አሳዛኝ ዜና!
ደሴ ንጉስ የተባለ ወጣት ከልዩ ኃይል በተተኮሰ ጥይት መገደሉን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፤ ግድያውን የፈጸመው አካል በአስቸኳይ በህግ እንዲያዝላቸው ጠይቀዋል።
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ጥር 12 ቀን 2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ሸዋ
ደሴ ንጉስ የተባለ ወጣት የፋኖ አባል ከልዩ ኃይል በተተኮሰ ጥይት ጥር 10/2015 ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ መገደሉን አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ያነጋገራቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ
ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሟች በወቅቱ ጀሌ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች በገንዳውሃ ከተማ 01 ቀበሌ አቦ ሰፈር አካባቢ ስለመገደሉ አክለው ተናግረዋል።
ግድያው ምንን መነሻ ምክንያት አድርጎ እንደተፈጸመ የጠራ መረጃ እንደሌላቸው የገለጹት ምንጮች ይህ ድርጊት ብዙዎችን ማስቆጣቱን አልሸሸጉም።
በዚህም ከተለያዩ አካባቢዎች የጥይት ድምጽ እየተሰማ ነው ብለዋል።
የከተራ በዓል በሰላም ተከብሮ ከዋለ በኋላ ምሽት ላይ ይህ መከሰቱ እንዳሳዘናቸው የተናገሩት የዐይን እማኞች ግድያውን የፈጸመው ብሎም በዓሉ በተረጋጋ ሁኔታ እንዳይከበር ያደረገው አካል በአስቸኳይ በቁጥጥር ስር እንዲውልላቸው ጥሪ አድርገዋል።
ትጥቁን ይዞ በራሱ ግሮሰሪ በር ላይ ተቀምጦ የነበረውን የአማራ ፋኖ በመተማ ዮሃንስ አመራር ሻለቃ ጎሼ ገበየሁን ጥር 10/2015 ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ “ጦር መሳሪያህን ወደ ቤትህ አስገባ፣ ይዘህ መቀመጥ አትችልም” በሚል ወከባ ፈጥረዋል ከተባሉት የመከላከያ እና የጸረ ሽምቅ አባላት ጋር አለመግባባትና ውጥረት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የጉዳዩ ዋነኛ መነሻ ግን “በቀበሌ ሰላም እና ደህንነት ታቅፋችሁ ተንቀሳቀሱ የሚለውን አቅጣጫ አንቀበልም፤ በራሳችን የፋኖ አደረጃጀት እየተንቀሳቀስን የጸጥታ ስራውን እናግዛችኋለን” ማለታቸውን ተከትሎ ደስተኛ ያልሆኑ አካላት ያደረጉባቸው ትንኮሳ ነው ብለው እንደሚያምኑ ምንጫችን ተናግረዋል።
በተፈጸመው የግድያ ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ ያዘኑ እና የተቆጡ የገንዳውሃ ነዋሪዎችም የወጣት ደሴ ንጉስን ስርዓተ ቀብር በእለተ ጥምቀት ጥር 11/2015 ፈጽመዋል።