የሱዳን ወታደር በኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ ከገባ ከወር በላይ አስቆጥሯል። ጥሶ መግባት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በእርሻ የሚተዳደሩ ወገኖቻችን ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲሁም የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ ከገባ ከወር በላይ ቢሆነውም መንግስት በቸልታ ማየቱ የአማራ ማህበር በዩናይትድ ኪንግደምን እጅግ እያሳሰበ ይገኛል።
የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ በመግባት እስካሁን ድረስ አብፅይር፣ መድረያ፣ አልያ ፣ ወዲከወሊ፣ ኮረደመ፣ ግረሮ በኮና እና በስም ያልጠቀሱ ቦታዎችን በወረራ ይዞ ይገኛል። የሱዳን የፀጥታ አካላት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት በአማራ ገበሬዎች ላይ በርካታ ግፍና በደሎችንም እያደረሱ ነው። በተለይ ከመጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሱዳን ከፍተኛ ጦር በማዝመት የለየለት ወረራ ፈፅማለች።
የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት እንኳን ለማረስ ለህይወታቸውም አስጊ ነው ይላሉ ። የሱዳን መከላከያ ሰራዊት የጓንግን ወንዝ በወረራ መቆጣጠሩ የቀንድ ከብቶችን ውሀ ማጠጫ እንኳ እስከማጣትም ተደርሷል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ በመንግስት በኩል ችግሩ ይፈታል ብለን ብንጠብቅም ውይይቱ እንቆቅልሽ ነው የሆነብን ስለምን እንደሚወያዩም ግልፅ አይደለም ብለዋል።
ከምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ደለሎ ቁጥር 1 አካባቢ የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ድንበር ጥሰው የኢትዮጵያን ሰፊ መሬት ከመቆጣጠራቸው ባሻገር በአርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ላይ ተኩስ በመክፈት ተደጋጋሚ ትንኮሳ እና የቀንድ ከብቶች ዝርፊያም እየፈፀሙ ይገኛል። እንዲሁም በኮርሁመር ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከእርሻ ማሳቸው 3 ሰራተኞቻቸው በሱዳን ወታደሮች ታፍነው የተወሰዱት ልጆች በገዳሪፍ ግዛት ዶካ በወታደር ካምፕ ውስጥ ታስረው እንዳሉ ነዋሪዎቹ ይወሳሉ።
ይሁን እንጂ ሱዳን ከመጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሳ መግባቷን ተከትሎ መንግስት በሉአላዊነት ላይ ቸልተኝነት እያሳዬ ነው። መንግስት በሉአላዊነት ጉዳይ ግልፅ መረጃ እየሰጠ አይደለም፤ የተለሳለሰ አቋምም እያሳየ ይገኛል።
ከሱዳን ወረራ በተጨማሪ በናይጀሪያ ፈላታዎች በቁጥጥር ስር ያለው የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ ነገርም ያሳስባል። አልጣሽ ፓርክ በፈላታዎች አማካኝነት እንስሳቱ እየተሳደዱ ነው፤ ነዋሪው በየአመቱ በሽህ የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችን እየተዘረፈ ስለሆነ አስቸኳይ መፍትሄ መንግስት ሊሰጥበት ይገባል።
የአማራ ማህበር በእንግሊዝ ክልሉን አስተዳድራለው ለሚለው አዴፓና የኢትዮጵያን መንግስት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ እያሳሰብን በመላው ዓለም ላሉት የአማራ ማህበራትና አደረጃጀቶችም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን እየተዋጋ ስለሆነ ይህንን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡት የበኩላችሁን ግፊት እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
1.የሱዳን ጦር ባስቸኳይ ከኢትዮጵያ ግዛት ለቅቆ እንዲወጣ መንግስት እንዲያደርግ እንጠይቃለን ።
2. በሱዳን ጦር በሃይል የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ቦታቸው እንዲመለሱና በሱዳን ጦር ታፍነው የተወሰዱ ወገኖቻችን በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን።
3. በአልጣሽ ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለውን ዝርፊያና ውድመት መንግስት እንዲያስቆምና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅለት እንጠይቃለን ።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ
ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ
Read Time:1 Minute, 44 Second