0 0
Read Time:4 Minute, 5 Second

አቻምየለህ ታምሩ

ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ፣ በ1953 ዓ.ም. እነ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ የሞከሩትን ስዒረ መንግሥት በቀዳሚነት ያከሸፉትንና ደርግ ከጭሰኞቻቸው ጋር በግፍ የረሸናቸውን የጄኔራል ታደሰ ብሩን ሐውልት በትናንትናው እለት በምድረ ሸዋ በጥንታዊቷ የአማራና ርስት በሆነችው በሰላላ/ሰላሌ መርቋል።

ጀኔራል ታደሰ ብሩ አባታቸው አቶ ብሩ ኬኔ ናቸው። አቶ ብሩ ኬኔ የከረዩ ኦሮሞ ሲሆኑ የትውልድ ሀረጋቸው እንደሚከተለው ነው፤ ብሩ ኬኔ ጅሩ ኡመቶ ጉታ ሞገር ደራ አቦቴ ሲንቼል ሲቡ ኢሌ አባዶ ሊበን ከረዩ ኦቦ። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አዋሽን ተሻግሮ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ወደ ነበሩበት ወደ አማራ ምድር ወደ ግራርያ አውራጃ ሰላላ ወረዳ የመጣው የመጀመሪያው ትውልዳቸው አባዶ ሊበን ነው።

የጄኔራል ታደሰ አባት አቶ ብሩ ኬኔ ጸረ ፋሽስት አርበኛ የነበሩ ሲሆኑ ሕይዎታቸው ያለፈው ከራስ ካሳ ጋር በመዝመት ለአገራቸው ተሰልፈው ሲዋጉ በፋሽስት ጥሊያን የመርዝ ጭስ ነው። አባቱ ሲሞቱ የ13 ዓመት ልጅ የነበረው ታደሰ ብሩ የአባቱን ፈለግ በመከተል ፋሽስት ጥሊያንን ለመፋለም ዱር ቤቴ ባለበት ወቅት በፋሽስት ጥሊያን ተማርኮ ወደ ሞቃድሾ እስር ቤት ውስጥ ተሰቃይቷል።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት እንደገና ሲቋቋምና ፋሽስት ጥሊያን ያሰራቸው የኢትዮጵያ አርበኞች ከሶማሊያ እስር ቤት ሲለቀቁ ወጣቱ ታደሰ ብሩም የጦር ሰራዊት አባል በመሆን አገሩን ማገልገል ጀምሯል። የኢትዮጵያ ፖሊስ እንደ ተቋም ሲመሰረት ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ከሶስተኛው ክፍለ ጦር ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው ከመጡት ወጣት የሰራዊቱ አባላት መካከል አንዱ ታደሰ ብሩ ነበሩ። በጊዜ ሂደት በሹመት ላይ ሾመት እየደረቡ በማደግ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ ሆነው በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተሹመዋል።

መግቢያዬ ላይ እንዳወሳሁት ጀኔራል ታደሰ ብሩ የተወለዱበት አገር ሰላሌ ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመስፋፋቱ በፊት የአማራ አገር ነበር። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቱለማ የኦሮሞ ጎሳዎች ከብቶቻቸው እየነዱ ሸዋን ወረው ባለ ርስቱን ገበሮ፣ ጠለታና ገርባ በማድረግ የቦታውን ስያሜ ሰላሌ ብለው corrupt ከማድረጋቸው በፊት የቦታው ትክክለኛ መጠሪያ ሰላላ የሚል የአማርኛ ስም ነበር። ሰላላ አማርኛ ነው። ሰላላ የሚለው የአካባቢ መጠሪያ ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመስፋፋቱ በፊት በተጻፈው የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። የዐፄ ሱንዮስ ጸሐፌ ትዕዛዝ አዛዥ ተክለ ሥላሴ ዐፄ ሱስንዮስ በአያታቸው ምድር በሸዋ ያሳለፉትን የወጣትነት ዘመን በገለጹበት የዜና መዋዕሉ ክፍል እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፤

“ወበውእቱ ምድረ ረከቦ ዓብይ ምንዳቤ ረኅብ እስከ በልኡ ሠራዊቱ አሣእነ እግሪሆሙ። እስመ ተኃጥ አእክል ለሲሳይ በእንተ ዘኮነት ይእቲ ምድር በድወ ወዓጸ። ወእምዝ ተንሥአ እምይእቲ ምድር ወአመልአ ፍኖቶ መንገለ ግንድ በረት ። ወእምዘ የሐውር በጽሐ ምድረ ሰላላ።” [Pereira, F. M. E. (1892). Chronica de Susenyos, Rei de Ethiopia: Texto ethiopico: destinado á X sessão do congresso internacional dos Orientalistas. Imprensa nacional; Page 22 ]

ትርጉም፤

ያንጊዜም ሐንገታሞ በሚባል ስፍራ ተቀመጠ። በዚያም ስፍራ ታላቅ የርሐብ ችግር ገጠመው፤ ተከታዮቹ የእግራቸውን ጫማ እስኪበሉ ድረስ። ለምግብ የሚሆን እህል ታጥቷልና፤ቦታዋ ምድረ በዳና ደረቅ ስለሆነች። ከዚህ በኋላ፣ ከዚያች ቦታ ተነስቶ ወደ ግንደ በረት ጉዞ አደረገ። ሲሄድም ሰላላ ደረሰ።

ሐንገታሞ ደብረ ብርሀን አካባቢ የሚገኝ አገር ነው። ግንደ በረትም አሁንም ድረስ ሸዋ ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው። ዜና መዋዕሉ እንደሚነግረን ዐፄ ሱስንዮስ ከደብረ ብርሀን አካባቢ ተነስቶ ወደ ግንደ በረት ለመሄድ ሰላላ አድሯል። ይህ ሁሉ ታሪክ የተፈጸመው ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመምጣቱ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ነው።

ሰላላ በአማርኛ አነጋገር ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል። ጎጃም ስናድግ ልጆች ሳለን የዘመን መለዋጫ በዓልን ሲከበር በወጣቶች በሚዜሙ ጥዑመ ዜማዎች ውስጥ ሰላላ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በበዓሉ እለት ከሚዜሙት ጥዑመ ዜማዎች መካከል ሴት ቆነጃጅት እንዲህ እያሉ ያዜሙ ነበር፤

የቅዱስ ዮሐንስ ያልዘፈነች ቆንጆ፣
ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ፤
እቴ አደይ አበባ ነሽ፣
ዉብ ነሽ ዉብ ነሽ፤

ልጃገረዶች ይህንን ዜማ እንግጫ እየነቀሉ ሲያሰሙ፤ ጎረምሶች ወንዶች ደግሞ የሚከተለውን እያዜሙ ወደ ልጃገረዶች ይሄዳሉ፤

እንግጫችን ደነፋ፣
ጋሻዉን ደፋ፤
እንግጫዬ ነሽ ወይ፤

ኮረዶች ይህንን ሲሰሙ እንዲህ ብለው ይመልሳሉ፤

እሰይ እሰይ፣
የቅዱስ ዮሐንስ የመስቀል የመስቀል፤
የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ፣
መልሰህ ዉሰደዉ ጉዳይም አይሞላ፤

በዚህ ጊዜ ጎረምሳው ለወደዳት ልጃገረድ ማተብ ያስርላታል። ጨዋታው እንዲህ እንዲያ እያለ ይደራ ነበር. . .

የሆነው ሆኖ የኦሮሞው ጀኔራል የታደሰ ብሩ መታሰቢያ ሐውልት የቆመበት አገር ስላሌ/ ሰላላ የአማርኛ ስም ያለው የአማራ ምድር ነበር። ሰላሌ ወደሚል የኦሮምኛ ድምጸት ያለው ስያሜ የተለወጠው ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ነው።

ሐውልቱ የዘመኑን እውነት የሚያንጸባርቅ አይደለም። ጀኔራል ታደሰ ብሩ በደርግ ሲገደሉ ብቻቸውን አልነበሩም። ጄኔራል ታደሰ ብሩን ደርግ የገደላቸው ከጭሰኞቻቸው ጋር ነበር። ሐውልት ሲቆምላቸው ግን አብረዋቸው የተገደሉት የታደሰ ብሩ ጭሰኞች መታሰቢያ አልቆመላቸው።

ኦነጋውያን ጀግና ለመፍጠር ስለሚፈልጉ የነሱን ትርክት ፈጥረው በጄኔራሉ ታሪክ ዙሪያ የራሳቸው ትርክት ፈጥረው ብዙ ውሸት አምርተዋል። ኦነግ የጀኔራል ታደሰ ብሩን የኢትዮጵያ አርበኛነትና የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የፈጥኖ ደራሽ አዛዥ እንደነበሩ ማውሳት አይፈልጉም። በመኢሶን ቋንቋ ጀኔራል ታደሰ ብሩና ኮለኔል ኃይሉ ረጋሳ ፊውዳሎች ነበሩ። ጀኔራል ታደሰና ኮሎኔል ኃይሉ ጫካም የገቡት ኦነጋውያኑ እነ ባሮ ቱምሳ፣ ዲማ ነገዖና ዘገዬ አስፋው ያረቀቁትን የደርግን «የመሬ ላራሹ» አዋጅ ተቃውመው ነው።

ይህ ደርግና መኢሶን ያቀረቡት ትርክት ብቻ አይደለም። ለእድገት በኅብረት ዘመቻ የመሬት ላራሹን አዋጅ ሊያስፈጽሙ ከዘመቱ ተማሪዎች መካከል ጀኔራል ታደሰ ብሩ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ መሬት ለጭሰኞች ለማከፋፈል ሲሞክሩ ጀኔራል ታደሰ ተማሪዎችን መሬት ለጭሰኞች ማከፋፈል አትችሉም ብለው ያባረሯቸው ተማሪዎችም አረጋግጠዋል። የኃይሌ ፊዳ ድርጅት መኢሶንም እነ ታደሰ ብሩና መለስ ተክሌ በአንድ ቀን በተረሸኑበት ወቅት በልሳኑ ባወጣው መግለጫ ተራማጆቹ እነ መለስ ተክሌ ከፊውዳሎቹ ከነ ታደሰ ብሩ ጋር መገደል የለባቸውም የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ለማንኛውም ኢትዮጵያ እንዲህ ነች! በአማራ ጥንተ ርስት ላይ የኦሮሞ ጄነራል ሐውልት ማቆም የሚቻልባት ምድር ናት (smiley)

ከታች የታተመው ፎቶ መጋቢት 5 ቀን 1967 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጀኔራል ታደሰ ብሩ ከነ ጭስኞቻቸውና ኮሎኔል ኃይሉ ረጋሳ በሻለቃ ተስፋዬ ገብረ ኪዳን [ኋላ ጀኔራልና ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት የበነበረው – የኦሮሞ ነገድ ተወላጅ ] በሚመራው የደርግ አሳሾች በተያዙበት ወቅት የተነሱፎቶ ነው።

About Post Author

Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator