በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ድበደባ እንደተፈጸመበት ጠበቃው እና ወንድሙ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የጋዜጠኛው ታናሽ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ በተመስገን ላይ ድብደባው የተፈጸመው ሐሙስ ረፋድ ግንቦት 25/2014 ዓ.ም. ታስሮ በሚገኘበት 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ገልጿል።
ታሪኩ ጋዜጠኛ ተመስገንን ለመጠየቅ ሄዶ በመካከላቸው ባለው ርቀት ምክንያት ሲነጋገሩ መደማመጥ ባለመቻላቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ወደ እርሱ ለመጠጋት መሞከሩን ተከትሎ፣ ከጠባቂ የፖሊስ አባላት ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ድብደባ እንደተፈጸመበት አስረድቷል።
“በጠያቂ እና በተጠያቂ መካከል ያለው ርቀት ሰፊ ነው። በአንድ ጊዜ ከ10 ሰው በላይ ነው የሚያወራው። መጯጯህ ነው። ከዚህ በፊት በእስር ላይ ሳለ ጆሮው ላይ ጉዳት አጋጥሞት ነበር። በዚህ ሁኔታ መደማመጥ ይከብደዋል” የሚለው ታሪኩ፤ ለመጠጋት ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ድበደባ እንደተፈጸመት ተናግሯል።
“ዓይናችን እያየ በጫማ ጥፊ እና በቦክስ መቱት። . . . ከዚያ ወደ እስረኛ ክፍል ሳይሆን ወደ ሌላ ክፍል ይዘውት ሄዱ። ‘ካላየነው’ ብለን አስቸገርን። ይሄ ከሆነ ከ40 ደቂቃ በኋላ ለሁለት ደቂቃ ያክል አሳዩን። ከግራ ዓይኑ በታች አብጧል። ለብሶት ያለው ካናቴራ ተቀዷል። ምንም ነገር ማድረግ አልቻልንም። ለጠበቃው ተናግረን ወጣን” ብሏል የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዳ።
በተመሳሳይ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ጋዜጠኛው በመንግሥት ፀጥታ ኃይል አባላት ድበደባ እንደተፈጸመበት ከቤተሰብ አባላት መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠበቃ ሄኖክ ከቀናት በፊት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ለማቅረብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደነበሩ አስታውሰው፣ ተመስገንን ባያገኙትም ስለደረሰበት ጉዳት ከቤተሰብ አባላት ሰምቻለሁ ብለዋል።
ታናሽ ወንድሙ ሊጠይቀው ሄዶ መደማመጥ ባለመቻላቸው ለጠጋት በሚሞክርበት ጊዜ አለመግባባት ተፈጥሮ “በጥበቃ ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት ተመስገንን ጎትተው በማውጣት በጥፊ እና በእርግጫ ድብደባ ፈጸሙበታል” ሲሉ ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል።
“ይህ ሰው ፊት የተፈጸመ ድርጊት ነው። ኋላ ደግሞ ወደ ውስጥ አስገብተው ድብደባ ፈጽመውበታል። ቆይቶ ቤተሰብ ተመስገንን ሲያገኘው ልብሱ ተቀዳዶ እና ብዙ ጉዳት ደርሶበታል” ብለዋል።
ጠበቃ ሄኖክ እንደሚሉት ጋዜጠኛ ተመስገን በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሳለ ድበደባ ቢፈጸምበትም ለፍርድ ቤትም ሆነ ለሚመለከተው አካል ቅሬታ ማቅረብ ስላልፈለገ የቅሬታ ማመልከቻ አላስገባንም ብለዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት ተጠርጥሮ ግንቦት 19/2014 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል።
በዕለቱ ፖሊስ ጋዜጠኛ ተመስገንን ገንዘብ ተከፍሎት በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረበ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት መጠርጠሩን ተናግሯል።
ጠበቃ ሄኖክ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን እና መስከረም አበራ ጉዳያቸው ቀርቦበት ለነበረው ፍርድ ቤት ክሱ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንጂ በመደበኛ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሆን የለበትም ብለው ያቀረቡት ክርክር በፍርድ ቤቱ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ዛሬ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከሥራ ቦታው በሁለት መኪና ተጭነው በመጡ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መወሰዱ ይታወሳል።
የጋዜጠኛው ቤት እንዲሁም ቢሮው በፖሊስ የተፈተሸ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ የታተሙ የፍትህ መጽሔቶች፣ ሃርድ ዲስኮችና ሌሎች ፖሊስ ለምርመራ ያስፈልገኛል የሚላቸውን ሰነዶች መውሰዳቸውን ጠበቃ ሄኖክ አስረድተዋል።