አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ ሸዋ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሎ በተባለው ቀበሌ ባሉ በርካታ መንደሮች ላይ በሚኖሩ አማራዎች ላይ የመንግስታዊ መዋቅር ድጋፍ ባለው በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ
እጅግ አሳዛኝ ዘር ተኮር ጅምላ ፍጅት ተፈጽሟል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኔ 11/2014 በዋናነት ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ እስከ ቀኑ 8:00 ድረስ ሲሆን ይሁን እንጅ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልፎ አልፎ ጥይት እየተተኮሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ለሰዓታት በቆዬው በቡድን መሳሪያ የታገዘ ዘር ተኮር የሽብር ጥቃት ንጹሃን ሴቶች እና ህጻናት በዋናነት በጅምላ ተጨፍጭፈዋል።

የወራሪው ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት የአካባቢው የመስተዳድር አካላት እየጣሉ ወደ ግምቢ ማቅናታቸው ተሰምቷል።

አሸባሪው ኦነግ ሸኔ በተደራጀ መልኩ በጭካኔ እንደ አውሬ እያሳደደ የጅምላ ፍጅት ከፈጸመባቸው የቶሌ መንደሮች መካከልም:_

1) አሶሳ ሰፈር፣
2) ሰኔ ሰፈር፣(በቤንሻንጉል ያለ የቶሎ አዋሳኝ)
3) ሀያው ሰፈር፣
4) ካራቆሪ፣
5) በገኔ፣
6) ጨቆርሳ፣
7) ጃታማ፣
8) ጉትን፣
9) ስልሳው ፣
10) 13ቱ የተባሉ አካባቢዎች ይገኙበታል።

ስልሳው ከተባለ መንደር አስከሬን ቆጥሬያለሁ ያሉት የዐይን እማኝ 71 ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ተገድለዋል፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት ናቸው ይላሉ።

የዐይን እማኙ ሲቀጥሉ ከአንድ ቤት ብቻ የሼህ መሀመድ አሊ 6 ቤተሰቦች፣ ከሌላ ቤት ደግሞ 4 ተገድለዋል፤ 26 የሚሆኑትን ሰብስበው አንድ ላይ ረሽነዋል፤ ከ6 ሽህ በላይ አማራዎች ወደ ጫካ ገብተዋል ሲሉ አሳዛኙን የዘር ፍጅት ተናግረዋል።

እኒህ በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው መለስተኛ ባለሃብት የሆኑት ሼህ መሀመድ አሊ ባለቤታቸውን ወ/ሮ ኮኮቤ ኢብራምንና 5 ልጆቻቸውን ነው በጨካኞች የተነጠቁት።

አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ያነጋገራቸው ጫካ ውስጥ የገቡ እናት አንዲት የ15 ቀን ህጻን የያዘች ልጇ፣ እና ሌሎች 2 አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በድምሩ 4 ልጆች እንደተገደሉባት ተናግራለች።

ሌላኛዋ እናት መንታ ህጻን ልጆቿን ይዛ ጫካ ብትገባም 3 ልጆቿ እና አራስ እህቷ የት እንደገቡ አላወቀችም፤ ለተረፍነው ድረሱልን፤ አስከሬንም ይነሳ ሲሉ ተማጽነዋል።

ክብራችን ከአውሬ በታች ተዋርዷል የሚሉት እኒህ እናት ይህን ያህል ጭፍጨፋ ሲፈጸም አንድም የመንግስት አካል አልደረሰም ብለዋል።

ሌላኛው ምንጫችን የሟቾችን ቁጥር ከ80 በላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

በእነዚህ ሰፈሮች በከፈቱት ጦርነት ከአደጋው ተርፈው በጫካ የገቡ ወገኖች እንደሚሉት ቢያንስ ከ1,000 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል።

ሰኔ በተባለ የቶሌ አዋሳኝ የቤንሻንጉል ክልል አካባቢ ደግሞ የማውቃቸው ኑሩ ሙሄ እና ሁሴን ሙሄ የተባሉ ወንድማማቾች አስፓልት ላይ ተገድለዋል ይላሉ አስተያየት ሰጭው።

ጉትን ላይ ደግሞ አቶ ሙሌ ሰይድ የተባሉ ነጋዴ 1 ሽህ ኩንታል እህል ተቃጥሎባቸዋል።

በየሁሉም መንደሮች በተደራጀ እና በተናበበ መልኩ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ በመፈጸሙ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በእጅጉ እንደሚያሻቅብ እየተነገረ ነው፤ የደረሰ የመንግስት አካል የለም፤ ይልቁንስ በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደተለመደው ቀደም ብለው እየጣሉ በመውጣት ጭፍጨፋው እንዲፈጸም አድርገዋል።

ሙሉ መረጃውን በአሚማ የዩቱብ አድራሻ ይከታተሉ።

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator