ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት በስዊድን ለአልፍሬድ ኖቤል የሽልማት ድርጅት የታፈኑ የአማራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደብዛ መጥፋትን አስመልክቶ ድርጅቱ በሽምግልና ገብቶ ተማሪዎችን እንዲያስለቅቅና በተማሪዎቹ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት አብይ አህመድ ተጠያቂ መሆኑን ለሽልማት ለድርጅቱ በፃፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል።
ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት ለኖቤል የሽልማት ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ እንደምትገኝ ገልጾ አስቸኳይ ማሻሻያ ካልተወሰደ በቀጣይም የህዝቡን ሰላምና ደህንነትን ይበልጥ አደጋ ላይ የሚጥሉ አዳዲስና አስፈሪ የሆኑ ጎሳ ተኮር ግጭቶችና ውጥረቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አፅኖት ሰጥቶ ገልጧል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እያጋጠማት ካሉት ውስብስብ ችግሮች መካከል አንዱ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ጠቁሟል።
ሞረሽ ወገኔ በደብዳቤው የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ለብሄራዊ መግባባት ትኩረት አለመስጠቱን ይልቁንስ የራሱን አጀንዳ በህዝቡ ላይ እየጫነ መሆኑን አስፍሯል።
ሞረሽ ወገኔ እንደአብነት ሲጠቅስም ባለፉት በርካታ ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈፀም የነበረው ጥቃት ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣነ መንበሩ ከወጡ ማግስት ጀምሮም በባሰ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ለድርጅቱ አስታውቋል።
ባለፉት 2 ዓመት ህገ ወጥና አመፀኛ በሆኑ የተደራጁ ታጣቂዎች አስከፊ የሆነ የእገታ ወንጀል እና የባንክ ዝርፊያ መፈፀሙን አውስቶ
በተለይ ከታገቱና ደብዛቸው ከጠፉ ከ5 ወራት በላይ ያስቆጠሩ በአብዛኛው ሴቶች የሆኑ የአማራ ተማሪዎች ፍትህ አለማግኘትን በአሳሳቢነት ጠቅሷል።
የኖቤል የሽልማት ድርጅት ለጠ/ሚኒስትሩ ሽልማት የሰጠው በሰላምና አለም አቀፍ ትብብር በተለይም ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ሰላም እንዲመጣ ላደረገው ጥረት መሆኑን የጠቀሰው ሞረሽ ወገኔ ምንም እንኳ ይህ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ቢችልም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰላም አለመኖሩን አትቷል።
ሰላም የሚጀምረው ከቤት መሆኑን የጠቀሰው ሞረሽ ወገኔ ዶ/ር አብይ በአገር ውስጥ እያጋጠሙ ላሉ የሰላም እጦቶች መፍትሄ ሊያመጣበት እንደሚገባ በተለይም የታገቱ ተማሪዎችን በአስቸኳይ እንዲያስለቅቅና በአመፀኛ ታጣቂዎች ላይም ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
በዚህ በኩል እንደ መጀመሪያ የኖቤል ሽልማት ድርጅትም ይህን ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ ሀቀኛ መፍትሄ እና መረጋጋት ይመጣ ዘንድ በመንግስት ላይ ግፊት እንዲፈጥር በአፅኖት ማሳሰቡን ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት ጠይቋል።
ድርጅቱ ለሲዊዲን መንግስት ፓርላማ፣ ለሲዊዲን አለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም፣ ለአምኒስቲ፣ ለሲቪል መብት ተሟጋቾች፣ ለህይውማን ራይትስ ዎች፣ለኦክስፋም እና ለህፃናት አድን ድርጅት መልዕክቱን ያስታወቀ መሆኑን ገልጧል።
በመጨረሻም የተጻፈው ደብዳቤን በተመለከተም የኖቤል ሽልማት ድርጅቱ ደብዳቤውን መቀበሉንና ጉዳዩን እንደሚያጤነው መግለፁን የዐማራ ድምፅ ራዲዮ አስታውቋል።
Read Time:1 Minute, 36 Second