በጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ
አሊ ሚካኤል በሚኖሩ አማራዎች ላይ ለ3 ቀናት ያህል በተደራጀ መልኩ የተከፈተው ተኩስ እልባት ያገኝ ዘንድ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ፤ እስካሁን 28 አማራዎች ተገድለዋል፤ ሽህዎች ተፈናቅለው በየጫካው ተበታትነዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ አሊ ሚካኤል አካባቢ የቀበሌው መስተዳድር አካላት ከአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር በአማራዎች ላይ የከፈቱት ጥቃት 3 ቀናት አስቆጥሯል፤ እስካሁን 28 አማራዎች ተገድለዋል፤ ከ1 ሽህ በላይ አባዎራዎች ተፈናቅለዋል።
ለኦነግ ሸኔ የሚደረገው ድጋፍ እንዲቆም፣ አለመግባባትና ጥርጣሬ እንዲወገድ፣ አጉል ፍረጃ ቀርቶ አንድነትና ወንድማማችነት እንዲነግስ፣ አማራውም አዝመራውን በሰላም እንዲሰበስብ በሚል ምክክር ተጀምሮ ነበር።
አሊ ሚካኤል ላይ ህዳር 19 ቀን 2014 የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በመምከር በማግስቱ ወደ ስራ ሊገቡ መሆኑን የሰሙ፣ አንድነትን የሚጸየፉ፣ ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑት የሽብር ቡድኑ አባላት ናቸው ቀድመው ተኩሱን የከፈቱት ተብሏል።
የጥቃቱን መጀመር ተከትሎም ኔትወርክ ለ3 ቀናት ያህል እንዲቋረጥ ተደርጎ ህዳር 21 ቀን 2014 ነው ተኩሱ ፋታ መስጠቱን ተከትሎ ነው መከፈቱ የተገለጸው።
ጥቃቱን በጀመረውና በተመታው የኦነግ ሸኔ አባል ቤት በተደረገ ፍተሻም 2 የጥፍር መንቀያና ኦነጎች ለማስፈራሪነት የሚጠቀሙበት 13 ጥቅል የአርቲፊሻል ጸጉር ዊግ ተገኝቶበታል።
ነዋሪዎች ሲቀጥሉ ህጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች በየጫካው ተበታትበዋል፤ በየጫካው የወለዱ እናቶችም አሉ፤ ለቆሰሉት ህክምና ለማግኘት አልተቻለም፤ የብዙዎች አድራሻ በትክክል አልታወቀም ብለዋል።
አሚማ በጫካ ከተበተኑ ሽህዎች መካከል ከአራት አማራዎች ጋር ያደረገው ቆይታ እንዳመለከተው ጥቃቱን የሚፈጽሙት የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ልብስ የለበሱ ናቸው።
በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በአንዶዴ ዲቾ ቀበሌ በአሊ ሚካኤል ከተማ የሚገኙ የአማራ ሚሊሾችም ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተገልጧል።
የፌደራል የመንግስት የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ ገብተው መፍትሄ እንዲያመጡ፣ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ተጎጅዎች ጠይቀዋል።