አገዛዙ መቶ አሥራ አንድ ሚዲያዎችን ሊዘጋ መሆኑን ፖሊስ ፍንጭ ሰጠ
የተረኛው ኦሕዴድ-ብልፅግና የአፈና መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ያለው እና ከፍተኛ አመራሩ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚቀርብ ደረጃ በኦሮምኛ ተናጋሪ ጀማሪ ፖሊሶች የተጠቀለለው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፤ አገዛዙ 111 የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን በሕገ ወጥነት ፈርጆ ለመዝጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ፍንጭ ሰጥቷል። ይህ ፍንጭ የተገኘው ፖሊስ ዛሬ ረቡዕ፤ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም . ባወጣው መግለጫ ነው። መግለጫው መገናኛ ብዙሃኑን በስም ከመግለፅ የተቆጠበ ሲሆን በሌላኛው የአዛዙ የመገናኛ ብዙሃን አፈና ድርጅት በኩል የስርጭት ፈቃድ ያልተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሷል።
እነኝህ መገናኛ ብዙሃን “ሕዝብን ከመንግሥት ለመነጠል ይሠራሉ” ሲልም እሮሮውን አሰምቷል።
በዚሁ ምክንያት ፖሊስ 10 ጋዜጠኞችን አስሮ እያንገላታ መሆኑን አምኗል።
በፕሬስ ነፃነት ከዋጁ መሰረት ማንኛውም ጋዜጠኛ በሥራው ምክንያት ቢከሰስ እንኳን፤ ዶሴውን በውጭ ሆኖ መከታተልና መከራከር እንጂ በእስር ቤት እንዲቆይ አይገደድም።
ይሁን እንጂ አገዛዙ ጋዜጠኞችን በግፍ ከማሰሩም በላይ እያፈነ አድራሻቸውን ማጥፋቱን የዕለት ከዕለት ግብሩ አድርጎታል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአማሮችን አፈና ለማሳለጥ ከተለመደው የውትድርና ሥራቸው ይልቅ፤ እንደ ደህንነት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ወደ ስለላ ተቋምነት እያዘነበሉ ይገኛሉ።
በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በየጠረፉ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር መጠበቅ ሲገባው መሀል ከተማ ተቀምጦ ጆሮ ጠቢ መሆኑ አሳዛኝ ነው።