0 0
Read Time:6 Minute, 51 Second

ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን በሐኛው ክፍለ ዘመኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ስመ ጥር የነበሩት የስሜኑ ገዢ የደጃዝማች አያሌው ብሩ የጦር መሪ ነበሩ። መቀመጫቸውን ዳባት አድርገው ከባምብሎ እስከ ተከዜ የተዘረጋውን ስሜንን ከ1909/10 ዓ.ም. – 1928 ዓ.ም. ያስተዳደሩት ደጃዝማች አያሌው ብሩ ከራስ ገብሬ ተስፋና ከልጅ ልጃቸው ከደጃዝማች ውቤ ኃይለ ማርያም ገብሬ በኋላ ካስተዳደያሩት አውራጃ አለፈው በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ዝነኛ ለመሆን የበቁ የስሜን አውራጃ አስተዳዳሪና የጦር መሪ ነበሩ። የአንቺምና የመኤሶ አውደ ውጊያዎች ደጃዝማች አያሌው ብሩ በመሪነት ከተሳተፉባቸው ጦርነቶች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በፈረስ ስማቸው አባ ይርጋ እየተባሉ የሚጠሩት ደጃዝማች አያሌው ብሩ ስለ ፍርድ አዋቂነታቸውና ስለ ደግነታቸው ብዙ ተብሎላቸዋል። የሚከተሉት ስንኞች ለደጃዝማች አያሌው ብሩ አገሬው ከተቋጠራቸው ውስጠ ወይራ ግጥሞች መካከል ይገኙበታል፤

እንደ እናት እንጎቻ የሚለው ቅርቅር፣
ያባ ይርጋ ሰፈር ዳባት እንዴት ይቅር፤
***
አወይ ቀብጦ መልመድ ምንኛ ጨነቀኝ፣
አባ ይርጋ አያሌው ብርሌው ናፈቀኝ፤
ጠጁን እንደ ውኃ የጠጣንበት፣
ስጋም እንደ ጐመን የበላንበት፣
ዳባት እንዴት ይፍረስ ያባ ይርጋ ቤት፤


ለመግቢያ ይሆን ዘንድ ስለ ደጃዝማች አያሌው ብሩ ይህንን ያህል ካልሁ ዛሬ ላስታውሳቸው የወደድሁትን የጦር መሪያቸው የነበሩትን የፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁንን አስደናቂ የጀግንነት ታሪክ ወደማቅረቡ ልሸጋገር። ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን ትውልዳቸው ከበጌምድር ጋይንት ሲሆን እንዳባጉና ላይ የማርሻል ፔትሮ ባዶግሊዮን የጦር ኃይል ከጎጃም የዘመተው የአርበኛ ጦር መሪ ከነበሩት ከፊታውራሪ ክንፌ ማንያህልሀል ጋር በመሆን እስካፍንጫው የታጠቀውን የፋሽስት ጦር ግንባር ለግንባር ገጥመው፤ ከመሬት በታች የገነባውን ጥልቅ ምሽግ ጥሰው በመግባት የተከለውን መትረየስ ነቅለው፤ ያሰለፈውን ታንክ በእግረኛ ጦር ደምስሰውና ባዶግሊዮ ያሰማራውን ባንዳ ሶላቶ ማርከውና እጅ አልሰጥም ያለውን ፈጅተው ድል ካደረጉ በኋላ የወደቁ ጀግና ናቸው።

እንዳባጉና ላይ ታኅሣሥ 6 ቀን 1928 ዓ.ም. የተካሄደውን ፍልሚያ በሚያስደንቅ ጀግንነት ድል አድርገው የወደቁት የጋይንቱ ጀግና ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን ወደ እንዳባጉና የተሰማሩት ተከዜን በሊማሊሞ በኩል ተሻግረው የምስራቁን ግንባር እንዲይዙና ተከዜ አጠገብ እንዳባጉና የተባለውን ጣሊያኖች መሽገው የተቀመጡበትን ቦታ ከብበው እንዲጠብቁ ነበር። ሆኖም ግን እንዳባጉና አጠገብ ከደረሱ በኋላ ጦራቸው በጠላት እይታ ስር በመግባታቸው መሸሽ በማይችልበት ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ በመውደቃቸው የያዙት ቅኝት አድራጊ ጦር ትንሽ በመሆኑ ሳይዋጋ ከሚደመሰስ ከፋሽስት ጋር ተዋግተው በጀግንነት ለመወደቅ በማሰብ በታኅሣሥ 5 ቀን 1928 ዓ.ም. ወደ አዛዣቸው ወደ ደጃዝማች አያሌው ብሩ የሚከተለውን አስቸኳይ መልዕክት ላኩ፤

«ሌሊቱን ተከዜን ተሻግረን አፋፉን ከወጣን በሁኋላ ተሸሽገን የምንቆይበት ጫካ ፍለጋ ወደ ፊት ስንሄድ፥ እንዳባጉና አጠገብ እንደ ደረስን ስለ ነጋብን፥ ትንሽ ቁጥቋጦ አግኝተን እዚያ መስፈር ግድ ሆነብን። ይህ የሰፈርንበት ቦታ ትንሽ ቁጥቋጦ እንጂ ጫካ የሌለበት በመሆኑ ዛሬ እንደምንም ብንውል ነገ ልንውል አንችልም። ስለዚህ ጦራችን ጠላት ባለበት እንኩዋ ሳይደርስ ባይሮፕላን ተደብድቦ ሳያልቅ ነገ እንጋት ላይ እንዳባጉናን እንመታለንና ረዳት ጦር ቶሎ እንዲደርስልኝ [ይሁን]»

ፊታውራሪ ሽፈራው የስሜንንና የትግሬ ወሰን የሆነውን ተከዜን አቋርጠው የሰፈሩበት ሽሬ የሚገኘው እንዳባጉና የሚባለው የትግራይ ምድር በወቅቱ ጣሊያን በቦምብ ስላቃጠለው እንኳንስ ሰውና ወፍ የሚሸሽግ ጫካና ቁጥቁዋጦ ባለመኖሩ ነበር ጦራቸው አንድ ስራ ሳይሰራ በሰፈረበት ባይሮፕላን ተደብድቦ ከሚያልቅ ለምሳ ያሰባቸውን ፋሽስትን ለቁርስ አድርሰውት ለመውደቅ የተነሱት። ይህንንም በማሰብ ነበር እንዳይሰበር ተደርጎ የተሰራውን የእንዳባጉናውን የፋሽስቶች ምሽግ ለመደምሰስ ረዳት ጦር ይላክላቸው ዘንድ ወደ አዛዣቸው ወደ ደጃዝማች አያሌው አስቸኳይ መልዕክት የላኩት።

የመልዕክቱን አስቸኳይነት የተረዱት ደጃዝማች አያሌው ብሩ ለጦር መሪያቸው ለፊታውራሪ ሽፈራው ረዳት የሚሆን ጦር ፈጥነው ለመላክ ሲነሱ ያደረጉት ነገር ቢኖር ከጎጃም ጦር ተቀንሶ ለፊታውራሪ ሽፈራው ረዳት የሚሆን ጦር ወደ እንዳባጉና እንዲላክ የፊታውራሪ ሽፈራው ደብዳቤ በደረሳቸው እለት ካረፉበት ቦታ ለነበረው ለሐዲስ አለማየሁ መልዕክት አስይዘው ባስቸኳይ ያደርስላቸው ዘንድ የጎጃም አስተዳዳሪና ከጎጃም የዘመተውን ጦር እየመሩ ወደ ሰሜን ግንባር ወደ ዘመቱት ወደ ራስ እምሩ መላክ ነበር። የመልዕክቱም ይዘት የሚከተለው ነው፤

« ያለኝን ጦር ሁሉ በሶስት ከፍየ ወደ ግንባር ስለላክሁት፥ እኔ ጋር ከቀሩት ጥቂት ወታደሮች በቀር ተጨማሪ [ወደ ፊታውራሪ ሽፈራው] የምልከው ጦር ስለሌለኝ፤ ‹አዲያቦንና› መሀከለኛውን ግንባሮች ይዘው እንዲጠብቁ የሄዱትም ነገ ጧት ለሚካሄድ ጦርነት ርዳታ ለማድረግ እንዳይደርሱ ያሉበት የተራራቀ በመሆኑ ሌሊቱን ከጎጃም ብርቱ ረዳት ጦር ተልኮ ለነገ እንዲደርስለት በጥብቅ አደራ [እላለሁ]!»

ከደጃዝማች አያሌው ሰፈር ታኅሣሥ 5 ቀን 1928 ዓ.ም. አስር ሰአት ግድም ተነስቶ ሲጓዝ ሲጨልም የጎጃም ጦር ከሰፈረበት የደረሰው ሐዲስም የደጃዝማች አያሌውን መልዕክት ለራስ እምሩ አደረሰ። ራስ እምሩም መልዕክቱ እንደደረሳቸው ሳይዘገዩ ከጎጃም ጦር አዝማቾች ጋር ምክር አድርገው የጎጃም ጦር አዛዥ በነበሩት በፊታውራሪ ክንፌ ማንያህልሀል የሚመራ ጦር ሌሊቱን በግስጋሴ ተከዜን ተሻግሮ ለፊታውራሪ ሽፈራው ርዳታ እንዲደርስ አደረጉ።

ከጎጃም የተላከው ረዳት ጦር ከደረሰ በኋላ በፊታውራሪ ሽፈራው መሪነት የተካሄደውን የእንዳባጉናውን የጦር ሜዳ ውሎ፣ የጦርነቱን ዝርዝርና ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን የፈጸሙትን ጀብድ እዚያው በቅርብ ርቀት የነበረው የታዋቂው የፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድ ደራሲና አርበኛው ሐዲስ አለማየሁ «ትዝታ» በሚል በጻፈው ታሪካዊ መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 58 እንከ ገጽ 59 የከተበው እንዲህ ይነበባል፤

«የእንዳባጉና ጦርነት ታኅሣሥ 6 ቀን 1928 ዓ.ም. ነበር የተደረገው። በሰው ቁጥር እንዳባጉና መሽጎ ከተዋጋው የጣሊያን ጦር የፊታውራሪ ሽፈራውና የፊታውራሪ ክንፌ ጦር ባንድነት ይበዛ እንደ ነበረ፥ በጦርነቱ ተካፋዮች የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ። በመሳሪያ በኩል ግን በሁለቱ ወገኖች መሀከል የነበረው ልዩነት የሰማይና የምድርን ያክል የተራራቀ ነበር! የኢትዮጵያውያን መሳሪያ አብዛኛው ያው አሮጌ ጠመንጃ ነበር። በዚያ አንፃር የጣሊያኖች ጦር ምሽጉን አጠንክሮ ሰርቶ ይዋጋ የነበረ ከመሆኑ ሌላ መድፎች ብዙ ከባድና ቀላል መትረየሶች እንዲሁ የእጅ ቦምብ በብዛትና ታንኮች ነበሩት። ያም ሆኖ በመጨረሻ ድሉ ለኢትዮጵያውያን ሆነ።

በጦር ሜዳ፥ እንኩዋንስ የጠላትን ሙታንና ቁስለኞች የራሳችንንም ቆጥሮ የመያዝ ልምድ ስለሌለን በእዳባጉና ጦርነት ከኛም ከጠላትም ምን ያክል ሞተው ምን ያክል እንደ ቆሰሉ በኛ በኩል እርግጡን የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም መቸም እኔ አላውቅም። ማርሻል በዶሊዮ ግን እ.ኤ.አ. በ1936 ዓ.ም. በጻፈው የጦርነቱ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ከጣሊያን ጦር ወገን የሞቱና የቆሰሉ 392 ወታደሮችና 9 መኮንኖች በድምር 401 መሆናቸውን ጽፏል። ታዲያ እንዳባጉና ጦር ሜዳ ላይ ከሞቱት ተርፈው የእንዳ ስላሴን መንገድ ይዘው ሲሸሹ እስከ ብዙ ኪሎ ሜትር ድረስ ወድቀው ይታዩ የነበሩት የጣሊያንና የመለዮ ለባሽ «አሽከሬ» ሬሳዎች ቁጥር ተይዞ ሲገመት ማርሻ ባዶሊዮ የሰጠውን የሙታንና የቁስለኞች ቁጥር የሚያስተባብል ሆኖ ይገኛል፤ ከጣሊያንም ከኢትዮጵያም ወገን የሞቱትና የቆሰሉት ትክክለኛ ቁጥራቸው ባይታወቅም ብዙ ነበሩ። ከጣሊያኖች የተማረከው መሳሪያም እጅግ ብዙ ነበር። ከባዱና ቀላሉ መትረየስ ጠመንጃው የመተረየሱና የጠመንጃው ጥይት በሳጥን በሳጥን እንዳለ ሁሉም ብዙ ነበር። ሊሬው ከወታደሩ ተርፎ በባላገሩ እጅ በብዛት ይገኝ ስለ ነበረ እኛ ስንደርስ፥ ባንድ ብር እስከ ሺህ ሊሬ ይለወጥ ነበር። የተሰባበሩም ያልተሰባበሩም ታንኮችና ብረት ለበስ ካሚዎኖች በጦሩ ሜዳ በእንዳ ስላሴ መንገድ ቆመውም ተገልብጠውም በብዛት ይታዩ ነበር።

ማርሻል ባዶሊዮ ስለ ጦርነቱ በመጽሐፉ ሲተች «የእንዳባጉና ጦርነት ከጠቅላላው ጦርነት አንፃር ሲታይ ከቁም ነገር የሚቆጠር አይደለም» ብሏል። እርግጥ ከጠቅላላው ጦርነት አንፃር ሲታይ የእንዳባጉና ጦርነት ትንሽ ነው። ነገር ግን ብቻውን ሲታይ፥ – ብቻውን መታየትም ይገባዋል – ታሪካዊ ነው። የእንዳባጉና ጦርነት የተደረገበት ቦታ የተደረገበት ቀን በጦርንቱ ድል ያደረጉት ኢትዮጵያውያንና ድል የሆኑት ጣሊያኖች የራሳቸው የሆኑ መልክና ጠባይ ያሏቸው ናቸው። ስለዚህ፥ ጣሊያን በመጨረሻ በጠቅላላው ጦርነት ድል አድራጊ ሆኖ ኢትዮጵያን መያዝዋ የእንዳባጉና ን መልክና ጠባይ አይለውጠውም።

ጣሊያን በመጨረሻ ኢትዮጵያን ድል አድርጋ መያዝዋ እንዳባጉና ያለቁንት ሽማምንትዋንና ወታደሮችዋን ከሞቱበት በግዝፈ – ሥጋ አያስነሳቸውም፤ አካላተ ጎደሎዎች የሆኑትን ባለሙሉ አካላት አያደርጋቸውም። ይህ የተደረገ አድራጎት ስለሆነ፥ የተደረገው እንደ ገና እንዳልተደረገ ሊሆን አይችልም! እርግጥ በሌሎች ቦታዎችና በሌሎች ቀኖች ጣሊያን ድል አድርጋ ኢትዮጵያን ይዛለች። ነገር ግን ያ ሁሉ ጀግናው ፊታውራሪ ሽፈራውና ጀግኖች ተከታዮቻቸው ምሽግ አፍርሰው የመድፍና የመትረየስ አጥር ጥሰው ታንክ ሰባብረው የሚበዙትን ጣሊያኖች ገድለው የተረፉትን መሳሪያቸውን እያስጣሉ አባርረው የእንዳባጉና ን ድል የተቀዳጁ መሆናቸውን በምንም መንገድ ሊለውጠው አይችልም! ጣሊያን ኢትዮጵያን ድል አድርጋ መያዝዋ የሽፍራውን ጀግናነት ሊቀማው አይችልም! ሽፈራው ድል ባደረገበት ቦታ፥ እንዳባጉና ላይ ቢወድቅም ምድርን ከነታሪኳ የሚያጠፋ መአት እስካልመጣ ድረስ ጀግናነቱና ስሙ ከእንዳባጉና ተራራ ጋር ለሁልጊዜ ይኖራሉ።»

በዚህ መልክ መስዕዋት ለሆኑትና በፈረስ ስማቸው አባ ከንትር እየተባሉ ለሚጠሩት ለእንዳባጉናው ጀግና ለፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን አብረዋቸው ተሰልፈው በእድል ሕይዎታቸው የተረፈው ረዳቶቻቸው እንዲህ ሲሉ ፎክረውላቸዋል፤

እትት… እትት ስሜንን በረደው፣
አባ ከንተር ነበር አልፎ ሚጋርደው፤
አባ ከንትር ሽፌ ቀጭን ዘመናይ፣
ነጭ አንጥፎ ተኛ ከበረሀው ላይ፤


እነ ፊታውራሪ ሽፈራው የወደቁላት አገራችን ኢትዮጵያ የአርበኞች ልጆች በመስነፋቸው በባንዳ ልጆች ቁጥጥር ስር ወድቃ የጀግኖቿን ውለታ ቅርጥፍ አድርጋ የምትበላ አገር ሆናለች። አገር ላቆዩ አርበኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ንጉሠ ነገሥቱ ያቆሙት የአርበኞች ምልክት «የነፍጠኛና ፊውዳል ምልክት» ተደርጎ ስለተቆጠረ ፈርሶና ተፍቆ አገር ለማፍረስ ለታገሉት ለምንደኞቹና ለእንደራሴዎቻቸው የፋሽስት ወያኔ ደንገጡሮች መታሰቢያ ሆኗል። ጣሊያን ከሽሬ አውራጃ ተነስቶ ተከዜን ተሻግሮ ወደ በጌምድርና ስሜን ሲያቀና እንዳባጉና ላይ በቆፈረው ምሽግ የቀበሩት፤ ያለ ታንክና መሣሪያ አበሳውን አሳይተው ምሽጉን ሰብረው ግዙፉን የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን ግንባር ድል መትተው የወደቁት ወደር የማይገኝላቸው ጀግና ግን አንድም መታሰቢያ የላቸውም።

በፋሽስት ወያኔ አተላ ተሸካሚዎችና የአማራው እርግማን በሆነው በብአዴን ኮልኮሌዎች እየታመሱ ያሉት እነ ፊታውራሪ ሽፈራውና ፊታውራሪ ክንፌ የተወለዱበት በጌምድርና ጎጃም ለፋሽስት ወያኔና ለምንደኞቹ መታሰቢያዎች ይሁኑ ዘንድ በስማቸውና የድል ቀን አድርገው በሚቆጥሩት ግንቦት ሐያ ስም ተሰይመው የሚገኙ ብዙ ተቋማት አሉ። ጎጃሜና ጎንደሬ ሳይባባሉ፤ አካባቢና ወንዝ ሳይወስናቸው፤ አንዱ ለሌላው ደራሽ ሆነው ከራሳቸው በላይ ለሆነ አላማ አብረው የወደቁት የፊታውራሪ ክንፌና የፊታውራሪ ሽፈራው ልጆች ግን በብአዴን ችግር ተጠልፈው በመውደቅ በብአዴን ገመድ እየተጓተቱና ምክንያቱ በበዛ ጎጠኛነት እየተቆራቆሱ አባቶቻቸው የሚያፍሩባቸው ከንቱዎች ለመሆን የቁልቁለቱን መንገድ ተያይዘውታል። ቢያውቁበት አብረው የወደቁትና በጋራ ያሸነፉት ያባቶቻቸው ታሪክ ካለፉ በኋላ እንዳባቶቻቸው የሚታወሱበትን ታሪክ እንዲሰሩና ለዘላለለም የሚታወስ ስም እንዲተክሉ የሚያስችል በብዙ አለም የሌለ እርሾ ነበር። የአባቶቻቸው ምልክቶች መሆን የሚገባቸውን መታሰቢያዎች በፋሽስት ወያኔና በምንደኞቹ ስም እየጠሩ [ይህ በንጉሡ ዘመን ተጀምሮ በወያኔ ዘመን ተቋርጦ በቅርቡ በረራ እንደሚጀምር እየተነገረለት ያለውን የደብረ ታቦሩን የአውሮፕላን ማረፊያ ይጨምራል] በጎጥ ተወስነው በደም አረንቋ የሰጠሙትን የአቤልና ቃኤልን ታሪክ ለማስናቅ የክፋት ሁሉ ማደሪያ ሲሆኑ ቢውሉ ባካባቢና በጎጥ ሳይወሰኑ ከራሳቸው በላይ ለሆነ አላማ አብረው የወደቁት የፊታውራሪ ሽፈራውና የፊታውራሪ ክንፌን አጥንት ከማስወቀስ አልፈው ፤ ለማያንቀላፋው፣ ባካባቢ ሳይወስንና በጎጥ ሳይለይ እኩል ጠላት ላደረጋቸው አካል ሲሳይ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የላቸውም።

Achamyeleh Tamru

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator