የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 

መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በአማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ወራት ያክል ያደረገውን ምርመራ ባለ 110 ገፅ ሪፖርት መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት በተለያየ ደረጃ የተፈጸሙ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚዘረዝር ሲሆን፣ ፍትሕን ለማረጋገጥ እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችና አካባቢዎችን መልሶ ለመጠገን እና ለማቋቋም የሁሉንም ወገኖች እና ተቋማት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግም ገልጿል። 

ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (UNOHCHR) ጋር በጣምራ ካደረጉትና በትግራይ ክልል ላይ ካተኮረው ሪፖርት ቀጣይ በሆነው በዚህ ሪፖርት፤ በተለይ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች በአፋርና በአማራ ክልሎች በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ከነፆታዊ እንድምታቸው መርምሯል፡፡ 

በአጠቃላይ 29 አባሎች የነበሩት የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነቱ በተጎዱ በርካታ ቦታዎች በአካል በመገኘትና በተከታታይ የምርመራ ስልቶች ምርመራ ያከናወነ ሲሆን፣ እነዚህም በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ እና አውሲ ረሱ ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎችንና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ የሚገኙ በአጠቃላይ 50 ስፍራዎችን ይጨምራሉ፡፡ የዚህ ምርመራ ዋነኛ ትኩረት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ቢሆንም፤ በተወሰነ መጠን በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን በሚመለከትም ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ አድርጓል። 

ኮሚሽኑ በዚህ የምርመራ ሂደት በአጠቃላይ 427 ሚስጥራዊ ቃለ መጠይቆችን፣ ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ጋር 136 ስብሰባዎችን እና ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 12 የቡድን ውይይቶችን ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የየአካባቢው ነዋሪዎችንና የዓይን ምሰክሮችን፣ የሆስፒታልና ጤና ባለሙያዎችን፣ የእርዳታ ድርጅቶችንና፣ ሲቪል ማኅበራትን ይጨምራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ለምርመራው ስራ የሚያስፈልጉትን መረጃዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ጭምር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ልዩ ልዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ምንጮች ሰብስቧል፡፡ 

ኮሚሽኑ ምርመራውን ያካሄደው አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በተለይም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች፣ በሰብአዊነት ሕጎች ወይም ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎች፣ በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ፣ በሌሎችም ዓለም አቀፍ መርሆዎች እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕግጋት መሰረት ነው፡፡ ኢሰመኮ በሰበሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች መነሻነት ግኝቶች ወይም ድምዳሜዎች ላይ ለመድረስ የተጠቀመው የማስረጃ ምዘና ስልት፤ በተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራዎች ጥቅም ላይ የሚውለውን “ምክንያታዊ አሳማኝነት” (reasonable grounds to believe) የተሰኘውን የማስረጃ ምዘና ስልት ነው። 

የምርመራው ዋና ዓላማ በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን ከነፆታዊ እንድምታቸው መለየት፣ የምርመራውን ግኝቶች መሰረት በማድረግ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችንና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ማገዝ፤ ተጎጂዎች ተገቢውን የካሳ እና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ እና ወደፊት ተመሳሳይ ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ማስቻል ነው።

በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት ወገኖች በአንድ በኩል የትግራይ ኃይሎችና ተባባሪ ታጣቂዎች (በአንዳንድ አካባቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” በመባል የሚጠሩትን ታጣቂ ኃይሎችን ጨምሮ) እና በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች (የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አባላት፣ የአማራና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎችንና ተባባሪ ሚሊሺያን ጨምሮ) ናቸው፡፡ 

ይህ ሪፖርት ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ ሁሉንም ጥሰቶችን የሚሸፍን ባይሆንም፣ ምርመራው በተከናወነባቸው ስፍራዎች በሙሉ የተፈጸሙ ዋና ዋና ጥሰቶችን እና አጠቃላይ የጥሰት ዓይነቶችን ወካይ በሆነ መልኩ አካቷል፡፡ 

ጦርነቱ በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው የከተማ እና ገጠራማ አካባቢዎች በመካሄዱ በተሳታፊ ኃይሎች በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፣ ለአካል እና ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፣ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችም ተፈጽመውባቸዋል። 

የምርመራው ግኝቶች እንደሚያሳዩት በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በሲቪል ሰዎች ላይ በተለይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለአረጋዊያን፣ እንዲሁም ለሲቪል ሰዎች ቁሶች ተገቢው ጥንቃቄ ያልተደረገበት፣ የመለየት መርህን ያልተከተለና ያልተመጣጠነ ጥቃት ፈጽመዋል። ሲቪል ሰዎችን እንደከለላ በመጠቀም፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በከተሞች ውስጥ ጦርነት በማካሄድ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት እንዲከሰት አድርገዋል። ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አካባቢዎች ሆነ ተብለው የተፈጸሙ ሕገወጥ ግድያዎችን ሳይጨምር፣ በጦርነት ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ በደረሰ የሕይወትና የአካል ጉዳት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት፤ እንዲሁም 309 ሲቪል ሰዎች ለቀላል እና ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል። 

ኢሰመኮ ምርመራ ባደረገባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በተለይም እና በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ተገድለዋል። በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን ፈጽመዋል። በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም፤ የትግራይ ኃይሎች እና የኦነግ ሸኔ አባላት ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል፣ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል። 

የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ስልታዊ የሆነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ አድርሰዋል፡፡ ይህ ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃት የተጎጂዎችን እና የጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሰብአዊ ክብር ለመጉዳት እና ለማዋረድ፣ በአብዛኛው በሴቶች ላይ በሙሉ ያለልዩነት፣ አልፎ አልፎም አጥቂዎቹ ሆነ ብለው ለጥቃቱ ዒላማነት በመረጧቸው ሴቶች ላይ ሆነ ተብሎ ታቅዶ በግፍና በጭካኔ፣ በግልጽ የበቀል ስሜት፣ በቡድን አስገድዶ በመድፈር፣ ድርጊቱን ሆነ ተብሎ በቤተሰብ ፊት በመፈጸምና፣ ባዕድ ነገር በማኅፀን በመክተት ጭምር፣ በታጣቂዎቹ ኃላፊዎች ይሁንታ እና ዝምታ የተፈጸመ በመሆኑ፤ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለጦርነት ዓላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ ነው።

የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር ፈጽመዋል። የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን የፈጸሙ ሲሆን፤ የፌዴራል፣ የአማራ እና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዐውድ ውስጥም ቢሆን የጥብቅ አስፈላጊነት፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ የመሆን መርሆዎች ከሚፈቅዱት ውጪ መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ እስር ፈጽመዋል፡፡

የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን ገንዘብ አምጡ፣ መረጃ አምጡ፣ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ፣ በሚሉና በመሳሰሉ ምክንያቶች በሲቪል ሰዎች ላይ በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት ተግባር ፈጽመዋል።

ጦርነቱ ወደ አጎራባች ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ በተለይም የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና በአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከቤታቸውና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳቶች ተዳርገዋል። በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረው የፀጥታ ስጋት እና በትግራይ ኃይሎች በተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና የንብረት ዝርፊያዎች ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ተፈናቃዮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከመለያየት በተጨማሪ፤ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመኝታ፣ የጤና አገልግሎቶች የመሳሰሉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች የተሟሉላቸው ባለመሆኑ፤ በተለይም የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ፣ ለሕፃናት፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች የተለየ እና የተሟላ አቅርቦት ባለመኖሩ ልዩ ድጋፍ የሚሹትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግር ይበልጥ አባብሶታል። 

በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በተደራጀ መልኩ የትግራይ ኃይሎች በመንግሥት አስተዳደር ተቋማት፣ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (በተለይ የጤና ተቋማት እና የትምህርት ተቋማት) ፣ በግል ንብረቶች እና በንግድ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና የንብረት ውድመት ፈጽመዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ሕግና ሥርዓት መፍረሱን ተከትሎ የተወሰኑ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የሆኑ ሰዎችም በዝርፊያው ተግባር ተሳትፈዋል። 

በአብዛኛዎቹ ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ሆነ ተብሎ በታቀደ፣ በተጠና፣ በተደራጀ መንገድ ስልታዊ የዘረፋና ገፈፋ ተግባር፣ በተለይም የሕክምና መሳሪያ ቁሳቁስ፣ ማሽኖችን እና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመዝረፍና በመግፈፍ፣ በመኪና በመጫን ወስደዋል። ከሆስፒታሎች እና ከሕክምና መስጫ ተቋማት መድኃኒቶችን፣ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች፣ አምቡላንሶችና ሌሎችም የሕክምና መሳሪያዎች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡ በአፋርና በአማራ ክልሎች በአጠቃላይ በ 2,409 የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት፣ ጉዳትና ዝርፊያ በመድረሱ አገልግሎታቸው ተቋርጧል፡፡ በተጨማሪም 1,090 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ፣ 3,220 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ወድመዋል። 

በፋይናንስ ተቋማት በተለይም በ18 የንግድ ባንኮች 346 ቅርንጫፎች ላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ዘረፋ እና ውድመት ደርሷል።

ይህ ምርመራ በተመለከታቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የበርካታ ሰዎች የንግድ መደብሮች እና የመኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ከዕለት የምግብ ፍጆታና አልባሳት ጀምሮ እስከ ንግድ እቃዎች እና ሸቀጦች፤ አላቂ የምግብ ፍጆታዎች፣ እህሎች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ የቤት እንስሳትና ሰብሎች እንዲሁም ገንዘብ በትግራይ ኃይሎች ተዘርፈው ተወስደዋል፣ የቀንድ እና የጋማ ከብቶችን በጥይት ተመተው ተገድለዋል። 

በሌላ በኩል በአማራ ክልል የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩ ስፍራዎች ከለቀቁ በኋላ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተባብረዋል የተባሉ ሰዎች እና ለደኅንነታቸው በመስጋት ከተሞቹን ጥለው የሸሹ የትግራይ ተወላጆች ንብረቶች በልዩ ልዩ የመንግሥት ታጣቂዎችና በተወሰኑ የየአካባቢው ነዋሪ ሰዎች ተዘርፈዋል፡፡

በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ የተከሰተ ሲሆን፣ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ በተለይ በአፋር ክልል ጦርነቱ አሁንም በመቀጠሉ ምክንያት በአፋር እና ትግራይ ክልሎች ሰብአዊ እርዳታን ለማድረስ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የጦርነቱ እና የፀጥታ መደፍረስ ሁኔታ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የፈጠረው እንቅፋት የሚታወቅ ቢሆንም፤ በተለይ ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ ላይ በፌደራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት የሚደረጉ አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ መስፈርቶችና የስራ ሂደቶች አስፈላጊው እርዳታ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል።

በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ አካላት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ሕፃናት ለሞት፣ ለአካል እና ለሥነልቦና ጉዳት እንዲሁም ለወሲባዊ ጥቃት ተጋልጠዋል፤ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው የጤና፣ የትምህርት እና በቂ የኑሮ ሁኔታ የማግኘት መብቶቻቸው ተጥሰዋል። ወላጆቻቸው እና ሌሎች የቤተሰብ አባላት ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የአካል ጉዳቶች፣ እንዲሁም በርካታ ሲቪል ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በመሆኑ ካስከተለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሥነልቦና ጉዳት በተጨማሪ፤ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ሊያገኙት ይገባ የነበረውን ጥበቃ እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል።

በጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎች በተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ምክንያት በርካታ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ተገድለዋል፤ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ እንዲሁም አረጋዊያን ሴቶች በትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል። በተጨማሪም ቤት ንብረታቸው ወድሟል እንዲሁም በሚጦሯቸው እና በሚደግፏቸው ቤተሰቦቻቸው ላይ በተፈጸሙ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች እና የንብረት ዘረፋ እና ውድመቶች ምክንያት ያለጧሪ እና ደጋፊ ቀርተዋል፤ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል። 

በተለይ የአዕምሮ ሕሙማን በትግራይ ኃይሎች የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል። የትግራይ ኃይሎች ወደ ተቆጣጠሯቸው ከተሞች ሲገቡ የአዕምሮ ሕሙማኑ በመንገድ ላይ በመገኘታቸው፣ ወይም መንቀሳቀስ በተከለከለባቸው ሰዓታት ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው፣ ወይም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ባለመቻላቸው፣ ወይም ለሚጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ባለመቻላቸው፣ ወይም የመንግሥት ሰላዮች ናቸው በሚል ጥርጣሬ ተገድለዋል።

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ባቀረባቸው መደምደምያዎችና ምክረ ሃሳቦች እንዳመለከተው፤ ምርመራው በተካሄደባቸው የአፋር፣ የአማራ እና የትግራይ ክልል አካባቢዎች የደረሱት የሰብአዊ መብቶችና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን የተከተለ የወንጀል ምርመራ ሂደት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጿል። ይህንንም ለማድረግና በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም ኃይሎች የተፈጸሙ ጥሰቶች ላይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ የመጀመሪያው ኃላፊነት በመንግሥት ላይ የሚወድቅ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡ 

በዚህ ሪፖርት የተመለከቱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጠነ ሰፊና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሲቪል ሰዎች ሰለባ ያደረጉ በመሆናቸው፤ ጉዳዩ ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት ብቻ የሚተው እንዳልሆነ የኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦች ያስረዳሉ። ስለሆነም የጤናና የትምህርት ተቋማትንና ሌሎች አገልግሎቶችን ወደ መደበኛ ስራቸው በአፋጣኝ መመለስን ጨምሮ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ አቅርቦት እርዳታዎች ማድረስና የመሳሰሉት በአፋጣኝ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች ከመንግሥት አካላት በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቁ ናቸው። 

እነዚህንና ከላይ የተጠቀሰውን የጣምራ ሪፖርት ምክረ ሃሳቦች ለማስፈጸም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጨምሮ የሌሎች ሀገራዊ ተቋማት ሚና አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ “በቀዳሚነት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች እና ኃይሎች በአባላቶቻቸው እና አመራሮቻቸው ለተፈጸሙ ከባድ የመብት ጥሰቶች ኃላፊነት መውሰድ እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ግዴታቸውን መወጣት ለፍትሕ፣ ለእውነት፣ ለተጎጂዎችና ለተጎጂዎች ቤተሰቦች የማይታለፍ እርምጃ መሆኑን በድጋሚ ሊታወስ ይገባል” ብለዋል። አክለውም “ከአስራ አምስት ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት ከዚህ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም አድርገው ለፖለቲካዊ መፍትሔ ንግግር መጀመር ይገባቸዋል” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፣ በሪፖርቱ የተካተቱን ምክረ ሃሳቦች የመተግበሩ ሂደት በአፋጣኝ እንዲጀመር ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቅርበዋል።

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator