አሳዛኝ ዜና!
በኪረሞ ወረዳ ባጊን ቀበሌ አሸባሪው የኦነግ ሸኔ ቡድንና ተባባሪዎቹ በከፈቱት ተኩስ ከ11 በላይ አማራዎች ሲገደሉ፣ ከ16 በላይ ቆስለዋል፤ የድረሱልን ጥሪም አሰምተዋል።
የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ከተባባሪዎቹ ጋር በመሆን በኪረሞ ወረዳ ባጊን ቀበሌ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ከመስከረም 10 እስከ 12 ቀን 2014 ለተከታታይ 3 ቀናት ጥቃት ፈጽመዋል።
ከጅምሩ ህዳር 10 ቀን 2014 ባል እና ሚስትን በግፍ በመግደል ልጃቸውን አፍነው መውሰዳቸው ይታወቃል።
የሽብር ቡድኑና ተባባሪዎቹ ህዳር 12 ቀን 2014 ለሶስተኛ ቀን በከፈቱት ተኩስ ከ11 በላይ አማራዎች ተገድለዋል፤ ከ16 በላይ የሚሆኑም ቆስለዋል፤ ከ15 በላይ ቤቶች ወድመዋል።
ህዳር 12 ቀን 2014 በአራት አቅጣጫ_ከዋስቴ ቀበሌ፣ ከጊዳ ወረዳ ድሪ ጉዳ እና ጃንግር ቀበሌ ተነስተው ድቡክን ወንዝ ተሻግረው በአራት አቅጣጫዎች በመምጣት ነው ባጊን ቀበሌ ሰጊ፣ ወፍጭ፣ማዶረብ እና አምቦ ላይ ጥቃት የፈጸሙት።
አሚማ ከነዋሪዎቹ የደረሰውን የሟቾችና የቁስለኞችን ስም በቀጣይ የሚገልጽ ይሆናል።
የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና ባለሙያዎች ባለመኖራቸውም ከቁስለኞች መካከል የአንዱ ህይወት አልፏል።
መንግስት ለቅሷችን እና ጭሆታችን እየሰማ ባለመሆኑ በቡድን መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ለተከታታይ ቀናት ተከፍቶብን ንጹሃንን እየገበርን እንገኛለን፤ አሁንም ተከበናል፤ ለከፋ ርሃብ ተጋልጠናል፤ ህክምና ለማግኘት ባለመቻላችን እናቶችና ህጻናት እየሞቱብን ነው ሲሉ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ከዋስቴ በተጨማሪም በአሙሩ ወረዳ ሀሮቤራ አካባቢም በከፍተኛ ከበባ ላይ እንገኛለን የሚሉት ነዋሪዎቹ የሀገር ያለህ ድረሱልን ሲሉ ተማጽነዋል።
በተያያዘ ህዳር 10 ቀን 2014 ከአዲስ አበባ ወደ ኪረሞ በአንድ የጭነት መኪና ሲጓጓዝ የነበረው ሸቀጣሸቀጥ ቆቆፌ በተባለ የገጠር ከተማ በስርዓት አልበኞች መነጠቁን አሚማ መዘገቡ ይታወሳል።
ወደ ቆቆፌ አቅንተው ልመና በቆሙ ሽማግሌዎች የተነሳ የአማራዎችን በማስቀረት የኦሮሞ ተወላጆችን መኪና እና ሸቀጥ የለቀቁላቸው መሆኑ ተነግሯል።
ኦነግ ሸኔ እና ተባባሪዎቹ ፍትሃዊ ናቸው እንዲባል በማሰብም ህዳር 12 ቀን 2014 ንብረቱን በማራገፍ ባዶውን መኪና የለቀቁ ሲሆን የኦሮሞዎችን ሸቀጥ ቀስ እያደረግን በባጃጅ እንልካለን መባሉም ተሰምቷል።
የህግ የበላይነትን የሚያስከብር ፍቃደኛ የሆነ የመንግስት አካል በመጥፋቱ በኑሮአችን ላይ ከባድ አደጋ ከተደቀነ ከራርሟል የሚሉት ነዋሪዎቹ እስኪገድሉን ወይም ፍትህ እስክናገኝ ድረስ ለታሪክም ቢሆን መጮሃችን አይቀርም ብለዋል።
በሌላ በኩል ከ30 በላይ የሚሆኑ ተሰሚነት ያላቸው አማራዎች በማንነታቸው ብቻ ከ5 ወራት በላይ ያለምንም ፍትህ በሆሮ ጉድሩ ዞን አቢደንጎሮ ወረዳ ታስረው እንደሚገኙ ተገልጧል።