Amhara Today

የመላኩ አላምረው ምክር
………………………

Image may contain: 1 person, smiling, close-up

በእውኑ አሁን ላይ ምንስ ዓይነት የግል/የቡድን/የድርጅት/የጎጥ/የዘመድአዝማድ… ወዘተ ጉዳይ ቢኖረን በሕዝባንና በማንነታችን ላይ ከተደቀነው ፈተና በልጦ ይሆን የጋራ ጉዳያችንን እየተውን ሌላ አጀንዳ መዘዛ ውስጥ እየገባን ያለነው??? እንዲያው ማን ይሙት የትኛው ጉዳያችን ነው በየቀኑ ከየቦታው በማንም ከሚፈናቀለውና ከሚገደለው ሕዝባችን በላይ ሆኖብን የሚያነታርከን??? አሁን ይህ ወቅት ለአማራ አመራርም ሆነ የፖለቲካ አራማጅና የማኅበረሰብ አንቂ/አክቲቪስት… እየሆንን እንዳለነው እንሆን ዘንድ፣ እየሄድንበት ባለነው ዝግመት ከመዛግም አልፎ እንጥላለፍ ዘንድ የሚፈቅድ ወቅት ነው??? የትኛውን የአማራ መሠረታዊ ጥያቄ አስመልሰነው ይሆን ወደየግል/ጎጥ/ቡድን… አጀንዳ የዞርነው??? (ይህ ነጥብ ዝርዝር ውስጥ የምንገባበት ጊዜ እስኪደርስ ይቆየን።)

………….አንዳንዴ… በሁኔታዎችም በድርጅቶችም በሰዎችም መለዋወጥ ፈጽሞ ተገማች አለመሆን አለማፈርም አለማዘንም አለመብገንም ባይቻልም… እንዲህም ሆኖ ግን ተስፋ አንቆርጥም። ይልቁንስ ነገሮች ከዚህም በላይ ሊበላሹ እንደሚችሉ እያሰብን ትክሻችንን ሌላም ብዙ ፈተና ለመሸከም እናደረጃለን።
—> 
እንደ አማራ አሁን ያለንበት ወቅት የበለጠ መስከንንና መደራጀትን፣ መግባባትንና መተባበርን፣ መተማመንንና በጋራ መቆምን የሚጠይቅ ወሳኝ ጊዜ እንጅ አለመደማመጥንና አለመግባባትን፣ ጥርጥርንና መለያየትን፣ መቃቃርንና እርስ በርስ ተለያይቶ በዝርውነት መቀጠልን የሚፈቅድ አይደለም። ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። ለጋራ አሸናፊነት እንተባበር እንጅ ለውድቀት አንጠላለፍ። ልዩነቶቻችንን አክብረን መግባባት እንችላለን። ልዩነት እንዳይኖረን ከፈለግንና “የእኔ ሐሳብ ብቻ ይደመጥ በእኔ መንገድ ብቻ እንጓዝ” ካልን አንግባባም። በሁሉም ነገር የግድ መግባባትም መስማማትም አይጠበቅብንም። ነገር ግን ተፈጥሯዊ የሆነውን ልዩነት ማክበርና በልዩነት ውስጥ መስማማት ግድ ይለናል። ምክንያቱም እስከልዩነታችንም ቢሆን በጋራ ለመኖር ካልተስማማን እንጠፋፋለን እንጅ ልዩነትን ማጥፋት አይቻለንምና። ልዩነት ተፈጥሯዊ ነውና ልናስወግደው ከቶውኑ አይቻለንም። ልናስወግደው ካልቻልን ብቸኛው ምርጫችን አክብረነው መኖር ነው። ልዩነትን ከማክበርም አልፈን ውበትና ጸጋ ልናደርገው የምንችለው በመጀመሪያ ሰከን ብለን መነጋገር፣ መደማመጥና መግባባት ስንችል ነው። 
—>
(((ሀገራችን ከሶስት ሺህ ዘመናት በላይ ተጉዛና እስካሁን ቀጥላ ያገኘናት ልዩነት ስላልነበረና ሁሉም አንድ አይነት ሐሳብና ፍላጎት ስለነበረው አይደለም። አባቶቻችን ልዩነትን አቻችለው መጓዝ ስለቻሉበት እንጅ። እኛም ሀገርን እስከሙሉ ነፃነትና ክብሯ ጠብቀው ካስረከቡልን አባቶቻችን በልዩነት ውስጥ ተከባብሮ ብቻ ሳይሆን ተፋቅሮም የመኖር ጥበብን ልንማር ይገባል።)))
->
በሰከነ መንፈስ ከተነጋገርን፣ በመደማመጥ ከተግባባን፣ በልዩነትም ውስጥ ከተስማማን፣ የተጀመረው የተስፋን ብርሃን ሀገራችንን ሆነ ሕዝባችንን የሚጠቅም ሆኖ ይቀጥላል። ልዩነትን ማስፋትና መጠላለፍ ላይ ካተኮርን ደግሞ ጭላንጭል ብርሃኑን አጥፍተን የውድቀት ታሪክ እንቀጥላለን። ይህ እንዲሆን ግን በፍጹም መፍቀድ የለብንም። የአማራ ሕዝብ ሌላ የመጠላለፍና የመጠፋፋት ዘመንን አይሻም። ሌላ መከራን የሚሸከምበት ትክሻም የለውም።
->
ለአማራ ክልልና ሕዝብ ያገባኛል ብለን የምንንቀሳቀስ አካላት ከምንም በላይ ትኩረታችንን የሕዝባችንን ወቅታዊ ችግር መፍታትና ዘላቂ ጥቅሙን ማስከበር ላይ ማድረግ አለብን። ወቅታዊ ችግሩን ብቻ ከተመለከትን ስሜታዊ ሆነን ዘላቂ ጥቅሙን ልናሳጣው እንዳንችልም፤ አይገባምም። ነውር ነው። ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ በምንም አይነት ልዩነት ውስጥ ብንሆን ለሕዝባችን ስንል ተቻችለንም ቢሆን መተባበርና ኃይል አሰባስበን “ስትራቴጂካሊም” ሆነ “ታክቲካሊ” ተግባብተን በጋራ መታገል እንጅ አንዱ ሌላውን በመጥለፍና ጥሎ በማለፍ ስሌት ለመጓዝ መሞከር ብልህነት አይደለም። መንገዱም የትም አያደርሰንም። የውርደት ቁልቁለት ነው። 
—>
አንዳንዴ ወቅቱንም ሆነ የሕዝቡን ዋና ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት እያመመንም የምናልፈው ጉዳይ መኖር አለበት። ሁሉም አይነገርም። በሁሉም ነገግ አማርረን አንችለውም። ክፉ ሁሉ በክፉ አይመለስም። ለሁሉም ጥፋት የመልስ ምት እንስጥ ካልን ሌላ ተግባር ሳንከወን ዘመናችን ያልቃል። ሁሉንም በጉልበት ለማስተካከል ካሰብን ሰውነታችንን ረስተናል። ሰው በአእምሮውም እንጅ በስሜቱ ብቻ ይኖር ዘንድ ተፈጥሮው አይደለም። በስሜት በሚገፋ ጉልበት ብቻ የሚመጣ ለውጥም ሆነ የሚከበር መብት ወይም የሚቀየር ነባራዊ ሁኔታ አይኖርም። ከኖረም አንድ ትውልድ ጨርሶ ነው የሚሆነው። ይህ መጨራረስ እንዳይመጣ ነው ሰከን ማለት የሚያስፈልገው። ዝም ብሎ በስሜትና በምኞት ብቻ መጋለብ ራስንም ሀገርንም ሕዝብንም አደጋ ላይ ይጥላል። ምንም አይነት ችግር ውስጥ ብንገባ በሰከነ መንፈስ መከባበርና መደማመጥ ያሻል። በውይይትና በምክክር አምኖ ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣትና በሰለጠነ መንገድ መፍትሔ መሥራት እንጅ እንዲያው በልብ ያሰብነውን በምዕናብ ያለምነውን ሁሉ በጉልበት ለማስፈጸም መሮጥ ደም ከማፋሰስ ያለፈ ትርፍ አይኖረውም።
—>
የአማራ ብሔርተኝነት ለምን እና እንዴት እንደተጀመረ እስከየትም እንደሚሄድ እንደአዲስ መስበክ ያለብን አይመስለኝም። የአማራ በብሔርተኝነት የመደራጀት አስፈላጊነት ሳይገባን ወይም መፍትሔነቱን በውል ሳንረዳ ወይም የነገርዮውን ምንነትና የአጨዋወቱን እንዴትነት ሳንገነዘብ ወደ ጨዋታ ሜዳው ዘው ብለን የገባን ካለን ቆም ብለን እናስብ። የመጨረሻው ግባችን ላይ መድረስ የማንችል ከሆነ እስከየትም መድከም የለብንም። ብዙዎቻችን የአማራ ብሔርተኝነትን እያቀነቀን ነው ብንልም አሁንም እርስ በርስ ከመጠላለፍ አልወጣንም። እየተጫወትነው ያለውን ጨዋታ ምንነትና እስከየት እንዴት መሄድ እንዳለብን አለመረዳታቻን በዚህ ያስታውቃል። አንድነት የበለጠ በሚያስፈልገው ወሳኝ ወቅት የጎጠኝነት ካርድ ከመዘዝን፣ በመደጋገፍ ዘመን ከተገፋፋን፣ ኃይል ማሰባሰብና ከየአቅጣጫው የሚዘመትብንን የጥፋት እንቅስቅልሴ ተደራጅተንና ደርጅተን መመከት ሲገባን ጭራሽ ምክንያት እየፈለግን ልዩነት ካሰፋን፣ አማራን ባንድ ላይ ጠላት አድርጎ የዘመተበት ስንት ኃይል እያለ ከውስጣችን በጠላትነት ተፈርጆ የሚዘምትበት የውስጥ ጠላትን ማፈላለግ ላይ ከተጠመድን፣ አማራው መሪ እንዳይኖረው የሚዘመትን በሴራ የተሞላ ዘመቻ ፊታውራሪና ደጃዝማች ሆነን ካቀጣጠልን፣ ወዘተ ያለንበትን ወቅትም ሆነ መውጫ መንገዳችንን አልተረዳንም። (እርግጥ የአማራ ብሔርተኝነት በተደራጀ መልኩ የተጀመረው ከሌሎቹ እጅግ ዘግይቶ በመሆኑ መሰል ችግር የማይጠበቅ አይደለም። እንዲያውም ከሚጠበቀው በላይ ፈጥኖ ብዙ ውጤት አስመዝግቧል። ይሁንና ይህ በየምክንያቱ ብቅ ብቅ የሚል ራስን በራስ የማጥፋት አካሄድ ሊታረም ይገባል። በሐቅ ላይ ያልተመሠረተና በመግባባት/በመናበብ የማይጓዝ ምንም ዓይነት ዘመቻ ለአሸናፊነት አያበቃም። ለመሸነፍ ደግሞ መዝመት አያስፈልግም።
->
አማራ ሲተርት “ሳያጠሩ ሰው አይጠሩ” የሚለው ለድግሥ ብቻ አይደለም፡፡ ለትግልም እንጅ። አማራ የጠራ አቋም ሳይዝና ብርቱ በትሩን ሳይመረኮዝ፣ ከውሃ የጠሩ ከብረትም የበረቱ ጀግኖች እንደሚመሩት ሳያረጋግጥ ትግል አይጀምርም። የሚመጥነውን መሪ ካላገኘም አያነግስም። ስለዚህ ሕዝቡንና ወቅቱን ለመመጠን መበርታት እንጅ ሌላ መጠላለፍ ውስጥ መግባት የትም አያደርስም። ውድቀትን ያፋጥናል። ውድቀት ስል የእኛን የእንመራሃለንና የእንታገልልሃለን ባዮችን እንጅ የሕዝቡን አይደለም። ሕዝቡ ወዳጄ… እንኳን አሁን ያኔም በጥልያን ጊዜ መሪ አላጣም። ከውስጡ አምጦ ጀግና መውለድን ያውቅበታል። እንመን። አማራን ያስቸገርነው እኛ ሐሳዊ መሪዎቹ ነን። እውነተኞቹ ልጆቹ እንዳይገለጡ መንገድ ዘግተንበት እንጅ… ዛሬም ብንፈልግ ቴዎድሮስን ቢያሻን በላይን ወይም ምኒልክን ወልዶ በተግባር ያሳየናል። እኛ ምንም ብልን ግን እስካልመጠንነው ድረስ አማራ ታዝቦ ነው የሚያልፈን። አማራ ሳያጠራ አይጠራም፣ ሳናሳምነው አይከተለንም፤ በተግባር ጀግነን ካላሳየነው አያነግሠንም።

(ችግሩን ወደማንም ከመግፋትና ውስን አካላትን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ አካሄድ ወጥተን የጋራ መፍትሔ መሥራት ላይ ማተኮር እንጀምር። በመወቃቀስም በመገፋፋትም የትም አንደርስም።)
ሰላም !!!

Translator