በምዕራብ ሸዋ ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በባኮቲቤ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች ላለፉት ሳምንታት አንድም የሰብአዊ እርዳታ አልተደረገልንም ይላሉ።
መንግስት በባኮ ከተማ በየዘመዱ እና በየበረንዳው ወድቀው በችግር ላይ ለሚገኙ በሽህ ለሚቆጠሩ ተፈናቃይ ወገኖች አስፈላጊ የሆነውን የሰብአዊ እርዳታ እንዲያቀርብላቸውና ጊዜያዊ መጠለያም እንዲሰጣቸው ተጠይቋል።
በባኮቲቤ ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ እና በተባባሪዎች ምሽትና ሌሊት ላይ የሚተኮሰው ጥይት ነዋሪዎችን በእጅጉ እረፍት እየነሳ መሆኑ ተገልጧል።
በባኮ ከተማ ግቤ ወንዝ አካባቢ ህዳር 10 ቀን 2014 ምሽት ላይ ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር ተወስቷል።
ባኮ ቲቤ ወረዳ አህመድ ሲራጅ የተባሉ የአማራ አባት ጤፍ አጨዳ ላይ እያሉ ጥቅምት 29 ቀን 2014 በጥይት መገደላቸው ይታወቃል።
በተመሳሳይ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ከባኮ ወደ ሻምቡ መስመር በባጃጅ እየተጓዙ የነበሩ አህመድ ወዳጅ እና ሰይድ ጋታው የተባሉ አማራዎችን በማገት ባጃጇን አቃጥለዋል።
ከቀናት በኋላም ከቤተሰብ ጋር በተደረገ ድርድር እስከ መቶ ሽህ ብር ገንዘብ ተከፍሎ መለቀቃቸው ተሰምቷል።
ባል እና ሚስትን፣ ልጅ እና እናትን፣ ልጅ እና አባትን እያለያዩ ያሉት ጽንፈኛ ኦነጋዊያን “የአማራን ከብት አትግዙ” በማለት ክልከላ እያደረጉ መሆኑን ተፈናቃዮች ለአሚማ ተናግፈዋል።
25 ሽህ ብር የሚያወጣ በሬን ድንገት “ካሳለፉን” ለትራንስፖርት ይሆነናል በማለት በርካሽ እስከ 5 ሽህ ብር ለመሸጥ ተገደናል ሲሉም አክለዋል።
በተያያዘ በምስራቅ ወለጋ ዞን ስቡስሬ ወረዳም ጉንዶ ማርያም በተባለ አካባቢ ህዳር 10 ቀን 2014 ሁለት ሰዎች በእርሻ ማሳ ላይ እያሉ በጽንፈኞች ተይዘው በከፍተኛ ሁኔታ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።