በአማራ ክልል ከ4ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የጸጥታ ቢሮው ዛሬ ግንቦት 15/2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሰሞኑ መንግሥት ያካሄደውን “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ተከትሎ መሆኑን አመልክቷል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች ብዛት 4 ሺህ 552 እንደሆነና ከእነዚህ ውስጥ 210 የሚሆኑት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ምርመራ ተጣርቶባቸው የተከሰሱና በሕግ ጥላ ስር ማድረግ ሳይቻል የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።

ከ40 በላይ የሚሆኑት የወንጀል ፍርደኞች ሆነው ከማረሚያ ቤት ያመለጡ፣ ከ39 በላይ የሚሆኑት ወንጀለኞች ሆነው በሌሉበት የተፈረደባቸው፣ 917 ግለሰቦች ደግሞ “በጽንፈኞች እና የክልሉ ጠላቶች ተልዕኮ የተሰጣቸው” መሆናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም “ፀጉረ ልውጦችን ጨምሮ በፀጥታ እና መንግሥት መዋቅር ሆነው ለወንጀል ተባባሪነት” የተጠረጠሩ ከ1 ሺህ 780 በላይ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ታክሏል።

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ክልል “ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል” ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። አቶ ደሳለኝ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ከሚደርገው ሥራ ውጭ “ክልሉ አስተማማኝ ሰላም ላይ ነው” ማለታቸውም ተዘግቧል።

እንደ አገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ከሆነ፣ “ትክክለኛውን የፋኖ ስም የማይወክሉ፣ በፋኖ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ የተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስም” ብለዋል።

አቶ ደሳለኝ በመግለጫቸው፣ “የመንግሥትን የማድረግ አቅም እና የሕግ የበላይነትን በመፈታተን በክልሉ ሥርአት አልበኝነት እንዲነግሥ” አድርገዋል በተባሉት ግለሰቦች ምክንያት “መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብትን፣ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ” እንደተቸገረም ጠቁመዋል።

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator