በመርዓዊ እና በእናሸንፋለን ቀበሌ እነ አርበኛ ዘመነ ካሴን ለመያዝ ተልዕኮ ተሰጥቶት እየዘመተ ያለው መንግስታዊ አፋኝ ቡድን በሰው ኃይል እና በእንቅስቃሴው እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ።
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ ሸዋ
በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ በመርዓዊ እና በእናሸንፋለን ቀበሌ እነ አርበኛ ዘመነ ካሴን ለመያዝ በማሰብ ተልዕኮ ተሰጥቶት እየዘመተ ያለው መንግስታዊ አፋኝ ቡድን ከቀን ወደ ቀን በሰው ኃይል እና በእንቅስቃሴው እየጨመረ መሆኑ ተገልጧል።
በመርዓዊ እና በእናሸንፋለን ቀበሌ በተለይም በእነ አርበኛ ዘመነ ካሴ ቤተሰቦች እና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ ያለው ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥር እየጨመረ ስለመሆኑ የአሚማ ምንጮች እየገለጹ ነው።
“ቤት ንብረታችንን አውድመው የ85 ዓመት እናታችንን አንገላተዋል” ሲል
የዘመነ ወንድም ፋኖ ንብረት ካሴ በኢትዮ 360 ሚዲያ ባደረገው ቃለመጠይቅ መግለጹ ይታወሳል።
ከሳምንታት በፊት የያዙትን ሙሀባው ንብረቱን አስረው እነ ዘመነ ካሴ ያሉበትን ንገረን ካለዛ ግን እንገድልሃለን እያሉ የአስራ አምስት ዓመት ልጅን መደብደባቸው እንዲሁም እስካሁንም ድረስ አለመፍታታቸው ተነግሯል።
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ለማፈን ወደ ጎንቻ እና አካባቢው የተንቀሳቀሰው መንግስታዊ ቡድንም በቤተሰቦቹ ላይ እስር፣እንግልት፣ ወከባ እና ድብደባ ጭምር እየፈጸመባቸው ስለመሆኑ መዘገቡ አይዘነጋም።
በመያዣነት” እስር ቤት የገባው የመቶ አለቃ ማስረሻ ወንድም ቢተው ሰጤም ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞበታል፤ ቢተው ሰጤን ለመጠየቅ ሲጓዙ የታሰሩ ሁለት ጎረቤቶቹም እስካሁን ፍትህ አላገኙም።
በመጨረሻም አሁንም የአማራ ህዝብ አንድ ሆኖ የሞቱለትን ፋኖ ልጆቹን፣ ራሱንና አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቧል።