህል ምክንያት በደረደርለት የአማራ ህዝብ አይታለልም፡፡ አይደለልምም፡፡
የብልጽና መንግስትም ሆነ የመከለከያ ሰራዊት እኮ ዳግመኛ የትግራይን መሬት መርገጥ ፈርቶ ካለበት ሊቆም የቻለው ያረፈበትን የሕዝብ ብትር በመቅመሱ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ህዝብ ኪስ በተዋጣ በጀት ለትግራይ ህዝብ ከደረሰባቸው ውድመት እንዲያገግሙ እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ የአማራ ህዝብ ትጥቁን እንዲፈታ ይበየንበታል፤ ይታሰራል፤ ይሰደዳል፤ ይገደላልም፡፡
ይህ ሁሉ እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ፣ ወይም ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ለመጥቀም ቢሆን ኖሮ ባልከፋ ነበር፤ ግን ጨርሶ አይደም፡፡
የኦሮሞን ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር አቃቅረው፤ ወይም ደግሞ ለሌላ እልቂትና ኪሳራ በማዘጋጀት የኦህዴደድ ብልፅግና ካድሬዎችን ቢሊየነር ማድረግ ነው አይነተኛ አላማቸው፡፡
የሕወሓት ባለሥልጣናት ለሠላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ዘርፈው፣ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን በአውሮፓና አሜሪካ እንዳቀማጠሉት ሁሉ የኦህዴድ ሰዎችም ይህንን እኩይ አላማ መተግበር ነው የሚፈልጉት፡፡
የኦህዴድ ዘመነኞች በሥልጣን እስካሉ ድረስ ራሳቸውን ከአፍሪካ ቢሊየነሮች ተርታ ማሰለፍ፣ የሥልጣን እድሜያቸውም ካከተመለት ሕወሓት የጀመረውን አገር የማፈራረስ ሴራ ተግባራዊ የማድረግ እቅድ አላቸው፡፡
ይህንን እኩይ እቅዳቸውን ለማስፈጸም የሚችሉት ደግሞ ጠንካራውና አይበገሬውን፣ በኢትዮጵያዊ አንድነቱ የጸና አቋም ያለውን የአማራ ሕዝብ ደጋግሞ ማጥቃት፣ ማደህየት፣ ማፈናቀል፣ መግደል፣ ሠላምና ተስፋውን ከአእምሮው በማውጣት በአጠቃላይም በሁሉም አቅጣጫ የማዳከም ስራ በመሥራት ይሆናል፤ አዎ እያደረጉት ነው፡፡
የለውጡ መንግሥት ተብዬው የኦህዴድ የሥነልቦና የበላይነት ያለው ኃይል፣ አንቀጽ 39”ን ከህገ መንግስቱ ያላወጣው፣ አንዱን ክልል ከሌላው የማጋጨት ሴራ የሚሸርበው፣ ህወሓት ወደ ሥልጣን የመጣበት ግንቦት 20ን በየአመቱ የሚያከብረው … ወዘተ የፖለቲካ ድራማዎችን እየከወነ ያለው አላማና ግቡ አገርና ህዝብን ማፈራረስ በመሆኑ ይሆናል፡፡
“ወርቅ ላበደረ ጠጠር አይመለስም”
የአማራ ህዝብ ታፍራና ተከብራ ለኖረችው ኢትዮጵያ ትልቅ ዋስትና ሆኖ ቆይቷል፡፡
አማራ ከጠላት ጋር ቢያብር ኖሮ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነትና ጀግንነት ለአለም ሕዝብ መተረክ አይቻልም ነበር፡፡
እንዲያውም ከኢትዮጵውያንም አልፎ የመላው አፍሪካ የነፃነት ታሪክም እውን መሆን አይችልም ነበር፡፡
ይህን ሁሉ ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ዛሬ ላይ በገዛ ወንድሞቹ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ! በአማራ ሕዝብ ላይ ታላቅ ክህደት ተፈጽሞበታል፡፡
የአማራ ህዝብ መከራና እንግልት በእየሱስ ክርስቶስ ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር ይመሳሰላል፡፡
ጌታ እየሱስ ክርስቶስ እኮ እጆቹ በምስማር የተከነቸሩት፣ ጎኑን በጦር የተወጋው፣ በመሣለቂያነት የእሾ አክሊል በጭንቅላቱ ላይ እንዲደፋ የተደረገው፣ 666 ጊዜ በጅራፍ የተገረፈውና በሥቅላትም የተቀጣው የሰው ልጆችን ሁሉ ከሀጢያት ባርነት ነፃ ላውጣ በማለቱ ነበር፡፡
ለሰው ልጆች ደህንነት ውድ ዋጋ በመክፈሉ ምክኒያት ሞት እንደተፈረደበት ሁሉ የአማራ ህዝብም የክርስቶስን ሁለንተና ተጋሪ ሆኖአል፡፡ ያሳዝናል፤ ያናድዳልም፡፡