0 0
Read Time:5 Minute, 26 Second

ክፍል~፩

ሊላይ ኃይለ ማርያም የተባለ የወያኔ የአፓርታይድ አገዛዝ ሰላይና “የቀዳማይ ወያኔ” መሪ የነበሩት የብላታ ኃይለ ማርያም ረዳ ልጅ ከሰሞኑ በፋና ቴሌቭዥን በመቅረብ ተዘርዝሮ የማያልቅ የፈጠራ ድርሰቱን ሲያቀርብ ሰንብቷል። ሊላይ ኃይለ ማርያም በፋና ቴሌቭዥን ቀርቦ ካስተጋባው የፈጠራ ታሪክ ውስጥ በዛሬው ጽሑፌ በቅድሚያ የምተቸው ከአባታቸው ሞት በኋላ የአባታቸውን ሹመትና ግዛት በልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ በመነፈጋቸው የተነሳ ሸፍተው ሲኖሩ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ ቀን ስለወጣላቸው፣ ፋሽስት ጣሊያንንም አምስት ዓመታት ሙሉ በታማኝነት ስላገለገሉት እና ፋሽስት ጣሊያን “ብላታ” የሚል ማዕረግ ሰጥቶ ስለሾማቸው የትግራይ አርበኞች ጸርና ልጃቸው ሊላይ ኃይለ ማርያም ግን ሳያፍር አርበኛ አድርጎ እያቀረባቸው ስለሚገኙት ስለባንዳው ብላታ ኃይለ ማርያም ረዳ የቀባጠረውን የፈጠራ ታሪክ ነው። በቀጣይ ክፍል የማቀርበው ደግሞ ፋሽስት ጥሊያን በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር ሲባረር የጣሊያን ሹም የነበሩት ባንዳው ብላታ ኃይለ ማርያም ረዳ ፋሽስት ጣሊያን የሰጣቸው ግዛት በድል አድራጊ አርበኞች ከተነጠቁ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በመሸፈት የመሩትንና “ቀዳማይ ወያኔ” እየተባለ ስለሚተረከው የሽፍተነት እንቅስቃሴ ሊላይ ኃይለ ማርያም ያስተጋባውን ልብ ወለድ ታሪክ የሚተች ይሆናል።ታሪኩን ወደ ማቅረብ ከመሸጋገሬ በፊት አንባቢን አንድ ነገር ለማሳሰብ እሻለሁ። ወረድ ብዬ በማቀርበው ሀተታ በተለምዶ “ብላታ ኃይለ ማርያም ረዳ” እየተባሉ የሚጠሩትን የሊላይ ኃይለ ማርያምን አባትና “የቀዳማይ ወያኔ” መሪ ተደርገው የሚቀርቡትን ሰው አቶ ኃይለ ማርያም እያልሁ ነው የምጠራቸው። ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ሲል እንደጠቆምሁት አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ “ብላታ” የሚለውን ማዕረግ ያገኙት ለፋሽስት ጣሊያን በባንዳነት ሲያድሩ የተሰጣቸው የባንዳነታቸው ማኅተም በመሆኑ ባንዳውን ኃይለ ማርያም ረዳን ለፋሽስት ጣሊያን ባገለገሉበት ማዕረግ መጥራጡ ለፋሽስትን ስላገለገሉ እናመሰግናለን ማለት ስለሚሆንብኝና አገር ያገለገሉ አርበኞች እንዲጠሩነት የሚሰጠውን የብላታነት ማዕረግ ፋሽስት ጣሊያን እንዲያገለግሉት ብላታ ብሎ በሾማቸው ማዕረግ መጥራቱ ስለአገር በወደቁና በደሙ አርበኞቻችን ላይ መሳለቅ ስለመሰለኝ ነው። አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ማን ናቸው?አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ከአባታቸው ከግራዝማች ረዳ ገብሩ አጽቀ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ብስራት ወልደየስ ትግራይ ውስጥ እንደርታ በሚባል አውራጃ ከመቀሌ ከተማ በስተ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 17 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ዳንደራ ተብላ በምትጠራ የገጠር ቀበሌ ሐምሌ 21 ቀን 1900 ዓ.ም. ተወለዱ። የአቶ ኃይለ ማርያም ረዳ እናት ወይዘሮ ብስራት ወልደየስ በዘመነ መሣፍንት ወቅት ትግሬንና ባሕረ ነጋሽን ጠቅልለው የገዙት፣ የኢትዮጵያን የባሕር ጠረፍ በወታደር ኃይል ለማስጠበቅ ከደጋው ሰብል፣ ከቆላው ፍየል፣ ከባሕሩ ዓሣ እየተመገበ የሚኖር ሠራዊት የመለመሉትና ‹‹ስሞት ፊቴን ወደ ቀይ ባሕር አዙራችሁ ቅበሩኝ››ማለታቸን ታሪካቸው ከሚያስረዳው ከአጋሜ ከደጃዝማች ስባጋዲስ ወገን የሚወለዱት የደጃች ወልደየስ ልጅ ሲሆኑ አባታቸው ግራዝማች ረዳ ገብሩ ደግሞ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ምስራቅ ትግራይ ውስጥ ጭቃ ሹም የነበሩ ሲሆን ዐፄ ዮሐንስ መተማ ዘምተው ሲወድቁ አብረው በመዝመት ለአገራቸው ተዋግተዋል። ከመተማ ጦርነት በኋላ ወደ ትውልድ ቅያቸው በመመለስ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት እስከ 1927 ዓ.ም. ድረስ መጀመሪያ በልዑል ራሽ መንገሻ ዮሐንስ፤ በመቀጠል በልዑል ራስ መንገሻ ልጅ በልዑል ራስ ስዩም መንገሻ አማካኝነት ከጭቅነት እስከ አውራጃ ገዢነት እየተሾሙ አገራቸውን አገልግለዋል[1]። አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ የወጣትነት ዘመናቸው ያሳለፉት “ጋዝ” እየተባለ በሚታወቀው ወደ አፋር የሚደረግ የግድያና የዘረፋ ዘመቻ ተሳታፊ በመሆን ነበር[2]። “ጋዝ” ማለት የደቡብ ትግራይ ለየት ያለ መጥፎ ልማድ ነው። ይህ መጥፎ ልማድ የእንደርታና የዋጅራት ወንዶች በየዓመቱ ወደ አፋር እየዘመቱና እየወረሩ የሚመለሱበት ባሕል ነው። ይህ የመዝረፍ ባሕል በተለይ የወንዶች ጉብዝና መለኪያም ተደርጎ ይቆጠራል[3]። ባለታሪካችን አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ግን ወደ አፋር ያደርጉት የነበረው የወረራና የዘረፋ ዘመቻ የጋዝን ወቅት የጠበቀ ብቻ አልለበረም። ይሆም የሆነበት ምክንያት በአንዱ የጋዝ ዘመቻ ታላቅ ወንድማቸው አቶ ነጋ ረዳ በአፋሮች ስለተገደለባቸው ነው[4]። በዚህም የተነሳ በአፋሮች ላይ ቂም ቋጥረው የወንድማቸውን ደም ለመበቀል በተለያዩ ዙሮች ወደ አፋር እየዘመቱ ግድያና ዘረፋ ይፈጽሙ ነበር[5]። ወጣትነታቸው በዚህ መልኩ ያሳለፉት አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ በ1927 ዓ.ም. ወላጅ አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የአባታቸው ግዛትና ማዕረግ ተሰጥቷቸው እንዲሾሙ ለወቅቱ የምስራቅ ትግሬ ገዢ ለልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ ማመልከቻ አቀረቡ። ሆኖም ግን ማለምከቻቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱና አባታቸው ያስተዳድሩት የነበረው ግዛት ለሌላ የትግራይ ባላባት በመሰጠቱ ተቀይመው ሸፈቱ። ይህንን ታሪክ የሚነግሩን የአክሱም ተወላጁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ “Peasant Resistance in Ethiopia: The Case of Weyane” በሚል ርዕስ ጽፎ በ1977 ዓ.ም. The Journal of African History, በተባለ ጆርናል ቅጽ 25 ቁጥር 1 ገጽ 88 ላይ በጻፉት የጥናት ውጤት ነው። አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ የጠየቁት ሹመት ስላልተሰጣቸው አኩርፈው በሽፍትነት በተሰማሩበት ወቅት የትግራይን በተለይም የእንደርታን ገበሬዎች ምግብና ገንዘብ ካልሰጣችሁኝ እያሉ ይገድሉና ያሰቃዩ እንደነበር ታሪካቸውን በመመርመር የመዘገቡት ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁር ፕሮፈሰር ፍሥሐ በርኼ ናቸው[6]። አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ በዚህ አኳኋን እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ ሸፍተው ጫካ ከቆዩ በኋላ በ1928 ዓ.ም. ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያ በመውረሩ ሰርግና ምላሽ ስለሆነላቸው ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን እንደተቆጣጠረ ለፋሽስት በማደር ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ በከለከሏቸው ግዛት ላይ “ብላታ” የሚል ማዕረግ ሰጥቶ ፋሽስት ጣሊያን ሾማቸው። አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ለፋሽስት ጣሊያን አድረው፤ አርበኞችን በተለይም የመሳፍንትነት ዘር ያላቸውን የትግራይ አርበኞች እያሳዱ በመውጋት ፋሽስት ጣሊያን በሰጣቸው የብላታነት ማዕረግ እየተጠሩ ለአምስት ዓመታት ሙሉ ማለትም ከ1928 ዓ.ም. – 1933 ዓ.ም. ደረስ ፋሽስት ጣሊያንን እስኪያልባቸው ድረስ አገልግለዋል። ይህንን የአቶ ኃይለ ማርያም ረዳን የባንዳነት ዘመንና ፋሽስት ጣሊያን ስለተሰጣቸው የብላታነት ማዕረግ ታሪክ የሚነግሩን የቀዳማይ ወያኔን እንቅስቃሴ በጥልቀት ያጠኑት የትግሬ ተወላጆቹ ፕሮፌሰር ፍስሐ በርኼ[7] እና የታሪክ ምሁር ፕሮፈሰር ገብሩ ታረቀ [8][9] እንዲሁም የሐድያ ተወላጁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ላጲሶ ዴሌቦ ናቸው[10]። ፋሽስት ጥሊያን በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር ከተባረረ በኋላ የጣሊያን ሹም የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም በቅድሚያ መቀሌ ወደነበሩት ወደ ልዑል ራስ ሥዩም፤ ይህ አልሳካ ሲል ደግሞ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ቀርበው ፋሽስት ጣሊያን የሰጣቸው ሹመት በድል አድራጊ አርበኞች ስለተነጠቁ ባንዳ ሆነው ፋሽስትን አምስት ዓመት ሙሉ ያገለገሉት ኀጢያት ተሰርዮላቸው ፋሽስት ጣሊያን የሰጣቸው የብላታነት ማዕረግ እንዲጸላቸውና በፋሽስት ጣሊያን ዘመን የተሰጣቸው ሹመት እንዲከበርላቸው አመለከቱ [11]። ሆኖም ግን ልዑል ራስ ሥዩምን ሆነ ንጉሠ ነገሥቱን ደጅ ጠንተው የፈለጉትን ባለማግኘታቸው ቅር የተሰኙት አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ እንደተመለሱ ድጋሜ ሸፈቱ[12]። ይታያችሁ! ሊላይ ኃይለ ማርያም አርበኛ አድርጎ ሊያቀርባቸው የሚፈልጋቸው አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጥሊያን ነጻነቷ ሲገፈፍ፣ ክብሯ ሲደፈርና ሰንደቅ አላማዋ ሲታጠፍ ባንዳ ሆነው ፋሽስት ጣሊያንን እስመጨረሻው ሰዓት ድረስ በማገልገል ላይ ተጠምደው ያልሸፈቱትንና ኢትዮጵያ ነጻነቷን ስትቀዳጅ ግን በአርበኞች ላይ ለመሸፈት የበቁትን ባንዳ አባቱን ነው። ይቀጥላል. . . በቀጣይ ክፍል አቶ ኃይለ ማርያም ረዳ ለሁለተኛ ጊዜ ሸፍተው ስለመሩት “ቀዳማይ ወያኔ” ስለሚባለው የሽፍትነት እንቅስቃሴ ታሪክ እውነቱን ከነምንጩ አቀርባለሁ። ምንጮች፤ [1] Berhe, Fesseha(2011). Studies on the Biography of Blatta Hayle Maryam Redda (1909-1995); Page 78-79. [2] Ibid; Page 80. [3] Tarekegn Gebreyesus, “Gaz”, in Siegbert Uhlig(ed): Encyclopedia Aethiopica, vol.2 (D-H), Wiesbaden, 2005[4] Berhe, Fesseha(2011). Studies on the Biography of Blatta Hayle Maryam Redda (1909-1995); Page 80. [5] Ibid; [6] Ibid; Page 83. [7] Ibid; Page 84-85. [8] Tareke, G. (1984). Peasant resistance in Ethiopia: The case of Weyane. Journal of African History, 77-92. Page 88;[9] Tareke, G. (1991). Ethiopia: Power and protest: Peasant revolts in the twentieth century. Cambridge University Press. Page 116፤ [10] ላጲሶ ጌ. ዴሌቦ(1983). የኢትዮጵያ የገባር ስርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም 1900- 1966፣ አዲስ አበባ፡ ንግድ ማተሚያ ቤት; Page 141. [11] Haggai Erlich, “Tigrean Nationalism, British Involvement and Haile-Sellasse’s Emerging Absolutism-Northern Ethiopia, 1941-1943”, in: Asian and African Studies 15 (1981), p. 220[12] Gebru, “Peasant Resistance in Ethiopia”, p. 88; Gebru, Ethiopia: Power and Protest, p. 116; Lapiso, p. 145

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator