ፖሊስ ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ ጠርጥሬሃለሁ ማለቱን ተከትሎ በትናንትናው እለት ለ4ኛ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የቀረበው ካፒቴን ማስረሻ ሰጠኝ ለዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው መሆኑን የአማራ ሚዲያ ማዕከል መዘገቡ ይታወቃል።

ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም በነበረው ችሎት ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ለጠቅላይ አቃቢ ሕግ መዝገቡን መላኩን በማስታወቅ አቃቢ ሕግ መዝገቡን መርምሮ “ያስከስሳል አያስከስስም” በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ያመቸው ዘንድ ፍ/ቤቱ የመሰለውን ጊዜ እንዲሰጥ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ አስረስ ማረ ዳምጤ በበኩላቸው ይህንን ጥያቄ ማቅረብ የሚችለው ራሱ አቃቢ ህግ እንጅ ፖሊስ አቃቢ ህግን ወክሎ መዝገብ የሚመረመርበት ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ መጠየቅ የሚችልበት ምንም አይነት የህግ ማዕቀፍ የለውም ሲሉ መቃወማቸውም ይታወሳል።

የባህር ዳር ወረዳ ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ሀሳብ መርምሮ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠቱ ካፒቴን ማስረሻ በቀጠሮው መሰረት ከማ/ቤት ቀርቧል።

ችሎቱም ዛሬም ጠበቃ አለመቅረቡንና የክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ አለመጠየቁን በማረጋገጥ ትናንት ፖሊስ በአቃቢ ሕግ ስም የጠየቀውን የውሳኔ ማሳረፊያ ጊዜን ውድቅ በማድረግ መዝገቡን ዘግቷል።

ፖሊስም ተጠርጣሪው የት መቆየት እንዳለበት ዳኛ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ሲጠይቅ ዳኛውም በፈለጋችሁበት ማቆየት ትችላላችሁ የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ተከትሎ ከችሎት ወጥተዋል።

ነገር ግን ለ40 ደቂቃ ገደማ ከችሎት ውጭ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ በድጋሜ ችሎት እንዲሰየም ተደርጎ በማ/ቤት ይቆይ በሚል ዳግማዊ ትዕዛዝ ስለመስጠቱ ጠበቃ አስረስ ማረ ተናግረዋል።

ጠበቃ አስረስ ማረም ፍ/ቤቱ እንዴት ብይን በሰጠበት ጉዳይ ላይ በድጋሜ ትዕዛዝ ይሰጣል በሚል ስለመጠየቃቸው አውስተዋል።

የባህር ዳር ከተማ የወረዳ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ዳኛውን በመጥራት ሲያነጋግረው ከቆዬ በኋላ ተመልሶ ዳግም በመሰዬምና ወደ ችሎት እንድንገባ በማድረግ እርስ በርሱ የሚጋጭ በብይን ላይ ብይን ሰጥቷል ያሉት ጠበቃ አስረስ ማረ ደንበኛዬ ከህግ አግባብ ውጭ እየታሰረ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

ፍ/ቤቱ መጀመሪያ ላይ መዝገቡን መዝጋቱን ተከትሎ ካፒቴን ማስረሻ በፖሊስ እጅ ታስሮ የሚቆይ ከሆነ እስሩ ህገ ወጥ ስለሚሆን፣ ጠበቃው አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ ለማቅረብ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጅ ዳኛው ባልተገባ ተፅዕኖ ተመልሶ በማ/ቤት እንዲቆይ ማዘዙ አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታቱን ውድቅ አድርጎብናል ሲሉም አክለዋል።

ከባህር ዳር ሰባታሚት ማ/ቤት የቀረበው ካፒቴን ማስረሻ ሰጠኝ በበኩሉ ከዚህ በኋላ በፍ/ቤት በኩል ያለው የሕግ ጉዳይ አልቋል፤ እስሩ የሚቀጥል ከሆነ የጉልበተኞች ጉዳይ ነው የሚሆነው ስለማለቱ ተገልጧል።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ


By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator